Quantcast
Channel: እኔ የምለዉ
Viewing all 475 articles
Browse latest View live

አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በኦዲት ጥቅል ሪፖርት ባሰራቸው ተጠርጣሪዎች ላይ ፍርድ ቤት የተለያዩ ትዕዛዞች ሰጠ

$
0
0

 

  • ስምንት ተጠርጣሪዎች ዋስትና ተፈቀደላቸው

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአስተዳደሩ ዋና ኦዲተር ጥቅል ሪፖርትን መሠረት በማድረግ በቁጥጥር ሥር ባዋላቸው በፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ የተለያዩ የሥራ ድርሻ ያላቸው 26 ተጠርጣሪዎች ላይ ፍርድ ቤት የተለያዩ ትዕዛዞች ሰጠ፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ነሐሴ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በተጠርጣሪዎች ላይ ያቀረበውን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ በሰጠው ትዕዛዝ፣ ምርመራ መካሄድ ያለበት በጥቅል ሳይሆን የእያንዳንዱን ተሳትፎ በመግለጽ በተናጠል እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

ዓርብ ጳጉሜን 3 ቀን 2009 ዓ.ም. መርማሪ ቡድኑ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት የአሥር ተጠርጣሪዎችን የወንጀል ተሳትፎ ለይቶ ያቀረበ ቢሆንም፣ 16 ተጠርጣሪዎች ማቅረብ አለመቻሉን አስረድቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በተለያዩ ሥራዎች ምክንያት ጊዜ ስላጠረው መሆኑን አስረድቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ግን የመርማሪ ቡድኑ ምላሽ አላሳመነውም፡፡ ፖሊስ የተለያየ ሥራ እንደሚሠራ ግልጽ መሆኑን ፍርድ ቤቱ አስታወቀ፣ ‹‹ሥራ ሲሠራ የወንጀል አስተዳደር ፖሊሲው የሚለውን መከተል ግድ ነው፤›› ብሏል፡፡

የእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ተሳትፎ ጭብጥ ሲታይ ከሃያ በላይ ጥፋቶችን ስለሚያሳይ በጥልቀት ለመመርመር መረጃ እያሰባሰበ መሆኑን፣ መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡

የመርማሪ ቡድኑ ምላሽ ያልተዋጠለት ፍርድ ቤቱ ግን፣ ‹‹ተጠርጣሪን መያዝ ሳያስፈልግ ተሳትፎውን በክትትል መለየት ይቻላል፡፡ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ሳይውል መለየት ካልተቻለ ደግሞ በቁጥር ሥር አውሎ መለየት ይቻላል፤›› ካለ በኋላ፣ መርማሪ ቡድኑ ያቀረበው የምርመራ መዝገብ ግን ያንን እንደማያሳይ አስታውቋል፡፡

በምርመራ ሒደቱ ችግር እያጋጠመው መሆኑን የገለጸው መርማሪ ቡድኑ፣ በአንድ ተቋም ውስጥ ይሠሩ የነበሩ 20 ተጠርጣሪዎች ስላሉ መረጃ ማግኘት ችግር እንደሆነበትና ጊዜ እንደሚፈልግ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

ለፖሊስ ምርምራ አለመተባበር ወንጀል መሆኑ በሕግ ተደንግጎ እንደሚገኝ የጠቆመው ፍርድ ቤቱ፣ ተቋሙ የሕግ አካልን የማይተባበር ከሆነ የሕዝብ ተቋም መሆኑ ቀርቶ ሌላ አካል መሆኑን የሚያሳይ ከመሆን ባለፈ፣ እንደዚህ ዓይነት ተግባር ካጋጠመ የማይሆንና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስረድቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ግን አቋሙን ሳይቀይር በጊዜ እጥረት ምክንያት የ16ቱን ተጠርጣሪዎች የድርጊት ተሳትፎ ለይቶ ማቅረብ አለመቻሉን በድጋሚ በመግለጽ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በአቋሙ በመፅናት ‹‹የጊዜ ቀጠሮን ጉዳይ ፍርድ ቤቱ ቀደም ባለው ቀጠሮ አግዶታል፤›› በማለት የእያንዳንዱ ተጠርጣሪ የድርጊት ተሳትፎ በተናጠል በግልጽ ተለይቶ ሳይቀርብ ምንም ማለት እንደማይችል አሳውቋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ የድርጊት ድርሻቸው ተለይቶ በቀረቡት የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደለ ደመቀን ጨምሮ፣ በአሥር ተጠርጣሪዎች 12 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ለመስከረም 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ድርሻቸው ያልተለየው 15 ተጠርጣሪዎችን በሚመለከት ምንም የሚለው ነገር እንደሌለ ገልጾ፣ እስከ መስከረም 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ለይቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ አንድ ተጠርጣሪ የአስተዳደሩን የፋይናንስ መመርያ ተጥሶ ከፍተኛ የሆነ አበል እንደተከፈላቸው የተገለጸ ቢሆንም፣ ተጠርጣሪዋ ተነግሯቸው መመለሳቸውን በማስረዳታቸው በ5,000 ብር ዋስ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በጥቅሉ ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸውን መርማሪ ቡድኑ መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ሌላው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ቡድን የአከራይ ተከራይ መመርያ ቁጥር 4/2004 በመተላለፍና ሐሰተኛ ምስክርን በመቀጠም፣ አንድ የንግድ ቤት ለአንድ ነጋዴ በሕገወጥ መንገድ እንዲሰጠው ውሳኔ አስተላልፈዋል በተባሉ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አፈ ጉባዔና ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ በሰባት ሰዎች ላይ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ከነሐሴ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በተሰጠው አራት ቀናት ውስጥ ከአንዱ ተጠርጣሪ በስተቀር፣ የሁሉንም ቤት መበርበሩንና የተለያዩ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

ከተጠርጣሪዎቹ አንዱ፣ ‹‹ቤታቸውን እንዲበረብሩና ሥራቸውን እንዲጨርሱ›› ሲለምኗቸው ሆን ብለው ጊዜ ቀጠሮ ለመጠየቅ እንዲያመቻቸው ሳይበረብሩ መቅረታቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሆን ተብሎ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ለማሳጣትና እነሱን ለማጉላላት የተደረገ መሆኑንም አክለዋል፡፡

በመሀል ፍርድ ቤቱ፣ ‹‹ብርበራ እንድታደርጉ ማን ፈቀደላችሁ?›› የሚል ጥያቄ ለመርማሪ ቡድኑ ሲያቀርብ፣ መርማሪ ቡድኑ ‹‹የሥር ፍርድ ቤት›› የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ቀደም ባለው የችሎት ቀን ፍርድ ቤቱ የምርመራ መዝገቡን ሲመረምር ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ማዘዣ የተወሰደው ከፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት መሆኑን አስመልክቶ ስህተት መሆኑንና ሕግ የጣሰ አሠራር መሆኑን እንደገለጸላቸው በማስታወስ፣ ‹‹ማን ፈቅዶላችሁ ነው? ብርበራ ማድረጉ ከጉዳዩ ጋር የሚያገናኘው ምንድነው? ተጠርጣሪዎቹ የተያዙበት ዋና ጉዳይ ለአንዱ የተሰጠ የንግድ ቤት ለሌላ ተሰጥቷል የሚል ነው፤›› በማለት መርማሪ ቡድኑ ምላሽ እንዲሰጥ ፍርድ ቤቱ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን አንስቷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ሕገወጥ ድርጊቱን ሲፈጽሙ የያዙት ቃለ ጉባዔ የነበረ ቢሆንም፣ በመጥፋቱ እሱን ለመፈለግ ብርበራ ማድረጉን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ቀድሞ ባስቻለው ችሎት ለመርማሪ ቡድኑ የፈቀደው ተጨማሪ ጊዜ የሰው ምስክሮችን ቃል እንዲቀበልና የወረዳውን ፋይል እንዲፈተሽ ብቻ መሆኑን አስታውሶ፣ የተደረገው ምርመራ ሒደት (ብርበራ) ስህተት መሆኑን አስታውቋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ደግሞ እንዳስረዳው ብርበራ ያካሄደው ከምርመራ ሒደቱ ጋር የተገናኘ ነገር ስለነበር መሆኑን አስረድቷል፡፡ ንግድ ቤቱ ለሌላ አካል በመተላለፉ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ መርማሪ ቡድኑ እንዲያስረዳ ፍርድ ቤቱ ሲጠይቀው፣ የንግድ ቤቱ የገቢ መጠን ስንት እንደሆነና የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ ንግድና ኢንዱስትሪ ሠርቶ እንዲሰጠው መጠየቁን ተናግሯል፡፡ ተሠርቶ እንዳለቀም ለፍርድ ቤቱ እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪዎችን የደመወዝ መጠን ጠይቆ ከተገለጸለት በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ ሦስት ተጠርጣሪዎች እያንደንዳቸው 15,000 ብር ቀሪዎቹ ደግሞ እያንዳንዳቸው 10,000 ብር ዋስትና አስይዘው ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ይህንን ያደረገበት ምክንያት ደግሞ ምርመራው ከተጀመረ ስምንት ወራት ያለፈው ከመሆኑ አንፃር፣ ሕገ መንግሥታዊ መብትን ከማስከበርና የተፋጠነ ፍትሕ ከመስጠት አንፃር፣ እንዲሁም ክስ ቢመሠረትባቸው እንኳን ዋስትና የሚያስከለክል የሕግ አንቀጽ ይጠቀስባቸዋል የሚል እምነት የሌለው መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት መሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

 

Standard (Image)

በሰሜን ጎንደር ዞን በዓመት ውስጥ 597 ታጣቂዎች መገደላቸው ተገለጸ

$
0
0

 

  • ከ700 በላይ ደግሞ ትጥቅ መፍታታቸው ተገልጿል

በአማራ ክልል የሰሜን ጎንደር ዞን በ2009 ዓ.ም. ጫካ ገብተው ከነበሩ የታጠቁ ኃይሎች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ 597 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ፡፡

የዞኑ አስተዳደርና ፀጥታ መምርያ ኃላፊ አቶ ዳኘው በለጠ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኤርትራ በመሄድ ከግንቦት ሰባትና አርበኞች ግንባር ጋር ተቀላቅለው በመሠልጠን በዞኑ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ እንግልት ሲያደርሱና ግፍ ሲፈጽሙ የነበሩ በአጠቃላይ 708 ታጣቂዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከልም 111 በሕይወት መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የዞኑ ፀጥታ በአንፃራዊነት ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት የመምርያው ኃላፊ፣ የሻዕቢያ መንግሥት እነዚህን ኃይሎች በገንዘብና በሎጂስቲክስ እገዛ ያደርግላቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ‹‹እነዚህ የታጠቁ ኃይሎች በሕዝቡ ውስጥ ሰፊ የሆነ ግፍ ሲፈጽሙ የነበሩና ሕፃናትንና ከብቶችን በመዝረፍ ሰቆቃ ሲያደርሱ የነበሩ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

አሁንም ቢሆን ከኤርትራ ሠልጥነው የመጡና በየቦታው እየተንቀሳቀሱ በሕዝቡና በመንግሥት ንብረት ላይ ጉዳት ለማድረስ ያለሙ ሰባት ግለሰቦች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ በቀላል ወንጀል የታሰሩና ሰው ገድለው የሸሹ 23 ያህል ሽፍቶች በዞኑ ውስጥ ባሉ ጫካዎችና በሱዳን ድንበር አካባቢ እንዳሉም አስረድተዋል፡፡ የዞኑ የፀጥታ ኃይልና አስተዳደር በ2010 ዓ.ም. መስከረም ወር እነዚህን ኃይሎች ለማጥፋት አቅዶ እየሠራ እንደሆነም አቶ ዳኘው ተናግረዋል፡፡ እስካሁን በተደረገው ዘመቻም ከ500 በላይ የጦር መሣሪያዎች መማረክ ተችሏል ብለዋል፡፡

በሰሜን ዞን የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቅማንት ሕዝብ አንስቶት የነበረውን የማንነት ጥያቄ ለመመለስ ሲባል በ12 ቀበሌዎች ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በጭልጋ ወረዳ ያሉ አራት ቀበሌዎች በሕዝበ ውሳኔው ላይ ቅሬታ ማንሳታቸውን አቶ ዳኘው ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ዳኘው ገለጻ፣ ጭልጋ ወረዳ ሕዝበ ውሳኔው ከሚካሄድባቸው 12 ቀበሌዎች መካከል ስድስቱ የሚገኙበት ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል አራቱ ማለትም ገለድባ፣ አንከራደዛ፣ ሹምየና አውርደርዳ ቀበሌዎች ውስጥ ከነዋሪዎች ቅሬታ ቀርቧል፡፡

በእነዚህ ቀበሌዎች የሚኖረው ሕዝብ ዋነኛ ጥያቄም፣ ‹‹ቅማንቶች ከ20 በመቶ በታች ሆነውና በቁጥር ደረጃ እኛ አማራዎች በልጠን ሳለ ሕዝበ ውሳኔው ለምን አስፈለገ የሚል ነው፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት ለቅሬታው በሰጠው ምላሽ እንደተባለው የአማራዎች ቁጥር የሚበልጥ ከሆነ በድምፅ መስጠት ሒደት የሚረጋገጥ እንደሚሆን፣ መጭበርበር እንዳይኖር ተብሎም ታዛቢዎች የሚመጡት ከሌላ ክልል እንደሆነም እንደተገለጸ ጠቅሰዋል፡፡ እንደ አቶ ዳኘው ማብራርያ፣ ሕዝበ ውሳኔ ከሚካሄድባቸው 12 ቀበሌዎች መካከል ሁለቱ ጎንደር ከተማ ውስጥ ሲገኙ፣ አራቱ ደግሞ መተማ ውስጥ የሚገኙ ቀበሌዎች ናቸው፡፡

የቅማንትና የአማራ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ከተነሳባቸው መካከል በ12 ቀበሌዎች ላይ ሕዝበ ውሳኔውን መስከረም 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ለማድረግ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

Standard (Image)

ኦሕዴድ በውጭ ከሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ጋር ለመሥራት የሚያስችል አደረጃጀት ፈጠረ

$
0
0

 

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) በውጭ ከሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ጋር ለመሥራት የሚያስችል አደረጃጀት ፈጠረ፡፡

ኦሕዴድ ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባ አዳዲስ መዋቅሮችንና ሹመቶችን አፅድቋል፡፡ በዚህም መሠረት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የድርጅቱን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ለሦስተኛ ጊዜ ለመቀየር ተገዷል፡፡ በሦስተኛ የኃላፊነት ምደባ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንትና የኮንስትራክሽንና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ የነበሩትን ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አድርጎ መድቧል፡፡

በ2009 ዓ.ም. ነሐሴ ወር ላይ የቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ በከር ሻሌ ወደ ኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊነት ቢመጡም፣ እስከ ግንቦት 2009 ዓ.ም. ድረስ አገልግለው ለትምህርት ወደ ውጭ አገር ሄደዋል፡፡ ቀጥሎም የቀድሞ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ አብዱላዚዝ አህመድ የተተኩ ቢሆንም፣ ከወራት በላይ እንዲቀጥሉ በፓርቲው አልተፈለገም፡፡

‹‹በኦሮሚያ ውስጥ ላለው ፖለቲካዊ ችግር መንስዔው የፓርቲው ደካማነትና የሕዝቡን ፍላጎትና ጥያቄ አለመመለስ ነበር፡፡ በፓርቲው ውስጥ ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ በተደረገ መሻሻል ውጤቶች ቢመዘገቡም፣ አሁንም አሸንፎ ለመውጣት ጠንካራ ኦሕዴድን መገንባት ያስፈልጋል፤›› ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የፓርቲው አመራር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ሲባል በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ንቅናቄን እየፈጠሩ የሚባልላቸው ዶ/ር ዓብይ አህመድን ወደ ፖለቲካ ሥራ እንዲመጡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ዓብይ በአጭር ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መሰላልን በመራመድ ወደ ጫፍ የደረሱ ሲሆን፣ በአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከፓርላማ አባልነት ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርነት ከፍ ብለዋል፡፡

እዚህ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት በውትድርና መስክ በአገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ሻለቃ ነበሩ፡፡ በኋላም በመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተርነት ለአጭር ጊዜ አገልግለዋል፡፡ በኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፣ ከዚህ ጋር ተያያዥነት ባላቸው መስኮች እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡

ኦሕዴድ በተለይ 2008 ዓ.ም. ከገባበት ፖለቲካዊ ቀውስ ለመውጣት ባካሄደው የለውጥ እንቅስቃሴ፣ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንትነትና ለክልሉ የኮንስትራክሽንና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊነት ተሹመዋል፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት የፓርቲው አመራር በኦሮሚያ የፖለቲካ ቀውስ እንዲፈጠር ካስቻሉ መሠረታዊ ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ፣ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ የወሰንና የፖለቲካ ግንኙነት፣ እንዲሁም የሥራ አጥነት ችግሮች ተጠቃሽ ናቸው ይላሉ፡፡

ዶ/ር ዓብይ በኦሮሚያ ክልል የኃላፊነት ጊዜያቸው የተጠቀሱትን ችግሮች የመፍታት ቀጥተኛ ኃላፊነት በተሰጠው የኮንስትራክሽንና ከተማ ልማት ቢሮ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውንም ገልጸዋል፡፡

በቆይታቸው የኦሮሚያና የአዲስ አበባ ወሰን ተለይቶ እንዲከለል ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማስጀመራቸውን፣ በአዲስ አበባ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ጉዳይ ሕጋዊ ጥበቃ እንዲያገኝ ከሌሎች የፓርቲው አባላት ጋር በመሆን ጥረት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ኦሕዴድ ዶ/ር ዓብይን ከክልሉ መንግሥት ሥራ አስፈጻሚነት ወደ ፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊነት ሲያመጣቸው በመንግሥት ሥራ አፈጻጸም ላይ የተወሰነ ጉድለት ይፈጠራል የሚል ሥጋት ቢጎላም፣ የፓርቲውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማጠናከር ሲባል ግን ወደ ፖለቲካ ሥራ እንዲዘዋወሩ ማድረግ አስፈላጊ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር ዓብይን ወደ ኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊነት እንዲመጡ ፓርቲው ሲወስን ተቋማዊ የመዋቅር ማሻሻያም ማድረጉ ታውቋል፡፡ ከዚህም መሀል ግንባር ቀደሙ በውጭ አገሮች የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆችን ያማከለ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ፣ የፌዴራል ቢሮዎችና የውጭ አገር የአባላት አደረጃጀት ዘርፍ በፓርቲው ውስጥ ተፈጥሯል፡፡ የኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በሆኑት አቶ ፍቃዱ ተሰማ እንዲመራ ተወስኗል፡፡ የምሁራን አደረጃጀት ኃላፊ ደግሞ አቶ ስለሺ ጌታሁን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አደረጃጀት ኃላፊ ሆነው የተሾሙት ደግሞ አቶ ጌታቸው ባልቻ ናቸው፡፡

የገጠር የፖለቲካ አደረጃጀትን በአቶ ብርሃኑ ፀጋዬ፣ የከተማ የፖለቲካ አደረጃጀትን ደግሞ አቶ ሀብታሙ ኃይለ ሚካኤል እንዲመሩት ተወስኗል፡፡ ይህ የኦሕዴድ አወቃቀር ከሌሎች የኢሕአዴግ መሥራች አባል ፓርቲዎች የተለየ ነው፡፡ ሌሎቹ በአንድ የፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ የሚመሩ ናቸው፡፡

የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ አብዱላዚዝ አህመድ ምክትል ፕሬዚዳንትና የኮንስትራክሽንና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል፡፡

ኦሕዴድ አምስት አዳዲስ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን መርጧል፡፡ በድርጅቱ ታሪክ ሦስት ሴቶች ማለትም ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ ወ/ሮ ሎሚ በዶ፣ ወ/ሮ አዚዛ አብዲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሆነዋል፡፡ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬና አቶ ፍቃዱ ተሰማም ተካተዋል፡፡ ወ/ሮ ብርቱካን አያኖ (አምባሳደር) የክልሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነዋል፡፡ 

Standard (Image)

የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ

$
0
0

 

መንግሥት ከነሐሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለአሥር ቀናት አዲሱን ዓመት ለመቀበል ቅድመ በማድረግ፣ አሥሩን ቀናት የተለያዩ ስያሜዎች በመስጠት አክብሯል፡፡ ጳጉሜን 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት በሚሊኒየም አዳራሽ የአዲስ ዓመት አቀባበልን በተመለከተ በነበረው ዝግጅት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው በ2009 ዓ.ም. የነበሩ ተግዳሮቶችንና በጎ ጎኖችን የጠቀሱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ችግሮች ግንዛቤ በመውሰድና የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል የ2010 ዓ.ም. የአገሪቱ የከፍታ ዘመን እንዲሆን መንግሥት የተሻለ ሥራ ለማከናወን ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ባለፉት አሥር ዓመታት የተመዘገበው ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት በአዲሱ ዓመት እንዲሳካ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ዝግጅት ቀደም ብሎ ጳጉሜን 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ደግሞ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በጽሕፈት ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ አገሪቱ ባለፈው ዓመት ስላስመዘገበችው ድልና ስለገጠሟት ተግዳሮቶች፣ እንዲሁም በ2010 ዓ.ም. ሊከናወኑ ስለታሰቡ ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸውም ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ወሰን አካባቢ ስላለው ወቅታዊ ግጭት፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች በተለይም በጠገዴና በፀገዴ መካከል ስለነበረው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ አፈታትና ሌሎች ጉዳዮች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በጋዜጣዊ መግለጫቸው መግቢያ ላይ እንደተናገሩት፣ ለአሥር ቀናት ተዘጋጅቶ የነበረው ፕሮግራም በ2010 ዓ.ም. ተግባራዊ የሚሆኑ አጀንዳዎችን ለማስተዋወቅ ያለመ ነው፡፡ በእነዚህ አሥር ቀናት የተከበሩ ፕሮግራሞች በኅብረተሰቡ መካከል መከባበርና መፈቃቀር ተፈጥሮ አገሪቱ የከፍታ ዘመኗን እንድታረጋግጥ የሚያስችል እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በ2009 ዓ.ም. አገሪቱ ትልልቅ ድሎችን እንዳስመዘገበች የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ይህ ሲባል ግን ያለምንም ችግር ዓመቱ ታልፏል ማለት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱ ተከስተው የነበሩ ችግሮችን የዘረዘሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በአገሪቱ ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት፣ ድርቅና የሳዑዲ ዓረቢያ ተመላሾች ጉዳይ ግንባር ቀደም እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ዓመቱ አገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳየት መቀጣሏንም አመልክተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ በላይ ማደግ ይገባት እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ይህ ዕድገት ሊመጣ የቻለው ደግሞ በኢንቨስትመንት የተከናወነ ሥራ ጠንካራ በመሆኑ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊመዘገብ የቻለው በተለያዩ ዘርፎች እንደሆነ ጠቁመው፣ ይህ ቀጣይ እንዲሆን ግን ቀጣይነት ያለው ሰላምና ዴሞክራሲ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡  

መንግሥት የጀመረውን የጥልቅ ተሃድሶ ጉዞ በመቀጠል ከዚህ የተሻለ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ዕድገት እንዲመጣ መሠራት እንደሚገባውም አመልክተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ጎርፍና ሌሎች አደጋዎች በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ነገሪ፣ የአዋሽ ወንዝና የቆቃ ግድብ ሞልተው ከፍተኛ ችግር እያደረሱ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታትም ከፌዴራል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንና ከክልል የሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ከ8.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች በተለይም በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች በድርቅ ችግር ምክንያት ጉዳት እንደደረሰባቸው የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ጋር በመተባበር ችግሩ ከዚህ የባሰ እንዳይሆን እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡  

ጋዜጠኞች በአገሪቱ ውስጥ በ2009 ዓ.ም. ውስጥ ስለነበሩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችና የ2010 ዓ.ም. ዕቅዶችን በተመለከተ ለሚኒስትሩ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡

ከሪፖርተር በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች ሰሞኑን ስለተፈጠረው ግጭት ወቅታዊ ሁኔታና ዋነኛ መነሻ ምክንያት፣ እንዲሁም ኃላፊነቱን ማን እንደሚወስድ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡ ሚኒስትሩ በምላሻቸውም፣ ‹‹በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል የነበረው ግጭት ከዚህ በፊት የሁለቱ ክልሎች አመራሮች፣ እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በተሳተፉበት በፊት ተደርጎ በነበረው ሕዝበ ውሳኔ መሠረት የወሰን መካለሉ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ አሁንም ቢሆን ያ ስምምነት አልፈረሰም፡፡ በስምምነቱም መሠረት የሁለቱም ክልል አመራሮች ሥራውን እያከናወኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ሥራ እየተከናወነ ያለው ከሚመለከተው የፌዴራል ተቋም ጋር መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ነገር ግን ይህም ሆኖ በቅርቡ ሕይወት የጠፋበት ግጭት እንደተፈጠረ መረጃ እንደደረሳቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይኼኛው ግጭት ከዚህ የወሰን አከላለል ጋር ምንም የሚገናኝ አይደለም፡፡ በደረሰን መረጃ መሠረት የሁለቱም ክልሎች አመራሮች በነበራቸው ስምምነት ተገዥ ሆነው ሥራቸውን እያከናወኑ ባሉበት ወቅት ማን እንዳሰማራቸው የማይታወቁ ኃይሎች አልፎ አልፎ ትንኮሳዎች እንደፈጸሙ፣ ሕዝቡ ደግሞ ለዚህ ምላሽ ለመስጠት በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፡፡ እስከ ትናንት [ዓርብ ጳጉሜን 3 ቀን 2009 ዓ.ም.] ድረስም የሁለቱ ክልሎች አመራሮች በተገኙበት ይህንን ችግር በመፈተሽ እንዲፈታና እንዲቆም ተደርጓል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

‹‹በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በመሬት ምክንያት፣ ያውም በአንድ አገር ዜጎች መካከል ደም መፋሰስና ሕይወት እስኪያልፍ ድረስ የሚደርስ ግጭት መኖር አልነበረበትም፡፡ ይህ ለማንኛውም አካል ለመንግሥት አመራርም ሆነ ለዜጎቻችን ትልቅ ሐዘን ነው፡፡ ይህ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል ባለው የድንበር ግጭት ምክንያት የደም መፍሰስ መከሰቱ ለመንግሥትም ሆነ ለሕዝብ ውርደት ነው፡፡ ውድ የሰው ሕይወት እንዲጠፋ ያደረጉ ግጭቶች በሁለቱ ክልሎች መካከል አሉ፡፡ በምሥራቅ ኦሮሚያ በሐረር፣ በባሌና በቦረና በኩል የተደረገው ለመናገርም በጣም የሚያሳፍር ነው፡፡ በየቀኑ እንከታተላለን፡፡ መረጃውን በትክክል መግለጽ እንችላለን፡፡ በሚመለከተው አካል ወደፊት እንገልጻለን፡፡ መረጃው እኛ ጽሕፈት ቤትም አለ፡፡ በሁለቱም ወገን እየሞተ ያለው ሕዝብ በጣም ያሳዝናል፡፡ መሆን አልነበረበትም፡፡ ለዚህ መንስዔው ምንድነው የሚለው ጥያቄ እንደ አመራር የእኛም ጥያቄ ስለሆነ ይህን ችግር እያደረሰ ያለው የሶማሌ ልዩ ኃይል ነው ወይ? በማለት ለክልሉ ፕሬዚዳንት ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ምላሻቸው ግን በእነሱ ዕውቅናና ምሪት የተደረገ እንዳልሆነ ነው የተገለጸው፡፡ ሕዝቡ የሚለው ግን ይህን ችግር የሚያደርሰው የታጠቀ ኃይል እንደሆነ ነው፡፡ አሁን ግን ይህንን የሚመራው አካል በትክክል ተይዞ ዕርምጃ መወሰድ ስላለበት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፤›› በማለት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የአተት በሽታ በአማራ፣ በትግራይና በሶማሊያ ክልሎች እስካሁን ድረስ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰና የሰው ሕይወት እየቀጠፈ ቢሆንም መንግሥት ብዙም ትኩረት ሲሰጠው አይታይምና በዚህ ላይ የመንግሥት ምላሽ ምንድነው የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡ በምላሻቸው፣ ‹‹ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የሚመለከታቸው የጤና ቢሮዎች በጋራ እየሠሩ በመሆኑ በሽታው ከቁጥጥር ውጭ አልሆነም፤›› ብለዋል፡፡ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በአገሪቱ ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች አነስተኛ ናቸው ሲባል ይሰማልና ይህ ሁኔታ በሚቀጥለው ዓመት እንዳይደገም፣ ችግሮች ከመድረሳቸው በፊት መንግሥት ቀድሞ ለመተንበይና ለመከላከል ምን አስቧል? የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ሚኒስትሩም ለችግሮች መፍትሔ ሲሰጥ የቆየው በችግሮቹ ግዝፈት መጠን መሆኑን ጠቅሰው፣ ባለፈው ዓመት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው የሕዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህንን አስቀድሞ መከላከል ይቻል ነበር ወይ? ለተባለው የተለያዩ መላምቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በመንግሥት በኩል ለአገር ዕድገትና የዜጎችን ጥቅም ለማስከበር ሲባል በየጊዜው ከሕዝቡ ጋር በመወያየት በተቻለ መጠን እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች እንዳይፈጠሩ፣ ልዩነቶችና ጥያቄዎች ሲኖሩም በሰላማዊ መንገድ ማንም ሰው ሕገ መንግሥታዊ መብቱን ተጠቅሞ ጥያቄ ማንሳት ይችላል፡፡ ይህም ተደርጎ ግን አንዳንድ ጊዜ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ ስለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ዓላማው ግልጽ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ደግሞ ዓላማውን አሳክቶ በጊዜው እንደተነሳ እናስታውሳለን፤›› ብለዋል፡፡ ለመጪው ተመሳሳይ ችግር ይከሰታል ተብሎ እንደማይጠበቅ ተስፋ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

መንግሥት የሚጠበቅበትን አገልግሎት ለመስጠት ራሱን ማዘጋጀት እንደሚገባውም ጠቁመዋል፡፡ የተጀመረው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴም በጥልቀትና ትርጉም ባለው መንገድ፣ እያንዳንዱ የመንግሥት መዋቅር ሕዝቡን የሚያረካ ሥራ እንዲያከናውን አስፈላጊ ዝግጅት በማድረግ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

የሚነሱ ጥያቄዎች የዴሞክራሲ ባህል እንዲያብብና ማንኛውም ጥያቄ ያለው አካል በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲያነሳና እንዲስተናገድ፣ አስፈላጊው ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡  

‹‹ስለዚህ 2010 ዓ.ም. የምንቀበለው ተመሳሳይ ችግር ይፈጠራል ብለን ሳይሆን፣ የታቀዱት እያንዳንዱን ዜጋ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን እያከናወንን ዕቅዳችንን የምናሳካበትና የተያዙ ትልልቅ ፕሮጀክቶች የሚያብቡበት ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡ ለዚህም ደግሞ መንግሥትን ብቻ መጠበቅ ሳይሆን አጠቃላይ ኅብረተሰቡ የሚጠበቅበትን ሚና መጫወት እንደሚገባው አስረድተዋል፡፡ ምክንያታቸውን ሲያብራሩም መንግሥት ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ብቻ አገርን እንደሚመራ ተናግረዋል፡፡ የአገር ባለቤት የሆኑ ዜጎች ፀረ ሰላምና ፀረ ልማት የሆኑ አመለካከቶችን ለይተው መታገል እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል፡፡

የፀረ ሙስና ትግሉን በተመለከተም ዕርምጃው አዲስ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ነገር ግን አሁን ባለበት ደረጃ በተለየ ሁኔታ መንግሥት በቁርጠኝነት አስፈላጊውን ዕርምጃ እየወሰደ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህ ዕርምጃ ደግሞ በቀጣይ ሰዎችን በማሰር ብቻ ሳይሆን ይህንን የሙስና ተግባር ለመዋጋት ቀድሞ መከላከል ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡ አስፈላጊው ሙስናን የሚገታ መዋቅር በመዘርጋት በተለይም የሙስና ወንጀል በሚበዛባቸው ተቋማት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡ በተገኘው መረጃ መሠረትም እየተወሰደ ባለው ዕርምጃ ሕዝቡ ደስተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወደሚፈለገው ከፍታ የሚወስዱ ጉዳዮች ተለይተው መሠራት እንደሚባቸውም አክለው ጠቅሰዋል፡፡

ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ቀድሞ በመከላከል ረገድ ሰፊ ሥራዎች መከናወን እንዳለባቸው፣ እነዚህ ችግሮች በየትኛውም ዓለም የሚከሰቱና የተለመዱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት ባለፈው ዓመት የተከሰቱ ችግሮችን ለምሳሌ ቆሼን በተመለከተ ችግሩ ሊከሰት እንደሚችል ቀድሞ ያውቀው እንደነበረና በዚህ ጊዜ ሊከሰት ይችላል ተብሎ ግን እንዳልተገመተ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ቀድመን በመተንበይ መቆጣጠር ያለብንን በተመለከተ በተለይ ከአፍሪካ አገሮች ጋር ሲወዳደር እንደ ኢትዮጵያ ቀድሞ የሚዘጋጅ አገር የለም፤›› ብለዋል፡፡ ሁሉንም ቀድሞ በመተንበይ ከአደጋ መከላከል ይቻላል ተብሎ እንደማይታሰብም አክለው ገልጸዋል፡፡

ሌላው ከጋዜጠኞች የተነሳላቸው ጥያቄ በ2009 ዓ.ም. አገሪቱን ብዙ ተግዳሮቶች ቢገጥሟትም 10.5 በመቶ ማደጓን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዚህ ደረጃ የመንግሥትዎ ሪፖርት ምንድነው? በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥስ እንዴት ዕድገት ሊመዘገብ ቻለ? የሚል ነው፡፡ በምላሻቸው፣ ‹‹የ2009 ዓ.ም. የኢኮኖሚ ዕድገት በታሰበው ደረጃም ባይሆን ከፍተኛ ውጤት ነው ማለት እንችላለን፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያን የአገር አመራር ሁኔታውን በምናይበት ጊዜ በፅኑ መሠረት ላይ የቆመ ነው፡፡ ፖሊሲያችን ዘላቂ ልማትን ለማስመዝገብ በሚያስችል ሁኔታ የተቀረፀ ነው፡፡ አንዱ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ፖሊሲው ራሱ ነው፡፡ በአንድ ሌሊት ግርግር አቅጣጫውን የሚቀይር ፖሊሲ አይደለም፡፡ መንግሥት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንኳ የኢንቨስትመንት ሁኔታው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ሌላው መመስገን ያለበት የሕዝባችን የልማት ፍላጎት ነው፡፡ በኢንዱስትሪው ዙሪያ የተደረገው ርብርብም ቀላል አይደለም፡፡ ለኢኮኖሚ ዕድገቱም የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡ ዛሬ ምርታማነት ጨምሯል፡፡ ሌሎች የኢኮኖሚ ዕድገት አመላካቾችን ስንመለከትም ችግሮች ቢኖሩም ዕድገታችን መሠረታዊ ስለሆነ ያንን ሊያናጋ አልቻለም፡፡ ይህ ቀጣይነትና ትክክለኛ ቁመና እንዲኖረው ለማድረግ የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ ተላብሶ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣ መንግሥት በቅርበት እየሠራ ነው የሚገኘው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በመሆኑም በ2010 ዓ.ም. ምንም ዓይነት ተግዳሮት ቢኖርም፣ የታቀዱ ጉዳዮች እንደሚሳኩና ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች ይከናወናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በቅርቡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተያዘላቸውን በጀት በትክክል እንዲጠቀሙና አላስፈላጊ ወጪዎችን እንዲቀንሱ መመርያ አውጥቶ ሳለ፣ ትልቅ በጀት ይዞ የአዲስ ዓመት መግቢያ ዋዜማን በሚሊኒየም አዳራሽ ለማክበር ማቀድ ከመንግሥት ፖሊሲ ጋር አይጋጭም ወይ? የሚል ጥያቄም ተጠይቀዋል፡፡ በሰጡት ማብራሪያም፣ ‹‹አዲስ ዓመቱን ለመቀበል በምናደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ዝግጅት ያለ ወጪ አይከናወንም፤›› ብለዋል፡፡

ክብረ በዓሉን ለማከናወን በዋናነት በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የሚመራና ሌሎች የተለያዩ አካላት የተሳተፉበት አገራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡ ይህ ኮሚቴም ወጪ እንደሚያስፈልገው ስለሚታወቅ ወጭውን በተመለከተ ፈንድ አፈላላጊ ንዑስ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ በዚያው መሠረት ፈንድ ለማፈላለግ የተደረገው ጥረት በጣም ውጤታማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የተያዘው ዕቅድ እስከ አራት ሚሊዮን እንደሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ገንዘብ ከመንግሥት ተቋማት ወጥቶ የሚሠራ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደተባለው ወጪው 20 ሚሊዮን ይሆናል የተባለው ሐሰት መሆኑንና ትክክለኛ መረጃ የሚፈልግ አካል ካለም ከጽሕፈት ቤታቸው ማግኘት እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡  

የእንቦጭ አረም በጣና ሐይቅ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በተመለከተ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ ውስን እንደሆነና በዚህ ላይ የመንግሥት አቋም ምን እንደሆነ ተጠይቀው፣ የእንቦጭ አረም የአንድ ክልል ጉዳይ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኔ ያለኝ መረጃ የሚያሳየው የክልሉና የፌዴራል የሚመለከታቸው አካላት በመነጋገር እየሠሩ እንደሆነ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአገሪቱ በ2009 ዓ.ም. የውጭ ምንዛሪ እጥረት የነበረ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ በአዲሱ ዓመት ይህንን ችግር ለመቅረፍ ምን እየተሠራ ነው? የሚል ጥያቄም የቀረበላቸው ሲሆን፣ ሚኒስትሩ ሲመልሱም፣ ‹‹የውጭ ምንዛሪ ችግር የለም ያልንበት ጊዜ የለም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የውጭ አቅማችንን ስናሳድግና ወደ አገር ቤት የሚገቡ ዕቃዎችን የሚተኩ አገር ውስጥ ማምረት እስክንችል ድረስ ግዴታ ከውጭ የሚመጡት ላይ ኢንቨስት ማድረጋችን አይቀርም፡፡ ይህ የሽግግር ጊዜ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ስለዚህ እጥረቱ ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደሆነ በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ደግሞ በመንግሥት በኩል በተለይ በወጪ ንግድ ትኩረት አድርገን መሥራት አለብን፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል በነበረው የወሰን ችግር በተለይም በጠገዴና በፀገዴ ወረዳዎች መካከል በቅርቡ ስለተደረገው ስምምነት ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቀው፣ ‹‹ከዚህ በፊትም ቢሆን የማይፈታ ችግር አልነበረም፡፡ ስለዚህ ጊዜ በመውሰድና በጥልቀት በመመርመር እንደዚህ ዓይነት ችግር እንዳይቀጥሉ ለማድረግ፣ አሁን በሁለቱም ክልሎች አመራር በኩል የተደረሰው ስምምነት ይህን ችግር በዘላቂነት የሚፈታው ይሆናል ብለን ነው የምንጠብቀው፡፡ በፌዴራል መንግሥት በኩል ክትትል ሲደረግና ድጋፍ ሲደረግ ነበር፡፡ ይህንን ችግር እንዲፈቱ ሲደረግ ነበር፡፡ ምክንያቱም ክልሎች ከፌዴራል የተነጠሉ ናቸው ብለን መገመት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የፌዴራሉን መንግሥት የመሠረቱት ክልሎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ይህንን በቅርበት ስንከታተል ነበረ፡፡ አሁንም የተደረሰው ስምምነት በዘላቂነት ችግሩን እንዲፈታ፣ በፌዴራሉ መንግሥት በኩል አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል፤›› በማለት  ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ያንን አካባቢ የችግር ቀጣና ለማድረግ ይሠሩ የነበሩ አካላት እንዳሉ ጠቁመው፣ ‹‹ከአሁን በኋላ አጀንዳው ተዘግቷል፤›› ብለዋል፡፡

 

Standard (Image)

በቤቶች ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የቀድሞ ኃላፊዎች ላይ ክስ መመሥረት አለመቻሉን ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ

$
0
0
  • ፍርድ ቤቱ ክሱ ያልመሠረተበት ምክንያት አሳማኝ አይደለም ብሏል

 የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በቤቶች ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የቀድሞ ኃላፊዎች በእነ ወ/ሮ ፀዳለ ማሞ (አምስት ሰዎች) ላይ ምርመራውን አጠናቆ መዝገቡን ያስተላለፈለት ቢሆንም፣ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ክስ መመሥረት አለመቻሉን ማክሰኞ መስከረም 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ለፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን ዓቃቤ ሕግ ክስ ላለመመሥረት ያቀረበው ምክንያት አሳማኝ አለመሆኑን ገልጿል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በእነ ወ/ሮ ፀዳለ ላይ ክስ ያልመሠረተው የተሰጠው ጊዜ አጭር ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በእነሱ መዝገብ መካተት ያለባቸው ሌሎች ተጠርጣሪዎች በመኖራቸውና የምርመራ ሒደቱን አጠናቆ አንድ ላይ ለማቅረብ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በጠበቆቻቸው አማካይነት ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ተጠርጣሪዎቹ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ ጉዳት አድርሰዋል? ወይስ አላደረሱም? የሚለውን ለማወቅ መሥራት የጀመረው በ1999 ዓ.ም. ነው፡፡ የምርመራ መዝገብ የተከፈተውም በ2003 ዓ.ም. መሆኑንና ተጠርጣሪዎቹም በቁጥጥር ሥር ከዋሉ አንድ ወር ከ15 ቀናት እንደሆናቸው አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን የምርምራ ሥራውን ማጠናቀቁንና ለዓቃቤ ሕግ በማስረከቡ፣ ዓቃቤ ሕግ በተሰጠው ጊዜ ክስ እንዲመሠርት ትዕዛዝ መስጠቱን አስታውሰው፣ መርማሪ በድኑ በዘጋው የምርመራ መዝገብ ውስጥ አዲስ ተጠርጣሪዎች ይካተቱና የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ማለቱ ተገቢና የሕግ መሠረት ስለሌለው ሊሰጠው እንደማይገባ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ የተለያየ ምክንያት እየፈጠረ ጊዜውን ለመራዘም ጥያቄ ማቅረቡ የተጠርጣሪዎችን መብት ከመጋፋቱም በላይ፣ ተገቢ ያልሆነና የሕግ መሠረት የሌለው በመሆኑ የዋስትና መብታቸው ተከብሮላቸው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ከመርማሪ ቡድኑ የቀረበለትን የምርመራ መዝገብ ዓይቶና መርምሮ ሲቀበል ክስ ለመመሥረት በቂ መሆኑን ካረጋገጠና ፍርድ ቤት ቀርቦ የክስ መመሥረቻ ጊዜ አስፈቅዶ እያለ፣ ተጠርጣሪዎቹን አስሮ ለሌላ ተጠርጣሪ መያዣ ሊያደርጋቸው እንደማይገባም አስረድተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ ተጠርጣሪዎቹ የተጠረጠሩበት ወንጀል ከአሥር ዓመታት በላይ ሊያስቀጣቸው ስለሚችል ዋስትናውን እንደሚቃወም አስረድቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም ወገኖች ክርክር ካደመጠ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ ዓቃቤ ሕግ ክስ ላለመመሥረቱ ያቀረበው ምክንያት እንዳልተቀበለው በመግለጽ፣ ቀደም ብለው የክስ መመሥረቻ ከሚፈቀድለት ጊዜ ቀንሶ እንደነበር በማስታወስ፣ መስከረም 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ክሱን መሥርቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

 

 

Standard (Image)

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ በቁጥጥር ሥር ውለው ፍርድ ቤት ቀረቡ

$
0
0

 

  • 10.5 ሚሊዮን ብር ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረዋል
  • የእነ አቶ ዓለማየሁ ጉጆ የምርመራ ሒደት ተጠናቀቀ

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የፋይናንስና አስተዳደር ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ደጉ ላቀው፣ ጳጉሜን 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው መስከረም 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ተጠርጣሪውን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልዩ ምድብ  ተረኛ ችሎት አቅርቦ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪው በሚኒስቴሩ የፋይናንስና አስተዳደር ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ናቸው፡፡ ግለሰቡ ትራንስናሽናል ኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር ያለውን የሥራ ውል እንዳቋረጠ እያወቁ ስምንት ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ማድረጋቸውን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡

አቶ ደጉ ከድርጅቱ ጋር በጥቅም በመመሳጠር ተሽከርካሪዎቹ እንዲገቡ በማድረጋቸው፣ መንግሥት ከቀረጥ ሊያገኝ ይችል የነበረውን ከ10.5 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲያጣ ማድረጋቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

በመሆኑም ተጠርጣሪው በእነ አቶ ዓለማየሁ ጉጆ የምርመራ መዝገብ 17ኛ ተጠርጣሪ ሆነው እንዲካተቱለት ፍርድ ቤቱን ከጠየቀ በኋላ፣ በተጠርጣሪው ላይ ቀሪ ምርመራዎች እንዳሉት በመጥቀስ 14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ አማካሪው የተጠረጠሩበትን የጉዳት መጠን ያወቁት ከምርመራው ውጤት ስለመሆኑና አለመሆኑን መርማሪ ቡድኑን ጠይቆት፣ የአቶ ደጉ የወንጀል ተሳትፎ የተገኘው ከሌሎቹ ተጠርጣሪዎች የምርመራ ውጤት መሆኑን አስረድቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ በተመሳሳይ የምርመራ መዝገብ ከወር በፊት በቁጥጥር ሥር ውለው በምርምራ ላይ ያሉትን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለማየሁ ጉጆን ጨምሮ፣ በ16 ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራውን አጠናቆ የምርመራ መዝገቡን ለዓቃቤ ሕግ ማስረከቡን አስታውቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የምርመራ መዝገቡ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መድረስ አለመድረሱን ተወክለው ከቀረቡት ዓቃቤ ሕግ አቶ ሰይፉ ገብር አረጋግጧል፡፡ ዓቃቤ ሕጉ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት የምርመራ መዝገቡ ለተቋሙ መድረሱን ሰምተዋል፡፡ የምርመራ መዝገቡ እንደሚያስረዳው ደርሷል የተባለው ወንጀል ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት በመሆኑና ከአሥር ዓመታት በላይ ሊያስቀጣ እንደሚችል በመግለጽ ዋስትና እንደሚቃወሙ ተናግረዋል፡፡ ክስ የሚመሠረትባቸው ተቋማትን ጨምሮ 19 በመሆናቸውና ሰፊና ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ሕጉ የሚፈቅደውን ሙሉ 15 ቀናት እንዲፈቀድላቸው አመልክተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ በተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ለመጀመርያ ጊዜ የቀረቡት የፋይናንስና አስተዳደር ጉዳዮች አማካሪ አቶ ደጉ ላቀው፣ የተጠረጠሩበት ድርጊት ቀደም ብለው በቁጥጥር ሥር በዋሉት ተጠርጣሪዎች የምርመራ ውጤት የተገኘ በመሆኑ፣ መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን ቀጥሎ ዓቃቤ ሕግ በሌሎች ተከሳሾች ላይ ከሚያቀርበው ክስ ጋር የእሳቸውንም አካቶ እንዲያቀርብ አሳስቧል፡፡

ክስ ለመመሥረት ዓቃቤ ሕግ 15 ቀናትን የጠየቀ ቢሆንም 11 ቀናት በቂ መሆኑን በመግለጽ መስከረም 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ክስ እንዲመሠረት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

 

 

Standard (Image)

ዳንጎቴ ሲሚንቶ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ዕርቅ አወረደ

$
0
0

 

በ2008 እና በ2009 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ተቀጣጥሎ በነበረው ሕዝባዊ አመፅ ሳቢያ ሁለት ጊዜ ንብረቶቹ የተጎዱበት ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ የ2010 ዓ.ም. ዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ባዘጋጀው የዋዜማ ድግስ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ዕርቅ አወረደ፡፡

ቅዳሜ ጳጉሜን 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ 85 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምዕራብ ሸዋ ዞን አዳበርጋ ወረዳ፣ ልዩ ስሙ ረጂ በተባለ አካባቢ በሚገኘው ግዙፉ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ቅጥር ግቢ ፍሪዳዎች ተጥለው፣ የተለያዩ መጠጦች ቀርበው የአገር ሽማግሌዎች በተገኙበት፣ የድርጅቱ ማኔጅመንትና ሠራተኞች የአዲስ ዓመት አቀባበል በዓል ባከበሩበት ሥነ ሥርዓት ላይ የዕርቅ ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የዳንጎቴ ሲሚንቶ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ዲፕ ካማራ በሥራ ላይ ብዙ አለመግባባቶችና ግጭቶች መፈጠራቸውን አስታውሰው፣ ይህን ሁሉ ተቋቁሞ ዳንጎቴ ሲሚንቶ ኢትዮጵያ በየዕለቱ እያደገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹እያንዳንዳችሁ የዳንጎቴ ቡድን አባል ናችሁ፡፡ የዳንጎቴ ኢትዮጵያ ቡድን አፍሪካ ውስጥ ካለው ምርጡ ነው፡፡ ለምን እንጣላለን? እስከ መቼ እንጋጫለን? አብረን በጋራ ሠርተን በጋራ መበልፀግ ይኖርብናል፤›› ያሉት ሚስተር ዲፕ፣ በሥራ ላይ ለተፈጠሩ ስህተቶች ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

‹‹የኦሮሞ ሕዝብ ደግና ይቅር ባይ እንደሆነ ተነግሮኛል፡፡ ይቅር በሉና እንደ ጉዲፈቻ ልጃችሁ ተቀበሉኝ፤›› ሲሉ የአገር ሽማግሌዎችንና የአካባቢውን ሕዝብ ተማፅነዋል፡፡ በዝግጅቱ ላይ ከ1,500 በላይ የአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የድርጅቱ ሠራተኞችና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ባለሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡

የአካባቢው ሽማግሌዎች የሚስተር ዲፕን የይቅርታ ጥያቄ ተቀብለው መርቀው የኦሮሞ ስም አውጥተው የድርጅቱ ሠራተኞችና የአካባቢው ነዋሪ አብረዋቸው እንዲሠሩ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በተወካያቸው አቶ ብርሃኑ ፈይሳ አማካይነት ባስተላለፉት መልዕክት፣ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ለኩባንያው እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

ሚስተር ዲፕ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያቸው ከኅብረተሰቡ ጋር አብሮ ተባብሮ ለመሥራት ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ‹‹አብሮ የመሥራት መንፈስ ለመፍጠር ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ሆን ብለን የፈጸምነው ስህተት የለም፡፡ ነገር ግን ብዙ አለመግባባቶች ነበሩ፡፡ በሥራ ሒደት የወሰድናቸው አንዳንድ የአስተዳደር ውሳኔዎችን እኔ እንደ ስህተት ባላያቸውም አንዳንድ ግለሰቦችን ቅር አሰኝተው ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የከተማና ቤቶች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኢንቨስትመንት ለአንድ አካባቢ በረከት ነው፡፡ ‹‹አንድ ኢንቨስትመንት ወደ አንድ ክልል ሲመጣ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፣ የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ ይቀይራል፣ የሕዝቡን አምራችነት ያሻሽላል፡፡ ከዚህ አንፃር የዳንጎቴ ቡድን ወደ ክልላችን መምጣቱ ትልቅ በረከት ነው፤›› ያሉት አቶ ሽመልስ፣ በዳንጎቴ ሲሚንቶ ኢትዮጵያ የቀድሞ ማኔጅመንት በኩል የታዩ አንዳንድ ችግሮች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

‹‹የቀድሞ ማኔጅመንት በአካባቢው ማኅበረሰብና በሠራተኛው ላይ ችግር ፈጥሯል፡፡ በአብዛኛው ሥራውን ለኤጀንሲዎች ሰጥቶ ኤጀንሲዎቹ ደግሞ ለጥቅማቸው ብቻ ትኩረት በመስጠታቸው፣ በሠራተኛውና በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ ችግር ሲፈጥሩ ቆይተዋል፤›› ያሉት አቶ ሽመልስ፣ ጥቂት ግለሰቦች በኩባንያውና በክልሉ መንግሥት ላይ የነበሩ አንዳንድ የአሠራር ክፍተቶችን በመጠቀም ግጭቱን ሲያባብሱ እንደቆዩ ተናግረዋል፡፡

አቶ ሽመልስ የክልሉ መንግሥት ካካሄደው ጥልቅ ተሃድሶ በኋላ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ በመግባት ባሳለፈው ውሳኔ ኤጀንሲዎች እንዲወጡ በማድረግ፣ የአካባቢው ወጣቶች በማይክሮ ኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው ሥራውን በቀጥታ ከኩባንያው ውል ፈጽመው እንዲረከቡ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ዕርምጃው ሁለት ትልልቅ ጥቅሞች አሉት፡፡ አንደኛ ሕዝቡ ግልጽነት ባለው አሠራር ተሳትፎ በሠራው ልክ ተጠቃሚ እንዲሆን ዕድል ይሰጣል፡፡ በባለቤትነት ስሜት ፋብሪካው የእኔ ነው ብሎ እንዲያስብ ያደርገዋል፡፡ ሁለተኛ ሠራተኛው በአግባቡ ከተያዘ አምራችነቱ ስለሚጨምር ፋብሪካው የበለጠ ምርታማ ይሆናል፡፡ ይኼ ጥሩ የሆነ የሥራ ድባብ ይፈጥራል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ሽመልስ ያለፈውን ስህተት በማረምና ከስህተቶች በመማር አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን አብስረዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል የውጭና የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ሰፊ ሥራ ማከናወኑን የገለጹት አቶ ሽመልስ፣ ዳንጎቴ ሲሚንቶ ዘግቶ ሊወጣ ነው ተብሎ የተዛመተው ዜና ‹‹ተራ አሉባልታ ነው፤›› በማለት አስተባብለዋል፡፡

‹‹የነበሩ ችግሮችን ፈትተን፣ ፋብሪካው በአዲስ ምዕራፍ የበለጠ ምርታማ ሆኖ፣ የአካባቢውን ሕዝብ ተጠቃሚ አድርጎና ሌሎች የውጭ ኢንቨስትመንቶችን የሚስብበትን ሁኔታ ነው ያመቻቸነው፤›› ብለዋል፡፡

ዳንጎቴ ሲሚንቶ በናይጄሪያዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ የተቋቋመው ዳንጎቴ ኢንዱስትሪስ ኩባንያ አንድ አካል ሲሆን፣ የኢትዮጵያው ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በ700 ሚሊዮን ዶላር ተገንብቶ በሰኔ 2007 ዓ.ም. ምርት መጀመሩ ይታወሳል፡፡ በዓመት 2.5 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካው፣ ለ1,500 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡

ኩባንያው በአሁኑ ወቅት የሲሚንቶ ከረጢት ፋብሪካ በመገንባት ላይ ሲሆን፣ ሁለተኛ የሲሚንቶ ፋብሪካ ለመገንባት አቅዶ የነበረ ቢሆንም በተፈጠሩ አንዳንድ ችግሮች ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ አቋርጦታል፡፡

ምንጮች ለሪፖርተር እንደናገሩት ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ የተገነባው 700 ሚሊዮን ዶላር ሙሉ በሙሉ ከናይጄሪያ በመጣ ገንዘብ ሲሆን፣ ከአገር ውስጥ የተወሰደ ምንም ዓይነት ብድር የለም፡፡ በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረው ሁከትና ግጭት ሁለት ጊዜ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የተገዙ ተሽከርካሪዎችና ማሽኖች ቢቃጠሉበትም ለመንግሥት ምንም ዓይነት የካሳ ጥያቄ እንዳላቀረበ የገለጹት ምንጮች፣ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሚስተር አሊኮ ዳንጎቴን አስጠርተው ኩባንያቸው በእርሻው ዘርፍ በተለይ በስኳር ልማት ኢንቨስት እንዲያደርግ ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች አዎንታዊ ምላሽ እንደሰጡ ተናግረዋል፡፡

ዳንጎቴ ኢንዱስትሪስ በኢትዮጵያ ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ያደረገ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በብር የሚያገኘውን ትርፍ በዶላር መንዝሮ ወደ አገሩ ለመውሰድ አገሪቱ በገጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት በመቸገሩ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ ለማስቀመጥ መገደዱን የገለጹት ምንጮች፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባደረገለት ቀና ትብብር በቅርቡ ለመጀመርያ ጊዜ ናይጄሪያ ወደሚገኘው ዜኒት ባንክ ዶላር ማስተላለፍ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ 

Standard (Image)

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተው ግጭት መቆሙ ተነገረ

$
0
0

 

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር  ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በሚኖሩ ዜጎች የተነሳው ግጭት ለሰው ሕይወት መጥፋትና ለንብረት መውደም ምክንያት ቢሆንም አሁን ግን ቆሟል፡፡

የዚህ ችግር ዋነኛ መንስዔ ምን እንደሆነ እስካሁን ድረስ እየተጣራ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ ለዚህ ችግር መንስዔ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ነው የተባለውን ለማጣራት መንግሥት ባደረገው ጥረት ይህ ኃይል እንዳልሆነ የክልሉ መንግሥት መናገሩን ጠቅሰዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው ማክሰኞ መስከረም 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በዚህ ግጭት ላይ እየተሳተፉ ያሉ አካላት ሦስት ናቸው፡፡ እነሱም የሶማሌ ክልል ልዩ የፖሊስ ኃይል፣ የሶማሌ ክልል የሚሊሻ አባላትና ከሶማሊያ ሪፐብሊክ የመጡ ግለሰቦች ናቸው፡፡ በተለይም የሶማሊያ ዜግነት ያለው ሹኔኬኖ አብዲ የሚባል ሰው በግጭቱ መሀል መያዙንና ይህም በወቅቱ ከተያዙ ሰዎች ማረጋገጥ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

አቶ አዲሱ፣ ‹‹ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያሉ አስተዳደራዊ ወሰኖች የግጭት መነሻ እንዳይሆኑ ስንሠራ ቆይተናል፤›› ብለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጋር ያለውን አስተዳደራዊ ግጭት ለመፍታትም በ1997 ዓ.ም. በሁለቱ ክልሎች መካከል ተደርጎ በነበረው ሕዝበ ውሳኔ መሠረት፣ ሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር አማካይነት ከ85 በመቶ በላይ ያለውን አስተዳደራዊ ወሰን ማካለል መቻሉን አስታውሰዋል፡፡

ሁለቱ ክልሎች በመቀራረብ የነበሩ ችግሮችን ፈትተው በጋራ በመሥራት ላይ እያሉ በድጋሚ ግጭት መቀስቀሱን አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡ ቦረናና ሞያሌ በሚባል ወረዳ በተለምዶ ጫሙክ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተነሳው ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት መውደም መከሰቱን አስታውቀዋል፡፡

አቶ አዲሱ በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግሥት ሕዝቡን አስተባብሮ ራሱን እንዲከላከል እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ እንዲከላከል ብቻ ሳይሆን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግሥት ጋር በመገናኘት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

‹‹ይህንን ግጭት ከአስተዳደራዊ ወሰኑ ጋር የማያያዝ ነገር አለ፡፡ ሁለተኛ ግጭቱ የኢትዮጵያ ሶማሌና የኦሮሞ የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት አድርጎ የማየት ነገር አለ፤›› ያሉት አቶ አዲሱ፣ እነዚህ ሁለቱ ጉዳዮች እጅግ የተሳሳቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኦሮሞና የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝብ አብሮ የኖረና አሁንም ድረስ አብሮ እየኖረ ያለ በመሆኑ፣ በሕዝቦች መካከል ግጭት እንደሌለና ወደፊትም እንደማይኖር እምነታቸው መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በተያያዘ ዜና በኦሮሚያ ክልል በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሁለቱ ክልሎች መካከል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ባወጡት መግለጫ፣ የችግሩ ምንጭ የሶማሌ ልዩ ኃይል ነው ብለዋል፡፡ ፓርቲዎቹ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ)፣ የኦሮሞ አንድነት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦአዴፓ)፣ የኦሮሞ አቦ ነፃነት ግንባር (ኦአነግ)፣ የገዳ ሥርዓት አራማጅ ፓርቲ (ገሥአፓ)፣ የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር (ኦነአግ) እና የኦሮሞ ነፃነት ብሔራዊ ፓርቲ (ኦነብፓ) ናቸው፡፡ ፓርቲዎቹ ባወጡት የአቋም መግለጫ በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ የጦር መሣሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀና በወታደራዊ ፓትሮል ተሽከርካሪዎች የሚታገዝ የሶማሌ ልዩ ኃይል ባዶ እጁን በሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ሚሊሻ ላይ ከፍተኛ ጉዳትና ዕልቂት እያደረሰ መሆኑን ፓርቲዎቹ ገልጸዋል፡፡

ግጭቱ በሕዝብ መካከል እንዳልሆነ የጠቆሙት ፓርቲዎቹ፣ ይህን ችግር እያደረሰ ያለው የሶማሌ ልዩ ኃይል በኦሮሞ ሕዝብ ላይ እያደረገ ነው ያሉትን ድርጊት ‹‹ያልታወጀ ጦርነት›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡

ፓርቲዎች የንብረትና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸውና ለሞቱ ወገኖች አጥፊው ወገን ተገቢው ካሳ እንዲከፍልና በሕዝቦች መካከል ዘላቂነት ያለው ሰላም እንዲወርድ አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል ማክሰኞ ምሽት ማተሚያ ቤት ከመግባታችን በፊት በኦሮሚያ ክልል በተለይም በምዕራብ ሐረርጌና በምሥራቅ ሐረርጌ አንዳንድ አካባቢዎች የተቃውሞ ሠልፎችና ግጭቶች እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስላደረሰው ጉዳት ግን ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ 

Standard (Image)

የቤቶች ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤትና የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ከፍተኛ ኃላፊዎች ተከሰሱ

$
0
0

በሁለቱ ተቋማት ከ74.9 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ደርሷል ተብሏል

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ወ/ሮ ፀዳለ ማሞን ጨምሮ 13 የተለያየ ኃላፊነት በነበራቸው ግለሰቦች፣ በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ዘነበ ይማምን ጨምሮ ሦስት የተለያየ ኃላፊነት በነበራቸው ግለሰቦች ላይ፣ ዓርብ መስከረም 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሁለቱም ተቋማት ኃላፊዎች ላይ ክስ የመሠረተው በተለያየ የክስ መዝገብ ሲሆን፣ በሁለቱም ተቋማት በኃላፊነት ተመድበው ይሠሩ የነበሩት ግለሰቦች በድምሩ ከ74.9 ሚሊዮን ብር በላይ በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ላይ ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ሰባቱ ተከሳሾች ማለትም ዋና ሥራ አስኪያጇ ወ/ሮ ፀዳለ ማሞ፣ የሎጂስቲክስ አስተዳደርና ፋይናንስ መምርያ ኃላፊ አቶ የማነ ፀጋዬ፣ የመሬት ዝግጅት የመሠረተ ልማትና ዲዛይን ረዳት መምርያ ኃላፊ ወ/ሮ ሳባ ገብረ መድኅን፣ የፕላንና ዶክመንቴሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ሽመልስ ዓለማየሁ፣ የኮንስትራክሽንና ሱፐርቪዥን መምርያ ኃላፊ አቶ የማነ አብርሃ ተስፋ ሥላሴ (የአሰር ኮንስትራክሽን ባለድርሻ ሲሆኑ ያልተያዙ ናቸው)፣ የመሬት ዝግጅት መሠረተ ልማትና ዲዛይን መምርያ ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ደምረው (ያልተያዙ) እና የውስጥ ኦዲትና ኢንስፔክሽንና አገልግሎት መምርያ ኃላፊ አቶ ሲሳይ በቀለ (ያልተያዙ)፣ የጽሕፈት ቤቱ የማኔጅመንት ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡ ተከሳሾቹ የመንግሥትን የግዥ ሥርዓት ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዕቃና የአገልግሎት ግዥ መምርያ ቁጥር 4/1991 አንቀጽ 6(2)ን በመተላለፍና የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ሕገወጥ ክፍያ መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

ተከሳሾቹ የጥቅም ግንኙነት በመፍጠር የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ያወጣውን ጨረታ በመጠቀምና አሸናፊ የሆኑትን ለማሠራት በመወሰን አፈር ቆርጦ ለመጣል፣ ለማጓጓዝና ገረጋንቲ ለመሙላት የ33,384,526 ብር ግዢ ከየማነ ግርማይ ኮንስትራክሽን መሣሪያዎች አከራይ ድርጅት እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ ይህም ሕገወጥ ግዥ መሆኑን አክሏል፡፡

ማክሼብ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ቢኤ ኦሜጋ ቢዝነስ ግሩፕና ፍትዊ ወልዳይ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ድርጅቶች አፈር ቆርጦ ለመጣል፣ ገረጋንቲ ሞልቶ ለመጠቅጠቅና ለማጓጓዝ ካሸነፉበት የጨረታ ዋጋ በላይ ከ80 እስከ 120 በመቶ የሚሆን ከፍተኛ ዋጋ ላቀረበው የማነ ግርማይ ኮንስትራክሽን መሣሪያዎች አከራይ ድርጅት በመስጠት፣ በመንግሥት ላይ 11,979,848 ብር ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡

ተከሳሾቹ የአስተዳደሩን የግዥ መመርያ በማክበር የሚፈለገውን ዕቃ ይገኝባቸዋል ተብሎ የሚታመንባቸውን ተጫራቾች በአቅራቢዎች ዝርዝር ውስጥ የተመዘገቡትን በማሳተፍ ሦስቱን መርጠው ማወዳደር ሲገባቸው፣ ሥልጠናቸውን አላግባብ በመገልገል የሎደር ኪራይ አገልግሎት ግዥ ከመመርያው በተቃራኒ ሁለት ድርጅቶችን ብቻ ማወዳደራቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ የሎደር ኪራይ አገልግሎቱንም ለየማነ ግርማይ ኮንስትራክሽን መሣሪያዎች አከራይ ድርጅት በመስጠት 950,246 ብር እንዲከፈለው ማድረጋቸው አግባብ እንዳልሆነም አክሏል፡፡ ለገረጋንቲ ግዥና ለማጓጓዣያ ያላግባብ 206,638 ብር፣ እንዲሁም ገረጋንቲ ለመጠቅጠቅ 6,007 ብር፣ አፈር ቆርጦ ለመጣል 2,893 ብር በድምሩ 185,242 ብር ያላግባብ ክፍያ እንዲፈጸም በማድረግ በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ በዝርዝር አስረድቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በሌላ ክስ የመሠረተባቸው የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ዘነበ ይማም (ሁለት ክስ ቀርቦባቸዋል) እና የጠቅላላ ሒሳብ ቡድን መሪ አቶ በለጠ ዘለለው ናቸው፡፡ በሁለቱ ተከሳሾች ላይ የቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው በ2005 ዓ.ም. መጨረሻና በ2006 በጀት ዓመት መጀመርያ ላይ ፋብሪካውን ለማስጠገን በማሰብ፣ የህንድ ኩባንያ ከሆነው ስሪ ስታር ጋር ውል ይፈጽማሉ፡፡

ውሉን ሲዋዋሉ በድርጅቱ ውስጥ ቀደም ብሎ የተገዙ ለፋብሪካው ጥገና ሊውሉ የሚችሉ መለዋወጫዎች በፋብሪካው መደርደርያ ላይ እንዳለ እያወቁ፣ የዕቃ አቅርቦት፣ ጥገናና ሙከራ በማለት የ1,293,850 ዶላር ውል መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ በመሆኑም ፋብሪካው ዕቃው እያለው 861,850 ዶላር ወይም 16,289,180 ብር ያላግባብ ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጋቸውንም አክሏል፡፡

የፋብሪካው ጥገና የተፈለገው የማምረት አቅሙን ለማሻሻል ቢሆንም፣ ፋብሪካው በአግባቡ አለመጠገኑን በማየት በውሉ መሠረት ኃላፊዎቹ ውሉን ማቋረጥ ሲገባቸው፣ የውሉን 90 በመቶ 22,296,865 ብር ክፍያ በመፈጸማቸውና በፋብሪካው ላይ የምርት ብክነትና የ36,363,600 ብር ጉዳት መድረሱን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ በተጨማሪም ለሠራተኞች የተከፈለውን 97,325 ብር ባለመቀነሳቸው ጉዳት መድረሱን ዓቃቤ ሕግ አክሏል፡፡ በድምሩ በፋብሪካው ላይ የ54.6 ሚሊዮን ብር ጉዳት መድረሱንም አስታውቋል፡፡

አቶ ዘነበ ይማም የፋብሪካው የአገር ውስጥና የውጭ ግዥ ቡድን አስተባባሪ አቶ እንዳልካቸው ግርማና የውጭ አገር ግዥ ሲኒየር ኦፊሰር ከሆኑት አቶ ኃየሎም ከበደ ጋር ሌላ ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ እንደ ዓቃቤ ሕግ ክስ ሦስቱም የፋብሪካው ኃላፊዎች በድምሩ ከ7.1 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

ኃላፊዎቹ በመንግሥት ላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባለው ከተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች ጋር ከፈጸሟቸው አምስት የተለያዩ ግዢዎች ጋር በተያያዘ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ አስረድቷል፡፡

ለፋብሪካው የሚሆኑ መለዋወጫዎችን ሞካር ኢንተርፕራይዝ ከሚባል የህንድ ኩባንያ፣ ፋንታነ ቢቪ ከተባለ የኔዘርላንድ ኩባንያ፣ ዩኒንግ ሆላንድ ከተባለ የኔዘርላንድ ኩባንያ (ሁለት ጊዜ) እና ኤስኤኤፍ ሰልፈር ይክታሪ ከተባለ የሳዑዲ ዓረቢያ ኩባንያ በድምሩ በ13,104,049 ብር ግዥ መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ ግዥ የተፈጸመው ግን ከኩባንያዎቹ ጋር ውል ሳይፈጸም በመሆኑ አቅራቢዎቹ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ዕቃውን ባያቀርቡ፣ በዕቃ ግዥ ዋጋ ላይ በየቀኑ ዜሮ ነጥብ አንድ በመቶ ይከፈላል የሚለውን የስኳር ኮርፖሬሽን መመርያን የማያከብርና የሚጥስ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ አብራርቷል፡፡ በመሆኑም ኃላፊዎቹ በተለያዩ ጊዜያትት በድምሩ 7,151,146 ብር በመክፈል ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ በዝርዝር ጠቅሷል፡፡

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ)፣ 33 እና 411(2እና3) 407(1ሀ)ን በመተላለፍና ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም፣ 13,162,161 ብር በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽንም ኃላፊዎች ተመሳሳይ የወንጀል ሕግ ድንጋጌን በመተላለፍ በድምሩ 20,313,307 ብር ጉዳት በመንግሥት ላይ ማድረሳቸውንም የዓቃቤ ሕግ ክስ ያሳያል፡፡ በሁለቱ ተቋማት በድምሩ ከ74.9 ሚሊዮን ብር በላይ በመንግሥት ላይ ጉዳት መድረሱን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡

ፍርድ ቤቱ በችሎት እንደተናገረው በሁለቱም ተቋማት ኃላፊዎች ላይ የተጠቀሰው የሕግ አንቀጽ ከአሥር ዓመታት በላይ የሚያስቀጣና ዋስትናም የሚከለክል ነው፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የክስ መቃወሚያ ለመጠባበቅ ለጥቅምት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ የውጭ ግዢ ሲኒየር ኦፊሰር አቶ ኃየሎም ከበደ አቅም ስለሌላቸው ጠበቃ ማቆም እንደማይችሉ በመግለጻቸው ቃለ መሀላ እንዲፈጽሙ ተደርጎ፣ የተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤት ተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ጽሕፍት ቤት የፋይናንስ አስተዳደር መምርያ ኃላፊ ወ/ሮ አልማዝ አይናለምና የግዢ አቅርቦት መምርያ ኃላፊ አቶ ወንድሙ መንግሥቱ የተጠቀሰባቸው የወንጀል ሕግ አንቀጽ ዋስትና ስለማይከለክል፣ ፍርድ ቤቱ እያንዳንዳቸው 15 ሺሕ ብር ዋስ በማስያዝ ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ 

Standard (Image)

በሙስና የተጠረጠሩት የስኳር ኮርፖሬሽንና የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊዎች ክስ ተመሠረተባቸው

$
0
0

 

  • በድምሩ ከ228.2 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብሏል

  ከፍተኛ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ለ50 ቀናት በጊዜ ቀጠሮ ላይ የነበሩት የስኳር ኮርፖሬሽንና የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊዎች ላይ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ መሠረተ፡፡

 ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት መስከረም 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በተለያዩ መዝገቦች ክስ የመሠረተባቸው፣ በስኳር ኮርፖሬሽን የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ስድስት ኃላፊዎችና አንድ ነጋዴ ላይ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን አራት ኃላፊዎችና አንድ የውጭ አገር ዜጋ ላይ ነው፡፡

      በስኳር ኮርፖሬሽን የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ተከሳሾች የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ፈለቀ ታደሰ፣ የግዥና ንብረት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ኤፍሬም ዓለማየሁ፣ የአገዳ ተከላና ፋብሪካ ግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ አበበ ተስፋዬ፣ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ዮሴፍ በጋሻው፣ የመሬት ልማትና ዝግጅት ቡድን መሪ የነበሩት አቶ ወንድምአገኝ ታፈሰና የመሬት ልማትና ዝግጅት ሱፐርቫይዘር የነበሩት አቶ ሰለሞን ገነቱ ሲሆኑ፣ በንግድ ሥራ የተሰማሩት የየማነ ግርማይ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ የማነ ግርማይም የክሱ አካል ናቸው፡፡

      ተከሳሾቹ የማይገባ ጥቅም ለማግኘትና ለማስገኘት በማሰብ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመገልገል የኮርፖሬሽኑ የግዥ አፈጻጸም መመርያ ተከትለው ውል መዋዋልና የተዋዋሉትን ማሠራት ሲገባቸው፣ መመርያውን በመተላለፍና ከሌሎች ጋር በመመሳጠር በጠቅላላው ከ95,830,906 ብር በላይ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸው ክስ ያስረዳል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በክሱ እንዳብራራው በ2006 ዓ.ም. ለተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ መሬት ዝግጅት ሥራ ባቱ ኮንስትራክሽን በአንድ ሔክታር 25,818 ብር ሒሳብ 1,000 ሔክታር መሬት ለማዘጋጀት ተመጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ፣ በ29,691,551 ብር ለመሥራት የስምምነት ውል ፈጽሟል፡፡ ነገር ግን በስኳር ኮርፖሬሽን የግዥ አፈጻጸም መመርያ መሠረት የሥራ አመራር ኮሚቴው ሳይፈቅድ ተከሳሾቹ በውስን ጨረታ በተጋነነ ዋጋ ሥራውን ከባቱ ኮንስትራክሽን በመንጠቅ፣ ለየማነ ግርማይ ጠቅላላ ተቋራጭ መስጠታቸውን ገልጿል፡፡ ለ1,000 ሔክታር ተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ በ82,972,500 ብር መስጠታቸውንም ዓቃቤ ሕግ ጠቅሷል፡፡ ልዩነቱም 53,820,949 ብር መሆኑንና ሥራውን በዋናነት የፈጸሙትም ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ፈለቀ ታደሰ መሆናቸውንም አክሏል፡፡

ተከሳሾቹ በተጋነነ ዋጋና በውስን ጨረታ ለተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ መሬት ዝግጅት ለየማነ ግርማይ ጠቅላላ ተቋራጭ የሰጡት፣ አቶ የማነ ለከሰም ስኳር ኮርፖሬሽን ሰጥተውት የነበረውን ውል የተጋነነ ዋጋ ወደ ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በማዛወር መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ አቶ ኤፍሬምና አቶ አበበ የተባሉት ተከሳሾች በኮርፖሬሽኑ የግዥ አፈጻጸም መመርያ ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ የመሬት ዝግጅት ሥራ በውስን ጨረታ መፈጸም እንደማይቻል እያወቁ፣ ለከሰም ስኳር ፋብሪካ የተሰጠን ዋጋ ለተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በተጋነነ ዋጋ ሲሰጥ እያወቁ ዝም ብለው በማለፋቸው፣ በልዩነት 53,280,949 ብር ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ተንትኗል፡፡

አቶ ዮሴፍ፣ አቶ ወንድማገኝና አቶ ሰለሞን ከአቶ የማነ ግርማይ ጋር በመመሳጠር የተንዳሆ መሬት ዝግጅት ከባቱ ኮንስትራክሽን ተነጥቆ ለየማነ ግርማይ ጠቅላላ ተቋራጭ እንዲሰጥ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ ጠቁሟል፡፡ ባቱ ኮንስትራክሽን ከተሰጠው 1,000 ሔክታር ውስጥ 487.18 ሔክታር ተሠርቶ እያለ የማነ ግርማይ ጠቅላላ ተቋራጭ ሙሉውን ሥራ የሠራ በማስመሰል ክፍያ እንዲፈጸም በማድረግ፣ 42,549,957 ብር ያላግባብ እንዲከፈል ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ አብራርቷል፡፡ የመሬት ዝግጅቱ በአግባቡና ጥራቱን በጠበቀ ሁኔታ መሠራት አለመሠራቱን ዓይተው መረከብ ሲገባቸው ሳያረጋግጡ በመረከባቸው፣ በፋብሪካው የውስጥ አቅም በድጋሚ እንዲሠራ በማድረግ ፋብሪካው ተጨማሪ ወጪ እንዲያወጣ ማድረጋቸውንም ገልጿል፡፡

አቶ የማነ ከኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር የከሰም ስኳር ፋብሪካ መሬት ዝግጅት በተጋነነ ዋጋ ጨረታ ካሸነፉ በኋላ ከተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ጋር ምንም ዓይነት ውል ሳይኖራቸው ባቱ ኮንስትራክሽን 1,000 ሔክታር የመሬት ዝግጅት በ29,691,551 ብር እየሠራው የነበረውን ሥራ በ82,972,500 ብር በመሥራትና ጥራት የሌለው ሥራ በማስረከብ በፋብሪካው የውስጥ ኃይል እንዲሠራ በማድረግ በድምሩ ከ95,830,906 ብር የሚገመት ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በሌላ የክስ መዝገብ ክስ የመሠረተባቸው የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩት  ፈቃዱ ኃይሌ (ኢንጂነር)፣ የኮንትራት መንገዶች ቨርዢን ኃላፊ አህመዲን ቡሴር (ኢንጂነር)፣ የዲዛይን መገምገምና ማፅደቅ ኬዝ ቲም አስተባባሪ ዋሲሁን ሽፈራው (ኢንጂነር) እና የዲዛይን ዋና የሥራ ሒደት ሙሉጌታ አብርሃ (ኢንጂነር በሌሉበት) ሲሆኑ፣ የትድሃር ኤክስካቬሽን ኤንድ ኧርዝ ሙቪንግ ሊሚትድ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ሚናሼ ሌቪ በክሱ ተካተዋል፡፡

የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ከእስራኤላዊው ሚስተር ሌቪ ጋር በመመሳጠር በሕዝብና በመንግሥት ላይ የ132,436,433 ብር ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

ባለሥልጣኑ የባቡር ሐዲድ (መስመር) ተከትሎ ከማዕድን ሚኒስቴር በመገናኛና ለም ሆቴል እስከ ውኃ ልማት ሚኒስቴር ድረስ ያለውን መንገድ ለማስገንባት፣ የእስራኤሉን ኩባንያ ትድሃር ኤክስካቬሽን ኤንድ ኧርዝ ሙቪንግ ሊሚትድ ድርጅትን መምረጡን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡ ነገር ግን ባለሥልጣኑ ከድርጅቱ ጋር ውል ሲፈጽም የከተማ አስተዳደሩ የግዥ አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 3/2002 አንቀጽ 15(16)፣ 5(25) እና 15(26) በሚያዘው መሠረት ለቅድመ ክፍያና ለመልካም ሥራ አፈጻጸም የባንክ ዋስትና ማቅረብ የነበረበት ሲሆን፣ ሳያቀርብ ስምምነት ላይ በመድረሳቸው ሥራ ማስጀመራቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

ትድሃር በገባው ውል መሠረት ሥራውን ማስኬድ ባለመቻሉ ከነሐሴ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ውሉ ሲቋረጥ ባለሥልጣኑ ለሥራ ተቋራጩ ከሰጠው የማቴሪያል 17,558,963 ብር፣ የተሽከርካሪ ግዥ 8,360,000 ብርና ቅድመ ክፍያ 106,518,239 ብር በድምሩ 132,436,433 ብር መመለስ የሚገባው ቢሆንም፣ አለመመለሱን ዓቃቤ ሕግ አስታውቋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ተቋራጩ ያቀረበው ዋስትና መመርያው በሚያዘው መሠረት የባንክ ሳይሆን በሁኔታ ላይ የተመሠረተ የኢንሹራንስ ዋስትና በመሆኑ፣ ኢንሹራንስ የሰጠው የኢንሹራንስ ኩባንያ ክፍያ መፈጸም ባለመቻሉ የተጠቀሰውን ያህል የገንዘብ ጉዳት ሊደርስ መቻሉንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡ ሚስተር ሌቪም ከኃላፊዎቹ ጋር በመመሳጠር ማቅረብ የነበረባቸው በባንክ የተያዘ ኢንሹራንስ መሆኑን እያወቁ በጥቅም በመተሳሰር ከላይ የተጠየቁትን ንብረቶች የተረከቡ ቢሆንም፣ በውላቸው መሠረት ሥራውን ማከናወን ባለመቻላቸው ውሉ ሲቋረጥ መመለስ የነበረባቸውን የመንግሥት ንብረት አለመመለሳቸውንም ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ ባቀረቡት በሁኔታ ላይ የተመሠረተ ኢንሹራንስ ስም ክፍያ ሊፈጽሙ አለመቻላቸውን ዓቃቤ ሕግ አክሏል፡፡ የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀ)፣ 33 እና 411 (3) በመተላለፍና ከሚስተር ሌቪ ጋር በመመሳጠር የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት የከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ዓቃቤ ሕግ መሥርቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ ለተከሳሾች እንደገለጸው የተጠቀሰባቸው የወንጀል ሕግ በራሱ ዋስትና ይከለክላል፡፡ በስኳር ኮርፖሬሽን ተከሳሾች ላይ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 407 (1 ሀ እና 3)፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊዎች ላይ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 411( 3) መሆኑንም ፍርድ ቤቱ ጠቅሷል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ነግሮ የክስ መቀወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለጥቅምት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በቀጣይ ቀጠሮ ያልተያዙትን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የዲዛይን ዋና የሥራ ሒደት ኃላፊ ሙሉጌታ አብርሃን (ኢንጂነር) ፌዴራል ፖሊስ ተከታትሎና ይዞ እንዲያቀርብ፣ ሚስተር ሌቪም ከሚገኙበት ማረሚያ ቤት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

Standard (Image)

በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ላይ ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ አማካሪ ታሰሩ

$
0
0

 

  • በሚኒስቴሩና በባለሥልጣኑ ከፍተኛ ኃላፊዎች ላይ ምርመራ ተጠናቀቀ

 የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ ያላግባብ ክፍያ እንዲፈጸም በማድረግ የተጠረጠሩና በፓን አፍሪካ ድርጅት ውስጥ አማካሪ የሆኑ ግለሰብ፣ በቁጥጥር ሥር ውለው ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

ተጠርጣሪው አቶ እስክንድር ሰይድ የሚባሉ ሲሆኑ፣ በባለሥልጣኑ ላይ የተጠቀሰውን ጉዳት ያደረሱት ከሌላ ተቋማት ጋር በማገናኘት መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት አስረድቷል፡፡ የተቋሙን ማንነትና በምን ሁኔታ ግንኙነት ፈጥረው የተጠቀሰውን ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ እንዲፈጸም እንዳደረጉ ለማወቅ ገና በምርመራ ላይ መሆኑን የገለጸው መርማሪ ቡድኑ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀዱለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪው ጠበቃ ደንበኛቸው ባለሥልጣኑን ከየትኛው ተቋም ጋር እንዳገናኙና ክፍያ እንደተፈጸመ መርማሪ ቡድኑ ሳያስረዳ፣ ደንበኛቸውን አስሮ ማስረጃና መረጃ ሊፈልግ ስለማይገባ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ የዋስትና ጥያቄውን በመቃወም ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪው ከተያዙ ገና አንድ ቀናቸው ነው፡፡ የጉዳቱ መጠን የተገኘው ቀደም ብሎ በተጠረጠሩበት ከባድ የሙስና ወንጀል በቁጥጥር ሥር ከሚገኙት ተጠርጣሪዎች ምርመራ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ግለሰቡ አሁን በማማከር ከሚሠሩበት ፓን አፍሪካ ከሚባል ድርጅት ጋር ግንኙነት እንዳለው በማስረዳት ለተጨማሪ ምርመራ የጠየቀው ጊዜ እንዲፈቀድለት በድጋሚ ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪው የጠየቁትን የዋስትና መብት ውድቅ በማድረግ መርማሪ ቡድኑ ከጠየቀው 14 ቀናት አሥር ቀናትን ፈቅዷል፡፡ ለመስከረም 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ከሐምሌ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ቀናቶች በቁጥጥር ሥር በማዋል ሲመረምራቸው በከረሙት፣ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በነበሩት አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል የምርመራ መዝገብ የተካተቱ 12 ተጠርጣሪዎችን የምርመራ ሒደት ማጠናቀቁንና ለዓቃቤ ሕግ ማስረከቡን ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለማየሁ ጉጆ የምርመራ መዝገብ 19 ተጠርጣሪዎችም ላይ ምርመራ ጨርሶ መዝገቡን ለዓቃቤ ሕግ ማስረከቡን ገልጿል፡፡ ዓቃቤ ሕግም መቀበሉን በማረጋገጡ ክስ መሥርቶ መስከረም 12 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

አቶ ዛኪር አህመድ በእነ አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል የምርመራ መዝገብ ምርመራቸው የተጠናቀቀ መሆኑን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በኩል የተጠረጠሩበትን የወንጀል ጉዳይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኦዲተር ቢሮ ሒሳብ እያሠራ በመሆኑ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ የአቶ ዛኪር ጠበቃ ግን የመርማሪ ቡድኑን ጥያቄ በመቃወም እንደገለጹት፣ ደንበኛቸው ከነሐሴ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ ናቸው፡፡ እስካሁን መጨረስ ነበረበት፡፡ አሁንም ቢሆን ኦዲት የሚሠራው የመንግሥት ተቋም በመሆኑ ከእሳቸው ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም መርማሪ ቡድኑ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድለት እንደማይገባ በመግለጽ ተቃውመዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን በማፋጠን እንዲያጠናቅቅና ከሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ጋር ጎን ለጎን በመሥራት ክሱን እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በሌላ የምርመራ መዝገብ ስማቸው የተካተተው በስኳር ኮርፖሬሽን የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የአገዳ ተክልና ፋብሪካ ግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አበበ ተስፋዬን ጨምሮ፣ ስምንት ተጠርጣሪዎችና የኦሞ ኩራዝ አምስት ስኳር ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መልካሙን ጨምሮ ሰባት ተጠርጣሪዎችን የምርመራ ሒደት ማጠናቀቁንና ለዓቃቤ ሕግ ማስተላለፉን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም የምርመራ መዝገቡ ለዓቃቤ ሕግ መድረሱን ካረጋገጠ በኋላ፣ ለመስከረም 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

 

 

Standard (Image)

የኤርትራ መንግሥት የሥጋት ምንጭ የማይሆንበት ደረጃ ላይ መድረሱን መንግሥት አስታወቀ

$
0
0

 

ለዓመታት በአፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ አሸባሪ ቡድኖችን ሲደግፍና ሲያስታጥቅ እንደቆየ የሚነገርለት የኤርትራ መንግሥት፣ በአሁኑ ወቅት የሥጋት ምንጭ የማይሆንበት ደረጃ ላይ መድረሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ሐሙስ መስከረም 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ እንደተናገሩት፣ የኤርትራ መንግሥት አሁን የሥጋት ምንጭ የማይሆንበት ደረጃ ላይ ቢደርስም ዓለም ተለዋዋጭ ከመሆኗ አንፃር አሁን ካለው ሁኔታ ጋር የሚመጥን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መከተል ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ላይ አዲስ ፖሊሲ ለመከተል መወሰኑን ያስታወቀ ቢሆንም፣ ይኼ አዲስ ፖሊሲ ምን እንደሆነና መቼ ተግባራዊ እንደሚሆን እንደማይታወቅ አቶ መለስ አስረድተዋል፡፡ አዲሱ ፖሊሲ ለሕዝብ ሳይገለጽ ረዥም ጊዜ ሊወስድ የቻለው አዲስ ሥልት በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራን በተመለከተ ሦስት ፖሊዎችን ሲከተል መቆየቱንም አብራርተዋል፡፡ እነዚህም ውስጣዊ አቅምን በማጠናከር የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን እንዳይተነኩስ ማድረግ፣ ሁለተኛው ከማተራመስ ባህሪው እንዲወጣ የዲፕሎማሲ ሥራ ማከናወንና አስፈላጊ ሲሆን ተመጣጣኝ ዕርምጃ መውሰድ የሚባሉት መሆናቸውን አክለዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ በ2010 ዓ.ም. በሁለትዮሽና በዓለም አቀፍ ደረጃ የምታካሂደውን የውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴ አጠናክራ የምትቀጥል መሆኗን ተናግረዋል፡፡ በተለያዩ አገሮች በተወከሉ ሚሲዮኖችና በዋናው መሥሪያ ቤት በሚገኙ የሥራ ሒደቶች አማካይነት የተቀናጀ ጥረት በማድረግ፣ አገራዊ ተልዕኮን ለመወጣት የተጠናከረ ሥራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም. ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ጥቅሟና መብቷ እንዲጠበቅና በሌሎች መንግሥታት እንዲከበር ማድረግ፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላት ቅርበት እንዲጠናከር መሥራት፣ ከሌሎች መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የምታደርጋቸውን ግንኙነት ማስተባበር፣ የዳያስፖራውን ተሳትፎና መብት ማረጋገጥ፣ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው በኩል ኢንቨስትመንት መሳብና ሌሎች ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስረድተዋል፡፡

በ2009 ዓ.ም. በተከናወነው ሥራም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት በማስፈን፣ ውክልናን በማስፋትና አጋርነቶችን በመመሥረት በዓለም አቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያን ተደማጭነት ለማሳደግና ጥቅሟን ለማስጠበቅ የሚያስችል ተግባር መከናወኑን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የአፍሪካ ኅብረትን ጉባዔ ሁለት ጊዜ በማስተናገድ በመጀመርያው 43፣ በሁለተኛው ደግሞ 24 ፕሬዚዳንቶች፣ በድምሩ 67 ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም ከ20 ሺሕ በላይ እንግዶች የፕሮቶኮል ድጋፍ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. መስከረም 12 ቀን 2017 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ በኒውዮርክ እንደተጀመረ ያስረዱት አቶ መለስ፣ በዚህ ሳምንት በሚካሄደው ጉባዔ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንደሚገኙና ጉባዔውን በሊቀመንበርነት ይመሩታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡

Standard (Image)

ሰማያዊ ፓርቲ በሐራምቤ ሆቴል የጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ መከልከሉን አስታወቀ

$
0
0

 

ሰማያዊ ፓርቲ በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ መስከረም 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ለማድረግ ባቀደው ሰላማዊ ሠልፍና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ለመስጠት፣ በሐራምቤ ሆቴል ጠርቶት የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ባልታወቀ ምክንያት መከልከሉን አስታወቀ፡፡

የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፓርቲው በወቅታዊና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ለመስጠት ዓርብ መስከረም 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ጠርቶ የነበረ ቢሆንም፣ የፓርቲው ኃላፊዎች ሥፍራው ሲደርሱ የሆቴሉ ኃላፊዎች መግለጫውን መስጠት እንደማይችሉ ገልጸውላቸዋል፡፡

በጉዳዩ ግራ የተጋቡት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችም መግለጫውን ለመስጠት ለሆቴሉ ክፍያ የፈጸሙበትን ደረሰኝ በማሳየት ማብራሪያ ቢጠይቁም፣ የሆቴሉ ኃላፊ ምንም ዓይነት ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት  የፓርቲው አመራሮችና የሆቴሉ ኃላፊዎች ለአንድ ሰዓት ያህል ክርክር ቢያደርጉም፣ የሆቴሉ ኃላፊዎች በአቋማቸው በመፅናታቸው ፓርቲው መግለጫውን በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ዋና ጽሕፈት ቤት ለማድረግ መገደዱን አስታውቋል፡፡

በመኢአድ ዋና ጽሕፈት ቤት የተሰጠውን መግለጫ የመሩት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ አበበ አካሉና የጥናትና ስትራቴጂ ኃላፊው አቶ አሮን ሰይፉ ናቸው፡፡

‹‹በሐራምቤ ሆቴል የጠራነው ጋዜጣዊ መግለጫ መከልከሉ ሥርዓቱ ምን ያህል አፋኝ እየሆነ እንደሄደ ያሳያል፡፡ መንግሥት ከዚህ ቀደም ከተፈጠረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ምንም ዓይነት ትምህርት አለመውሰዱን በትክክል የሚያሳይ ነው፤›› ሲሉ አቶ አሮን ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው ስብሰባውን ለማድረግ ለሆቴሉ 4,400 ብር ከፍሎ እንደነበር ገልጿል፡፡ አቶ አሮን፣ ‹‹ይኼ ሰላማዊ ሠልፍ ወይም ሕዝባዊ ስብሰባ አይደለም፡፡ አንድ ፓርቲ ያዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ ይኼን ማድረግ አለመቻል ደግሞ አፈናው ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሁላችንንም ሊያሳስበን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ አስፈላጊውን ሁሉ ቅድመ ሁኔታ ቢያሟሉም ጋዜጣዊ መግለጫውን ከመስጠት መከልከላቸውን ያወሱት አቶ አበበ፣ ከክልከላው ጀርባ ማን እንዳለ ለማወቅ መቸገራቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት መስከረም 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ለማድረግ ስላቀደው ሰላማዊ ሠልፍ ከመግለጽ በተጨማሪ፣ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መሀል የተፈጠረው ግጭት ለአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ከመሆኑ አንፃር የሚመለከተው አካል በአስቸኳይ ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠርበትን አግባብ እንዲያመቻችም ጠይቋል፡፡  

Standard (Image)

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት በርካቶች ሞተዋል

$
0
0

 

  • ሁለቱ ክልሎች በሟቾች ብዛት የማይጣጣም መግለጫ ሰጥተዋል
  • ከ20 ሺሕ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች በተቀሰቀሰው ግጭት የበርካታ ዜጎች ሕይወት መጥፋቱን፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ዓርብ መስከረም 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ እንደተናገሩት፣ በሁለቱ ክልሎች መሀል በተቀሰቀሰቀው ግጭት የበርካታ ዜጎች ሕይወት ከመጥፋቱ በተጨማሪ፣ ከሃያ ሺሕ በላይ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የሞቱት ዜጎች ቁጥር በውል እንደማይታወቅ ሚኒስትሩ ቢገልጹም፣ ሁለቱ ክልሎች ግን የሟቾችን ቁጥር ይፋ አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በግጭቱ ምክንያት የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ከሃምሳ በላይ ሲያደርሰው፣ የኦሮሚያ ክልል በበኩሉ 18 ብቻ ናቸው ብሏል፡፡

በሁለቱ ክልሎች መካከል ሰሞኑን የተቀሰቀሰው ግጭት ዋነኛ መንስዔ ከወሰን ጋር የተገናኘ ተብሎ አንድም ቀን መግለጫ እንዳልተሰጠ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ጳጉሜን 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በቦረና በኩል በሞያሌና በሌሎች ወረዳዎች የነበረውን ግጭት ለማስቆም የሁለቱ ክልሎች መሪዎች ከፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሲሠሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ግጭቱ ከወሰን ጋር የተያያዘ እንዳልነበርም አስረድተዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ መስከረም 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በጭናክሰን አካባቢ በሁለት አመራሮች ላይ የተደረገው ግድያ፣ በአወዳይ ከተማ ሕዝባዊ ግጭት እንዲፈጠር መንስዔ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል የተከሰተው ግጭት በወሰን ምክንያት እንዳልሆነ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ከወሰን ጋር የተያያዘ ቢሆን ኖሮ ግጭቱ በወሰን አካባቢ ብቻ ይሆን እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

‹‹በሕዝብ ላይ ጥቃት የሚያደርሱ አካላትን በተመለከተ በኦሮሚያ ክልል በኩል ጥቃት አድራሽ አንደኛ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ፣ ሚሊሻና የሶማሊያ ሪፐብሊክ ወታደሮች ያሉበት እንደሆነ ሲገለጽ ሰምተናል፡፡ እነሱ የገለጹት ትክክል ነው ብለን የገለጽነበት ጊዜ የለም፤›› ብለዋል፡፡ ትክክለኛ መረጃ የያዘው አካል በሕጉ መሠረት ታይቶ ወደፊት የሚገለጽ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

‹‹በሁለቱ ክልሎች መካከል በተለያዩ ሚዲያዎች ሲገለጽ እንደነበረው ዜጎቻችን ያለውን ችግር በትክክል እንዲረዱ የማድረግ እንቅስቃሴው እንዳለ ሆኖ፣ አቅጣጫ እንዲስትና ሁከቱ እንዲባባስ የማድረግ ድርጊት ግን ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ማኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሁለቱን ክልሎች ኃላፊዎች በስልክ እንዳነጋገሯቸውና ይኼ ችግር በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት እንዳሳሰቧቸው አክለዋል፡፡

በሁለቱ ክልሎች መሀል የተቀሰቀሰውን ግጭት እንዲባባስ የሚያደርጉ ማኅበራዊ ሚዲያዎችም ሆኑ ሌሎች ሚዲያዎች ካሉ፣ መንግሥት እየተከታተለ ዕርምጃ እንደሚወስድ ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል፡፡

ከሶማሊያ ሪፐብሊክ ድረስ ወታደር መጥቶ በኢትዮጵያዊያን ላይ ጉዳት ሲያደርስ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል የት ነበር? የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች የቀረበላቸው ሲሆን፣ ‹‹ይኼንን ያለው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ነው፡፡ ስለዚህ አሁን እውነት ይሁን አይሁን አይታወቅም፡፡ ወደፊት ግን የፌዴራሉ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ መሠረት አጣርቶ ዕርምጃ ይወስዳል፤›› በማለት መልሰዋል፡፡

ባለፉት 26 ዓመታት ከወሰን ጋር በተያያዘ ጥያቄ ሲነሳ እንደነበር የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ይኼንን ችግር ለመፍታት መንግሥት ሲሠራ መቆየቱም ተናግረዋል፡፡

ግጭቱን ለማስቆምም በሁለቱ ክልሎች መካከል የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት የተሰማሩ ቢሆንም፣ እስካለፈው ዓርብ በሁለቱ ክልሎች መሀል ግጭት ነበር ብለዋል፡፡

‹‹የልማታዊ አስተሳሰብ የበላይነቱን ባልያዘበት ነባራዊ ሁኔታ ኪራይ ሰብሳቢነትና ወኪሎቹ የሆኑት ትምክህትና ጠባብነት ሰፊ የመንሸራሸሪያ ምኅዳር ማግኘታቸው የማይቀር በመሆኑ፣ በብሔሮች መካከል ቅራኔ በመፍጥር አንድነታችንን ለማላላት ሁሉንም አቅማቸውን አስተባብረው ሲረባረቡ ማየት የተለመደ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መሀል የተቀሰቀሰው ግጭት ከዚህ በላይ ጉዳት እንዳያደርስ ሲባልም፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በአካባቢው እንዲሰማሩ መደረጉንም አክለው ገልጸዋል፡፡ ይኼንን ችግር ለማስቆም የፌዴራል ፖሊስ አባላት ከክልሎች አመራርና ፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ኃላፊነት እንደተሰጠው ተናግረዋል፡፡

በሚወስደው ዕርምጃ የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አባላት አብረው ሄደው ሥራቸውን እያከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ማንኛቸውም አካላት እርስ በርስ ከመወነጃጀል በመታቀብ ችግሩን በሕጋዊ መንገድ ብቻ ለመፍታት እንዲንቀሳቀሱ ሚኒስትሩ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ በዚህ በኩል ችግር የሚፈጥሩ አካላት ከሕግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ አስጠንቅቀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በወሰን ምክንያት በሁለቱ ክልሎች ግጭት በመቀስቀሱ በርካታ ዜጎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡ በሚያዝያ ወር 2009 ዓ.ም. በፌዴራልና አርብቶ አደሮች ጉዳይ ሚኒስቴር አደራዳሪነት ግጭቱን ለማስቆም በሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ስምምነት መፈረሙ አይዘነጋም፡፡ አሁን ደግሞ በተቀሰቀሰ ግጭት በርካታ ዜጎች በመሞታቸው በክልሎቹ ብቻ ሳይሆን፣ በመላ አገሪቱ ሥጋት መፍጠሯ ብዙዎችን እያሳሰበ ነው፡፡

ሚኒስትሩ የቅማንት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ተነስቶባቸው በነበሩ 12 ቀበሌዎች እሑድ መስከረም 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ሊካሄድ የነበረው ሕዝበ ውሳኔ፣ በስምንቱ ቀበሌዎች ብቻ እንደሚካሄድም ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፣ አራቱ ቀበሌዎች ተጨማሪ ውይይት እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጻቸውና ጥያቄያቸውም ተቀባይነት በማግኘቱ በቀጣይ እንዲታዩ ተደርጓል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በስምንት ቀበሌዎች ብቻ ሕዝበ ውሳኔ ለመስጠት እየተሠራ መሆኑንና በዚህም ከ21 ሺሕ በላይ ዜጎች መመዝገባቸውን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ 

Standard (Image)

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል በድጋሚ ያገረሸው ግጭት

$
0
0

 

የኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓት፣ ለብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር እስከ መገንጠል  መብት ይሰጣቸዋል፡፡ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ያቀፉት ዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የራሳቸው አስተዳደራዊ ወሰን ኖሯቸው ክልላቸውን ወይም የከተማ አስተዳደራቸውን የማልማት፣ የማሳደግና ድንበራቸውን የመቆጣጠር ሥልጣንም ተሰጥቷቸዋል፡፡

እነዚህ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እርስ በርሳቸው በሚያገናኙዋቸው አካባቢዎች ወሰኖች አሏቸው፡፡ ይሁንና ክልሎች ይህ መሬት ለእኔ ይገባኛል፣ በሚል ሰበብ ሲጋጩና ሲጣሉ ብዙ ጊዜ ይታያል፡፡ ለምሳሌ አፋርና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች በጋራ ወሰን አካባቢ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲጋጩ ታይቷል፡፡ በግጦሽ መሬት አማካይነት ደም ያፋሰሰ ግጭት ውስጥ ገብተው ያለፉበት ጊዜም ነበር፡፡ በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል ተመሳሳይ ችግሮች ነበሩ፡፡ በተለይ ሁለቱ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው በጎንደርና በሌሎች አካባቢዎች ባለው የጋራ ወሰን ግጭቶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ለዓመታት ሲያወዛግብ የነበረው በጠገዴና በፀገዴ መካከል የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ብዙ ክርክሮችና ውዝግቦች አስነስቶ ቆይቷል፡፡ በአማራ ክልሉ የጠገዴ ወረዳና በትግራይ ክልል የፀገዴ ወረዳ መካከል ባለው የጋራ ወሰን ይገባኛል ጥያቄ ለዓመታት የዘለቀ ችግር ነበር፡፡ ይህን ችግር በቅርቡ፣ የሁለቱ ክልሎች አመራሮችና ሕዝቦች በመነጋገርና በመወያየት እንደፈቱት ቢነገርም፣ በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ችግሮች ይታያሉ፡፡

በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች መካከል ያለው ውዝግብ ሌላው ማሳያ ነው፡፡ በኦሮሚያና በጋምቤላ መካከል ያለውም እንዲሁ፡፡ በኦሮሚያና በአማራ በተለይም በሰሜን ሸዋና በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ችግሮች አሉ፡፡ በኦሮሚያና በደቡብ፣ በኦሮሚያና በአፋር ክልሎች መካከል ባለው አስተዳደራዊ ወሰን ምክንያት ግጭቶች ሲነሱና ከዚያም ታልፎ የሰው ሕይወት ሲጠፋና ደም ሲፈስ ይታያል፡፡ በተለይ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ መጠናቸው እየሰፋና እየገዘፈ መምጣቱን የተለያዩ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡  

በኢትዮጵያ ሰፊ የቆዳ ስፋትና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያለው ክልል ኦሮሚያ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኦሮሚያ ክልል ሰባቱን ክልሎችና ሁለቱን የከተማ አስተዳደሮች የሚያዋስን ነው፡፡ ይህ ክልል ሰፊ ከመሆኑና ከትግራይ ክልል በስተቀር ሁሉንም የኢትዮጵያ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የሚያዋስን በመሆኑ ምክንያት፣ ከሚያዋስናቸው ክልሎች ጋር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአስተዳደራዊ ወሰን የማካለል ሥራ ሲያከናውን ነበር፡፡ ኦሮሚያ ክልል ከአማራ፣ ከቤንሻንጉል፣ ከጋምቤላ፣ ከአፋር፣ ከድሬዳዋ፣ ከአዲስ አበባና ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ጋር ውዝግቦች ነበሩበት፡፡ እነዚህ የወሰን ውዝግቦች ለዓመታት ሲንከባለሉና ደም አፋሳሽ ግጭቶች ውስጥ ሲያስገቡ ነበር፡፡

በአገሪቱ በ2008 ዓ.ም. ተከስቶ ለነበረው ቀውስ አንዱ ምክንያት በክልሎች መካከል ያለው አስተዳደራዊ ወሰን በቅጡ ባለመካለሉ ሳቢያ የሚነሱ ከማንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ወቅታዊ ምላሽ አለመሰጠቱ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህ መሠረት መንግሥት በ2009 ዓ.ም. አዲስ አወጣሁት ባለው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ፣ ከፌዴራል እስከ ክልል እንዲሁም ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ባሉ የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ ለመልካም አስተዳደር ቁርጠኛ ሆነው ሥራቸውን በተገቢው ሁኔታ አልሠሩም ያላቸውን አመራሮች አንስቷል፡፡ በዚህ ጥልቅ ተሃድሶ የአመራር ለውጥ ከተደረገባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ የኦሮሚያ ክልል ነው፡፡

የኦሮሚያ ክልል የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር ጨምሮ ሌሎች ቁልፍ፣ ቁልፍ ቦታ ላይ የነበሩትን አመራሮችን በአዲስ ተክቷል፡፡ አቶ ለማ መገርሳ የሚመሩት የክልሉ አዲሱ አመራር ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ ከዚህ በፊት አይነኬ የሚመስሉ ጉዳዮችን ሲያከናውንና የክልሉን ችግር ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመፍታት ደፋ ቀና ሲል ተስተውሏል፡፡ አዲሱ አመራር ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ የክልሉ ሕዝብና ወጣቶች በተደጋጋሚ ሲያነሱዋቸው የነበሩ ጥያቄዎችን ለመፍታት እየሞከረ ነው፡፡ ኦሮሚያ ከሚያዋስኑት ክልሎች ጋር ያለውን የአስተዳደራዊ ወሰን ችግር ለመፍታት ከቀድሞው በተለየ ሁኔታ ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡ በክልሉ ውስጥ ለረዥም ዓመታት በባለሀብቶች ታጥረውና አይነኬ ሆነው የነበሩ መሬቶችን በመንጠቅ ለወጣቶች መስጠቱም ይታወሳል፡፡ በዚህም የተነሳ በብዙ የክልሉ ተወላጆች ዘንድ ሲሞካሽ ተደምጧል፡፡ እርግጥ ነው ከመጀመርያውም ጀምሮ እነዚህን አዳዲስ ጥረቶች በጥርጣሬ ያዩ አልጠፉም፡፡

የክልሉ አመራር በተለይ ከሚያዋስኑት ክልሎች አመራሮች ጋር በመነጋገር የአስተዳደራዊ ወሰን ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ የቤት ሥራ አድርጎ መንቀሳቀሱም ይታወቃል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ከቤንሻንጉልና ከጋምቤላ ብሔራዊ ክልሎች አመራሮች ጋር በመነጋገር ችግሮችን ለመፍታት ያደረገው ጥረት ነው፡፡ ከእነዚህ ክልሎች ጋር ያለው ሥራም ከሞላ ጎደል መጠናቀቁን የክልሉ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አዲሱ አረጋ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል ያለው አስተዳደራዊ ወሰን ከ85 በመቶ በላይ መጠናቀቁ ቢነገርም፣ እስከ ዛሬ ድረስ በሁለቱ አዋሳኝ አካባቢዎች ደም አፋሳሽ ግጭቶች ቀጥለዋል፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለው አስተዳደራዊ ወሰን በ1997 ዓ.ም. በሕዝብ ውሳኔ እንዲለይ መደረጉን የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሄዱት የዕርቅ ሥነ ሥርዓት ቢገልጽም ችግሩ እስከ ዛሬ ድረስ እንደቀጠለ ነው፡፡  

በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለው የአስተዳደራዊ ወሰን ችግር የበርካታ ሰዎች ሕይወት የጠፋበት ግጭት አስከትሏል፡፡ በ2009 ዓ.ም. ከጥቅምት ወር ጀምሮ ለብዙ ወራት የዘለቁ ግጭቶች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ይህንን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚፈቱት በሚያዝያ ወር 2009 ዓ.ም. አካሂደውት በነበረው የዕርቅ ሥነ ሥርዓት ላይ ተናግረው ነበር፡፡

የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር አዳራሽ ባካሄዱት የዕርቅ ሥነ ሥርዓት ላይ ‹አልፋና ኦሜጋ ዕርቅ› ማካሄዳቸውን ተናግረው ነበር፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ይህን ስምምነት ከአሁን በኋላ የሚያፈርስ ካለ እንደ ጠላት ነው የምናየው፤›› ብለው ነበር፡፡ ‹‹ኦሮሚያ በቂ መሬት አለው፡፡ ሶማሌም በቂ ብቻ ሳይሆን ከበቂ በላይ አለው፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ግን በሆነ ትንሽ ቀበሌ ምክንያት የሰውን ደም ማፍሰስ ከዚህ በፊት ሆኗል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን መቼም እንደማይደገም እናረጋግጥላችኋለን፤›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡ ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትም በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ ሕዝቦችን በልማት ማስተሳሰር ተገቢ እንደሆነ አስታውቀውም ነበር፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው፣ ‹‹ይህ የፀረ ሰላም ኃይሎች አጀንዳ ሆኖ የቆየው የወሰን ጉዳይና ከዚህ ጋር ተያይዞ የነበረው ነገር ለአንዴና ለመጨረሻ ተፈትቷል፤›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡ ይህን ተመሳሳይ ባህል፣ ቋንቋና አኗኗር ያለው ሕዝብ በደም የተሳሰረና የተዋሃደ በመሆኑ ማንም ቢሆን ሊለያየው እንደማይችል ገልጸው ነበር፡፡ ‹‹በደረስንበት ደረጃ ሆኜ ሳስበው ድልም ነው፣ ውድቀትም ነው፡፡ ድሉ ምንድነው ካላችሁ የዘገየ ቢሆንም ከብዙ ጥፋት በኋላ ቢሆንም እዚህ ደረጃ ላይ መድረሳችን ሲሆን፣ ሌላው ትምህርት ልናገኝበት የሚገባ ትልቅ የአመራር ውድቀት ደግሞ ዛሬ የደረስንበት የስምምነት ፊርማ ላይ ቀደም ብሎ ደርሰን ቢሆን ኖሮ፣ ያላግባብ የጠፋውን ብዙ ሕይወት መታደግ እንችል ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ይህንን የጋራ ኅብረተሰብም በልማት በማስተሳሰር የቆየ አብሮ የመኖር ልማዱንና ወጉን ማጠናከር ተገቢ እንደሆነ ጠቁመው ነበር፡፡

በወቅቱ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩት አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን በበኩላቸው፣ የአካባቢው አስተዳደርና ማኅበረሰብ በንቃት እንዲሳተፍበት በማድረግ በተከናወነው ሰፊ የማግባባት ሥራ ሕዝበ ውሳኔ ከተካሄደባቸው ቀበሌዎች ውስጥ የአብዛኞችን ስኬታማና ውጤታማ በሆነ  መንገድ መከለላቸውን ገልጸው ነበር፡፡ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ቁርጠኛ በመሆንና ሕዝቡን ማዕከል በማድረግና ውይይት በማካሄድ ቀሪ ሥራዎች መሥራት እንደሚገባ ማሳሰቢያም ሰጥተው ነበር፡፡

በዚህ ማሳሰቢያ መሠረትም የሁለቱ ክልሎች አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት የሁለቱ ክልል ነዋሪዎች በድሬዳዋ ከተማ የውይይትና የዕርቅ ሥነ ሥርዓት ማካሄዳቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ ዕርቅ መሠረትም በ1997 ዓ.ም. በሁለቱ ክልሎች መካከል ያልተዋሰኑ አካባቢዎችን ሕዝቡን መሠረት ባደረገ መንገድ ሲከልሱና ሲወስኑ ቆይተዋል፡፡ በዚህ መሠረት ሁለቱ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ ሲያነሱባቸው ከነበሩ የአስተዳደራዊ ወሰን ጉዳዮች መካከል ከ85 በመቶ በላይ ማካለል እንደተቻለ መረጃዎች ይመለክታሉ፡፡ 

ከሁለቱ ወገኖች በኩል ሲሰማ የነበረው ጉዳይ ይህ ቢሆንም ድንገት ሳይታሰብ ከአሥር ቀናት በፊት በሁለቱ ክልሎች መካከል ባሉ አዋሳኝ አካባቢዎች፣ በተለይም የኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ውስጥ ባሉ ወረዳዎችና የኢትየጵያ ሱማሌ ክልል የሚያዋስኑ አካባቢዎች ግጭቱ እንደገና አገርሽቷል፡፡ በዚህ ግጭትም የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና ከሃያ ሺሕ በላይ ዜጎች ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ ተነግሯል፡፡

የዚህ ግጭት መንስዔው ምን እንደሆነ መንግሥት ቁርጥ ያለ ነገር ባይናገርም፣ ክልሎች እርስ በርሳቸው መወነጃጀልና አንዱ ክልል ሌላውን ጥፋተኛ ወደ ማድረግ ደርሰዋል፡፡ ግጭቱ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ከጉርሱም እስከ ሞያሌ ከ1,200 ኪሎ ሜትር በላይ ወሰን የሚጋሩ አካባቢዎች ናቸው፡፡ በአካባቢው የሚኖሩ ሕዝቦች በጋብቻ የተሳሰሩ ጭምር በመሆናቸው፣ ለግጭት የማያበቃ ጉዳይ እንደሌላቸው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ አንድ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ ጉዳዩን ሲገልጹት፣ ‹‹በሁለቱ ክልል አመራሮች መካከል እየተቆሰቀሰ ያለ እሳት እንጂ በሕዝቦች መካከል አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹ይህ ችግር የሚፈታበት ዘዴ በሕገ መንግሥቱ ላይ ሠፍሮ እያለ ከሁለቱ ወገኖች ይህን ያህል ሰው ማለቅ የለበትም ነበር፤›› ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሪፖርተር በላኩት መግለጫ ላይ በግጭቱ ምክንያት ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ወደ መኖሪያ ሠፈራቸው በመመለስ፣ ከተቋቋሙና ከተረጋጉ በኋላ በሕዝቡ ነፃ ፍላጎት፣ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር በመሆን ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ጠይቀዋል፡፡ የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦችን የጋራ ትስስርንና አብሮነት በምንም መልኩ አሳጥሮ መግለጽ እንደማይቻልም ገልጸዋል፡፡  የአሁኑ ችግር የሕዝብ ለሕዝብ ሳይሆን የፀረ ሰላም ኃይሎች ችግር መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሶማሌና የኦሮሚያ ክልል በሞያሌ በኩል በመንገድ ብቻ እንደተከለሉ አስታውሰዋል፡፡ ከዚህ መለስ የኦሮሞ፣ ከዚህ መለስ የሶማሌ ተብሎ መንገድ የሚከለልለት ከተማ ነው ያላቸው፡፡ ነገር ግን ኅብረተሰቡ አንድ ነው፡፡ አብሮ የሚኖር ሕዝብ ነው፡፡ ልትነጣጥለው የምትችለው ሕዝብ አይደለም፤››  በማለት አስረድተዋል፡፡

‹‹ድሬዳዋ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ሶማሌና ኦሮሞ ነው በጋራ እያስተዳደሯት ያሉት፡፡ ድሬዳዋን የመሰለ ከተማ ዕጣ ፈንታዋ ምንድነው የሚሆነው የሚለው ነገር በጣም ያሳስበናል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ዶ/ር ጫኔ ይህን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው እንደዚህ ዓይነት ግጭት የሚነሳባቸውን አካባቢዎች በአግባቡ መምራት የማይችሉ ክልሎች ካሉ፣ በፌዴራል መተዳደር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ ድሬዳዋ ለምሳሌ በፌዴራል መንግሥት መተዳደር እንደሚገባት፣ አዲስ አበባ ደግሞ ወደፊት ሌላ የግጭት ማዕከል ትሆናለች ተብሎ እንደሚያሠጋ ገልጸዋል፡፡

በሚያዝያ ወር 2009 ዓ.ም. ተካሂዶ የነበረው የዕርቅ ሥነ ሥርዓት ተሽሮ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች አሁን ይህን ያህል ደም አፋሳሽ ግጭት ይከሰታል ብሎ ያሰበ ሰው እንዳልነበረ አስተያየት ሰጪዎች ሲናገሩ እየተደመጠ ነው፡፡ የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮችና ሕዝቦች በድሬዳዋና በሌሎች አካባቢዎች የቀሩ የወሰን ጉዳዮችን ለመፍታት ሲመክሩ ሰንብተው፣ አሁን ግን ወደ ሌላ ደም አፋሳሸ ግጭት ውስጥ ገብተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ይባስ ብሎ ጉዳዩ በሰከነ መንገድ እንዲበርድ ከመሥራት ይልቅ፣ ክልሎቹ እርስ በራሳቸው በመወነጃጀልና ጥፋተኛ በመባባል ላይ የተጠመዱ ነው መሆናቸው ብዙዎችን አሳስቧል፡፡ ይህ መወነጃጀል ማቆሚያውስ የት ነው እየተባለ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሐሙስ መስከረም 4 ቀን 2010 ዓ.ም. መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡ የመግለጫው መግቢያ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሕዝብና መንግሥት የአገሪቱን የፌዴራል ሥርዓት በመጠበቅና ዘብ በመቆም ቆይቷል ይላል፡፡ ‹‹የክልላችን ሕዝብና መንግሥት በብዝኃነት ላይ የተመሠረተውን ልዩነት በማክበር በመቻቻልና በመፈቃቀር ለዘመናት ከብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በጋራና በጥሩ ጉርብትና አምኖና ተባብሮ የሚኖር ጨዋ ሕዝብ ነው፤›› ካለ በኋላ፣ ክልሉ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች በኦሮሚያ ክልል መንግሥት የሚደገፍና በክልሉ በታጠቁ ኃይሎች፣ በክልሉ ፖሊስ፣ ማሊሻና አሸባሪው የኦነግ ቄሮ አባላት በተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጽሙና ወረራ ሲያካሂዱ መቆየታቸውን አብራርቷል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በበኩሉ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያወጣውን መግለጫ እጅግ በጣም አሳፋሪና ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የቀረበ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ‹‹መግለጫው አሁን ያለውን ችግር ከማርገብ ይልቅ ወደ ሌላ አቅጣጫ ሊወሰድ የሚችልና አገርን ከሚያስተዳድር ትልቅ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ይሰጣል ተብሎ የማይጠበቅ አሳፋሪ መግለጫ ነው፤›› ሲል አጣጥሎታል፡፡ መግለጫው የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የተጣለበትን ሕዝባዊና መንግሥታዊ ኃላፊነት ከመሸከም አንፃር ያለበትን ደካማ ቁመናና ዝቅተኛ ደረጃ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ከመግለጫው ስህተቶች አንዱ ራሱን የፌዴራል ሥርዓቱ ብቸኛ ዘብና ጠባቂ አድርጎ የማቅረቡ ጉዳይ እንደሆነ ጠቅሷል፡፡ ሁለተኛው የመግለጫው ስህተት አድርጎ የወሰደው ደግሞ ኦሮሚያ ክልልን ‹‹የኦሮሞ ክልል›› ብሎ ከሕገ መንግሥቱ ውጪ መሰየሙን አስታውሷል፡፡ ‹‹መግለጫው ይህን አጻጻፍ የተከተለው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልልን ‹የኦሮሞዎች ብቻ› እንደሆነችና ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን የማታቅፍና አግላይ አስመስሎ የማቅረብ አደገኛ ተልዕኮ ያለው አጻጻፍ ነው፤›› ሲልም ኮንኗል፡፡

የመግለጫው ሦስተኛ ስህተት አድርጎ የወሰደው ደግሞ የክልሉን መንግሥት በአሸባሪነትና በኦነግነት መፈረጁ እንደሆነ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የወጣው መግለጫ ያመለክታል፡፡ መግለጫው ኦሮሚያና የኦሮሞ ሕዝብ የኢትዮጵያ አንድነት ምሰሶዎች መሆናቸውን ጠቅሶ የክልሉ አመራሮችም ለፌዴራላዊ ሥርዓቱ ማበብና መጎልበት፣ የሕዝቦች ወንድማዊ ግንኙነትና እኩል ተጠቃሚነት እንዲሰፍን ለማድረግ እየታገለና መስዋዕት እየከፈለ ያለ የሕዝብ ልጅ እንጂ፣ በአሸባሪነትና በኦነግነት የሚፈረጅ እንዳልሆነ አስገንዝቧል፡፡

የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በመግለጫው ላይ በኦሮሚያ ክልል ነዋሪ በሆኑ የሶማሌ ተወላጆች ላይ የዘረኝነት ጭፍጨፋ የተጀመረው፣ በተለይ በአወዳይ ከተማ ረቡዕ መስከረም 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ከ50 በላይ ንፁኃን ዜጎች ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ አካላቸውን በመቆራረጥና በእሳት በማቃጠል ሕይወት መቀጠፉን አስታውቋል፡፡ ከሦስት መቶ በላይ የሚሆኑ ደግሞ በመከላከያ ሠራዊት ኃይል ሕይወታቸው እንዲተርፍና ወደ ሐረር እንዲገቡ መደረጉን ገልጿል፡፡ ሐሙስ መስከረም 4 ቀን 2009 ዓ.ም. የ30 ዜጎች የተቆራረጠና የተቃጠለ ሬሳ ወደ ክልሉ መሄዱን ጠቁሟል፡፡ ክልሉ ዓርብ መስከረም 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በይፋ የቀብር ሥነ ሥርዓት ማከናወኑ ተገልጿል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ከላይ ያለውን መግለጫ የማይቀበለው መሆኑን ገልጾ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ግጭትን በሚያባብሱ አደገኛ ቃላትንና በተጋነኑ ውሸቶች መሞላቱን አመልክቷል፡፡ በተፈጠረው ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋቱን አስታውሶ፣ በዚህ ረገድ ግን ኦሮሞም ይሁን ማንም ሰው መሞት የሌለበት መሆኑን አብራርቷል፡፡ ለዜጎች የሕይወት መጥፋት እጃቸው ያለባቸው ሰዎች ለሕግ መቅረብ አለባቸው ብሎ የሚያምን መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ‹‹መስከረም 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ከጉርሱም ወደ ሐረር እየተጓዙ ያሉ ሰላማዊ የኦሮሞ ተወላጆችን የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፀጥታ አካላት ቦምባስ ከተማ ኬላ ላይ ይዘው ያስራሉ፡፡ እነዚህ ታሳሪዎች አቶ ሰለማ መሐመድ (የጉርሱም ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩ)፣ አቶ ታጁዲን ጀማልና ሌሎች ሁለት ሰዎች በነጋታው በደረሰባቸው ድብደባ መሞታቸው ተሰማ፡፡ የሰላማዊ ሰዎች ያልተጠበቀ ሞት የምሥራቅ ሐረርጌ ነዋሪዎችን በማስቆጣቱ በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን አወዳይ፣ ደደር፣ ቆቦና መልካ ራፉ ከተሞች ያልተጠበቀ የሕዝብ ቁጣና ሠልፍ አስከተለ፡፡ በተለይ አወዳይ የነበረው ሠልፍ ወደ ግርግር ተሸጋገረ፡፡ በተፈጠረው ግርግርም የ18 ሰዎች ሕይወት ሊያልፍ ችሏል፡፡ በዚህ ግርግር ሕይወታቸውን ካጡት 18 ሰዎች 12 የሶማሌ ተወላጅ ወንድሞቻችን ሲሆኑ፣ ስድስቱ ደግሞ የጃርሶ ጎሳ ተወላጅ ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ድንበር ላይ እየተፈጸመ ካለው ጥቃት ጋር ምንም ተያያዥነት የሌላቸው፣ በላባቸው ሠርተው የሚያድሩ ሰላማዊ ዜጎች ናቸው፤›› ሲል መግለጫው አስታውቋል፡፡ የሶማሌ ክልል ገለጻም ፍፁም ተቃራኒ የሆነን ምክንያት ለግጭቱ መነሻ ማድረጉን ይገልጻል፡፡ በዚህ ድርጊት ተሳትፈዋል ተብሎ የተጠረጠሩ 200 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም የኦሮሚያ ክልል መግለጫ ጠቅሷል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ዓርብ መስከረም 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፣ በሁለቱ ክልሎች መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማስቆም የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በአካባቢው እንዲሠፍሩ ተደርጓል፡፡ በዚህ ግጭት ቁጥራቸው እስካሁን በውል ያልታወቀ ዜጎች መሞታቸውን ጠቅሰው፣ ከሃያ ሺሕ በላይ ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግጭቱ ሙሉ በሙሉ ቆሟል ብሎ መናገር እንደማይቻል፣ ከአሁን በኋላም ግጭት እንዳይከሰት የፌዴራል መንግሥት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የዚህ ችግር መሠረታዊ ምክንያት የወሰን ማካለል ብቻ እንደማይሆን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ጉዳዩ ተጣርቶ ወደፊት የሚገለጽ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሸን ቢሮ ኃላፊን ለማናገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ እያከናወነ ያለውን ለማወቅ የተደረገው ጥረትም አልተሳካም፡፡

 

 

 

Standard (Image)

በሰሜን ጎንደር ዞን የተፋሰስ ፕሮጀክት ላይ የሽብር ጥቃት በመፈጸም የተጠረጠሩ ክስ ተመሠረተባቸው

$
0
0

 

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደምቢያ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው ሰርባ መስኖ ተፋሰስ ፕሮጀክት ላይ የሽብር ጥቃት በማድረስ፣ ሁለት ሠራተኞችን በመግደልና በአምስት ሠራተኞች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ 14 ተጠርጣሪዎች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው አቶ ደረጀ በላይ፣ አቶ ቸርነት ሀብቴ፣ አቶ እሸቱ መከተ፣ አቶ መሀሪ አዲስ፣ አቶ ማስረሻ ማንደፍሮን ጨምሮ 14 ተከሳሾች ሁሉም የሰሜን ጎንደር ዞን ደምቢያ ወረዳ፣ የጫሂትና ቆላድባ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ማሞ ግን ጎንደር ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ነጋዴ መሆናቸውን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ያቀረበው ክስ ያሳያል፡፡ ከነጋዴው በስተቀር ሁሉም ያልተማሩና አርሶ አደሮች መሆናቸውን ለፍርድ ቤት ተናግረዋል፡፡

ተከሳሾቹ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ድርጅት አባልና ታጣቂ በመሆን፣ በሰሜን ጎንደር ዞን ደምቢያ ወረዳ ‹‹መንድባ ጫካ›› ውስጥ ወታደራዊ ቤዝ በመመሥረትና ሙሉ የጦር መሣሪያ በመታጠቅ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሥልጠና ከኤርትራ በመጡ አመራሮች መውሰዳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ አቶ ደረጀ፣ አቶ ቸርነትና አቶ እሸቱ የተባሉት ተከሳሾች በመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም. በመንድባ ጫካ ውስጥ ከተሰበሰቡ በኋላ ባደረጉት ምክክር፣ መንግሥት በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደምቢያ ወረዳ ውስጥ በቻይና ኮንትራክተሮች እያስገነባ ባለው የሰርባ የመስኖ ተፋሰስ ፕሮጀክት ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም መስማማታቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ መጋቢት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት አካባቢ በሠራተኞች መኖሪያ ቤት ላይ ተኩስ በመክፈት፣ አቶ ተሻለ ተስፋሁንና አቶ መንግሥቴ አበበ የተባሉ ሠራተኞችን መግደላቸውን ገልጿል፡፡ አቶ አደገ ጌትነት፣ አቶ ሸጋው ቢክስ፣ አቶ ሀብታሙ እሸቱ፣ አቶ እውነቱ መሀሪና አቶ ጊዜ አዲስ አስማማው በተባሉት ሠራተኞች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረጋቸውን አክሏል፡፡ ጠቅላላ ግምቱ 1,933,760 ብር በሚገመት ንብረት ላይ የማውደም ተግባር መፈጸማቸውንም ጠቁሟል፡፡

ተከሳሾቹ በተጨማሪም ሚያዝያ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰሜን ጎንደር ዞን ደምቢያ ወረዳ ጉራምባ ቀበሌ ውስጥ፣ የልማት ሥራ በማከናወን ላይ በነበሩት የአማራ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ሠራተኞችና ማሽኖች ላይ ጥቃት በመፈጸም ግምቱ 134,686 ብር የሆነ ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡

ተከሳሾቹ ስዊድን ከሚገኘው አስማረ ብሩ ከሚባል የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር ጋር በስልክ በመገናኘትና የተለያዩ ተልዕኮዎችን በመቀበል፣ ከነሐሴ ወር 2008 ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ ወር 2009 ዓ.ም. ድረስ በሰሜን ጎንደር ዞን ደምቢያ ወረዳ በመዟዟር ከ23 በላይ አባላትን መመልመላቸውንና ጫሂት ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ጫካ ውስጥ የማደራጀት፣ የማስታጠቅና ወታደራዊ ሥልጠና እንዲወስዱ በማድረግ ሲዘጋጁ መቆየታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡ ተከሳሾቹ በሐምሌ ወር 2008 ዓ.ም. ጫሂት ከተማ ውስጥ አመፅ እንዲነሳ በማድረግ የከተማው ቀበሌ ጽሕፈት ቤት በእሳት እንዲወድም ማድረጋቸውንም በክሱ ጠቅሷል፡፡ ተከሳሾቹ እያንዳንዳቸው 350 ብር በመያዝ በመስከረም ወር 2009 ዓ.ም. ለሥልጠና በሁመራ በኩል ወደ ኤርትራ መሄዳቸውን፣ በተመሳሳይ ወር አስማረ ብሩ የተባለው የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር ከስዊድን 350,000 ብር ልኮላቸው በበለሳና በአርማጭሆ ወረዳ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት የቡድኑ አባላት ጋር በመሆን የሽብር ተግባር ድርጊቱን እንዲፈጽሙ ትዕዛዝ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡

ተከሳሾቹ በጎንደር ከተማ አካባቢ ለጊዜው ካልተያዙና ስማቸው ያልታወቁ ስምንት ሰዎችን ለሽብር ተግባር በመመልመል የፖለቲካና ወታደራዊ ሥልጠና እንዲሰጣቸው ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡ በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን ቃፍታ ሁመራ ወረዳ በማድረግ ወደ ኤርትራ መላካቸውን፣ መሠረተ ልማቶችን ለማውደም ተልዕኮ መቀበላቸውንና በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1ሀእናለ)፣ 35፣ 38 እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3 (1፣4እና6) የተደነገጉትን በመተላለፍ የሽብር ተግባር ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ዓቃቤ ሕግ ክስ አቅርቦባቸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም ለተከሳሾቹ ክሱን በችሎት አንብቦላቸው፣ ጠበቃ ማቆም አለማቆማቸውን ወይም መንግሥት ተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆምላቸው መፈለግ አለመፈለጋቸውን ለመጠባበቅ ለጥቅምት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

Standard (Image)

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ተሰማርተዋል

$
0
0

 

በዳዊት እንደሻው

ለበርካቶች ሕይወት መጥፋትና በአሥር ሺዎች ለሚቆጠሩ ከቀዬአቸው መፈናቀል ምክንያት የሆነው በኦሮሚያና ሶማሌ አጎራባች ክልሎች የተፈጠረውን ግጭት ለማረጋጋት፣ የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ተሰማርተዋል፡፡ ጥብቅ አካባቢዎች አልፎ የሚመጣ ማንኛውም የታጠቀ አካል ትጥቅ የማስፈታት፣ እንዲሁም ዕርምጃ የመውሰድ ሥልጣን ተሰጥቷቸው ሥራቸውን ቀጥለዋል፡፡

በተጨማሪም የፌዴራል ፀጥታ ኃይሎች የሁለቱ ክልሎች ዋና ዋና መንገዶችን እንዲጠብቁ ሥልጣን ተሰጥቶአቸዋል፡፡

ከሌላው ጊዜ በበለጠ በሁለቱ ክልሎች ተዋሳኝ አካባቢዎች ከተከሰቱ ግጭቶች አድማሱን ያሰፋው የአሁኑ ግጭት፣ በሁለቱ ክልሎች አመራሮች መካከል ልዩነቶችን ፈጥሮ ነበር፡፡ ግጭቱን አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት በሁለቱ ክልሎች ሲሰጡ የነበሩ እርስ በርስ የሚጋጩ መግለጫዎችም አመላካች ነበሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ኒውዮርክ ከማቅናታቸው በፊት የሁለቱን ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና አባገዳዎችን ካነጋገሩ በኋላ፣ የፌዴራል መንግሥት በሕገ መንግሥቱ መሠረት አፋጣኝ ዕርምጃዎችን ይወስዳል ብለው ነበር፡፡ የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት በመጠበቅ መረጋጋት እንዲፈጥሩ፣ የሰው ሕይወት በማጥፋት የሚጠረጠሩ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ የሁለቱ ክልሎች ዋና ዋና መንገዶችም በፌዴራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሥር እንዲውሉ አዘዋል፡፡

የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ግጭት በተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎችና አዋሳኝ ሥፍራዎች ማንኛውንም የጦር መሣሪያና ትጥቅ ያስፈታሉ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም የመብት ጥሰቶችን ያጣራል ተብሏል፡፡ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦችና የፀጥታ ኃይሎች በሕግ እንደሚጠየቁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡

ቅዳሜ መስከረም 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ግጭቱን ለማስቆም የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ፣ የሁለቱን ክልሎች ፕሬዚዳንቶች አቶ ለማ መገርሳንና አቶ አብዲ መሐመድን ለጋዜጣዊ መግለጫ ይዘው ቀርበው ነበር፡፡ በወቅቱ ሁለቱም ፕሬዚዳንቶች ግጭቱን አውግዘዋል፡፡ የተከሰተው ግጭት ሁለቱን ሕዝቦች አይወክልም ብለዋል፡፡

‹‹ይህ ችግር ሳይታሰብና ሳይጠበቅ የተፈጠረ ሲሆን ከ50 ሺሕ በላይ ወገኖች መፈናቀል፣ ለሶማሌ ወንድሞቻችንና ለኦሮሞ ቤተሰቦቻችን ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል፤›› ብለዋል አቶ ለማ፡፡

‹‹ሁለቱ ሕዝቦች በጠባብነት የመፈራረጅ ባህል የላቸውም፡፡ ከዚህ ግጭት ኪሳራ እንጂ አንዳችም ትርፍ አይገኝም፤›› ያሉት አቶ አብዲ፣ ግጭቱ ከአንገት በላይ ሳይሆን ከአንጀት መቆም አለበት ብለዋል፡፡

ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ በሚኒስትሩ የሚመራ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን፣ ኮሚቴው በዋናነት በግጭቱ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች ምግብ፣ ምግብ ነክና የሕክምና ዕርዳታ እንዲደረግ ያስተባብራል፡፡

ከፌዴራል መንግሥት ካዝና በሚወጣ ወጪ ዕርዳታው እንደሚከናወን ታውቋል፡፡ አሁን የሚፈናቀሉ ዜጎች የሉም ሲሉ በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት፣ የሕዝብና የሚዲያ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ሰይድ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በተያያዘም ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን ወደ ነበሩበት የመመለስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን፣ በግጭቱ የተሳተፉና ምክንያት የሆኑ አካላት ደግሞ በሕግ እንደሚጠየቁ በመንግሥት መገለጹ ይታወሳል፡፡

በዚህም በመንግሥት መዋቅር ውስጥም ሆነ ከውጭ ያሉ አካላት በሕግ ይጠየቃሉ ሲሉ አቶ ከበደ ጫኔ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

‹‹አሁን ላይ ሆነን የሟቾች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ መግለጽ ይከብደናል፤›› ያሉት አቶ መሐመድ፣ በቀጣይ ጉዳዩ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከተጣራ በኋላ ይፋ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

በተያያዘ ዜና አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭቱን ግልጽ በሆነ አካሄድ እንዲያጣራና አጥፊዎችን ተጠያቂ እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡  ‹‹ኢትዮጵያ ጠንካራ፣ የበለፀገችና ዴሞክራሲያዊት አገር መሆን የምትችለው ግጽልና ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት፣ ግልጽ የመንግሥት አሠራር፣ እንዲሁም የዴሞክራሲና የፍትሕ ተቋማት ማጠናከር ስትችል እንደሆነ እናምናለን፡፡ የሰሞኑ ሁነቶች በተጠቀሱት ዘርፎች ይበልጥ ፈጣንና ተጨባጭ ለውጥ አስፈላጊ እንደሆነ አመላካች ናቸው፤›› ሲል የአሜሪካ ኤምባሲ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

 

Standard (Image)

የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ኃላፊዎች የተጠረጠሩበት ጉዳት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በለጠ

$
0
0

 

ኢትዮጵያ በባህር ትራንስፖርት ዘርፍ የምታገኘውን ገቢና ወጪ በአግባቡ መጠቀም ሲገባቸው ኃላፊነታቸውን ያላግባብ በመጠቀም፣ በሕዝብና በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው ተጠርጥረው በምርመራ ላይ የሚገኙት የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ኃላፊዎች፣ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸውን የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን ለፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

መርማሪ ቡድኑ ሰኞ መስከረም 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ባቀረበው የምርመራ ሥራ እንደገለጸው፣ መንግሥት በ2006 ዓ.ም. የኅብረተሰቡን የስኳር ፍላጎት ለማሟላት 656,613.55 ቶን ስኳር ወደ አገር ውስጥ አስገብቷል፡፡ ኃላፊዎቹ ስኳሩ ከመርከብ ጂቡቲ በሚራገፍበት ወቅት፣ ተከታትለው መቆጣጠር ሲገባቸው ተገቢውን ጥንቃቄ ባለመውሰዳቸው የ13,800,000 ብር ጉድለት መድረሱን አስረድቷል፡፡

ኃላፊዎቹ ከግዥ መመርያው ውጪ ደረቅ ወደብን ከባቡር መስመር ጋር በማገናኝት ‹‹አመርትነት›› ለተባለ የቻይና ኩባንያ ለድሬዳዋ ደረቅ ወደብ 69 ሚሊዮን ዶላር፣ ለሞጆ ደረቅ ወደብ 39 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ውል መፈራረማቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡ ኃላፊዎቹ ለዚሁ የቻይና ኩባንያ በተደጋጋሚ ለአሥራ አንድ ጊዜያት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ሥራ በመስጠት ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ ለቦርድ ሳያሳውቁ ክፍያ መፍቀዳቸውንም መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡

በምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚሠሩት ስምንት ተጠርጣሪ ኃላፊዎች የዘጠኝ መርከቦች መጠባበቂያ ወጪ 1.5 ሚሊዮን ብር መሆኑን የሚያውቁ ቢሆንም፣ 3.8 ሚሊዮን ብር ያላወራረዱ መሆናቸውንም መርማሪው ጠቁሟል፡፡

ከደረቅ ወደብ የኮንቴይነር ማንሻ ሳይበላሽ ተበላሽቷል በማለት በሰዓት ሁለት ሺሕ ብር በቀን 16 ሺሕ ብር ያላግባብ ክፍያ እንዲከፈል መደረጉንም መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ የድርጅቱ የኮርፖሬት አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲሳይ አባፈርዳ የ250 ሚሊዮን ብር ኮንቴይነር ግዥ ያላግባብ ለመፈጸም ሦስት ሚሊዮን ብር ጉቦ መደራደራቸውን ቦርዱ ስለደረሰበት ግዥው እንዲሰረዝ ማድረጉንም ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

እንደ መርማሪ ቡድኑ የምርመራ ሪፖርት ኃላፊዎቹ ለሞጆ ደረቅ ወደብ የተለያዩ ፎርክ ሊፍቶችን ገዝቶ መሥራት ሲቻል፣ በኪራይ እንዲሠራ በማድረግ በአንድ ዓመት ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማውጣታቸውንና ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የግዥ ጥያቄ ሳያቀርቡና ቦርዱ ሳይፈቅድ 25 ፎርክ ሊፍቶችንና ስምንት ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን በመግዛት፣ ግምቱ ያልታወቀ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ድርጅቱ ለተለያዩ የመስተንግዶ አገልግሎቶች ለዓመት የሚመድበውን በጀት በማባከን 14 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ መጠቀማቸውን መርማሪ ቡድኑ አክሏል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በሞጆ ደረቅ ወደብ መታሸግ የነበረበትን የደንበኞች ንብረት ጂቡቲ እንዲታሸግ በማድረግ 470 ሚሊዮን ብር መንግሥት እንዲያጣ ማድረጋቸውንና ከ1,500 በላይ ወጣቶች ሥራ አጥ እንዲሆኑ ማድረጋቸውን፣ መርማሪ ቡድኑ በተፈቀደለት የምርመራ ጊዜ ለማወቅ መቻሉን አስረድቷል፡፡

በተጨማሪም የስድስት ሰዎች የምስክርነት ቃል መቀበሉንና መስከረም 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው የጭነት አስተላላፊነት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ተፈራ በስተቀር፣ የሰባት ተጠርጣሪዎች የተከሳሽነት ቃል ለመቀበል፣ በተጠረጠሩበት ጉዳይ ላይ የማነጋገር ሥራዎችን ማከናወኑን አስረድቷል፡፡ መኖሪያ ቤታቸውንና ቢሮአቸውን በመበርበርም፣ ከምርመራ ሥራው ጋር የሚገናኙ በርካታ ማስረጃዎችን መስብሰቡንም አክሏል፡፡ ከ2005 ዓ.ም. እስከ 2009 ዓ.ም. ድረስ ተጠቃለው የተሠሩ የኦዲት ሪፖርቶች ማሰባሰቡን፣ ሌሎች የተገኙ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን ለፎረንሲክና ለሚመለከታቸው ተቋማት ለማስመርመር መስጠቱን አስረድቷል፡፡

የ15 ምስክሮችን ቃል መቀበል፣ ከኦዲት ሪፖርቱ ጋር በተገናኘ የአምስት ኦዲተሮችን የሙያ ምስክርነት ቃል መቀበልና ከበርካታ ተቋማት ማለትም ከባንኮች፣ ከተቋሙ የተለያዩ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች፣ ከኢንፎርሜሽን፣ መረጃና ደኅንነት ኤጀንሲና ከሌሎችም ተቋማት ሰነዶችን ማሰባሰብ እንደሚቀረው በመግለጽ ለተጨማሪ የምርመራ ጊዜያት 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በራሳቸውና በጠበቆቻቸው አማካይነት ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹት፣ መርመሪ ቡድኑ እየገለጸ ያለው አገራዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ከእነሱ ጋር የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለና እነሱ የሚመለከቱ እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸው የሚተዳደሩት በእሳቸው ደመወዝ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ደመወዛቸውን ለቤተሰቦቻቸው እንዲለቀቅላቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸውና እሳቸውም የዋስትና መብታቸውን እንዲያስከብርላቸው የጠየቁት ተጠርጣሪ፣ የወደብና ተርሚናል አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደሳለኝ ገብረ ሕይወት ናቸው፡፡

የኮርፖሬት አገልግሎት ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሲሳይ አባፈርዳ ደግሞ፣ ‹‹በመርማሪ ቡድኑ የተነገረኝ የተጠረጠርኩበት ጉዳይና በችሎቱ ለፍርድ ቤቱ የተነገረው አይገናኝም፤›› ብለዋል፡፡ ሲያዙም እንዳልተነገረቸውና በፍርድ ቤቱ ደግሞ የማይመለከታቸውና ያልሆነ ነገር እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ ተገቢ አለመሆኑን በመጠቆም፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

የተጠረጠሩባቸው አብዛኛዎቹ ጉዳዮች በመርማሪዎች ተገልጾላቸው ማብራርያ መስጠታቸውን በመናገር ከመርከብ ግንባታ (ግዥ) ጋር በተገናኝ ግን እሳቸውን የሚመለከት ሳይሆን ዓለም አቀፍ ሕግጋትን ተከትሎ የሚከናወን መሆኑን የገለጹት ደግሞ፣ የሺፒንግ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቺፍ ኢንጂነር ዓለሙ አምባዬ ናቸው፡፡

የተጠረጠሩባቸው ጉዳዮች ዓለም አቀፍ የውል ስምምነቶች ከመሆናቸውም አንፃር አንድም የግል ባህሪያት የሌሉዋቸው መሆናቸውን ለመርማሪዎች የገለጹ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ተለውጥው መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ ላለፉት 31 ዓመታት ከጀማሪ መሐንዲስነት እስከ ኃላፊነት ሲሠሩ መቆየታቸውን የገለጹት ቺፍ ኢንጂነር ዓለሙ፣ ከ7,000 ዶላር እስከ 10,000 ዶላር እየተከፈላቸው ወይም ባሁኑ ምንዛሪ እስከ 150,000 ብር ሊከፈላቸው የሚችለውን ደመወዝ ትተው ከመርከብ የወረዱት  አገራቸውንና ሕዝባቸውን ለማገልገል ካላቸው ቅን አስተሳሰብ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ለአገራቸውም በርካታ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚያስገኙ ጥናቶችንና ፕሮጀክቶችን በመሥራት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዳደረጉ፣ መንግሥት ጭምር እንደሚያውቅ አስረድተዋል፡፡

ምርመራው እንዲቀጥልና እውነቱ እንዲወጣ የእሳቸውም ፍላጎት መሆኑን በመግለጽ ምንም እንኳን ፌዴራል ፖሊስ በጥሩ ሁኔታ ይዟቸው ቢገኝም ከባድ የሆነ የኩላሊት ሕመምና የደም ግፊት ስላለባቸው፣ በበቂ ዋስትና ከአገር እንዳይወጡ ጭምር ዕግድ ተጥሎባቸው በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

የጂቡቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ እውነቱ ታዬ ደግሞ፣ ቤተሰቦቻቸው ከእሳቸው ደመወዝ ውጪ ምንም የሚተዳደሩበት ገቢ እንደሌላቸው በመግለጽ፣ የታገደባቸው ደመወዝ እንዲለቀቅላቸው ጠይቀዋል፡፡ ከሚሠሩበትና ከቤታቸው ብዙ ሰነዶች እንደተወሰዱባቸው ገልጸው፣ ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

እሳቸው የተቀጠሩት በ2006 ዓ.ም. የገላን ወደብ ሥራ አስኪያጅ ሆነው እንደሆነ የተናገሩት ተጠርጣሪ፣ በአሁኑ ጊዜ የሞጆ ደረቅ ወደብ ሥራ አስኪያጅ ሌላ መሆናቸውን፣ መርማሪ ቡድኑ ወንጀል ተፈጽሟል የሚልበት ጊዜና እሳቸው የተቀጠሩበት ጊዜ ስለማይገናኝ፣ የታሰሩት በሌሉበትና በማይገናኙበት መሆኑን ጠቁመው በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

ለመጀመርያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡትና መስከረም 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር የዋሉት፣ የጭነት አስተላላፊነት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ተፈራም በጠበቃቸው አማካይነት ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ የተጠረጠሩበት ጉዳይ ሌሎች ኃላፊዎች ከተጠረጠሩበት ጋር በተገናኘ መሆኑን አስታውሰው፣ ንፅህናቸውን ስለሚያውቁና ከሥራ በስተቀር በመርማሪዎች በሚነገረው የጥፋት መጠን የሚናወጡ ባለመሆናቸው፣ እንዲሁም በአገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት እውነቱ እንደሚረጋገጥ በማመናቸው፣ በውጭ አገር ሆነው ጉዳዩን የሰሙት ቢሆንም መጥተው እጃቸውን መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ከአገር ይወጣሉ ወይም የሚያደርሱት ችግር አለ ሊባል ስለማይችል፣ ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብታቸው ተከብሮላቸው በውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ጠይቀዋል፡፡

መርማሪው ፖሊስም ጥያቄው ከአገር ይወጣሉ ወይም ያመልጣሉ ሳይሆን፣ የምርመራ ሰነዶችን ስለሚያጠፉና ምስክሮችን ስለሚያባብሉ ዋስትና ሊፈቀድላቸው አይገባም የሚል መሆኑን አስረድቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር አዳምጦ በሰጠው ትዕዛዝ፣ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ እንዳልተቀበለ አስታውቋል፡፡ ደመወዝ ሊከለከል ስለማይገባ የታገደ ደመወዝ እንዲለቀቅና መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን በተፋጠነ መንገድ በመሥራት በ12 ቀናት ውስጥ ማጠናቅቅ እንዳለበት አስታውቆ ለመስከረም 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

Standard (Image)

በአማራና በቅማንት ማኅበረሰብ በሕዝበ ውሳኔ ወቅት መጠነኛ ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር

$
0
0

የአማራና የቅማንት ማኅበረሰብ ተቀላቅሎ የሚኖርባቸውን ቀበሌዎች ለመለየት በጭልጋ ወረዳ የምትገኘውና ኳቤር ሎምየ ተብላ በምትጠራው ቀበሌ እሑድ መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል መጠነኛ ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር፡፡

ከጎንደር  ከተማ 140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘውና ኳቤር ሎምየ ተብላ በምትጠራው ቀበሌ በተካሄደው ምርጫ ሪፖርት እንዳረጋገጠው፣ በቅማንትና በአማራ ማኅበረሰቦች መካከል ለሰዓታት የዘለቀ ውዝግብ ተከስቶ ነበር፡፡

መራጮች በተለይም ነባሩ አስተዳደር እየተባለ የሚጠራው የአማራ ተወላጆች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የኳቤር ሎምየ ቀበሌ ነዋሪ ያልሆኑ ግለሰቦች ለመምረጥ ተገኝተዋል፡፡

አቶ ፈንታሁን አድነው የተባሉ ግለሰብ፣ ‹‹በደም ቅማንት የሚባለውን አምጥተው አስገቡብን፡፡ ከእንግድባ ቀበሌ አምጥተው ድምፅ እንዲሰጡ አደረጉ፡፡ እኛ ከሌላ ቀበሌ አማራ ብለን ማምጣት ግን አንችልም፤›› በማለት በቅሬታ ተናግረዋል፡፡

ሌላ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአማራ ተወላጅ ደግሞ፣ ‹‹በዚህ ቀበሌ ነዋሪ ያልሆኑና በአካባቢው አምስት ዓመት ያልሞላቸው ግለሰቦች መጥተው እንዲመርጡ እየተደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሪፖርተር ከሌላ ቀበሌ መጥተዋል የተባሉ ግለሰቦችን ተዟዙሮ ያነጋገረ ሲሆን፣ እነዚህ ግለሰቦች በቁጥር ከሃምሳ በላይ እንደሚሆኑና በዚህ ቀበሌ ከአምስት ዓመት በላይ የኖሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ሁለቱ ወገኖች በዚህ የተነሳ ባስነሱት ውዝግብ የምርጫ ሒደቱ ሳይጀመር ለሰዓታት ቆይቶ ነበር፡፡

የቅማንት ብሔር ተወላጅ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ አስማረ ዘለቀ በበኩላቸው፣ ‹‹እነዚህ ሰዎች የእንግድባ ቀበሌ ነዋሪዎች አይደሉም፡፡ የኳቤር ሎምየ ነዋሪ ናቸው፤›› ሲሉ መስክረዋል፡፡ በዚህ የምርጫ ጣቢያ የድምፅ አሰጣጥ ሒደቱ የተጀመረውም ከሁለት ሰዓት በኋላ እንደሆነ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ኦፕሬሽንና ሎጂስቲክስ ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ረቢራ ተናግረዋል፡፡ የቀበሌው ሊቀመንበር ለምርጫ አስፈጻሚዎች በመጨረሻ በጻፉት ደብዳቤ የቀበሌ ነዋሪነታቸውን በማረጋገጣቸው ግለሰቦቹ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ ይህንን ውሳኔ ግን የአማራ ተወላጆች ተቃውመዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ምርጫው የሚካሄደው ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት እንደሆነ ቢገልጽም፣ በዚህ ምርጫ ጣቢያ ለሰዓታት በቆየው የሁለቱ ወገኖች ውዝግብ ምክንያት የምርጫ ሒደቱ የተጀመረው ዘግይቶ ነው፡፡

በዚህ ውዝግብ የተሞላው የምርጫ ጣቢያ ሪፖርተር በአካል ተገኝቶ ለማረጋገጥ እንደቻለው፣ ድምፅ ለመስጠት የነበረው ሠልፍ ረዥም ከመሆኑም በላይ በግፊያና መጨናነቅ የተሞላ ነበር፡፡

በጎንደር ከተማ ዙሪያ ሕዝበ ውሳኔ ከሚካሄድባቸው ሁለት ቀበሌዎች መካከል አንዱ የብላጅግ ቀበሌ ሲሆን፣ በዚህ ቀበሌ በተካሄደው ምርጫ የቅማንት ተወላጆች ወደ ምርጫ ጣቢያው ሄደው እንዳይመርጡ የሚያከላክሉ አካላት እንደነበሩ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡ በዚህ ቀበሌ በሚካሄደው ምርጫ የቅማንት ብሔረሰብ ተወካይ አቶ ካሴ መለስ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ መራጮች ወደዚህ ምርጫ ጣቢያ መጥተው ድምፅ እንዳይሰጡ የሚያደርጉ ግለሰቦች ነበሩ፡፡

የእነዚህን ግለሰቦች ማንነት እንዲገልጹ ተጠይቀው፣ ‹‹እኔ አሁን እዚህ ሆኜ ሁኔታውን መከታተል አለብኝ፡፡ መጥተው ድምፅ እንዳይሰጡ የሚያደርጉ አካላት እንዳሉ ግን ሪፖርት ደርሶኛል፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ ምርጫ መካሄድ ቅር የተሰኙ አካላት እንዳሉ ሪፖርተር አረጋግጧል፡፡ ‹‹ለዘመናት ተዋልደንና በደም ተሳስረን እንደዚህ ዓይነት ጉድ በመጨረሻ መጣብን፤›› ሲሉ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰብ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሌላ ግለሰብ ደግሞ፣ ‹‹እኔ ዘጠኝ ልጆች አሉኝ፡፡ እኔ ቅማንት ነኝ፡፡ ሚስቴ አማራ ናት፡፡ ሁላችንም አማራን ነው የመረጥነው፤›› ብለዋል፡፡

ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ ዓመት የኢንጂነሪንግ ተማሪ ደግሞ የቅማንት ብሔር ተወላጅ መሆኑን ገልጾ፣ ባለፈው ጊዜ በአማራና በቅማንት ሕዝብ መካከል ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት የቤተሰቦቹ ንብረት የሆኑ 72 ከብቶች መቃጠላቸውን ተናግሯል፡፡ በመሆኑም ይህ ምርጫ መካሄድና ቅማንት ለብቻው መተዳደር እንዳለበት ያምናል፡፡ ምርጫ በመካሄዱም ደስተኛ መሆኑን ገልጿል፡፡

ምርጫ የተካሄደባቸው ስምንት ቀበሌዎችና 24 የምርጫ ጣቢያዎች ሲሆኑ፣ በእነዚህ የምርጫ ጣቢያዎችና ቀበሌዎች ወጣ ያለ ችግር እንዳልነበር የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳደር አቶ አየልኝ ሙሉ ዓለም ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ምርጫ የተካሄደባቸው ቀበሌዎችና ጣቢያዎች ሩቅ ቢሆኑም በጥሩ ሁኔታ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር ተዟዙሮ ባያቸው አራት የምርጫ ጣቢያዎች ማረጋገጥ እንደተቻለውም በምርጫው ዕለት ወጣ ያለ የፀጥታ ችግር አልነበረም፡፡ ነገር ግን በቅድመ ምርጫ ወቅት ጳጉሜን 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በአንከርደዛ ቀበሌ ግጭቶች እንደበሩና በዚህም አንድ የዞን መኪና በድንጋይ መሰበሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚሁ ዕለት ማታ ደግሞ የላዛ ሹምጌ ቀበሌ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በእሳት መቃጠሉ ታውቋል፡፡ በሚቀጥለው ቀን ደግሞ በጭልጋ ወረዳ በገለድባ ከተማ ሌሊቱን ሙሉ የጥይት ተኩስ እንደነበር ምንጮች ተናግረዋል፡፡

በቅድመ ምርጫው ወቅት በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች እንደነበሩም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ምርጫው ከተካሄደበት እሑድ መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም. እስከ ማክሰኞ ድረስ ችግር እንዳልነበር ዋና አስተዳዳሪው አቶ አየልኝ አስታውቀዋል፡፡

መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በቀድሞው ሰሜን ጎንደር ከስምንት ቀበሌዎች መካከል የሦስቱን ቀበሌ የምርጫ ሁኔታ በአካል በመገኘት ለመከታተል ተችሏል፡፡ በጎንደር ከተማ ዙሪያ ከሚገኙ ሁለት የምርጫ ጣቢያዎች መካከል አንዱ ብላጅግ ቀበሌ ሲሆን፣ በዚህ ቀበሌ በተካሄደው ምርጫ እስከ ሦስት ሰዓት ድረስ አብዛኛው ሰው ድምፅ ሰጥቶ ወደቤቱ የተመለሰ መሆኑን የምርጫ ጣቢያ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በዚህ የምርጫ ጣቢያ ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር እንዳልነበረም አስረድተዋል፡፡ ገና በጠዋቱ ሠልፍ እንደሌለና ለመምረጥ የመጣ ግለሰብ ቶሎ መርጦ እንደሚሄድም ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ሪፖርተር የቃኘው ሌላው የምርጫ ጣቢያ ነጋዴ ባህር የምርጫ ጣቢያ ‹‹ሀ እና ለ››ን ሲሆን፣ በእነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች የነበረው የምርጫ ሒደት በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁን የምርጫ ጣቢያ ሀ ኃላፊ አቶ ምናሴ ረጋሳ ተናግረዋል፡፡ ከአዳማ ከተማ እንደመጡ የተናገሩት አቶ ምናሴ፣ እስከ ቀኑ ሰባት ሰዓት ድረስ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ተመዝጋቢ ድምፅ መስጠቱን አረጋግጠዋል፡፡ ሌላውና ሦስተኛው ቀበሌ ኳቤር ሎምየ ሲሆን በዚህ ቀበሌ ረዣዥም ሠልፎች ታይተዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ የሚካሄደው በ12 ቀበሌዎችና በ34 የምርጫ ጣቢያዎች እንደሆነ ሲገልጽ ቢቆይም፣ የአራት ቀበሌዎች ምርጫ በመጨረሻው ሰዓት እንዲሰረዝ ተደርጓል፡፡ ለጊዜው ምርጫ እንደማይካሄድ የተወሰነባቸው ቀበሌዎች ላዛሹምየ፣ አንከርደዛ፣ ናራ አወደርዳና ገለድባ የሚባሉ ናቸው፡፡ ሁለቱ ቀበሌዎች ማለትም አንከርደዛና ላዛ ቀበሌዎች በፊትም ከሕዝቡ ጋር የተሟላ መግባባት ተደርሶ እንዳልነበር አቶ አየልኝ ጠቁመዋል፡፡

የእነዚህ አራት ቀበሌዎች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምንድነው የሚሆነው? በማለት ከሪፖርተር የቀረበላቸው ጥያቄ ሲሆን በምላሻቸውም፣ ‹‹በእነዚህ ቀበሌዎች ከዚህ ምርጫ በኋላ ከሕዝቡ ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጎ እንደገና እንዲካሄድ ነው የሚሆነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ለዚህ ምርጫ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ እንደተደረገበት እየተነገረ ሲሆን፣ ይህን ምርጫ ለማስፈጸም የተመደቡ ባለሙያዎች ከሦስት ክልሎችና ከአንድ የከተማዋ አስተዳደር ብቻ እንደሆነ አቶ ጌታቸው ረቢራ ተናግረዋል፡፡

አቶ ጌታቸው እንደሚሉት እነዚህ የምርጫ አስፈጻሚዎች በቁጥር በዛ ያሉ ሲሆኑ፣ ከዚህ በፊት ተካሂደው በነበሩ ምርጫዎች ተሳትፎ የነበራቸውና ልምድ ያላቸው እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ የመጡበት ክልልም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከደቡብ ክልል፣ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልልና ከኦሮሚያ ክልል መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት 23,283 ዜጎች ተመዝግበው 20,824 የሚሆኑ ድምፅ መስጠታቸውንም አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡ የምርጫው ውጤትም ያንኑ ዕለት ቆጠራ በማድረግ በየጣቢያዎች እንደተለጠፈ ገልጸው፣ አጠቃላይ ውጤቱ የሚገለጸው ግን ከመስከረም 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በኋላ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በቀሪዎቹ አራት ቀበሌዎች ሕዝበ ውሳኔ እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን መቼ እንደሆነ ግን ለማወቅ አልተቻለም፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምርጫ በተካሄደባቸው ስምንት ቀበሌዎችና 24 የምርጫ ጣቢያዎች ባለሙያዎችን በመመደብ መራጮች መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙ ማድረጉ ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ መራጮች በምርጫ ወቅት መብቶቻቸውን በትክክል እንዲጠቀሙና ተፅዕኖ እንዳይደርስባቸው ተደርጓል፡፡ እንደ ኳቤር ሎምየ የምርጫ ጣቢያ ዓይነት ግጭቶች ከነበሩና በዚህ ግጭት የመብት ጥሰቶች ከነበሩ እንዴት ነው ያያችሁት የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው በምላሻቸው፣ ‹‹በሁሉም የምርጫ ቀበሌዎች የተሰማሩ ባለሙያዎችን መረጃ አንድ ላይ ሰብስበንና አደራጅተን የመብት ጥሰቶች ከነበሩ ወደፊት የሚገለጽ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡ 

Standard (Image)

መሻሻሎችን አሳይቷል የተባለው የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ጉዳይ

$
0
0

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መካከል ተቀስቅሶ የነበረውን ግጭት ለማብረድ፣ ባለፈው ሳምንት የፌዴራሉ መንግሥት የፀጥታ አካላት ወደ ሥፍራው መሄዳቸው ይታወቃል፡፡

በዚህ ግጭት በርካቶች ሕይወታቸውን ሲያጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ለዚህ ግጭት ዳግመኛ መቀስቀስ ምክንያት እስካሁን ድረስ ቁርጥ ያለ አስተያየት ባይሰጥም፣ ግጭቱ ከዚህ የባሰ አደጋ እንዳያደርስና የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንዲመለሱ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን መንግሥት ሰሞኑን አስታውቀዋል፡፡

ስለግጭቱ መቀስቀስና ስለተፈናቀሉ ዜጎች፣ እንዲሁም ግጭቱ ከዚህ የባሰ ጉዳት እንዳያደርስ ሲባል የሁለቱ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳና የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አቻቸው አቶ አብዲ መሐመድ በሰጡት መግለጫ፣ ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት በሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች መካከል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

ርዕሳነ መስተዳድሮቹ በጋራ በሰጡት መግለጫ በጠፋው የሰው ሕይወትና ንብረት ጥልቅ ሐዘን እንደተሰማቸውም ተናግረዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የደረሰው ጉዳት የአንዱ ክልል ብቻ ሳይሆን፣ በሁለቱም ክልሎች ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አቶ አብዲ በበኩላቸው በግጭቱ ምክንያት የሞቱትም ሆነ የተፈናቀሉት ዜጎች የሁለቱም ክልሎች ወንድማማች ሕዝቦች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ግጭቱ በሁለቱ ክልል ሕዝቦች መካከል እንዳልነበረ ርዕሳነ መስተዳድሮች ጠቁመው፣ ይህንን ድርጊት አውግዘውታል፡፡ ሁለቱ ሕዝቦች የአንድ ኢትዮጵያ አካል ብቻ ሳይሆኑ ዘመናትን የተሻገረ የጋራ እሴትና ባህል ባለቤቶች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ በበኩላቸው፣ ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የኦሮሞ ሕዝብ ሶማሌዎችን፣ ሶማሌዎችም የኦሮሞ ተወላጆችን ለመከላከል መሞከራቸውን አስታውቀው፣ የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች የተፈናቀሉ ዜጎችን መደገፍ፣ አካባቢያቸውን ማረጋጋትና በግጭቱ ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ አካባቢያቸው መመለስ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ይኼንን ድርጊት የፈጸሙ አካላት እነማን እንደሆኑ እስካሁን እንዳልታወቀና እየተጣራ እንደሆነ መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገልጽ ተሰምቷል፡፡ የሁለቱ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ቢሮዎችም እርስ በራሱ የሚጣረስ መረጃ ሲያወጡ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የሁለቱ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች በዚህ ድርጊት ተሳታፊ የነበሩ አካላትን ለሕግ ለማቅረብ ቁርጠኛ መሆናቸውንም ቃል ገብተዋል፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔም፣ ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ከሁለቱ ክልሎች እጃቸው አለበት የተባሉ ግለሰቦች በአሁኑ ወቅት ተይዘው ምርመራ እየተደረገ መሆኑ ከዚህ በፊት የተገለጸ ሲሆን፣ ወደፊትም በዚህ ድርጊት ተሳታፊ ሆነው የተገኙ አካላት በቁጥጥር ሥር ውለው ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተናግረዋል፡፡  

የግጭት አካባቢዎች በፌዴራል መንግሥት እንዲጠበቁ የክልል የፀጥታ ኃይሎች ከወሰን አካባቢዎች ርቀው ሕዝባቸውን እንዲያረጋጉ፣ ዋና ዋና መተላለፊያ መንገዶች በመከላከያና በፌዴራል ፖሊስ እንዲጠበቁ የተላለፈው ውሳኔ መተግበር እንዳለበትም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

ርዕሳነ መስተዳድሮችም ሁለቱ ሕዝቦች ለዘመናት አብረው የኖሩ በመሆናቸው ሰላማቸውን በጋራ እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፣ የተቀሰቀሰው ግጭት ዳግመኛ እንዳይፈጠርና የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው በሚመለሱበት ጉዳይ ላይ ከሁለቱ ክልል ከተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎችና ርዕሳነ መስተዳድሮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፣ ይህን ግጭት ለማስቆም የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ አካላት ወደ ሥፍራው ሄደዋል፡፡ በዚህ ድርጊት ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦች በአፋጣኝ ለሕግ እንደሚቀርቡና በሕገ መንግሥቱ መሠረት ዕርምጃ እንደሚወስድባቸው ተናግረዋል፡፡ ግጭቱ በተከሰተባቸው የድንበር አካባቢዎችና ቀጣናዎች የፌዴራል መንግሥት ማንኛውንም የጦር መሣሪያ ወይም ትጥቅ የሚያስፈታ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በዚህ ድርጊት በሁለቱም ክልሎች መካከል ያሉ ልዩ ኃይሎች ተሳታፊ እንደነበሩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በኦሮሚያ ክልል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ለመፍታት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ልዩ ኃይል ከፍተኛ ሥራ ሠርቷል፡፡ አይከፈለውን ከፍሏል፡፡ ለዚህም ታላቅ ምሥጋና ይገባዋል፡፡ ይህ ቢሆንም ግን ሰሞኑን በተቀሰቀሰው ግጭት አንዳንድ የልዩ ኃይል አባላት ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ይኼን አጣርተን በሕግ እንጠይቃን፡፡ በሶማሌ ክልልም ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ እነሱንም አጣርተን ዕርምጃ እንወስዳለን፤›› ብለዋል፡፡ 

ይህ ግጭት ወደባሰ ደረጃ እንዲሄድ የሁለቱ ክልሎች መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ እንደነበረም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡ ይህ ድርጊት ከአሁን በኋላ መቆም እንዳለበት ማሳሰቢያ የሰጡ ሲሆን፣ ይህን ድርጊት የማያስተካክሉ ከሆነ ግን ዕርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል፡፡

‹‹የዜጎች ሰላም የማይዋጥላቸው ፀረ ሰላም ኃይሎች ችግሩ ወደ ከፍተኛ ሁኔታ እንዲሄድ በማድረጋቸው መንግሥት በሚያደርገው የማጣራት ሥራ ሁሉም ዜጋ ከመንግሥት ጎን በመቆም ትብብር ሊያደርግ ይገባል፤›› በማለት ያሳሰቡ ሲሆን፣ ችግሩን በሚያባብሱ ሚዲያዎች ላይ መንግሥት ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ ገልጸዋል፡፡

ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በግጭቱ ወቅት የደረሰን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጣርቶ፣ እጃቸው ያሉባቸው አካላት ከየትኛውም ወገን ይሁኑ የማያዳግም ዕርምጃ መንግሥት እንደሚወስድ አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሁለቱም ክልሎች በተለይም ግጭት በተከሰተባቸው አወዳይና ሌሎች አካባቢዎች መረጋጋት እየታየ እንደሆነ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ተፈናቅለው የነበሩ ግለሰቦች ወደ ቀያቸው በሚመለሱበት ሁኔታ ላይም ሁለቱ ክልሎች ከፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴር ጋር በመሆን እየሠሩ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከቀን ገቢ ግምት ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ፣ በአዲስ አበባና በአማራ ክልሎች ተቃውሞ ሲነሳ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ከበደ ጫኔ፣ በቅርቡ የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይታወሳል፡፡ የቀድሞውን የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለ ብርሃንን የተኩት አቶ ከበደ፣ ይህንን ችግር  ለመፍታት ትልቅ የቤት ሥራ ከፊታቸው እንዳለ እየተነገረ ነው፡፡

በዚህም የተነሳ የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮችን በጋራ አገናኝቶ የጋራ መግለጫ እንዲሰጡ ከማድረግ ባሻገር፣ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ተመልሰው በሚቋቋሙበት ላይ ከሁለቱ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጋር ከመስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ወዲህ ባሉት ቀናት በየቀኑ ውይይት እያደረጉ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት ሚኒስትሩ፣ ብአዴን በባህር ዳር ከተማ ዓመታዊ ጉባዔውን እስከ መስከረም 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ያካሄደ ቢሆንም፣ በዚህ ጉባዔ ላይ ከመስከረም 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እንዳልተሳተፉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ ኤምባሲ ማክሰኞ መስከረም 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች በተለይም በሐረርጌ የጎሳ ግጭትንና የበርካታ ሰዎችን መፈናቀል አስመልክቶ በሚወጡ አሳሳቢ ዘገባዎች ተረብሸናል፤›› ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ግልጽ በሆነ አካሄድ ጉዳዩን እንዲያጠራና አጥፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቋል፡፡ ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲሹ ማበረታታት እንዳለበትም አሳስቧል፡፡

አገሪቱ ግልጽና ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይት፣ ግልጽ የመንግሥት አሠራር፣ እንዲሁም የዴሞክራሲና የፍትሕ ተቋማትን በማጠናከር ስትችል የበለፀገችና ዴሞክራሲያዊት አገር ልትሆን እንደምትችልም አመልክቷል፡፡ የሰሞኑን ሁነቶች በተጠቀሱ ዘርፎች ይበልጥ ፈጣንና ተጨባጭ ለውጥ አስፈላጊ እንደሆነ አመላካች መሆናቸውንም በመግለው አስታውቋል፡፡

ሰሞኑን በሁለቱ ክልሎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ጥያቄ የሚያቀርቡ አሉ፡፡ የፖለቲካ ተንታኙ ንጋት አስፋው (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ለዚህ ግጭት መከሰት ዋነኛ መንስዔው በሁለቱ ክልሎች አመራሮች በኩል የጋራ ስምምነት ባለመደረሱ ነው፡፡ ‹‹ለፈሰሰው ደም ተጠያቂው የሁለቱ ክልሎች አስተዳዳሪዎች ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ ያደርሰኛል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩን በሰከነ መንገድ መፍታት ሲገባ በሚዲያ ላይ በሁለቱ ወገኖች በኩል አላስፈላጊ ነገሮች መወራወር ከአመራር ብስለት ጉድለት የመጣ ነው ይላሉ፡፡

ሁሉም በፌዴራል ጥላ ሥር እስካሉ ድረስ መወያየትና ጉዳዩን በውስጥ ወደ በመያዝ መፍትሔ መምጣት ይገባ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ወደ ሕዝቡ ዘለቅ ብሎ በመግባት የጉዳዩን መነሻ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አጥንቶ መፍትሔ መስጠት እንጂ፣ መዘላለፍ እንደ አርዓያ የሚታይ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ያለው ፖለቲካ ውጥንቅጡ የወጣ እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኖች ይናገራሉ፡፡ በሶማሊያ፣ በሊቢያ፣ በሶሪያ፣ በየመንና በሌሎች አገሮች ያለው ሁኔታ ምስቅልቅሉ የበዛና በሺሕ ለሚቆጠሩ ዜጎች ሞትና ስደት ምክንያት እንደሆነ ሲነገር ይሰማል፡፡ ዶ/ር ንጋት ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ የቤት ሥራዋን በትክክል መሥራት እንዳለባት ይናገራሉ፡፡ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለንን የቤት ሥራ በትክክል መሥራት የሚቻለውና አሸናፊ የምንሆነው በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል ያለው ግጭት ሲፈታ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ በአገር ጉዳይ ላይ ቀልድ እንደማያስፈልግ የገለጹት ዶ/ር ንጋት፣ ሕዝብና መንግሥት እንደዚህ ዓይነት ግጭቶች እንዳይከሰቱ መሥራት ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ግጭቶች በአገሪቱ መደጋገማቸውን አስታውሰው፣ የዚህ ችግር ዋነኛ መፍትሔ ደግሞ በአመራር አካላት ባለ ችግር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡  በአሁኑ ወቅት ሕዝቡን ያስመረሩና ለመልካም አስተዳደር ችግር የሆኑ አካላት እንዳሉ ተናግረው፣ ዛሬ ነገ ሳይባል ዕልባት እየሰጡ መሄድ ተገቢ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል ባለፈው ሳምንት ለተቀሰቀሰው ግጭት ዋነኛ ተጠያቂዎችን በመለየት፣ አሁንም ቢሆን ግን ሌላ ግጭት እንዳይከሰትና የተፈናቀሉ ዜጎች የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው  መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡   

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሰሞኑን ‹‹የሕዝቦች የቆየ ወንድማማችነት በጊዜያዊ ችግር ሳይገታ ተጠናክሮ ይቀጥላል፤›› በሚል ርዕስ መግለጫ አውጥቷል፡፡

‹‹አገራችን ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ገና ጨቅላ ዕድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም፣ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ባለፈባቸው ጥቂት ዓመታት ውስጥ በርካታ አንፀባራቂ ድሎችን ማስመዝገብ የቻለ ነው። ከአሁኑ ለሌሎች አገሮች ልምዶችን እያካፈለ የሚገኝም ሥርዓት ሆኗል፡፡ አገራችን ሰላም በራቀው የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ እየኖረች፣ የራሷን ሰላም አስተማማኝ ከማድረግ አልፋ ለአካባቢውና ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች የሰላም ዘብ ለመሆን የበቃችውም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ወደውና ፈቅደው በመሠረቱት ፌዴራላዊ ሥርዓት አማካይነት ውስጣዊ ሰላሟን በአስተማማኝ መልኩ ለማረጋገጥ በመቻላቸው ነው። ኢትዮጵያውያን እነዚህና ሌሎች በርካታ አንፀባራዊ ድሎችን ማስመዝገብ የቻሉት ግን መንገዳቸው ሁሉ አልጋ በአልጋ ስለሆነላቸው አልነበረም። በየወቅቱ የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ሁሉ በፌዴራል ሥርዓታቸው ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው በፅናት እየፈቱ በማለፋቸው እንጂ፤›› ይላል መግለጫው፡፡  

በቅርቡ ካጋጠሙ ፈተናዎች መካከል አንዱ በአንዳንድ አካባቢዎች ከወሰን ጋር ተያይዘው ይነሱ የነበሩት ችግሮች እንደሆኑ፣ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የፌዴራሉና የሚመለከታቸው የክልል አመራሮችና ወንድማማች ሕዝቦች በጋራ ሲሠሩ መቆየታቸው፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ እንዲሁም በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል ከወሰን ጋር ተያይዞ ተፈጥረው የነበሩትን ችግሮች በመፍታት ረገድ አበረታች ሥራዎች ተከናውነዋል ብሏል፡፡ ‹‹በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል ከወሰን ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በተካሄደው እንቅስቃሴ አበረታች ሥራዎች ቢከናወኑም፣ አሁንም ቀሪ ሥራዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ መሀል ግን ለዘመናት አብረው የኖሩትን የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ወንድማማች ሕዝቦችን ፈጽሞ ሊወክል የማይችል ግጭት ሰሞኑን በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ ለወገኖቻችን ሞትና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህ ግጭት ሳቢያ ሕይወታቸውን ላጡና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ሁሉ የኢፌዴሪ መንግሥት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ፣ ለቤተሰቦቻቸውም መፅናናትን ይመኛል፤›› በማለት ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡

ችግሩ ወደ ከፋ አደጋ እንዳይሸጋገር ለመቆጣጠር ሲባል የአገር መከላከያና የፌዴራል ፖሊስ ሠራዊት ግጭቱ ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ከክልሎቹ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በትብብር በመሥራት፣ ሁኔታውን በመቆጣጠርና በማረጋጋት ላይ እንደሚገኙም አስታውቋል፡፡ ግጭቱን በማነሳሳትና በማባባስ የተሳተፉ ወገኖችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ በሚከናወነው የቁጥጥር ሥራም በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም፣ አስቀድሞ ለመከላከል ሲባል የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተወካዮች በሥፍራው ተገኝተው ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተሉ ናቸው ብሏል፡፡ በግጭቱ ሳቢያ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በጊዜያዊ ማረፊያ ቦታዎች በማቆየት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ በመደረግ ላይ መሆኑን፣ በቀጣይም ወደ ቀድሞ መኖሪያ አካባቢዎቻቸው ተመልሰው የተረጋጋ ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡

ችግሩን ከማረጋጋት ባለፈ በዘላቂነት ይፈታ ዘንድ መንግሥት ከክልሎቹ አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሕዝቦች ጋር በጋራ በመሆን ከአሁን በፊት የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጿል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የሁለቱ ክልሎች ወንድማማች ሕዝቦች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በጊዜያዊ ግጭት ሳይረበሹ ችግሩን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አግባብ ለዘለቄታው ለመፍታት ሲያካሂዱት የነበረውን ጥረት አጠናክረው በመቀጠል፣ ለችግሩ ዘላቂ ዕልባት በመስጠት ላይ አተኩረው እንዲሠሩ መንግሥት ጥሪውን ያቀርብላቸዋል ብሏል፡፡ ‹‹የአገራችንን ሰላም፣ ልማትና ብልፅግናን የማይወዱ አንዳንድ ኃይሎች ጊዜያዊ ግጭቶችን በመቆስቆስና በማፋፋም አገራችንን ወደ ጥፋትና ውድመት ለመክተት እያደረጉት ያለው ማንኛውም እንቅስቃሴ ከሕዝቦቻችን ዕይታ የተሰወረ ባለመሆኑ፣ የአገራችንን ሰላም በመጠበቅ ረገድ ስትጫወቱት የነበረውን የመሪነት ሚና አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉም መንግሥት ጥሪውን ያቀርብላችኋል፤›› በማለት በመግለጫው አትቷል፡፡

‹‹የአንዱ ወይም የሌላኛው ሕዝብ ተቆርቋሪ በመምሰል፣ በሶሻል ሚዲያና በሌሎች የመገናኛ አውታሮች አማካይነት ችግሩን በማራገብና በማጋነን፣ በሽብርና የጥላቻ ቅስቀሳ እኩይ ተግባር ላይ የተሰማራችሁ አካላት ሁሉ ከድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ መንግሥት ያስጠነቅቃል፤›› ካለ በኋላ አንዳንድ አካላትም፣ በተፈጠረው ጊዜያዊ ችግር በመደናገጥ በደመ ነፍስ እየሰጡት ያለው መረጃና እርስ በርስ የመወነጃጀል ተግባር ችግሩን ከማባባስ ያለፈ ፋይዳ የሌለው በመሆኑ ከዚህ መሰሉ አድራጎት እንዲታቀቡ መንግሥት እንደሚያሳስብ አስታውቋል፡፡ ‹‹በዚህ መሰሉ ተግባር ላይ መሳተፍ የሕግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ከባድ ወንጀል እንደሆነም መንግሥት ማስገንዘብ ይወዳል፤›› ሲል የአቋም መግለጫው ደምድሟል፡፡

 

Standard (Image)
Viewing all 475 articles
Browse latest View live