Quantcast
Channel: እኔ የምለዉ
Viewing all 475 articles
Browse latest View live

የኤርትራ ማዕቀብና ውስብስቡ የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት

$
0
0

በኢሳያስ አፈወርቂ የምትመራው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተነገጠለች ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ተቆጥሯል፡፡ አነስተኛ የሆነ ሕዝብና የቆዳ ስፋት ያላት ኤርትራ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ አገሮች በተለያዩ ምክንያቶች አነጋጋሪና አወዛጋቢ ከሆነች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

የአሰብና የምፅዋ ወደቦች ባለቤት የሆነችው ይህች ትንሽ አገር የምትገኝበትን የጂኦ ፖለቲካ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ብዙ አገሮች ፊታቸውን ወደ እሷ ሲያዞሩም ይታያሉ፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ሁለት አገሮች ከተከፈሉ በኋላ የተለያየ አሠላለፍ እንደያዙ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ ወደ አውሮፓና አሜሪካ ፊቷን ስታዞር ኤርትራ ደግሞ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያና ግብፅ ማዘንበሏን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይኼ አሠላለፍ ቆይቶም ሁለቱ አገሮች በተቃራኒ ጎራ እንዲሠለፉ ከማድረግ ባሻገር ወደ ለየለት ጦርነት እንዲገቡም አድርጓቸው ነበር፡፡

በሁለቱ አገሮች አመራሮች አለመግባባት የተነሳም ሕዝቦቹ እንዲለያዩ ተገደዋል በማለት የሚተቹ ተንታኞች አሉ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ የወቅቱ ፕሬዚዳንት አቶ የሸዋስ አሰፋ በዚህ ጉዳይ ላይ ይስማማሉ፡፡ ‹‹እነዚህ አንድ የነበሩ ሕዝቦች አሁን ሁለት ከመሆናቸው ባሻገር በመሪዎች አለመግባባት የተነሳ ወንድማማችና እህትማማች ሕዝብ ወደ ጦርነት ገብቶ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ የአሰብን ወደብ በሊዝ ለመከራየት ከኤርትራ ፈቃድ አግኝታለች፡፡ ይኼ ለሳዑዲ ዓረቢያ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ሲነገር ይሰማል፡፡ ይህም በገልፍ አገሮች ዘንድ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ከማድረጉም ባሻገር፣ በቀይ ባህር በኩል ያለውን አካባቢ በቅርብ ርቀት ለመከታተል ዕድል እንደከፈተላት ይነገራል፡፡ ምንም እንኳ የአሰብና የምፅዋ ወደቦች እስከዛሬ ድረስ ከግመል ውኃ መጠጫነት እንዳልዘለሉ እየተነገረ ቢሆንም፣ አገሮች በተለይም የገልፍ አገሮች በዚህ አካባቢ የራሳቸው ቀጣና እንዲኖራቸው ደፋ ቀና ሲሉ ይታያል፡፡ ለአብነት ያህልም ግብፅ በተደጋጋሚ ጊዜ በዚህ ቀጣና ድርሻ እንዲኖራት ጥረት እያደረገች መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ግብፅ በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የዓባይ ወንዝ ሙግት በበላይነት ለመወጣት ዙሪያ ጥምጥም ስትሄድ ተስተውሏል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር እያደረገች ካለችው ዲፕሎማሲ ባሻገር በቀይ ባህር በኩል በተለይም በአሰብና በምፅዋ ወደቦች አካባቢ ወታደራዊ ቤዝ ለመገንባት ጥረት እያደረገች ነው፡፡ ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅማም አጋርነቷን አጠናክራለች፡፡ የኤርትራ ፕሬዚዳንት በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ ካይሮ ሲያቀኑ መታየት ሚስጥሩም ይኼ እንደሆነ ይነገራል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም በሶማሊያ እየተስፋፋ የመጣው የአሸባሪነት ድርጊት አንዱ መንስዔም ኤርትራ እንደሆነች በርካታ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ አልሸባብን በመደገፍና በማስታጠቅ በቀጣናው ያለው ሰላምና መረጋጋት እንዲደፈርስ ኤርትራ እየሠራች መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሲገልጽ ቆይቷል፡፡

ኢትዮጵያን በመተንኮስ ሳይቻላት ደግሞ አሸባሪዎችን በማስታጠቅና በመደገፍ አገሪቱ እንድትዳከም ሌት ከቀን እየሠራች እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይኼንን ጉዳይም ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ጊዜ ለተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አቤት ስትል መቆየቷን የውጭ ጉዳዩ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ተናግረዋል፡፡

በዚህም የተነሳ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ እ.ኤ.አ. በ2009 ማዕቀብ ጥሎባታል፡፡ በዚህ ማዕቀብ አገሪቱ ከውጭ የጦር ማሣሪያ እንዳታስገባ ከልክሏል፡፡

በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው የኤርትራ መንግሥት ከድርጊቱ ሊቆጠብ ባለመቻሉ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት እ.ኤ.አ. ታኅሣሥ 16 ቀን 2016 ባደረገው ስብሳባ በአገሪቱ ላይ ዳግመኛ ማዕቀብ ጥሎባታል፡፡ ይኼ ማዕቀብ እ.ኤ.አ. እስከ ኅዳር 15 ቀን 2017 የሚቆይ እንደሆነ በተመድ ውሳኔ 2317 ምዕራፍ ሰባት ላይ በዝርዝር ሰፍሯል፡፡ ማዕቀቡ ሩሲያን ጨምሮ በአንጎላ፣ በቻይና፣ በግብፅና በቬንዙዌላ ድምፅ ተአቅቦና በአሥር አገሮች ድጋፍ ፀድቋል፡፡

በዚህ ማዕቀብ ኤርትራና ሶማሊያ የጦር መሣሪያ ግዢ እንዳይፈጽሙ ዕግድ ተጥሎባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ አገሮች በተለይም ኤርትራ የተጣለባትን ማዕቀብ እየጣሰች መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለሦስተኛ ጊዜ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል አገር ነች፡፡ አባል ከሆነች አንድ ዓመት ባይሞላትም በቆይታዋ ብዙ ሥራዎችን ስታከናውን መቆየቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት አባል በመሆኗ በምሥራቅ አፍሪካ ያለውን ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው ተደርጓል፡፡ ከደቡብ ሱዳን እስከ ሶማሊያ፣ ከቻድ እስከ ኤርትራ ያለውን የፀጥታ ጉዳይ በማንሳትና ለውይይት በማቅረብ ትኩረት እንዲሰጠው መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ኤርትራ በአካባቢው ያላትን የጠብ አጫሪነት ድርጊትም ኢትዮጵያ እንዳጋለጠች ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ይኼን ዕድል ተጠቅማ ኤርትራ የተጣለባትን ማዕቀብ እያከበረች እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ስትገልጽ መቆየቷም ተጠቅሷል፡፡ በዚህም የተነሳ የፀጥታው ምክር ቤት ወደ ኤርትራ አጣሪ ቡድን ሊልክ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ ይኼ ውጤት ሊመጣ የቻለው ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆኗ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ አገሪቱ ምን ያህል አሸባሪ ቡድን እንደምትደግፍና ለቀጣናው ሰላም መስፈን አደናቃፊ መሆኗን እንደሚያጋልጥ ተስፋ እንዳላቸው እየተናገሩ ነው፡፡ አቶ መለስ በዚህ ጉዳይ ላይ አይስማሙም፡፡

አቶ መለስ እንደሚሉት፣ በኤርትራ ላይ ሲጀመር ማዕቀብ የተጣለበት ዝርዝር ምክንያቶች እንዳሉ ያብራራሉ፡፡ ከእነዚህ መካከልም የኤርትራ መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ባለው የአተራማሽነት ፖሊሲ፣ የጂቡቲን ደኅንነት አደጋ ላይ በመጣሉና  ከአልሸባብ ጋር አንድ ላይ ሆኖ በሽብር ተግባር ላይ መሰማራቱ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህን ጉዳዮች መሠረት በማድረግ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና የአፍሪካ ኅብረት ውይይት አድርገው ጉዳዩን ወደ ተመድ የፀጥታው ምክር ቤት እንደላኩት አቶ መለስ ተናግረዋል፡፡  በዚህ መሠረት በኤርትራ ላይ የተጣለውን ወይም ደግሞ ወደፊት ሊጣል የሚችለውን ማዕቀብ ከኢትዮጵያ ጋር አያይዞ ማቅረብ፣ የኤርትራ መንግሥት የአሸባሪነት ድርጊትን አሳንሶ ማየት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ተንታኞች በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ መጣሱን የሚያጣራ ቡድን ወደ አገሪቱ ሊላክ መሆኑን በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶችን እየሰጡ ነው፡፡ የመጀመርያው ጉዳይ ኤርትራ ይኼንን ቡድን አሜን ብላ ትቀበለዋልች ወይ የሚለው ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ አገሪቱ የባሰ የአተራማሽነት ድርጊቷን እንድትገፋበት የሚያደርግ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ በመስከረም ወር 2010 ዓ.ም. በሚኖራት የአንድ ወር የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንትነት፣ ኤርትራን በተመለከተ ለንግግር የሚጋብዝ አጀንዳ ማቅረብ እንደሚገባትም አክለው ያስረዳሉ፡፡

በተለያዩ አካላት ተጠንቶና ታይቶ በኤርትራ ላይ ማዕቀብ ቢጣልም፣ አሁንም ማዕቀቡን እየጣሰች ለመሆኑ የሚያጣራ ቡድን ሊላክ መሆኑ እተየሰማ ቢሆንም፣ አሁንም ኤርትራን ለንግግር መጋበዝ ተገቢ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በውጭ ግንኙነት ስትራቴጂካዊ ጥናት ኢንስቲትዩት የጂኦ ፖለቲካ ጉዳዮች ተመራማሪና ተንታኝ አቶ አበበ አይነቴ  በዚህ ጉዳይ ላይ ይስማማሉ፡፡ አቶ የሸዋስ በበኩላቸው ይኼንን ሐሳብ ይቃወማሉ፡፡ ድርድር መልካም ቢሆንም እነዚህ ፓርቲዎች እስካሉ ድረስ ለውጥ ሊመጣ እንደማይችል እምነታቸውን ይናገራሉ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ደግሞ የኤርትራ መንግሥት ከኢትዮጵያ ተደጋጋሚ የሆነ የእንነጋገር ጥያቄ ቀርቦለት እንዳልተቀበለው ግልጽ አድርገዋል፡፡ የኤርትራ መንግሥት አሁን ካለው የአተራማሽነት ባህሪው ለውጥ እንዳላመጣ፣ ይኼን ጉዳይ የሚከታተለው የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አጣሪ ቡድን ከወራት በፊት ማረጋገጡንም ጠቁመዋል፡፡

የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ኤርትራ የተጣለባትን ማዕቀብ ማክበርና አለማክበሯን በተመለከተ የሚያጣራ ቡድን ሊላክ የታቀደውም ከዚህ ቡድን ሪፖርት ተነስቶ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ተንታኞች ይኼን ይበሉ እንጂ አቶ የሺዋስ ኢትዮጵያ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆኗ የተነሳ ይኼንን ጉዳይ የቤት ሥራዋ አድርጋ በመሥራትና በመከተል የፈጠረችው ጫና ነው ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ላይ ሁለት ፖሊሲዎችን ሲያራምድ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አንደኛው ተመጣጣኝ ዕርምጃ የሚለው ሲሆን፣ ሁለተኛው መደራደር ነው፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ፖሊሲዎች በተደጋጋሚ ጊዜ ውጤት እንዳላመጡም ሲነገር ነበር፡፡

በዚህም የተነሳ መንግሥት ከወራት በፊት በኤርትራ ላይ የሚከተለውን ፖሊሲ ለመቀየር አዲስ ፖሊሲ እያረቀቀ መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡ ይኼ አዲሱ ፖሊሲ ምን እንደሆነ ባይታወቅም፣ አብዛኞቹ የዘርፉ ባለሙያዎች ኤርትራን ወደ ድርድር የሚያመጣት ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ሌላ ማዕቀብ እንዲጥልባት ግፊት ማሳደሯና አሁን ደግሞ ማዕቀቡን ማክበሯንና አለማክበሯን የሚያጣራ ቡድን እንዲላክ ሐሳብ ማመንጨቷ፣ አገሪቱ ልትከተል ካሰበችውና የብዙ ባለሙያዎች እምነት የሆነውን ተቀራርቦ የመነጋገር ፖሊሲ ሊያሻክረው እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ አቶ የሸዋስ ግን በዚህ ሁኔታ ሁለቱ መሪዎች ተቀራርበው መነጋገር እንደማይችሉ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ አበበ በበኩላቸው፣ ይኼ ሐሳብ የማይጣረስ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹የተለየ ፖሊሲ የተባለው ኤርትራ የያዘችውን ፖሊሲ እንድታስተካከል ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በኢጋድ መድረክ ውጤታማ የሆነችውም በዚህ ምክንያት ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ የሺዋስ ግን በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ ‹‹ፖሊሲዬን አሻሽላለሁ የሚለው በእኔ እምነት አይሠራም፡፡ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ያለው ግንኙነት የጌታና የአሽከር ነው፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡

‹‹የኤርትራ መንግሥት ሁሌም ጌታ መሆን ነው የሚፈልገው፡፡ ይኼኛው ደግሞ ትልቅ አገርና ሰፊ ሀብት ስለያዝኩ አይሆንም ይላል፡፡ ስለዚህ ይኼ ጉዳይ መቼም አይፈታም፡፡ ሰዎቹም እነዚያው ናቸው፡፡ የትውልድ ለውጥም የለም፤›› በማለትም ይገልጻሉ፡፡

አቶ የሸዋስ ሁለቱ ተስማምተው የሚኖሩበት ጊዜ አይኖርም ብለው፣ ‹‹የሕዝቡን ግንኙነት ግን ለብቻ እንዲታይ እፈልጋለሁ፤›› በማለት አክለዋል፡፡ የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች አንድ እንደነበሩና ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩ ሕዝቦች ለሁለት መከፈላቸውን አስታውሰዋል፡፡

ምንም እንኳ ኤርትራ ማዕቀብ የተጣለባት አገር ብትሆንም ወደ ዓረብ አገሮች እየተሳበች የጦር መሣሪያ ግዥና ሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦችን እንደምታስገባ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አቶ የሸዋስ እንደሚሉት፣ ማንኛውም አገር አንዱ ፊቱን ካዞረበት ወደ ሌላው ይሄዳል፡፡ ‹‹ኤርትራ በሕዝብ ቁጥር፣ በተፈጥሮ ሀብትና በቆዳ ስፋት ትንሽ አገር ነች፡፡ ኤርትራ ትንሽ አገር ብትሆንም ለዚህ ቁመና የበቃችው ደግሞ በዓረብ አገሮች ድጋፍ ነው፤›› ይላሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት እነዚህ የዓረብ አገሮች ወደ ቀይ ባህር እየተሳቡ ወታደራዊ ቤዝ እያቋቋሙ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚህ አካባቢ ወታደራዊ ቤዝ ማቋቋም በተመለከተ አቶ የሸዋስ ሲገልጹ፣ ‹‹ወታደራዊ ቤዝ በጂቡቲም ሆነ በኤርትራ ማቋቋም ቦታ የሰጡትን የእነዚህን አገሮች ድክመቶች፣ የእነዚያን ደግሞ ድንበር ተሻግሮ መምጣት የሚያሳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ በተለይም ከ1990 ዓ.ም. ወዲህ ዓይንና ናጫ ሆነው እየኖሩ ያሉ አገሮች ናቸው፡፡ በሁለቱ ድንበሮች መካከል ውዝግብ ከተፈጠረ ከሃያ ዓመታት በላይ ተቆጥሯል፡፡ ምንም እንኳ የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች አንድ የነበሩ ቢሆንም፣ በተፈጠረው የፖለቲካ ልዩነት ሳቢያ መለያየታቸውን በቅሬታ የሚያቀርቡ ድምፆች ከየአቅጣጫው ይሰማሉ፡፡

በተጠንቀቅ ላይ ያለው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በድንበር አካባቢ ያሉ የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች ተረጋግተው እንዳይኖሩ እያደረገ መሆኑም ይነገራል፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜ የኤርትራ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ዜጎችን አፍኖ እየወሰደና በጉልበት ሥራ እያሰማራ መሆኑ ደግሞ፣ ጉዳዩን የከበደ እንደሚያደረገው በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ተደጋጋሚ የሆነ የእንነጋገር ጥያቄ እንዳቀረበች ስትናገር ቢሰማምና ኤርትራን በተመለከተ አዲስ ፖሊሲ ለመከተል ብታቅድም፣ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ግፊት በማድረግ ኤርትራ የተጣለባትን ማዕቀብ ባለማክበሯ ጫና ለመፍጠር ጥረት ማድረጓ ግልጽ እየሆነ ነው፡፡ ኤርትራ በአካባቢው በበጥባጭነት ስሟ በተደጋጋሚ መነሳቱ ደግሞ ወደፊት ከበድ ላሉ ማዕቀቦች ሊዳርጋት እንደሚችል ብዙዎችን ያስማማል፡፡

Standard (Image)

አሜሪካ በኤርትራ መንግሥት ላይ የቪዛ ማዕቀብ ልትጥል እንደምትችል ገለጸች

$
0
0

አሜሪካ በኤርትራ መንግሥት ላይ የቪዛ ማዕቀብ ልትጥል እንደምትችል በመግለጽ አስጠነቀቀች፡፡

ዋሽንግተን ፖስትና ሌሎች የአሜሪካ ታዋቂ ጋዜጦች እንደዘገቡት፣ አሜሪካ በኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናትና ዜጎች ላይ የጉዞ ማዕቀብ (የቪዛ ማዕቀብ) ለመጣል የምትገደደው፣ ከአሜሪካ የሚባረሩ ኤርትራውያንን የኤርትራ መንግሥት ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነው፡፡

የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ዴቪድ ላፓን ባለፈው ሳምንት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ ኤርትራን ጨምሮ በአራት አገሮች ላይ የቪዛ ማዕቀብ እንዲጣል ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (ስቴት ዲፓርትመንት) በደብዳቤ ጥያቄ ቀርቧል፡፡

ቃል አቀባዩ የአገሮችን ስም በወቅቱ ይፋ ባያደርጉም ዋሽንግተን ፖስት ምንጮቹን በመጠቀም ኤርትራ አንደኛዋ አገር መሆኗን አስታውቋል፡፡

በኤርትራ ላይ ከሚጣለው የጉዞ ማዕቀብ በተጨማሪ በአሜሪካ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኤርትራውያን፣ አሜሪካ ከአገር ማስወጣት እንደምትጀምር አስታውቃለች፡፡

የኤርትራ መንግሥት ዜጎቹን በአስገዳጅ የውትድርና አገልግሎት ውስጥ በማስገባት፣ ሰብዓዊ መብቶችን በመርገጥና ዜጎችን በእስርና በግርፋት በማሰቃየት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሚታወቅ መሆኑን የገለጸው ዘገባው፣ አሜሪካ ይህንን እየተገነዘበች ኤርትራውያንን ከአገር እንዲወጡ ለማድረግ መወሰኗ ግልጽ አለመሆኑን ጠቁሟል፡፡

የኤርትራ መንግሥት በዜጎቹ ላይ በሚፈጽመው ግፍ ምክንያት በርካታ ኤርትራውያን አገራቸውን ጥለው ወደ ኢትዮጵያና ወደተለያዩ የአውሮፓ አገሮች በመሰደድ ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2014 እስከ 2016 ብቻ ከ95 ሺሕ በላይ ኤርትራውያን የሜዲትራኒያን ባህር አቋርጠው አውሮፓ መግባታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

አሜሪካ በኤርትራ መንግሥት ላይ የጉዞ ማዕቀብ እንደምትጥል ይፋ የሆነው ባለፈው ሳምንት ሲሆን፣ ባለፈው ዕትም ኤርትራ በተመድ የተጣለባትን ማዕቀብ በመጣሷ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አጣሪ ቡድን ለመላክ መወሰኑን መዘገባችን  ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ያገኘችውን ተለዋጭ አባልነት መቀመጫ ተጠቅማ፣ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግበት ጫና በማድረጓ የተገኘ ውጤት እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡

በተመድ የሚላከው ቡድን ኤርትራ ማዕቀቡን መጣሷን ካረጋገጠ የተጣለባት ማዕቀብ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል፣ እንዲሁም አሜሪካ የጉዞ ማዕቀቡን በአገሪቱ ባለሥልጣናት ላይ ከጣለች በፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ተወክላ ራሷን መከላከል እንዳትችል ያደርጋል፡፡

 

Standard (Image)

በሰሜን ጎንደር አዲሱ የዞን አወቃቀር የሚካተቱ ወረዳዎች ዝርዝር ታወቀ

$
0
0

 

በቅርቡ ይፋ በተደረገው አዲሱ ሰሜን ጎንደርን ወደ ሦስት ዞኖች የመክፈል አወቃቀር፣ በየዞኖቹ የሚካተቱ ወረዳዎች ዝርዝር ታወቀ፡፡

በአማራ ክልል የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አየልኝ ሙሉዓለም ማክሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ሰሜን ጎንደር ዞን ወደ ሦስት ዞኖች ማለትም መሀል ጎንደር፣ ሰሜን ጎንደርና ምዕራብ ጎንደር ይፈከላል፡፡ በእነዚህ ዞኖች የሚካተቱ ወረዳዎችን ዝርዝርም ለሪፖርተር ይፋ አድርገዋል፡፡ በዚህ መሠረት ማዕከላዊ እየተባለ የሚጠራው ዞን ዋና ከተማው ጎንደር ነው፡፡ የሚያካትታቸው ወረዳዎችም ጎንደር ዙሪያ ወረዳ፣ ምዕራብ በለሳ፣ ምሥራቅ በለሳ፣ ወገራ፣ ጠገዴ፣ ታች አርማጭሆ፣ ማሰሮ፣ አለፋ፣ ጣቁሳ፣ ምዕራብ ደንቢያና ምሥራቅ ደንቢያን ያካተተ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይኼ ዞን አሥራ አንድ ወረዳዎችንና 331 ቀበሌዎችን የሚያካትት እንደሆነ አቶ አየልኝ ጠቁመዋል፡፡

የዞኑ ሰሜን ክፍል ወይም ሰሜን ጎንደር ተብሎ የሚጠራው አዲሱ ዞን ደግሞ በስምንት ወረዳዎችና በ176 ቀበሌዎች የተከፈለ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ዞን ዋና ከተማው ደባርቅ ሆኖ፣ ወረዳዎችም ዳባት፣ ደባርቅ፣ ደባት ከተማ አስተዳደር፣ ጃን አሞራ፣ በየዳ፣ አደረቃይ፣ ጠለምትና ደባርቅ ከተማ አስተዳዳር እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ምዕራብ ጎንደር ዞን ተብሎ የሚጠራው አዲሱ ዞን ደግሞ በሰባት ወረዳዎችና በ98 ቀበሌዎች የተካተተ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የዚህን ዞን ዋና ከተማም ገንዳ ውኃ ሆኖ ወረዳዎችም መተማ፣ ቋራ፣ ምዕራብ አርማጭሆና በከተማ ወረዳ ደግሞ ገንዳ ውኃ፣ መተማ ዮሐንስና ምድረ ገነት እንደሆኑ ዋና አስተዳዳሪው አብራርተዋል፡፡

ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ተቃውሞና አመፅ በከፍተኛ መጠን ተሳታፊ ከነበሩ አካባቢዎች መካከል አንዱ ሰሜን ጎንደር ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የሰው ሕይወትና በሚሊዮን የሚቆጠር ንብረት መውደሙም ይታወሳል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አየልኝ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ሰሜን ጎንደርን ወደ ሦስት ዞኖች ለመክፈል ያስፈለጉበት ምክንያቶች ሦስት ናቸው፡፡ አንደኛ ዞኑ ሰፊ የሆነ ቆዳ ሰፋት ስላለው፣ ሁለተኛ የሕዝቡ ቁጥር ከፍተኛ መሆንና ሦስተኛ የመሬት አቀማመጡ አስቸጋሪ በመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በቅርብ ሆኖ ሕዝቡን ለመምራትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ አስቸጋሪ ሆኖ እንደነበረም አስረድተዋል፡፡

አቶ አየልኝ እንደሚሉት በራስ ዳሽንና በደባርቅ አካባቢ ያሉ ወረዳዎች በምግብ ዋስትና እጥረት የሚሰቃዩና በዕርዳታ የሚኖሩ ናቸው፡፡ በምዕራብ በኩል ያለው አካባቢ ደግሞ ሊለማ የሚችል መሬትና በርካታ ወንዞች ያሉት ነው ብለዋል፡፡ ይህ አካባቢ በቅርብ ርቀት ከኤርትራ ጋር የሚዋሰን በመሆኑ ከዚያ የሚመጣ የሻዕቢያ ተላላኪ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር እያደረገ መሆኑንና ከሱዳን ድንበር ጋር ተያይዞም የሕገወጥ መሣሪያ አዘዋዋሪዎች ሰለባ ሆኖ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡

ጣና ዙሪያንና ጎንደርን ማዕከል ያደረገው አካባቢ ደግሞ እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ የከርሰ ምድር ውኃ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ያለው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አቶ አየልኝ፣ ‹‹የሰሜን ጎንደር ዞን ወደ ሦስት ዞኖች መከፈልን ከግርግሩ ጋር የሚያያይዙት አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ውሳኔ ከአራት ዓመት በፊት የተወሰነ ነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡ ሰሜን ጎንደር ዞን እንዲከፈል ጥያቄዎች ከሕዝቡ ሲቀርቡ የነበረው ካለፈው ዓመት በፊት እንደነበር የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው፣ አሁኑ የመንግሥት አቅም እየተሻሻለ በመምጣቱና የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ ዞኑን ለመክፈል እንደተወሰነ አስረድተዋል፡፡ በዞኑ ባሉ ሁሉም ቀበሌዎች ውይይትና ክርክር በማድረግ ሕዝቡ ስምምነት ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡ በዚህም 98.5 በመቶ የሚሆነው የዞኑ ሕዝብ የዞኑን መከፈል የሚደግፍ እንደሆነ መረጋገጡን አመልክተዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት በዞኑ ውስጥ ያሉ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራን በተመለከተ አንስተውት የነበረውን ጥያቄም ለመፍታት አስተዳደሩ ሌት ከቀን እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም በ2009 ዓ.ም. ለ150 ሺሕ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ110 ሺሕ ወጣቶች ዕድሉን መፍጠር እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡  

 

Standard (Image)

ኢሕአዴግ በምርጫ ቦርድ ተቋማዊ ቅርፅ ላይ የማሻሻያ ሐሳብ ሊያቀርብ ነው

$
0
0

 

  • ተቃዋሚዎች ለምርጫ ሕጉ ድርድር ዝግጅት እያደረጉ ነው

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተቋማዊ ቅርፅ ላይ ማሻሻያ ለማድረግና የምርጫ ኮሚሽን ሆኖ እንዲቋቋም ጥናት እያከናወነ መሆኑን ምንጮች ገለጹ፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ከሳምንት በፊት በጉዳዩ ላይ የሚመክር ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጣ ቡድን በሐዋሳ ከተማ ሲመክር ነበር፡፡

ማሻሻያው በምርጫ ቦርድ ላይ የመዋቅር ለውጥ የሚያስከትል ብቻ ሳይሆን፣ በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ላይም ማሻሻያ እንዲደረግ የሚያስገድድ እንደሚሆን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ኢሕአዴግ በአሁኑ ወቅት ገና በጉዳዩ ላይ እየመከረ መሆኑን የተናገሩት ምንጮች፣ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ይሁንታን ካገኘ በመስከረም ወር መጀመርያ ላይ በሚካሄደው የኢሕአዴግና የተቃዋሚዎች የድርድር መድረክ ላይ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በመጪው መስከረም ወር መጀመርያ ላይ ሁለተኛው ዙር የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር የሚጀመር ሲሆን፣ የድርድር አጀንዳውም ምርጫ ቦርድን በሚያቋቁመው የተሻሻለው የምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532 ላይ መሆኑን፣ የድርድሩ የሚዲያ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ገብሩ በርሔ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በተቃዋሚዎች በኩል አሥር ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ በመሆን በምርጫ አዋጁ ላይ ሊሻሻሉ ይገባል ያሏቸውን፣ እንዲሁም ሊካተቱ ይገባል ያሏቸውን ሐሳቦች በማጠናቀር ላይ መሆናቸውን አቶ ገብሩ ገልጸዋል፡፡

የምርጫም ቦርድ አባላት አመላመል ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያካተተ እንዲሆን፣ ቋሚ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ እንዲዋቀርና የቦርዱ ጽሕፈት ቤት እስከ ክልል ወረዳዎች ድረስ እንዲዋቀር የሚሉት ከቡድኑ ሐሳቦች መካከል ይገኙበታል፡፡

 

Standard (Image)

ኢትዮጵያና ጃፓን ከሰሜን ኮሪያ ኑክሌር እስከ አፍሪካ ቀንድ ባሉ ሥጋቶች ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው ተገለጸ

$
0
0
  • ጃፓን ለመንገድ ግንባታ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር ማቅረብ ትፈልጋለች

እሑድ ነሐሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከአገሪቱና ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ባለሥልጣናት ጋር የተወያዩት የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታሮ ኮኖ፣ ከሰሜን ኮሪያ የኑክሌርና የሚሳይል ጥቃት ጀምሮ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በሚታዩት የፀጥታ ሥጋቶች ላይ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የሚስማማ አቋም እንዳላት አስታወቁ፡፡

የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፣ እንዲሁም በሚኒስቴሩ የፕሬስና ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጄኔራል ረዳት ሚኒስትር ኖሪዮ ማሩያማ፣ ከአገር ውስጥና ከውጭ መገናኛ ብዙኃን አባላት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስታወቁት፣ ጃፓን ከሰሜን ኮሪያ ተስፋፊ የኑክሌር፣ የሚሳይልና የጃፓን ዜጎችን ጠልፎ የመውሰድና የማገት ከፍተኛ ሥጋት እንደተጋረጠባት አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የማያወላዳ ማዕቀብ እንዲጥል የጃፓን ፍላጎት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

 የሰሜን ኮሪያ ጉዳይ ከቁጥጥር ውጪ ከመውጣቱ በፊት ሊገታ ይገባዋል ያሉት ቃል አቀባዩ ማሩያማ፣ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤትም ከባድ ማዕቀብ እንዲጣል ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል የሆነችው ኢትዮጵያም በሰሜን ኮሪያ ላይ ተመሳሳይ አቋም እንደሚኖራት ተናግረዋል፡፡ ይሁንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የድጋፍ ድምፅ እንድትሰጥ ጠይቀዋል ወይ ለሚለው የጋዜጠኞች ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ምንም እንኳ ጃፓንና አጋሮቿ የፀጥታው ምክር ቤት ከረረ ያለ ዕርምጃ እንደሚወስድ ይናገሩ እንጂ፣ ሩስያና ቻይና ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላቸው የንግድ ግንኙነት እንዲገታ ለማድረግ ከአባል አገሮች ከፍተኛ ግፊት ማድረግ ይጠበቃል ተብሏል፡፡ ሰሜን ኮሪያ ከ90 በመቶ በላይ የወጪ ንግዷ ከቻይና ጋር እንደሚከናወን ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን ላለፉት አምስት ዓመታት ሲንቀሳቀስ የቆየው የጃፓን ራስ ተከላካይ ጦር ተልዕኮ በማብቃቱ እንደወጣ ያብራሩት ማሩያማ፣ በእነዚህ ዓመታት 5,000 ያህል የጃፓን ራስ ተከላካይ ጦር አባላት ልዩ ልዩ የመሠረተ ልማትና የምህንድስና ሥራዎችን ሲያከናውኑ ይቆዩ እንጂ በመደበኛ ውጊያ የመሠማራት ዓላማ እንዳልነበራቸውም አብራርተዋል፡፡ ከደቡብ ሱዳን በተጨማሪ ጃፓን በጂቡቲ ስላላት ወታደራዊ ተልዕኮም ጥያቄ ቀርቦላቸው ማብራሪያ የሰጡት ማሩያማ፣ የመርከቦችን ህልውና ከባህር ወንበዴዎች ለመከላከልና በሰላይ አውሮፕላኖች የታገዘ የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ እንደሚከናወን አብራርተዋል፡፡ የሚሰበሰበው መረጃም አጋር ለሆኑ አገሮች ጭምር እንደሚሠራጭ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ማንሰራራት ከጀመረው የባህር ላይ ውንድብና እስከ አሸባሪዎች ጥቃት መንግሥታቸው ከአፍሪካ አገሮች ጋር አብሮ የመሥራት ፍላጎት እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ በፀረ አክራሪነት ዘመቻ ጃፓን ኢትዮጵያ የምታከናውናቸውን ተግባራት እንደምትደግፍ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም በላይ የአክራሪነትና የአሸባሪነት መነሻው የልማት መጓደል ስለሆነ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካ አገሮች የሚሰጠው ድጋፍ እንደሚጠናከር ማያማ ሲገልጹ፣ በአፍሪካና በጃፓን መካከል እ.ኤ.አ. ከ1993 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየውን የአፍሪካ ልማት ላይ ያነጣጠረ ጉባዔ አስታውሰዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በሞዛምቢክ የተካሄደውን የ‹‹ቶኪዮ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ለአፍሪካ ልማት (ቲካድ)›› የሚኒስትሮች ስብሰባ መርተዋል፡፡ እግረ መንገዳቸውን ወደ አዲስ አበባ የመጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ባለፈው ዓመት በናይሮቢ በተካሄደው ስድስተኛው የቲካድ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ወቅት ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮችና የድርጊት መርሐ ግብሮች አተገባበር ላይ መወያየታቸውም ተገልጿል፡፡

በናይሮቢው የቲካድ ስድስት ጉባዔ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ለአፍሪካ ልማት አገራቸው 30 ቢሊዮን ዶላር መመደቧን ይፋ አድርገው ነበር፡፡ ይህ ገንዘብ እ.ኤ.አ. እስከ 2018 ከጃፓን መንግሥትና ከግል ኩባንያዎች በመመንጨት ለአፍሪካ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች እንደሚውል መገለጹም ይታወሳል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ማሩያማ፣ ከተጠቀሰው ገንዘብ ውስጥ አምስት ቢሊዮን ዶላር መለቀቁን አውስተዋል፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥም 3.8 ቢሊዮን ዶላር ለመሠረተ ልማት ሥራዎች መዋሉን አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ኦፊሴላዊ የዕርዳታ ድጋፍ ከመስጠት ባሻገር፣ የጃፓን መንግሥት በአገሪቱ መገበያያ ገንዘብ (የን) ላይ የተመሠረተ ብድር ከ43 ዓመታት በኋላ ለኢትዮጵያ መስጠት መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ከተፈደቀው የ50 ሚሊዮን ዶላር ብድር በተጨማሪ፣ በቅርቡ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ብድር ለመስጠት መንግሥታቸው ፍላጎት እንዳለው ማሩያማ ይፋ አድርገዋል፡፡

ከጅማ ከተማ እስከ ጭዳ ላለው የመንገድ ዕድሳት የሚውል 100 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ እንደምትሰጥ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ያስታወቀችው ጃፓን፣ ከዚህ ገንዘብ በላይ እንደሚሆን የሚጠበቅ የብድር ስምምነትም በዚሁ አካባቢ ለሚገነባ የመንገድ ፕሮጀክት ለማበደር የሚያስችሉ ሥራዎች መጀመራቸውንና የሰነድ ስምምነት ለማድረግ የሚረዱ ዝግጅቶች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ማሩያማ አስታውቀዋል፡፡

በሞዛምቢኳ ማፑቶ ከተማ የተካሄደው የሚኒስትሮች ስብሰባ አምና በኬንያ የተደረገውን ጉባዔና ውጤቶቹን ከመገምገም ባሻገር፣ ለመጪው ጉባዔ የዝግጅት አጀንዳዎችም የሚደረጉበት እንደሆነ ታውቋል፡፡ የቲካድ ጉባዔ መላው የአፍሪካ አገሮች በከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው የሚታደሙበት ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በየሦስት ዓመቱ መካሄድ ጀምሯል፡፡ ከዚህ ቀደም በየአምስት ዓመቱ በጃፓን ይካሄድ የነበረው የቲካድ ጉባዔ ከእንግዲህ በአፍሪካና በጃፓን ከተሞች መካከል ይዘዋወራል፡፡

የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እሑድ ዕለት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

 

 

 

 

 

Standard (Image)

የለውጥ ያለህ የሚለው የግሉ ሚዲያ

$
0
0

 

በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ኢትዮጵያ በሚኖሩ ዜጎች ወይም ውጭ አገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል የሚደረጉ የሐሳብ ልውውጦችን የተመለከተ ሰው፣ የአገሪቱ ዜጎች የፖለቲካ አመለካከት በተለያየ ጽንፍ ላይ እንደሚገኝ ይገነዘባል፡፡ በአብዛኛው በጥላቻ የተሞሉት የሐሳብ ልውውጦች እየተባባሱ ሲመጡ እንጂ መሠረታዊ ለውጥ ሲያመጡ አልተስተዋሉም፡፡

እነዚህ ሐሳቦች ግን በአገሪቱ ዋና ዋና መደበኛ የሚዲያ ተቋማት በመጠኑም ቢሆን ሲስተናገዱ አይታይም፡፡ ከማኅበራዊ ድረ ገጾች በተቃራኒ መደበኛ የሚዲያ ተቋማት ኃላፊነት የሚሰማቸውና የሙያ ሥነ ምግባርን መሠረት አድርገው የሚሠሩ ናቸው ተብለው ስለሚገመቱ፣ በእነዚህ ሐሳቦች ላይ በሠለጠነ መንገድ፣ የሐሳብ ልውውጦች፣ ክርክሮችና ሙግቶችን በመደበኛነት በማስተናገድ በዜጎች መካከል የተሻለ ቅርርብ መፍጠር እንደሚቻል የሚዲያ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

ይህንኑ ጥረት እጅግ በቀጭን መስመርም ቢሆን የሚሞክረው የግሉ ሚዲያ ቢሆንም፣ የአገሪቱ የሚዲያ ኢንዱስትሪ ላይ ግዙፍ ተፅዕኖ ያላቸው በመንግሥት ሥር ያሉትና በተለምዶ ግን የሕዝብ ሚዲያ የሚባሉት ናቸው፡፡ የግሉ ሚዲያ ወቅታዊ ይዞታ ከቁጥርም ሆነ ከጥራት አኳያ አበረታች እንዳልሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ እርግጥ ነው ይህን ውጤት ያስከተለው መነሻ ምክንያት ላይ የተለያዩ ገለጻዎች ይቀርባሉ፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ነሐሴ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ በአዘጋጀው ስብሰባ የግሉ ሚዲያ ስኬቶችና ተጋዳሮቶች ላይ ምክክር ሲደረግም፣ የግሉ ሚዲያ ደካማ ይዞታ ላይ እንዲገኝ አስተዋጽኦ አድርገዋል የተባሉ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በዕለቱ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ “ሚዲያ ጠቃሚም፣ ጎጂም ሊሆን ይችላል፤” ያሉ ሲሆን፣ ይህ እንደ አያያዙ እንደሚወሰንም አስምረውበታል፡፡ ሚዲያ የዴሞክራሲ መድረክ የሚሆነው ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ መረጃ በሠለጠነና የሙያ ሥነ ምግባሩን በሚከተል ሙያተኛ ተዘጋጅቶ ሲቀርብ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡ “አቀራረቡ በሙያና በሥነ ምግባር የተደገፈ ካልሆነ ሕዝቦችን የማደናገር፣ ተስፋ የማስቆረጥ፣ ጥላቻን የማስፋፋትና የማጋጨት ዕድሉ ሰፊ ነው፤” ሲሉም አክለዋል፡፡

ዶ/ር ነገሪ ባለፉት ዓመታት የግሉ ሚዲያ ገንቢና አፍራሽ ሚና እንደተጫወተ ጠቅሰዋል፡፡ “በጣም ጥቂት የግል ሚዲያዎች ከሙያና ሥነ ምግባር ባፈነገጠ መንገድ መንግሥትን በመጣል ላይ ብቻ አልመው ከመንቀሳቀሳቸው ውጪ፣ በአጠቃላይ ሲታይ የግሉ ሚዲያ ለሰላም፣ ለልማት፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጠናከርና ለአገር ግንባታ የበኩሉን ገንቢ ሚና ተጫውቷል፤” በማለትም ገልጸዋል፡፡

ተደራሽነቱን በማስፋት፣ ጥራቱን በማሳደግና ተወዳዳሪነቱን በማጠናከር ረገድ ሰፊ የአቅም ክፍተት እንዳለበትም ዶ/ር ነገሪ ጠቁመዋል፡፡ ስለሆነም መንግሥት የግሉን ሚዲያ አቅም በማጎልበት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚጫወተውን ሚና አጠናክሮ እንዲወጣ ለማስቻል ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

“የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ በብዝኃነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የእምነት፣ የባህል፣ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የአስተሳሰብና የፍላጎት ጉዳዮችን በጥንቃቄና በኃላፊነት መንፈስ በማስተናገድና የሕዝብን ጥቅም ማዕከል ባደረገ መንገድ መንቀሳቀስ ከሁሉም የሚዲያ አካላት የሚጠበቅ ተግባር ነው፤” በማለትም አስገንዝበዋል፡፡

“በመረጃ የበለፀገና ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያለው ኅብረተሰብ በመፍጠር ረገድ ሁላችንም የበኩላችንን ሚና መወጣት ይኖርብናል፤” ያሉት ዶ/ር ነገሪ፣ ሚዲያው ካሉበት መሠረታዊ የአመለካከት፣ የሙያና የሥነ ምግባር ችግሮች ተላቆ በሰላም፣ በልማት፣ በዴሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ግንባታ ውስጥ የደረጀ ሚና እንዲጫወት ለማስቻል ታቅዶ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሪፎርም ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የመጡት አቶ ደሬሳ ተረፈ በአገሪቱ ያለው የግል ሚዲያ የሚገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ የቃኙበትን ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በብሮድካስት ዘርፍ አሥር የንግድ ሬዲዮ (አንድ ያልጀመረ)፣ አምስት የንግድ ቴሌቪዥን (ሦስት የጀመሩ ሁለት ያልጀመሩ)፣ አንድ ሰብስክሪፕሽን ጣቢያዎች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡

አብዛኞቹ በአዲስ አበባና በአካባቢው የሚሠራጩ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ደሬሳ፣ ዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተስፋፋ ገልጸዋል፡፡ በክልሎችና በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲስፋፉ ሰፊ ዕድል ቢሰጥም ወደ ዘርፉ የገቡት ውስን መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡

“ከአንድ ክልል በላይ የሚሠራጩ ከ1,000 በላይ የተመዘገቡ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት 18 የግል ጋዜጦችና 43 መጽሔቶች በሥርጭት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በቀጣይነትና በተከታተተይ ገበያ ውስጥ የሚሠራጩት የተወሰኑ ጋዜጦችና መጽሔቶች ናቸው፤” በማለትም የኅትመት ሚዲያው ያለበትን ወቅታዊ ይዞታ ገልጸዋል፡፡

አቶ ደሬሳ የግሉ ሚዲያ በተለይም የንግድ ብሮድካስተሮች በጥንካሬና በድክመት የሚገለጹባቸው ባህርያት እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ በጥንካሬ ከሚገለጹባቸው ባህርያት መካከልም አብዛኞቹ የንግድ ብሮድካስተሮች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የዜና ሽፋን የሚሰጡ መሆኑ፣ በአንዳንድ የንግድ ብሮድካስተሮች የሐሳብና የአመለካካት ብዝኃነትን በድፍረት በማስተናገድ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው አስተዋፅኦ በማበርከት ረገድ የሚታይ ጅምር ጥረት መኖሩ፣ እንዲሁም በአንዳንድ የንግድ ብሮድካስተሮች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በድፍረት በማቅረብ ረገድ የመልካም ጅምር ጥረት መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

በአንፃራዊነት በእጥረት የሚገለጹባቸው ደግሞ አብዛኞቹ የግል ሚዲያ በዓበይት አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን የሚያጎለብቱ ተከታታይ ይዘቶችን ከማሰራጨት አንፃር ሰፊ ክፍተት ያለባቸው መሆኑ፣ በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነትና መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ተከታታይነት ያላቸው ፕሮግራሞችን ከማቅረብ አንፃር ክፍተት መኖሩ፣ ሕገ መንግሥቱን የማሳወቅ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የማስጠበቅ ሚና ያላቸው ፕሮግራሞችን በቀጣይነት ከማቅረብ አንፃር ውስንነት መታየቱ፣ ወጣቱ በመልካም ሥነ ምግባር የታነፀ፣ ልማታዊ አስተሳሰብ ያለው፣ ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን የተላበሰ፣ በመከባበር፣ በመቻቻል፣ በእኩልነት፣ በሕግ የበላይነት፣ በምክንያታዊነት የሚያምን፣ መልካም ዜጋ እንዲሆን የሚያስችሉ ተከታታይ ፕሮግራሞችን ከማቅረብ አንፃር ሰፊ ክፍተት መኖሩ፣ አንዳንድ የንግድ ሚዲያዎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ከመወጣት ይልቅ ለስፖርትና ለመዝናኛ ፕሮግራሞች ትኩረት የሚሰጡ መሆናቸው ተጠቃሽ እንደሆኑ አስገንዝበዋል፡፡

የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን አስመልክቶ በሚቀርቡ አንዳንድ ፕሮግራሞች የሚመለከታቸው አካላትን አለማሳተፍ፣ በበቂ ጥናትና መረጃ  ላይ የተመሠረተ የምርመራ ጋዜጠኝነት ፕሮግራሞችን አለማቅረብና የችግሮችን መንስዔና መፍትሔን አለመጠቆም እጥረት መኖሩንም አቶ ደሬሳ ጠቁመዋል፡፡ አልፎ አልፎ በበቂ መረጃ ላይ ሳይመሠረቱና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትን ሳያሳትፉ ስም የሚያጠፉ ዘገባዎችን የማቅረብ አዝማሚያና በተሠራጨ ይዘት ላይ ለሚቀርቡ ቅሬታዎች በወቅቱ መልስ የመስጠት መብትን አለማክበር ከተስተዋሉ ድክመቶች መካከል እንደሚካተቱ ተናግረዋል፡፡

ከውጭ አገር ፈቃድ አግኝተው በአገር ውስጥ ቋንቋ በሳተላይት የሚሠራጩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቁጥር አምስት እንደደረሰ አቶ ደሬሳ አስታውሰው፣ አማራጭ የመዝናኛ ሚዲያ ቢሆኑም አስተሳሰብን የሚገነቡ ዜናና ትምህርታዊ ፕሮግራሞች፣ በዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞች የሌሉዋቸው መሆኑን፣ በዋነኛነት በመዝናኛና በውጭ አገር ፊልሞች ላይ የሚያተኮሩና አንዳንዶቹ ደግሞ አገራዊ ይዘት የሌላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የግል ሚዲያው በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉበት ያመለከቱት አቶ ደሬሳ፣ በተለይ መረጃ ከማግኘት መብት ጋር በተያያዘ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማትና ኃላፊዎች መረጃ ሲጠየቁ አለመስጠት፣ የሚዲያ ውይይትና የክርክር መድረክ መሸሽ፣ ሚዲያውን በጥርጣሬ ዓይን ማየት፣ መረጃን አደራጅቶ አለመያዝና ድረ ገጽ አለመኖር ትልቅ ችግር እንደፈጠረ አስገንዝበዋል፡፡ ከሚዲያው ነፃነት ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎ የአንዳንድ አስፈጻሚዎች ጣልቃ ገብነት መኖሩ፣ በተሠራጨ ፕሮግራም ላይ አንዳንድ አስፈጻሚዎች ቅሬታ ካላቸው ለባለሥልጣኑ ወይም ለፍርድ ቤት ከማቅረብ ይልቅ፣ ሚዲያው  ላይ ጣልቃ የመግባት አዝማሚያ እንዳላቸውም ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥትና የልማት ድርጅቶች ማስታወቂያ ክፍፍል ፍትሐዊ አለመሆኑ፣ ከብሮድካስት ማሠራጫና የስቱዲዮ መሣሪያዎች ግብዓቶች ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቀረጥ መጠየቁና ለዘርፉ ልዩ ልዩ የማበረታቻ ሥርዓት አለመኖር፣ በኅትመት ሚዲያው የኅትመት ግብዓቶች ከፍተኛ ቀረጥ፣ ለዘርፉ ልዩ ልዩ የማበረታቻ ሥርዓት አለመኖር፣ የኅትመት ዋጋ መናር፣ የአከፋፋዮች ጫና፣ የአማተር አሳታሚዎች ድጋፍ ማጣት ከኅትመት እያስወጣቸው መሆኑ፣ በዘርፉ የሚታይ የማስፈጸም አቅም ውስንነት (በአመለካከትና በክህሎት) እና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን የሚሠራ ማዕከል አለመደራጀቱ ሌሎች ተግዳሮቶች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህር አቶ ተሻገር ሽፈራው በበኩላቸው “የግል መገናኛ ብዙኃን የይዘት አቅጣጫዎች” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት፣ የኢትዮጵያ የግል መገናኛ ብዙኃን የይዘት ባህሪ ወጥነት እንደሚጎድላቸው አመልክተዋል፡፡ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን የመንግሥት አንደበት ሆነው የሚሠሩ፣ የተቃዋሚዎችን ዓላማዎች የሚያራምዱ፣ እንዲሁም በጋዜጠኝነት ሙያዊ መርህ መሠረት ማኅበረሰባቸውን የሚያገለግሉ ተብለው ሊከፈሉ እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡ “የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በሦስት ፈርጆች የተቀመጡባቸው ብያኔዎች የተመሠረቱት በዘገባዎቻቸው የይዘት አቀራረብና አተረጓጎም ላይ በተደረጉ የአጥኚዎች ትንተና ላይ ብቻ ተመሥርተው አይደለም፡፡ ብያኔው የመነጨው የመገናኛ ብዙኃን ተደራስያን አስተያየቶችንም መሠረት በማድረግ ነው፡፡ በተደራስያን ዘንድ የተቃዋሚዎች ድምፅ ተደርገው የሚወሰዱ ብዙኃን መገናኛዎች የመኖራቸውን ያህል፣ በሙያዊ መርሆዎች መሠረት የሚሠሩ ነፃ የሚባሉ መገናኛ ብዙኃን አሉ፤” ሲሉም አስረድተዋል፡፡

 አቶ ተሻገር የግል መገናኛ ብዙኃን ዓብይ ትኩረት የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የማይዘግቧቸውና ገበያው ግን የሚፈልጋቸው ጉዳዮች እንደሆኑም አስገንዝበዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሚያጓድሏቸው የዜና ይዘቶች ላይና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ቢዘግቧቸውም ተደራስያን ከዘገባ አንፃርና ከአተረጓጎም ልዩነት ሊሳቡ በሚችሉባቸው አርዕስቶች ላይ በማተኮር እንደሚሠሩ ጠቁመዋል፡፡

የልዩነቱ ዋና ምክንያት ዘገባዎቹን የሚያቀርቡባቸው ቅኝቶች እንደሆኑ የተናገሩት አቶ ተሻገር፣ በዚህ ረገድ የምንጮች አመራረጥና የምንጮቹ ፖለቲካዊ አቋም ከፍ ያለ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግም አመልክተዋል፡፡ “የዜና ምንጮች ድርሻ የዜና መረጃ ከመስጠት አልፎ መረጃ መተርጎምንም ስለሚያካትት፣ መገናኛ ብዙኃኑን የሁለት ጽንፍ ድምፆች የማድረግ ድርሻቸው ከፍ ያለ ነው፤” ብለዋል፡፡

በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩሩ የሚገልጹ የግል መገናኛ ብዙኃን በአብዛኛው በአገሪቱ ውስጥ አሉ የሚሏቸውን ከዴሞክራሲ፣ ከፍትሕ፣ ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ፣ ከሙስናና ከአስተዳደር በደሎች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ አተኩረው እንደሚሠሩም ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም ዘገባዎቹ የተሟላ መረጃና የሁሉንም ባለጉዳዮች ሐሳብ ከማካተት አንፃር ጉልህ ችግሮች እንሚታዩባቸው ከመግለጽ አልተቆጠቡም፡፡ 

“ብዙዎቹ ዘገባዎች የመንግሥትን ሕጎችና ፖሊሲዎች የሚተቹ፣ በአፈጻጸም እንከኖች ላይ የሚያተኩሩና በመንግሥት ቅቡልነት ላይ ጥያቄ በሚያስነሱ ማዕቀፎች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፤” ያሉት አቶ ተሻገር፣ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘወትር የሚዘገቡ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስኬቶችን እውነተኛነት በመጠየቅና ደካማ ጎኖችን ማሳየት ላይ እንደሚያተኩሩም አስረድተዋል፡፡

በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በቂ ሥፍራ ለማይሰጣቸው ለተቃዋሚ ቡድኖችና ድርጅቶች መሪዎችና አባላት፣ እንዲሁም እነሱ ለሚያራምዷቸው አስተሳሰቦችና ፖለቲካዊ እምነቶች ሥፍራ መስጠት አንደኛው የግል መገናኛ ብዙኃን የዜና ምንጭ ችግሮች መፍትሔዎች እንደሆኑም አቶ ተሻገር አመልክተዋል፡፡ የግል መገናኛ ብዙኃንም ይህንኑ ተግባራቸውን የድምፅ የለሾች ድምፅ እንዲሰማ የማድረግ ማኅበረሰባዊና ሙያዊ ግዴታቸውን እንደመወጣት እንደሚቆጥሩትም አክለዋል፡፡

የግል መገናኛ ብዙኃን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በማይዘግቧቸው ነገር ግን ተደራስያኑ በሚሿቸው ጉዳዮች ላይ በማተኮራቸው ምክንያት፣ ከተማን ማዕከል ባደረጉ ውስን ተደራሲዎቻቸው ዘንድ አንፃራዊ ተዓማኒነት ለማግኘት መብቃታቸውን አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩም አቶ ተሻገር ጠቅሰዋል፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የማይዘግቧቸው በማኅበረሰቡና በራሱ በመንግሥት ውስጥ የሚታዩ አሉታዊ ጉዳዮችም ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ መውደቅ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን  አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙ ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ዓበይት የሚባሉ የቡድንና የግለሰብ መብቶችን፣ የአገር አንድነትንና የሉዓላዊነት ጉዳይን የሚመለከቱ ነባር ጥያቄዎችን ከተለያዩ ፖለቲካዊ አንፃሮች በማንሳት የግል ሚዲያው ዘላቂ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸውም አቶ ተሻገር ጠቁመዋል፡፡ የግሉ ሚዲያ የማኅበረሰቡን ፍላጎቶች የማያሟሉ፣ የተዛቡና የመረጃ ጉድለት የሚታይባቸውና የአስተያየት ጭነት የሚበዛባቸው ዘገባዎችን እንደሚያቀርብ አመልክተዋል፡፡

“ከተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መረጃ ማግኘት ከባድ ፈተና በመሆኑ ብዙ የግል መገናኛ ብዙኃን በከፊል የበሰለ ወይም ያልተሟላ ዘገባ እንዲያቀርቡ አስገድዷቸዋል፡፡ በእርግጥ መረጃ በተቀላጠፈ ሁኔታ የማግኘት ችግር በግል መገናኛ ብዙኃን ላይ የበረታ ችግር ቢሆንም፣ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞችም የችግሩ ተጋሪዎች ናቸው፤” ብለዋል፡፡

አቶ ተሻገር የግል መገናኛ ብዙኃን ተደራሽነት በአብዛኛው ከተማ ተኮርና አካባቢያዊ በመሆኑ በከተሞችና በማዕከላት ላይ እንደሚያተኩሩ ገልጸዋል፡፡ በከተማ የሚታየው አድሎአዊ የሆነ ገበያ መር የመገናኛ ብዙኃን ባህሪ፣ እንዲሁም የኢኮኖሚያዊና የሙያዊ አቅም ውስንነት ለዚህ አዝማሚያ መነሻ ምክንያቶች እንደሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ “ይህም ብዝኃነት ዓብይ ገጽታ በሆነበት ማኅበረሰብ ውስጥ በውስን ባህላዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓቸዋል፤” ብለዋል፡፡

እነዚህ ጥናታዊ ጽሑፎች ከቀረቡ በኋላ ተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶችን ሰንዝረዋል፡፡ ከዛሚ ኤፍኤም ሬዲዮ የመጡት ወ/ሮ ሚሚ ስብሃቱ የሕዝብና የግል መገናኛ ብዙኃን ሚዲያው ራሱን በራሱ የሚቆጣጠርበት ሥርዓት ለመፍጠር የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት አቋቁመው፣ አስፈላጊውን መሥፈርት በሙሉ ቢያሟሉም ተቋሙ እስካሁን ሕጋዊ ሰውነት ለማግኘት አለመመዝገቡን አስታውሰዋል፡፡ “ይኼን ችግር በተመለከተ በተለያዩ መድረኮች ለመንግሥት ያነሳንና በአስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጠው የሚገባ ቢሆንም እስካሁን ይህ አልሆነም፤” ብለዋል፡፡

የጋዜጠኞችን መብት ከማስከበር አኳያ በተጨባጭ ምን እንደሠሩ በውል ከማይታወቁ የጋዜጠኛ ማኅበራት መካከል የአንዱ የኢነጋማ ሊቀመንበር አቶ ወንድወሰን መኮንን በበኩላቸው፣ የግል ሚዲያውን በተመለከተ ትልቁ ችግር ራሱ መንግሥት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ “መንግሥት የግል ሚዲያውን ለማገዝና የተሻለ ደረጃ ለማድረስ ተገቢ የሆነና የሚያዝና የሚጨበጥ ምንም የሠራው ነገር የለም፡፡ የግል ሚዲያ አሁን አለ ብዬ ለመናገር ይከብደኛል፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባለባት አገር በጣት የሚቆጠሩ ጋዜጦች ነው ያሉት፡፡ ሪፖርተር፣ ፎርቹን፣ ካፒታል፣ አዲስ አድማስና ሰንደቅ ብሎ ሌላ መጨመር የሚቻል አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ የመዝናኛ ጋዜጦችና መጽሔቶች አሉ፡፡ ነገር ግን ትልቁን የሕዝብ ችግር ሊያስተናግዱ፣ ሕፀፁን ሊያወጡና ለመንግሥት ለራሱ መስታወት ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉ አይደሉም፡፡ መንግሥት ረዥም ርቀት ሄዶ ልማት ላይ የሠራውን ያህል ሚዲያው ላይ አልሠራም፡፡ ስለዚህ ዜጎች አማራጭ የመረጃ ምንጭ ፍለጋ ወደ ውጭ ሚዲያ ዞረዋል፡፡ የግል ሚዲያው በአብዛኛው የገንዘብ አቅም የለውም፤›› ያሉት አቶ ወንድወሰን፣ ጋዜጠኞች በነፃነት ተንቀሳቅሰው እንዲሠሩ የሚያስችል ምኅዳርም እንዳልተፈጠረ ተችተዋል፡፡ “ሚዲያውን ማሻሻል የሚቻለው በመድፈቅ አይደለም፡፡ ማሻሻያ ለማድረግ በመጀመርያ የጠበቡት መድረኮች መስፋት አለባቸው፤” ብለዋል፡፡

የሰንደቅ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ አቶ ፋኑኤል ክንፉ፣ “በአሠራር የተጠፈሩና መንቀሳቀስ የማይችሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ኤክስፐርቶች ባሉበት የመረጃ ነፃነት ሊኖር አይችልም፡፡ ተጠሪ በሆኑለት ሥራ አስፈጻሚ ተፅዕኖ ሥር ያሉ ናቸው፡፡ ነፃ ያልወጣ የሕዝብ ግንኙነት ነፃ መረጃ ሊሰጥ አይችልም፡፡ መረጃ አሳልፈህ ሰጠህ የሚለው የተንሸዋረረው የአስፈጻሚው አስተሳሰብ መጀመርያ መነቀል አለበት፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ፋኑኤል የመንግሥት ድርጅቶች ማስታወቂያ የሚሰጡበትና የሚከለክሉበት መሥፈርት ግልጽ እንዳልሆነም አመልክተዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ማሻሻያ ለማድረግና ፍትሐዊ ክፍፍል ለማድረግ በተደጋጋሚ ቃል ቢገባም ወደ ተግባር እስካሁን እንዳልተገባ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮ ምኅዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ጌታቸው ወርቁ እንደ አቶ ወንድወሰን ሁሉ ለግል ሚዲያው የተመቸ ምኅዳር እንደሌለ ወቅሰዋል፡፡ መንግሥት የግል ሚዲያውን በአሉታዊ ጎን እንደ አፍራሽ ማየት እንደሌለበትም አሳስበዋል፡፡ “ላይመቸው ቢችልም መንግሥት ራሱ ከሚመራው ሚዲያ በላይ ሊያገለግለው የሚችለው የግሉ ወይም ነፃ ሚዲያ ነው፤” ብለዋል፡፡

 

Standard (Image)

በባህረ ሰላጤው አገሮች ቀውስና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ስብሰባ እየተካሄደ ነው

$
0
0

 

ከወራት በፊት በባህረ ሰላጤው አገሮች መካከል በተለይም በኳታርና በሳዑዲ መራሹ ቡድን መካከል ተፈጥሮ በነበረው ቀውስ፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው እየተጫወተችው ስላለው ሚናና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ስብሰባ እየተካሄደ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሚኒስትሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የ2009 ዓ.ም. የሚሲዮን መሪዎች፣ አምባሳደሮችና የዋናው መሥሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች ዓመታዊ ስብሰባቸውን ከነሐሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. እስከ ጳጉሜን 3 ቀን 2009 ዓ.ም. እያካሄዱ ነው፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይም ስለባህረ ሰላጤው አገሮች ቀውስና ኢትዮጵያ በቀጣናው እየተጫወተችው ስላለው ሚና፣ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ ባለው ወቅታዊ የጂኦ ፖለቲካ ተፅዕኖ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ከሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን እስከ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ስብሰባው በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን፣ ከእሑድ ነሐሴ 28 እስከ ጳጉሜን 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ደግሞ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ እንደሚካሄድ አቶ መለስ ጠቁመዋል፡፡

በዚህ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጨምሮ ከ56 ሚሲዮኖች የመጡ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች፣ እንዲሁም የዋናው መሥሪያ ቤት ሌሎች ኃላፊዎች እየተሳተፉበት እንደሆነ ታውቋል፡፡

በስብሰባው ላይ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ከራሳቸው አንፃር ያሉ ጉዳዮችን በተመለከተ ገለጻ ከማድረግ ባሻገር ስለውጭ ንግድ፣ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝም፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ስለህዳሴ ግድቡ ውይይት እንደሚደረግም አቶ መለስ ገልጸዋል፡፡

ለዘጠኝ ቀናት በሚቆየው ስብሰባ በአገሪቱ የዲፕሎማሲና ሌሎች ግንኙነቶች ላይ ሰፊ ልምድ ያካበቱ ምሁራን ጥናታዊ ወረቀቶችን እንደሚያቀርቡም አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር)፣ መስፍን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ አምባሳደር ተቀዳ ዓለሙ (ዶ/ር) እና አቶ አበበ አይነቴ እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡

ከነሐሴ 28 እስከ ጳጉሜን 3 ቀን በሐዋሳ በሚካሄደው ውይይት ላይም ኢትዮጵያ በመካከለኛው ምሥራቅ ካሉት አገሮች ጋር ስላላት ግንኙነት ጽሑፍ እንደሚቀርብ አስረድተዋል፡፡ በዚህ ውይይት የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የከተማዋ አስተዳደር ኃላፊዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አቶ መለስ ገልጸዋል፡፡

 

Standard (Image)

በአማራ ክልል የተሿሚዎች ሀብት ተመዘገበ

$
0
0

 

በአማራ ክልል የመንግሥት ተሿሚዎች የተሰጣቸውን ሥልጣን ተጠቅመው አላስፈላጊ ጥቅም እንዳያሰባስቡ ለመከታተል ያመች ዘንድ፣ ሀብታቸው መመዝገቡን የክልሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ የመረጃ ባለሙያ አቶ ዮሐንስ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በክልሉ ውስጥ ካሉ ተሿሚዎች መካከል የ1,945 ወንድና የ508 ሴት በጠቅላላው የ2,453 ተሿሚዎች ንብረት መዝገቦ የምስክር ወረቀት ሰጥቷል፡፡

እንደ አቶ ዮሐንስ ገለጻ፣ በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ የ5,721 ወንድና የ2,474 ሴት በድምሩ የ8,196 ሀብት አስመዝጋቢዎች፣ ሀብታቸውን አስመዝግበው የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የ3,741 ወንድና የ1,893 ሴት በድምሩ የ5,634 የመንግሥት ሠራተኞች እንደሚገኙበት ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡

በበጀት ዓመቱም ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በዜጎች ጥቆማ ከምዝበራ መዳኑንም አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ እንደሚሉት፣ ከፋይናንስ ደንብ ውጪ ያላግባብ በሙሰኞች ሊመዘበር የነበረ 16,235,286.05 ብር ማዳን ተችሏል፡፡

በባህር ዳር የውኃ አገልግሎት ከቆጣሪ ግዥ ጋር በተያያዘ ሰባት ሚሊዮን ብር፣ በአንጎለላና ጠራ ወረዳ ያላግባብ ሊከፈል የነበረ 444,228 ብር፣ በኦሮሚያ ዞን አርጡማ ፋርሲ ወረዳ ያላግባብ በሕገወጥ መንገድ ለግለሰቦች ጥቅም ሊውል የነበረ 1,450,400 ብር የሴፍቲኔት ገንዘብና በበየዳ ወረዳ ሳትኮን የመንገድ ሥራ ተቋራጭ የሠራተኞችን የሥራ ግብር ለመንግሥት ገቢ መደረግ የነበረበትን ሦስት ሚሊዮን ብር በጥቆማ እንዲከፍል መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ባለሙያው 2,184 ካሬ ሜትር የከተማ ቦታ ማዳን መቻሉንም ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አረርቲ ከተማ ከአዋጅና ከመመርያ ውጪ በማኅበራት ተደራጅተው በሕገወጥ መንገድ ሊወሰድ የነበረ 884 ካሬ ሜትር መሬት፣ በደቡብ ወሎ ዞን ከለላ ወረዳ ልጓም ከተማ ንዑስ ማዘጋጃ ቤት ሕገወጥ በሆነ መንገድ ለግለሰቦች ተሰጥቶ የነበረ 1,300 ካሬ ሜትር መሬት ማዳን እንደተቻለ አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ የሙስና ትግሉን ለማጠናከር በተሠራው ሥራም በድምሩ 1,606 ጥቆማዎች ቀርበው ከነዚህ መካከል 1,106 ጥቆማዎች የሙስና ወንጀሎች ሆነው በኮሚሽኑ የፀደቁ፣ 125 ጥቆማዎች የሙስና ወንጀል ሆነው ሥልጣኑ የሌላ የሆኑ፣ 365 ጥቆማዎች የሙስና ወንጀል ባህሪ እንደሌላቸውና አሥር ጥቆማዎች ደግሞ ባህሪያቸው ሳይለዩ ወደሚቀጥለው ዓመት መሸጋገራቸውን አቶ ዮሐንስ አብራርተዋል፡፡

ጥቆማዎቹ 252 ከመሬት ጋር የተያያዙ፣ 45 ከግብርና ከታክስ፣ 121 ከግዥና ከኮንስትራክሽን፣ 61 ከፍትሕና ከአስተዳደር፣ 167 ሐሰተኛ ሰነድ ከመፍጠርና ከመገልገል ጋር የተያያዙና 460 ያህሉ ደግሞ ሌሎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከታዩ መዛግብቶች መካከልም 516 መዛግብቶች በኮሚሽኑ መርማሪዎች የተጣሩና 457 መዛግብቶች ደግሞ በፖሊስ መርማሪዎች የተጣሩ መሆናቸውን አቶ ዮሐንስ አውስተዋል፡፡

በቅጣት ለመንግሥት ገቢ እንዲደረግ የተወሰነ ጥሬ ገንዘብን በተመለከተ በዋናው ኮሚሽን 349,466 ብር፣ በደሴ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት 89,200 ብርና በደብረ ብርሃን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ብር 344,400 በድምሩ 948,066 ብር በቅጣት ለመንግሥት ገቢ እንደተደረገ አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡

Standard (Image)

በባህር ዳር ታስረው የነበሩ 36 ነጋዴዎች በዋስ ተፈቱ

$
0
0

 

ባለፈው ዓመት በባህር ዳር ከተማ የሞቱ ዜጎችን ለማሰብ ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በተጠራው የሥራ ማቆም አድማ ተሳትፈዋል ተብለው ታስረው የነበሩ 36 ነጋዴዎች መፈታታቸውን፣ የከተማዋ ፖሊስ መምርያ አስታወቀ፡፡

የመምርያው ኃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ዳኘው ሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በከተማዋ ውስጥ ያሉ ነጋዴዎች መደብሮቻቸውን እንዲዘጉና የትራንስፖርት አገልግሎታቸውን እንዲያቋርጡ ግፊት ሲያደርጉ ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ በርካታ ነጋዴዎች በከተማዋ ፖሊስ መምርያ በቁጥጥር ሥር ውለው የነበረ ቢሆንም፣ 36 ነጋዴዎች የዋስ መብታቸው ተከብሮላቸው ተፈትተዋል፡፡ እንደ ኮማንደሩ ገለጻ ፈጽሙታል የተባለው ወንጀል ዋስትና የሚከለክል ሆኖ ባለመገኘቱ ከእስር ተለቀዋል፡፡

እነዚህ 36 ግለሰቦች በከተማዋ ውስጥ ከፍተኛ ሀብት ያላቸው እንደሆኑ ጠቅሰው፣ ከእነዚህ መካከልም የድብ አንበሳ ሆቴል ባለቤት አቶ ሽባባው የኔአባት እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡

ኮማንደር ዋለልኝ እንደሚሉት በከተማዋ ነሐሴ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ተደርጎ በነበረው የሥራ ማቆም አድማ ሌሎች ተጠርጣሪዎችም ተይዘዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም ቦምብ በማፈንዳት የተጠረጠሩና ለዚህ ድርጊት ግብረ አበር በመሆን የተሳተፉ እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡ እነዚህ ተጠርጣሪዎች በአሁኑ ወቅት ከ20 በላይ እንደሆኑ ገልጸው፣ ጉዳያቸውም በፍርድ ሒደት ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በባህር ዳር ከተማ ያለው ሁኔታ ሰላማዊና የተረጋጋ መሆኑን  የጠቆሙት ኃላፊው፣ የተፈጠረው መረጋጋት እንዳይደፈርስ የፖሊስ መምርያው ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

 

Standard (Image)

‹‹ያለፉት አሥር ዓመታት ጉዞ ስኬታማ የመሆኑን ያህል አልጋ በአልጋ ነበር ለማለት አያስደፍርም››

$
0
0

 

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ

ኢትዮጵያ ሦስተኛውን ሚሊኒየም የተቀበለችበት አሥረኛ ዓመትና የዘመን መለወጫ ክብረ በዓል መጀመርን ይፋ ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ ያለፉት አሥር ዓመታት ጉዞ አልጋ በአልጋ እንዳልነበር አስታወቁ፡፡  

ፕሬዚዳንቱ የክብረ በዓሉን መጀመር ሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ሆቴል ይፋ ሲያደርጉ ‹‹ባለፉት አሥር ዓመታት የሄድንበት የልማትና ፀረ ድህነት ትግል ስኬታማ የመሆኑን ያህል፣ አልጋ በአልጋ ነበር ማለት አያስደፍርም፤›› ብለዋል፡፡

ልማቱን ሊያደናቅፉ የሚችሉና ፈተና የነበሩ በርካታ ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች፣ ባለፉት አሥር ዓመታት አገሪቱን ገጥመዋታል ብለዋል፡፡

‹‹በተከታታይ የገጠመን የድርቅ አደጋ አንዱ ፈታኝ ችግር ነበር፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶች ቁጥር መጨመር በአንድ በኩል ደስታ በሌላ በኩል ተግዳሮት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በየዓመቱ የሚመረቁ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረና እነሱን ወደ ሥራ ፈጠራ ለማስገባት አለመቻል፣ ያለፉት አሥር ዓመታት ትልቅ ተግዳሮት እንደነበር ተናግረዋል፡፡

‹‹ከዚሁ እኩል የሕዝብ የልማት ፍላጎትና ይህንን ፍላጎት መመለስ አለመቻላችን ሌላው ተግዳሮት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ለመንግሥት ሥልጣን የተዛባ አስተሳሰብ ያላቸው የመንግሥት ሹማምንት የፈጠሩት የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ሌላ እንቅፋት እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡ ችግሮቹን ለመቅረፍ መንግሥት ዛሬ ላይ ቆም ብሎ መሥራት እንዳለት ያሳሰቡት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህንንም እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ድህነትን ወደ መቃብሩ ካልወሰድነው ከዓለም ተለዋዋጭ ባህሪ አንፃር አሸናፊ ሆነን መውጣት አንችልም፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በበኩላቸው፣ ‹‹በተግዳሮት በታጀበው የአሥር ዓመት ጉዞ በከተማዋ ስኬቶች ተመዝግበዋል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሚሊኒየሙን ስንጀምር የነበረው የአንዳንድ መንደሮች ገጽታ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ውበት  ተቀይሯል፡፡ በቀላል ባቡር የዘመነው የትራንስፖርት አቅርቦት በሜትር ታክሲና በሸገር ባስ ታጅቧል፤›› ሲሉ ከስኬቶቹ መካከል ጠቃቅሰዋል፡፡

ባለፈው ሐሙስ ምሽት የተበሰረው የአዲስ ዓመት (2010) የመቀበያና ያለፉት አሥር ዓመታት ጉዞ መዘከሪያዎች በተለያዩ ፕሮግራሞች እንደሚከናወኑ ተገልጿል፡፡

ከእነዚህ መካከልም የሰላም ቀን፣ የኢትዮጵያ ቀን፣ ያለፉት አሥር ዓመታት ስኬቶችና ተግዳሮቶች መገምገሚያ ቀን ይገኙበታል፡፡

Standard (Image)

የኬንያ ምርጫ ውጤት መሰረዝ አንድምታዎች

$
0
0

 

የአፍሪካ አገሮች ከኢትዮጵያና ከላይቤሪያ በስተቀር ለረጅም ዓመታት  በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ሥር ነበሩ፡፡ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ሊቢያ፣ ከኮትዲቯር እስከ ሶማሊያ በአራቱም አቅጣጫ ያሉ አገሮች በቅኝ ገዥዎች እጅ ወድቀው ነበር፡፡ እነዚህ ቅኝ ገዥዎች የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብት ወደ አገራቸው ሲያግዙ ነበር፡፡

ከዛሬ 50 እና 60 ዓመታት በፊት አፍሪካ የጨለማው አኅጉር እየተባለም ይጠራ ነበር፡፡ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ቦታ ያልነበራቸውና በቅኝ ገዥዎች በጎ ፈቃድ የሚመራ አኅጉር እንደነበር ታሪክ ይናገራል፡፡ አፍሪካዊያን ባደረጉት የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ሳቢያ እ.ኤ.አ. ከ1960ዎቹ ጀምሮ አኅጉሩ ሙሉ በሙሉ ከቅኝ ገዥዎች እጅ ወጥቷል፡፡ በ11ኛው ሰዓት ከቅኝ ገዥዎች እጅ ነፃ ከወጡ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኬንያ አንዷ ነበረች፡፡

ኬንያ ነፃ አገር ከሆነች 62 ዓመት ሞልተዋል፡፡ ከእንግሊዞች እጅ ነፃ የወጣችው እ.ኤ.አ. በ1955 እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ኬንያዊያን እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ስጦታ የሚቆጥሯቸው የቀድሞው ታጋይና መሪ ጆሞ ኬንያታ አገሪቱ ከቅኝ ገዥዎች እጅ እንድትወጣ ዋነኛውን ሚና እንደተጫወቱ ይወሳል፡፡ በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ዋና ዋና መንገዶችና ሌሎች ተቋማት በእርሳቸው ስም የተሰየሙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከልም አንዱ የኬንያ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ነው፡፡ የአገሪቱ ዋነኛውና ግዙፍ ዩኒቨርሲቲም በእሳቸው ስም ይጠራል፡፡

ኬንያ ነፃነቷን አግኝታ ራሷን ችላ እንደ አገር ከተመሠረተች ረጅም ዕድሜ  ባይኖራትም፣ በአሁኑ ወቅት በመሠረተ ልማትና በዴሞክራሲ ግንባታው ዘርፍ ከአፍሪካ ቀዳሚ አገሮች ተርታ የምትሠለፍ መሆኗን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እ.ኤ.አ. በ2010 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ የአገሪቱ ጠቅላላ ዕድገት 12.4 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው ዕድገትም 5.47 በመቶ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ በዓመት ብቻ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጥ የአገሪቱ ወጣት ኃይል የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርለት መረጃዎች ያመለክተሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚ በተለይም በትራንስፖርት፣ በሪል ስቴት፣ በኮንስትራክሽን፣ በትምህርት፣ በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ከአፍሪካ ቁንጮ አገሮች ተርታ እንደምትሠለፍ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዘርፎች እያደገች ከመምጣቷ በላይ፣ በፖለቲካው ዘርፍም በአኅጉሪቱ ካሉ አገሮች መካከል የተሻለ ሪኮርድ እንዳላት ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ኬንያዊያን በየአምስት ዓመቱ የሚያደርጉት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዘንድሮም እ.ኤ.አ. ነሐሴ 8 ቀን 2017 ተካሂዷል፡፡ የምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው ውጤት መሠረት ኡሁሩ ኬንያታ 54 በመቶ አብላጫ ድምፅ በማግኘት ዳግመኛ ማሸነፋቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ ኡሁሩ ዋነኛ ተፎካካሪ የነበሩት ራይላ ኦዲንጋ የምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገውን ውጤት አልቀበልም በማለት፣ በወቅቱ በኬንያ የተወሰኑ ከተሞች መጠነኛ ግጭቶች ተከስተው ነበር፡፡

በዚህም ሳቢያ በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ከመድረሱ በተጨመሪ ንብረት ላም ውድመት ደርሷል፡፡ ይህን ምርጫ ለመታዘብ ኬንያ ታድመው የነበሩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) የተሳተፉ መሆናቸው አይዘነጋም፡፡ የወቅቱ የኢጋድ ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ሌሎች የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ምርጫው ፍትሐዊና ትክክለኛ እንደነበር፣ ኬንያውያን ደግሞ ውጤቱን በፀጋ እንዲቀበሉ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ 44ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ባራክ ሁሴን ኦባማም እንዲሁ ብለው ነበር፡፡

የተቃዋሚው ዋነኛ መሪ አዲንጋ ይህን ዓለም አቀፍ ግፊት ተቋቁመው  ምርጫው ፍትሐዊ እንዳልሆነ በመግለጽ፣ ጉዳዩን ወደ አገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወሰዱት፡፡ ኡሁሩ ኬንያታ ማሸነፋቸው ከተበሰረ ወር ሳይሞላው በአፍሪካ ምድር ታቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ጉዳይ ተፈጸመ፡:፡ ይህም የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምርጫው ፍትሐዊነት የጎደለው ነው በማለት እንደገና በ60 ቀናት ውስጥ እንዲካሄድ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ ይህ በኬንያ ምድርም ሆነ በአፍሪካ ተደርጎም ሆነ ተሰምቶ የማይታወቅ ውሳኔ በመሆኑ፣ የኦዲንጋን ደጋፊዎች የደስታ ዕንባ ሲያራጭ ሰንብቷል፡፡ በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል ደረጃ በሥልጣን ላይ ያለውንና በድጋሚ አሸንፌያለሁ ብሎ ያወጀው የኬንያታ መንግሥት በፍርድ ቤት ውሳኔ ውጤቱ ሲሰረዝና ለድጋሚ ምርጫ ሲዘጋጅ የታየው ኬንያ ውስጥ ነው፡፡

ወደዚህ ጉዳይ እንዴት ሊመጣ እንደቻለ ባለሙያዎች የተለያዩ አስተያየቶችን ሲናገሩም እየተሰማ ነው፡፡ ምንም እንኳ ፍርድ ቤቱ ምርጫው ተሰርዞ እንደገና እንዲካሄድ የወሰነው፣ በምርጫ ሒደቱ ውስጥ መጭበርበሮችና የምርጫ ቦርድን ገለልተኛነት ጥያቄ የሚያስገቡ ጉዳዮች በመገኘታቸው እንደሆነ ጠቅለል አድርጎ ገልጿል፡፡

የፖለቲካ ተንታኞች የዚህ ዓመት የኬንያ ምርጫ በችግሮች የተሞላ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ከምርጫ በፊት በኬንያታና በኦዲንጋ ደጋፊዎች መካከል በማኅበራዊ ሚዲያዎች የነበረው ጦርነት፣ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ድንገተኛ ሞት እ.ኤ.አ. በ2007 በምርጫ ሰሞን በድንገት ከሞቱት የደኅንነት ኃላፊ ጋር መገጣጠሙ፣ በዚያ ምርጫ ሳቢያ ተካሂዶ የነበረው ብጥብጥና ሁከት ሊደገም እንደሚችል አመላካች መሆኑ፣ መንግሥት በከፍተኛ ወጪ የአድማ መበተኛ መሣሪያዎችን ከውጭ ማስመጣቱና የፀጥታ ኃይሎች ከምርጫው አንድ ወር አስቀድሞ ወደ ሥልጠና መግባታቸው፣ የምርጫውን ውጤት በኤሌክትረኒክስ መሣሪያዎች በመታገት በቀጥታ ለሚዲያዎችና ለሕዝብ ለማስተላለፍ የተቋቋመው የምርጫ ቦርድ የኦንላየን ሰርቨር ዋና ኃላፊ ተገድሎላ መገኘታቸውና የመሳሰሉት ጉዳዮች፣ ምርጫው በሰላም እንዳይጠናቀቅ አመላካች እንደነበሩ ተንታኞች ሲናገሩ ተደምጧል፡፡

ተቃዋሚው ራይላ ኦዲንጋ ምርጫው መጭበርበሩንና ውጤቱን እንደማይቀበሉ ምርጫ ቦርዱ ውጤቱን እያስተላለፈ በነበረበት ወቅት ተናገሩ፡፡ ጉዳዩንም ወደ ፍርድ ቤት ወስደው ህልማቸው ተሳክቷል፡፡ ወደ ፍርድ ቤት እንዲወስዱት መነሻ የሆናቸው ግን ምርጫውን ይታዘቡ ከነበሩ የአገር ውስጥ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የኬንያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (KNHRC) እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ይህ ተቋም ምርጫውን በታዛቢነት ከተሳተፉ ሌሎች ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ ተቋማት መካከል በብቸኝነት ምርጫው መጭበርበሩን ደፍሮ ለመናገር መቻሉ ተነግሯል፡፡

ምርጫውን ኢትዮጵያ የተወከለችበት የአፍሪካ ኅብረት፣ ኢጋድ፣ የካርተር ማዕከል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ሌሎች በታዛቢነት ተሳትፈውበታል፡፡ የካርተር ማዕከልና የአፍሪካ ኅብረት ምርጫው ትክክለኛና ፍትሐዊ እንደነበረም ገልጸዋል፡፡

ኡሁሩ ኬንያታም በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ማዘናቸውን፣ ነገር ግን ሁሉም ሰው ለሕግ ተገዥ መሆን ስላለበት ውሳኔውን በመቀበል በድጋሚ በሚካሄደው ምርጫ ለመሳተፍ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ስምንት ሚሊዮን ሕዝብ የሰጠኝን ድምፅ ስድስት ሰዎች አይገባህም ብለውኛል፡፡ እኔ ደጋፊዎቼ ወደ ሁከትና ብጥብጥ እንዲገቡ አልፈልግም፡፡ ደጋፊዎቼ በድጋሚ በሚካሄደው የምርጫ ቀን እንደገና ወጥታችሁ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ድምፃችሁን ስጡኝ፤›› ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔም ተጠያቂ ያደረገው የምርጫ ቦርዱን ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ኡሁሩ ኬንያን አሸናፊ አድርጓል በማለት ጥፋተኛ አድርጎታል፡፡ በምርጫው ውጤት ማሳወቅ ጊዜ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ወረቀቶች የምርጫ ቦርድ ትክክለኛ ማኅተም ያላረፈባቸው፣ የተቃዋሚዎችና የታዛቢ ተወካዮች ፊርማ ያላረፈበት የድምፅ መስጫ ካርዶች መኖራቸውን በምርመራ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

የተቃዋሚዎች መሪ ራይላ ኢዲንጋ ይህ ውሳኔ በተላለፈበት ዕለት ከደጋፊዎቻቸው ጋር በመሆን የደስታ ዕንባ ሲያነቡ ታይተዋል፡፡ ደጋፊዎቻቸውም እያቀፉ ሲስሟቸውና አምላካቸውን ሲያመሰግኑ ነበር፡፡ ኦዲንጋ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ይህ ውሳኔ ለኬንያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካዊያንም ኩራትና ትምህርት ነው፡፡ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች የሠሩት ስህተት በአገሪቱ ሕግ ወንጀል በመሆኑ ይጠየቁበታል፡፡ ለፍርድ ለማቅረብም ጠንክሬ እሠራለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ኡሁሩ ኬንያታና ምክትላቸው ዊልያም ሩቶ በድጋሚ ለሚካሄደው ምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ወደ ተለያዩ ቦታዎች እያመሩ መሆኑም እየገለጹ ሲሆን፣ ደጋፊዎች ግን እንደ ቀድሞው እየተቀበሏቸው እንዳልሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በአውሮፓ ወይም በአሜሪካ ሳይሆን በኬንያ ምድር የተካሄደው የምርጫ ቦርድን ውሳኔ የሻረው ፍርድ ቤት ውሳኔ በዓለም ዙሪያ እያነጋገረ ነው፡፡ ይህም ውሳኔ ምሥጋና የሚገባውና ለአፍሪካ አገሮች ተምሳሌት ሊሆን እንደሚችል የቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ተንታኞች ሲናገሩ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ ገለልተኛ ሆኖ የምርጫ ሒደቱን እንደገና የመፈተሽና ውጤቱ እንዲሻር የማድረግ ተሞክሮውን ኢትዮጵያ ልትማርበት እንደሚገባ የሚናገሩ አለ፡፡ የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር)፣ ኬንያ ኢትዮጵያን በሩጫ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካውም እንደምትበልጥ ይናገራሉ፡፡ ኬንያ ውስጥ ነፃ የሆነ ዳኝነት እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ዳኝነት ነፃነት የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ እነሱ ደግሞ ለሁላችንም ብርሃን ነው ጥለው የሄዱት፤›› ብለዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ በዶ/ር ዳኛቸው ሐሳብ አይስማሙም፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ በተለይ ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ ፍትሐዊና ትክክለኛ ምርጫ ስታካሂድ መቆየቷን ገልጸዋል፡፡ የነበሩ ምርጫዎች ፍትሐዊና ትክክለኛ ከመሆናቸው አኳያም ወደ ፍርድ ቤት እንዳልሄዱና የሄዱትም ቢሆን ተመርምረው ስህተት በመሆናቸው ውድቅ መደረጋቸውን ይናገራሉ፡፡

ፖለቲከኛውና ምሁር ንጋት አስፋው (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የኬንያ ፍርድ ቤት ውሳኔ የሕግ የበላይነትን የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ንጋት እንደሚሉት፣ ጆሞ ኬንያታና ጁልየስ ኔሬሬ አገራቸው ከቅኝ ገዥዎች ነፃ ሳይወጡ በ1955 ዓ.ም. አዲስ አበባ መጥተው ነበር፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና በጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድ፣ እንዲሁም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ከተማ ይፍሩ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ በወቅቱ ዶ/ር ንጋት ልጅ ስለነበሩ ለእነዚህ ሰዎች የአበባ ጉንጉን መስጠታቸውን አስታውሰዋል፡፡ እነዚህ አገሮች ነፃነታቸውን የተቀዳጁት በቅርብ ጊዜ መሆኑንና ኢትዮጵያ ደግሞ በወቅቱ የተሻለች አገር እንደነበረች ተናግረዋል፡፡

ኡሁሩ ማለት በስዋህሊ ነፃነት ማለት እንደሆነ የሚገልጹት ዶ/ር ንጋት፣ ኬነያ ውስጥ ከነፃነት ወዲህ ሦስት ወይም አራት መሪዎች ቢፈራረቁም አንዳቸውም ግን መፈንቅለ መንግሥት ወይም በኃይል ለመገልበጥ እንዳልሞከሩ ያስረዳሉ፡፡ የመቻቻል ዴሞክራሲ የሚባለውም በኬንያ እየታየ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡ ከራስ ፍላጎት ይልቅ የሕዝብ ፍላጎት ይቅደም የሚለው መርህ ተግባራዊ እየተደረገ ያለውም በኬንያ  እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ኬንያ በቅርቡ ባካሄደችው ምርጫ ምን ይፈጠራል የሚለው የዓለም አቀፉ  ማኅበረሰብ ትኩረት እንደነበር ዶ/ር ንጋት ጠቅሰው፣ ኡሁሩ ኬንያታ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ መቀበላቸው ለአፍሪካውያንን ፖለቲከኞችና ምሁራን ትምህርት የሰጠ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ የተስፋ ጭላንጭል በአፍሪካ መታየት መጀመሩ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ትልቅ ተሞክሮ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ምርጫ ኢትዮጵያ የምትማረው ትልቅ ነገር እንዳለም ዶ/ር ንጋት ያብራራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄደው የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ብዙ ውስብስብ ጉዳዮች እንደነበራት አስታውሰዋል፡፡ በዚህም ሦስቱ የመንግሥት አካላት ከኬንያ ምርጫ ብዙ የሚማሩት ነገር እንዳለ ተናግረዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የመንግሥት ኃላፊ በበኩላቸው ከዶ/ር ንጋት ሐሳብ ጋር አይስማሙም፡፡ በ1997 ዓ.ም. ኢሕአዴግ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ መሸነፉ እንደሚታወቅ ጠቅሰው፣ ተቃዋሚዎች በመላ አገሪቱ እንዳሸነፉ አድርገው ያነሱት የነበረው ጉዳይ ሚዛን የሚደፋ አልነበረም ይላሉ፡፡ መንግሥት ሕገ መንግሥቱ እንዲከበር ግዴታ ስላለበትና አገሪቱ ወደለየለት ሁከት እንዳትገባ በወሰደው ዕርምጃ የሰዎች ሕይወት እንዳለፈ አስታውቀዋል፡፡ የኬንያ በተመለከተ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ፍትሐዊነቱንና ትክክለኛነቱን የመሰከሩለት ምርጫ በፍርድ ቤት መሻሩ ግን የታዛቢዎችን ክፍተት የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ንጋት ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ የከፋ ችግር እንዳይከሰት ፖለቲካውን ፕራይቬታይዝ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኬኒያ ከ1963 ተነስታ የሦስት ሺሕ ዘመን ታሪክ ያላትን ኢትዮጵያ በልጣ በመገኘቷ በጣም አዝናለሁ፤›› ብለዋል፡፡

የኬንያ ምርጫ ከታዘቡት ተቋማት መካከል አንዱ የአፍሪካ ኅብረት ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ምርጫው ትክክለኛና ፍትሐዊ እንደነበር በመገለጽ፣ ዶ/ር ንጋት፣ ‹‹የአፍሪካ ኅብረት ሲጀመር የአምባገነኖች ኅብረት ነው፤›› በማለት የኅብረቱን የታዛቢነት ውጤት ኮንነዋል፡፡ የአፍሪካ መሪዎች እከከኝ ልከክህ እንጂ በአፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ የሚታገሉ አይደለም ብለዋል፡፡ ለአብነትም የኡጋንዳ፣ የጂቡቲ፣ የኤርትራና የዚምባብዌ መሪዎች ሥልጣንን የዕድሜ ዘመን መጠቀሚያ እያደረጉ እንደሆኑና ከእነዚህ አገሮች ለውጥ እንደማይታሰብ ሞግተዋል፡፡

የቀድሞው የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፣ የምርጫ ቦርድ በተወሰነ መልኩ ገለልተኝነት ይንፀባረቅባቸዋል በሚባሉት አገሮች ውስጥ ሳይቀር ለገዥው ፓርቲ በቀላሉ ሰለባ እንደሚሆንና የምርጫ ውጤቱን እንዴት ሊያዛባ እንደሚችል የኬንያ ምርጫ ያሳያል ይላሉ፡፡

ሁለተኛ መከራከሪያ ነጥባቸው ደግሞ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በምርጫ ወቅት ሁሌም ምስክር ሆኖ ሲቀርብ ምርጫው ትክክለኛና ፍትሐዊ ነው ማለቱ ነው፡፡ ከፖለቲካ ጥቅምና ሽብርን በመዋጋት ኬንያ ባላት ሚና ብቻ ተመዝኖ የምርጫውን ውጤት አንቆላጳጵሰውት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የካርተር ማዕከልና ሌሎች እንደዚህ ዓይነት ምርጫ ታይቶ እንደማይታወቅ ከከረሙ በኋላ፣ መጨረሻ ላይ ማንነታቸው ፍንትው እንደወጣ ተናግረዋል፡፡ የተናገሩት ቃል ሳይደርቅ ውሳኔው መሻሩ በጣም የሚያሳፍር እንደሆነ አክለዋል፡፡ የካርተር ማዕከልና ሚዲያዎች ጭምር እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን አውስተዋል፡፡ ስለዚህ አፍሪካውያን ነጮችን ተማምነው የምርጫ ውጤቱን መቀበልና አለመቀበል ላይ መድረስ እንደሌለባቸው አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ሙሼ ሦስተኛ መከራከሪያ አድርገው የሚያቀርቡት የፍትሕ አካላት ገለልተኝነት ላይ ነው፡፡ በኬንያ የታየው የፍርድ ቤት ነፃነት እስከ ታች ድረስ ወርዶ ሕዝቡ በሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲኖረው እንደሚያደርግ ገለጸዋል፡፡ ከዚህም ኢትዮጵያ ብዙ የምትማራቸው ነገሮች አሉ ሲሉ አቶ ሙሼ ያስረዳሉ፡፡ በምርጫ መሸነፍም ሆነ ማሸነፍ የዓለም መጨረሻው እንዳልሆነ የሚጠቅሱት አቶ ሙሼ፣ ‹‹ከስህተትህ ተምረህ፣ ነገ ከዚህ የተሻለ ተጠናክረህ መጥተህ አገርህን የምታገለግልበት አዲስ አማራጭ ቀርፀህና አሸንፈህ ውጤታማ መሆን ላይ ነው ትኩረትህ መሆን ያለበት እንጂ፣ ዕድሜ ልክህን መሳሳት መብት ነው እያልክና እየተሳሳትክም እንደ መንግሥት መቀጠል ውጤቱ ከባድ ነው የሚሆነው፤›› ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር እየሆነ የመጣው መራጩ ሕዝብ መረጠም አልመረጠም፣ ተቀበለም አልተቀበለም፣ ውጤቱ የአንድ አካል እንደሆነ እርግጠኛ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ስለዚህ ለምርጫ ያለው እምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ ደምፅ ለመስጠት መውጣትን እየተወ፣ መረጥኩም አልመረጥኩም ውጤቱ አንድ እንደሚሆን የታወቀ ስለሆነ ምን ትርጉም አለው? ኪሳራ ነው እንጂ ምን ትርፍ አለው? እያለ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ለመማር የሚያዳግታት አገር እንዳልሆነች የሚየስረዱት አቶ ሙሼ፣ ኬንያውያን የተለዩ ሰዎች ስለሆኑ ወይም ደግሞ ተዓምረኛ ስለሆኑ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡ በእርግጥ ኬንያዊያን በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ አንድ ዕርምጃ ወደፊት እንደሄዱና ኢትዮጵያ ከዚህ ለመማር ባህሉ፣ አስተሳሰቡና የአገር ፍቅሩ እንደሚፈቅድ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የዳኝነት ሥርዓት ፓርላማውን ሙሉ በሙሉ በያዘው ገዥው ፓርቲ የሚሾም መሆኑን ጠቅሰው፣ ተሿሚዎቹ ሁልጊዜ ሹመቱን ለሚያፀድቅላቸው ፓርቲ ተጠሪ ነናቸው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዚያው ልክ አገሪቱ ውስጥ ፍትሕ እንዲሰፍን የሚታገሉ፣ በምንም ነገር የማይታለሉና እጃቸው የማይጠመዘዝ እንዳሉ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትሕን በተመለከተ በአብዛኛው ሰው የሚማረርበትና ተስፋ የቆረጥበት ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹ከመክሰስ መከሰስ› ይሻላል እየተባለ የሚተረትበት ዘመን ላይ መደረሱንም አስረድተዋል፡፡

አንድ ፓርቲ ብቻውን ሥልጣን ላይ ተቀምጦ የሚፈልገውን ሰው የሚሾምበትና የሚያነሳበት አካሄድ እስካለ ድረስ አዲስ ነገር መጠበቅ እንደማይቻል ገልጸው፣ የኬንያና የኢትዮጵያ ልዩነትም የእውቀት ማነስ ሳይሆን ቃለ መሃላ ለገቡለት አገርና ሕዝብ የመቆምና ያለመቆም ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህ ግን ሁሉንም ሰው ይመለከተዋል ማለት እንዳልሆነ አክለዋል፡፡

ኬንያና ኢትዮጵያ የጋራ ድንበር ያላቸው አገሮች ሲሆኑ፣ ሁለቱ አገሮች አልሽባብን ከመዋጋት ጀምሮ የጋራ የንግድ ቀጣና እስከ መመሥረት የደረሱ አገሮች ናቸው፡፡ በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ ኃያል እየተባሉ የሚጠሩት እነዚህ አገሮች፣ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከአፍረካ ኅብረትና ከተመድ ጋር የተሠለፉ ናቸው፡፡

ኬንያ በእንግሊዞች ሥር ለብዙ ዓመታት ብትቆይም፣ በአሁኑ ወቅት ኢኮኖሚያቸው እያደገ ከመጡ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች መካከል ቀዳሚ ናት፡፡ አሁን የአገሪቱን የምርጫ ቦርድ ውሳኔ በመሻር ሌላ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲካሄድ ተወስኗል፡፡ በዚህም በአገሪቱ ጠንካራ የፍትሕ ሥርዓት ለመኖሩ ማሳያ እንደሆነ እየተነገረ ሲሆን፣ ከዚህም የአፍሪካ አገሮች በተለይም ኢትዮጵያ ብዙ መማር ያለባት ነገር እንዳለ ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡

ቀጣዩ የኬንያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 17 ቀን 2017 እንዲካሄድ ተወስኗል፡፡ ተፎካካሪዎቹም ካሁኑ የምርጫ ቅስቀሳቸውን ጀምረዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

                                          

Standard (Image)

ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገለጸ

$
0
0

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር)፣ በ2009 ዓ.ም. ኮሚሽኑ ባከናወናቸው ተግባራት፣ ስላስመዘገባቸው ውጤቶችና ስለገጠሙት አስቸጋሪ ሁኔታዎች መግለጫ ሰጡ፡፡ ግንዛቤ ማስጨበጥ ዋነኛው ትኩረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መግለጫው የተሰጠው ማክሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በኮሚሽኑ ዋና ጽሕፈት ቤት ሲሆን፣ ኮሚሽነሩ በ2009 ዓ.ም. ሰብዓዊ መብትን ከማስከበር አንፃር የተከናወኑት ዓበይት ክንዋኔዎችን ላይ ዘለግ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በዓመቱ ያከናወናቸውን ተግባራት በዝርዝር የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ከማብራሪያቸው በመከተል ከጋዜጠኞች በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ሪፖርት ከማቅረብ ባለፈ ለምክር ቤቱና ለሚመለከተው አካል በሪፖርቱ መሠረት የምትሰጡት ምክረ ሐሳብ መተግበር አለመተግበሩን ትከታተላላችሁ ወይ? በዚህስ አካሄድ እስካሁን የተመዘገው ውጤት ምንድነው? ከሪፖርተር ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡

‹‹ኮሚሽኑ ምርመራና ክትትል ካደረገ በኋላ ለፓርላማው ከሚያቀርበው ሪፖርት ጋር አያይዞ ምክረ ሐሳብ ያቀርባል፡፡ ምክረ ሐሳቡም በዋናነት ጥሰቶችም ይሁኑ ሰብዓዊ መብት ማክበር ማስከበር ላይ የሚታዩ ችግሮች የሚቀረፉበት፣ ተጠያቂነት የሚረጋገጥበትና የሕግ የበላይነት የሚሰፍንበት ጉዳይ ላይ በዋነኛነት የሚያተኩሩ ናቸው፤›› ሲሉ ኮሚሽነሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች በተለይም በደቡብ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተፈጠረውን አለመረጋጋት አስመልክቶ በሚያዝያ ወር ሪፖርት ካደረግን በኋላ ወደ ሥፍራዎቹ በግንቦት ወር የክትትል ቡድን ልከናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ይህም የተደረገበት ዋነኛ ምክንያት አንደኛ ምክረ ሐሳቦቹ የፀደቁት በምክር ቤቱ በመሆኑ፣ ምክር ቤቱ ደግሞ የራሱ የሆነ የሚከታተልበት መንገድ አለው፡፡ ኮሚሽኑም የራሱ የሆነ የክትትል ሥራ አለው፡፡ ሁለቱም ተመጋጋቢ ናቸው፡፡ ቢሆንም ግን ኮሚሽኑ ተከታትሎ ሪፖርት የማቅረብ ኃላፊነት አለበት፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹የክትትል ኃላፊነታችን ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህንንም ለማረጋገጥ በሦስቱም ክልሎች የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ አስመልክቶ የቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ ከ50 በላይ አባላት ያሉት የባለሙያ ቡድን ለክትትል ወደ ሥፍራዎቹ አንቅንቶ ሪፖርቱን አጠናቅሯል፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

‹‹የክትትል ሪፖርቱ ዋና ዓላማ ፓርላማው የወሰነው ምክረ ሐሳብ ምን ያህል ተፈጻሚነት አገኘ የሚለውንም ለመገምገም ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም ፓርላማው ሪፖርቱን መሠረት አድርጎ ሲወስን ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አኳያ ተጠያቂ መሆን ያለባቸውን በዝርዝር አቅርቧል፡፡ በዚህ መሠረት የፓርላማው ውሳኔ ምን ያህል ተፈጻሚ ሆኗል የሚለውን ለመገምገም ነው ኮሚሽኑ የክትትል ቡድን ሥምሪት ያደረገው፡፡ የቡድኑ ውጤትም ምክር ቤቱ ሥራውን ሲጀምር የሚቀርብ ይሆናል፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በቅርቡ በአሜሪካ ስላደረጉት ጉብኝትና ውይይት ከሪፖርተር ጥያቄ ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ወደ አሜሪካ የተጓዙበት ዋነኛ ዓላማ በአገሪቱ ካሉ ከሴኔት፣ ከኮንግረስ፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማትና ከሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ወገኖች ጋር ስብሰባ ለማካሄድ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽኑ እያከናወነ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ አጠባበቅና ሁኔታ ለማወቅና ለመገንዘብ ፍላጎት ስላሳደሩ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት የተዘጋጀ ስብሰባ እንደነበርም አውስተዋል፡፡ በስብሰባው ወቅት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ደግሞ በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ቡድኖች አማካይነት ስለሚወጡ ሪፖርቶች እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

‹‹በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የተለያዩ ዘገባዎች ይወጣሉ፡፡ የሰብዓዊ መብት አስከባሪዎች ነን የሚሉ ድርጅቶችም የራሳቸው የሆነ ሪፖርት አላቸው፡፡ ከሩቅ ሆነው ሪፖርት፣ ምርመራና ክትትል አድርገናል ይላሉ፡፡ በእኛ ግምት ግን እዚያ ሆኖ ክትትልም  ሆነ ምርመራ ማድረግ በሳይንሱም እንደማይቻል አስረድተናል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

‹‹ምርመራ የሚደረገው መሬት ተወርዶና በኅብረተሰቡ መሀል ሆኖ ነው፡፡ ሳይንሱም የሚፈቅደው ይህንኑ ነው፡፡ አሜሪካ ተቀምጦ ምርመራ አደረግኩ የሚል ድርጅት ምን ያህል የተሳሳተ ጭምር መሆኑንም ተነጋግረን ተግባብተናል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የኮሚሽኑ በ2009 በጀት ዓመት ዕቅድ የሰብዓዊ መብት ግንዛቤና አስተምህሮ በማስፋት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማጠናከር፣ የሰብዓዊ መብት አገልግሎቶች ተደራሽነት ማረጋገጥ፣ ለሴቶችና ሕፃናትና ሌሎች ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ማከናወን እንደሆነ፣ ቅንጅታዊ አሠራርንና አጋርነትን ማጠናከር የሚሉ ዓበይት ተግባራትን ለማከናወን መንቀሳቀሱን በመግለጫው ወቅት ተገልጿል፡፡

በዚህ መሠረት ከላይ የተዘረዘሩትን ከማከናወን አንፃር በርካታ ሥልጠናዎች መሰጠታቸውን የተገለጹ ሲሆን፣ በሁሉም ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ያሉ የኮሚሽኑ ሠራተኞች የተለያዩ ተግባራትን ማከናወናቸው እንዲሁ ተገልጿል፡፡

በዋናው መሥሪያ ቤትና በስምንቱም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በጠቅላላው 2,090 አቤቱታዎች መስተናገዳቸው ተገልጿል፡፡ ከእነዚህ አጠቃላይ የመብት ጥሰት አቤቱታዎች መካከል 1,086 ቅሬታዎች በፌዴራልና በክልል ምክር ቤቶች ወይም በየደረጃው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች በመታየት ላይ ያሉ፣ እንዲሁም ከያዟቸው ጭብጦች አኳያ በሌሎች ተቋማት ሥልጣን ሥር የሚወድቁ በመሆናቸው ተቀባይነት አላገኙም ተብሏል፡፡

ተቀባይነት ካላገኙ አቤቱታዎች መካከል ለ994 አቤት ባዮች የምክር አገልግሎት በመስጠት፣ እንዲሁም 92 ለሚሆኑ አቤቱታዎች ደግሞ ወደ ሌሎች የሚመለከታቸው አስፈጻሚዎች ለቀጣይ ዕርምጃ በደብዳቤ መሸኘታቸው ተገልጿል፡፡

ከቀረቡ አጠቃላይ አቤቱታዎች መካከል ተቀባይነት አግኘተው ወደ ምርመራ የተመሩና በመስማማት ሒደት ላይ ያሉ አቤቱታዎች 514 ናቸው፡፡ ከእነዚህ ፋይሎች መካከል 328 የሚሆኑት ጉዳዮች በምርመራ እንዲሁም ቀሪዎቹ 186 ጉዳዮች ደግሞ በማስማማት ሒደት ላይ የሚገኙ ናቸው ተብሏል፡፡

 

Standard (Image)

ለአሥር ቀናት ለሚካሄደው ክብረ በዓል አራት ሚሊዮን ብር ወጪ ይደረጋል ተብሏል

$
0
0

በዳዊት እንደሻው

ለአሥር ቀናት ‹‹መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው›› በሚል መሪ ቃል እየተደረገ ያለው ክብረ በዓል፣ እስከ አራት ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚያስፈልገው ተገለጸ፡፡ ወጪው በዋናነት ክብረ በዓሉን ለማዘጋጀት በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት የተቋቋመው ኮሚቴ ባደረገው ግምት የተገኘ ነው ተብሏል፡፡

መከበር ከጀመረ ቀናትን ያስቆጠረው ይህ ክብረ በዓል ከግለሰቦች በተደረገ የዓይነት ዕገዛና የልማት ድርጅቶች ለማስታወቂያ ከመደቡት ገንዘብ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ከመንግሥት በጀት ግን ምንም የሚነካ ነገር የለም ብለዋል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ ለዚህ ክብረ በዓል ተብሎ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ፈቃድ በተከፈተ የባንክ ሒሳብ የገንዘብ ድጋፎች እየተደረጉ ነው፡፡ እስከ ማክሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ በነበረው መረጃ መሠረት፣ ያስፈልጋል ተብሎ ከተገመተው ገንዘብ አብዛኛው ተሰብስቧል፡፡ ገንዘቡም በዋናነት ከልማት ድርጅቶች የተገኘ ነው፡፡

ይህ ክብረ በዓል በዋናነት በሠራዊት መልቲ ሚዲያና በሸዋፈራው መልቲ ሚዲያ ከአራት ወራት በፊት በቀረበ ፕሮፖዛል መሠረት የተዘጋጀ እንደሆነ፣ አቶ ሠራዊት ፍቅሬ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሠረት ለአሥር ቀናት የተለያዩ ክብረ በዓላት ስም እየተሰጣቸው የፍቅር ቀን፣ የኢትዮጵያ ቀንና በመሳሰሉት እንዲከበሩ ውሳኔ ላይ ተደርሶ፣ ከሳምንት በፊት በፕሬዚዳንት ሙላት ተሾመ (ዶ/ር) በይፋ ተጀምሯል፡፡

ከአራት ወራት በፊት ፕሮፖዛሉ በሁለቱ ድርጅቶች፣ ‹ዳር እስከ ዳር› በሚል ርዕስ ለጽሕፈት ቤቱ ቀርቦ እንዲፀድቅ መደረጉ ታውቋል፡፡ ‹‹በወቅቱ ፕሮፖዛሉ የኢትዮጵያን ሦስተኛው ሚሊኒየም በማስመልከት፣ በአገሪቱ ባላፉት ሁለት ዓመታት የነበሩትን ችግሮች፣ የተለያዩ ተግዳሮቶችና ስኬቶችን ግምት ውስጥ በማስገባት አዘጋጅተናል፤›› ሲሉ አቶ ሠራዊት አስረድተዋል፡፡

ከዚህም በመነሳት አዲሱን ዓመት በተስፋና በበጎ ምኞት ለመቀበል ታሳቢ ተደርጎ የቀረበ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት፣ ከመንግሥት ግዢዎችና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በተገኘ ፈቃድ መሠረት፣ በቀጥታ ሁለቱ ድርጅቶች በዝግጅቶቹ እንዲሳተፉ መደረጋቸውን አስታውቋል፡፡

በአገሪቱ የግዢ አዋጅ መሠረት ስድስት ዓይነት የጨረታ ሥርዓቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የቀጥታ ግዢ አንዱ ነው፡፡ አዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀጽ 52 የመንግሥት የበጀት መሥሪያ ቤቶች በሚያቀርቡት አሳማኝ ምክንያት ኤጀንሲው መሥሪያ ቤቶቹ የቀጥታ ግዢ እንዲያደርጉ ይፈቅዳል፡፡

‹‹ይህም ግዢውን በሚያከናውነው መሥሪያ ቤት የበላይ ኃላፊ ታምኖበት ለኤጀንሲው ይቀርባል፤›› ሲሉ፣ የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሰጠኝ ገላን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት ግዢውን መፈጸም ያስፈለገበትን ምክንያት፣ የማቅረቢያ ጊዜና ሁኔታዎችን፣ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ለግዥ አጄንሲው አቅርቦ ማፀደቅ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሠረት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኤጀንሲውን በማስፈቀድ ለሁለቱ ድርጅቶች ሥራውን መስጠቱን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትሩ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አገልግሎቱን ከሚሰጡት ከሁለቱ ድርጅቶች ጋር በተደረገ ደርድር ለእያንዳንዳቸው እስከ 500 ሺሕ ብር እንደሚከፈል አቶ ሠራዊት ተናግረዋል፡፡ ይህ ገንዘብ እስካሁን ለሁለቱም ድርጅቶች አልተከፈለም ያሉት አቶ ሠራዊት፣ በአሁኑ ጊዜ በእሳቸው ሥር ብቻ 50 ያህል ሠራተኞችን አሰማርተው በክብረ በዓሉ ዝግጅቶች እየተሳተፉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

እስከ መስከረም 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ዋዜማ ድረስ የሚከናወነው ይኼ ክብረ በዓል፣ በተለያዩ ዝግጅቶች በሚሊኒየም አዳራሽ በሚደረግ የመዝጊያ ፕሮግራም ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡ የዚህ ክብረ በዓል ዋና ዓላማ ላለፉት አሥር ዓመታት እንደ አገር የተለፋበትን ጉዞ መለስ ብሎ ለመቃኘት፣ በዚህም የጎደሉትንና የተገኙትን ስኬቶች ለመገንዘብና ለመጪው አዲስ ዓመት የተሻለ ስኬት ለመትጋት በአዲስ መንፈስ ለመነሳሳት መሆኑን፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡   

  

 

Standard (Image)

ኢትዮጵያ በሰሜን ኮሪያ ላይ ተገቢው ፍትሐዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ፍላጎቷ መሆኑን ገለጸች

$
0
0

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታውን ምክር ቤት ፕሬዚዳንትነት ለመምራት ባለፈው ሳምንት ወንበሩን የተረከበችበትና የዓለምን ትኩረት የሳበው የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ቦምብ ሙከራ በመገጣጠማቸው፣ በሰሜን ኮሪያ ላይ ፍትሐዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ጠየቀች፡፡

ኢትዮጵያ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል የሆነችው እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 2017 ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ደግሞ ምክር ቤቱን ለአንድ ወር በፕሬዚዳንትነት የመምራት ተራው ደርሷታል፡፡

ኢትዮጵያ የፕሬዚዳንትነት ወንበሯን በተረከበችበት ባለፈው እሑድ ነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ሰሜን ኮሪያ የዓለምን በተለይም የኃያላኑን ትኩረት የሳበውን የኃይድሮጂን ቦምብ ሙከራ አድርጋለች፡፡ በዚህም ምክንያት የፀጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባውን ሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. አካሂዷል፡፡

ስብሰባውን የመሩት በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መልዕክተኛ አምባሳደር ተቀዳ ዓለሙ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፣ ምክር ቤቱ ሰሜን ኮሪያን ወደ ድርድር ጠረጴዛው ለማቅረብ ማንኛውንም ዓይነት አማራጭ መጠቀም አለበት ብለዋል፡፡

አግባብነት ያለውና ፍትሐዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ኢትዮጵያ እንደምትፈልግም አስታውቀዋል፡፡

ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ቦምብ ሙከራ ማድረጓን ያሳወቀችው ጃፓን ስትሆን፣ 6.3 ሬክታር ስኬል የመሬት መንቀጥቀጥ በኮሪያ ልሳነ ምድር መከሰቱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ይህ የመሬት መንቀጠቀጥ ቻይና ድረስ የተሰማ ሲሆን፣ ጃፓን የመሬት መንቀጥቀጡ ተፈጥሯዊ አለመሆኑን ገልጻለች፡፡ የመሬት መንቀጥቀጡ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ሙከራ በማድረጓ መሆኑን ወዲያውኑ አመልክታለች፡፡

ሰሜን ኮሪያ የኃይድሮጅን ቦምብ ሙከራ ማድረጓን በይፋ ያሳወቀች ቢሆንም፣ ተዓማኒነትን ማግኘት አልቻለችም፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ የጠየቀችው አሜሪካ በአምባሳደሯ አማካይነት ‹‹ሰሜን ኮሪያ ጦርነትን እየለመነች ነው፤›› ብላለች፡፡

በመሆኑም ጠንካራ ማዕቀብ በተለይም የነዳጅ ማዕቀብ እንዲጣልባት ጥሪ አድርጋለች፡፡ ከአሜሪካ ጎን ፈረንሣይ፣ ጀርመንና እንግሊዝ የተሠለፉ ሲሆን፣ ቻይናና አሜሪካ የተጣለውን ማዕቀብ ተግባራዊ በማድረግ ሰሜን ኮሪያን ወደ ድርድር መመለስ እንደሚገባ አቋም ይዘዋል፡፡

የተመድ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ጀፍሪ ፌልትማን በበኩላቸው፣ የፀጥታው ምክር ቤት የሰሜን ኮሪያ የኃይድሮጂን ቦምብ ሙከራ ጠብ አጫሪነት በመሆኑ ፈጣን ምላሽ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ለዚህም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሰሜን ኮሪያን ወደ ድርድር ማምጣት ተገቢ መሆኑን ጠቁመው፣ ጠንከር ያለ ማዕቀብ ደግሞ መታለፍ የለበትም ብለዋል፡፡

የሰሜን ኮሪያ የሰሞኑ የኃይድሮጂን ቦምብ ሙከራ ማድረግ ከፍተኛ ሥጋት የፈጠረ ሲሆን፣ በፀጥታው ምክር ቤት የተጣለባትን ማዕቀብ ከምንም ባለመቁጠር ተደጋጋሚ አኅጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳይሎች ሙከራ ማድረጓ አይዘነጋም፡፡ በዚህ ሳቢያ የዓለምን ሰላም የሚያናጋ አደጋ ሊኖር እንደሚችል ብዙዎችን እያስማማ ነው፡፡

 

 

  

Standard (Image)

የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚጠቀሙባቸው ተሽከርካሪዎች ከአገር ውስጥ እንዲገዙ መመርያ ወጣ

$
0
0

 

በዳዊት እንደሻው

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በቅርቡ ባወጣው መመርያ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚጠቀሙባቸው ተሽከርካሪዎች ከአገር ውስጥ አምራችና ገጣጣሚዎች ብቻ እንዲገዙ አዘዘ፡፡

ምክር ቤቱ ከሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚ እንዲሆን ያወጣው መመርያ፣ የፌዴራል ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ሌሎች ተቋማት ኃላፊዎችን ይመለከታል፡፡ የተሽከርካሪ አጠቃቀም ወጪ ቆጣቢ፣ የሚመደቡ ተሽከርካሪዎችም ደረጃ ሲኖራቸው አመዳደቡም ፍትሐዊ እንዲሆን ለማድረግ ሲባል የወጣ መመርያ ነው ተብሏል፡፡

ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎችና ምክትል አፈ ጉባዔዎች፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ኮሚሽነሮች፣ ምክትል ኮሚሽነሮች፣ ዋናና ምክትል ዳይሬክተሮች፣ እንዲሁም የተለያዩ የተቋማት ኃላፊዎች የሚጠቀሙባቸውን ተሽከርካሪዎች ያካትታል፡፡

እስከ ዛሬ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚጠቀሙባቸው እንደ ቪኤይት፣ ጂናይን ፓጄሮና ፕራዶ ያሉ ውድና ወጪያቸው ከፍ ያሉ ተሽከርካሪዎች ለመስክ ሥራ ብቻ እንዲውሉ መመርያው ያዛል፡፡

ባለሥልጣናቱ በከተማ ማለትም በአዲስ አበባ ከተማ ለሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች አነስተኛ ተሽከርካሪዎች ብቻ እንዲጠቀሙ ይገደዳሉ፡፡

እነዚህ አነስተኛ ተሽከርካሪዎች ወጪ ቆጣቢ፣ ውጤታማ ሆነው ቀጣይነት ያለው የሰርቪስ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ አገር ውስጥ ከሚገጣጠሙ ድርጅቶች እንዲገዙ መመርያው ያዛል፡፡

በፌዴራል መንግሥት ተቋማት ሥር ያሉ ማናቸውም ጥቅም ላይ የሚውሉ ተሽከርካሪዎች፣ እንደማንኛውም የመንግሥት ተሽከርካሪ ለተፈቀደው ሥራ ብቻ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጋል፡፡

እንዲሁም መሥሪያ ቤቶቹ ከተመደቡላቸው ተሽከርካሪዎች በላይ ሲያስፈልጋቸው፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሥራቸውን ጠባይና ስፋት አገናዝቦ ጉድለት ለታየባቸው ተቋማት ተጨማሪ ተሽከርካሪዎች ይመደባሉ፡፡

የነዳጅ አጠቃቀምን አስመልክቶ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለከተማ ሥራ ለሚገለገሉበት ለአንድ አውቶሞቢል በወር 135 ሊትር ቤንዚን ይፈቀድላቸዋል፡፡

ለመመርያው ተፈጻሚነት የየተቋሙ አመራሮች ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የተሽከርካሪ አጠቃቀሙ በመመርያው መሠረት ተግባራዊ መደረጉን ተጠሪ ለሆኑበት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የአፈጻጸም ሪፖርት እንዲያቀርቡ በመመርያው ተገልጿል፡፡

ይህ መመርያ በተሽከርካሪ አስመጪዎች ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል በማለት ሪፖርተር ለኒያላ ሞተርስ ኩባንያ አንድ ኃላፊ ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ ኃላፊው ኩባንያውም ሆነ የተሽከርካሪ አስመጪዎች ማኅበር መመርያውን እንዳላዩት ገልጸው፣ ነገር ግን መመርያው በቀጥታ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ ለጊዜው ከዚህ በላይ ማለት እንደማይችሉም አክለዋል፡፡   

 

Standard (Image)

የአንበሳ አውቶቡስ ዋና ሥራ አስኪያጅና ሌሎች ኃላፊዎች ታስረው ፍርድ ቤት ቀረቡ

$
0
0
  • በፌዴራልና በአዲስ አበባ ፖሊስ የተያዙ ተጠርጣሪዎች 125 ደረሱ

ለበርካታ ዓመታት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ በድሉ አሰፋን ጨምሮ፣ ስድስት ኃላፊዎች በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታስረው ነሐሴ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ነሐሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው ገልጾ፣ ነሐሴ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ያቀረባቸው የድርጅቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ፋንታሁን፣ የቴክኒክ መምርያ ኃላፊ አቶ ንጉሡ ላቃቸው፣ የየካ ቴክኒክ ቨርዥን መሪ አቶ ሙሔ አወል፣ የሸጎሌ ቴክኒክ ኬዝ ቲም መሪ አቶ መገርሳ ጌታቸውና የአውቶሞቲቨ ቨርዥን መሪ አቶ ደመላሽ ፈጠነ ናቸው፡፡

ተጠርጣዎቹ ድርጅቱን በመምራት ላይ እያሉ በ2006 ዓ.ም. ድርጅቱን መልሶ የማቋቋም ሥራ ሲያከናውን፣ ግብፅ ከሚገኝ ኢጅፕት ፓወር ከሚባል ድርጅት ግልጽ ባልሆነ ምክንያት የአንድ አውቶብስ ሞተር በነፃ እንደተሰጣቸው መግለጻቸውን፣ መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡

በመቀጠልም አንድ የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም በስጦታ የተበረከተውን ሞተር በአንድ የዳፍ አውቶብስ ላይ ተገጥሞ እንዲሞከር ሲያደርጉ፣ ሞተሩ እንደማይሠራ ባለሙያዎች ለቴክኒክ ኮሚቴው መግለጻቸውንም መርማሪ ቡድኑ አክሏል፡፡ የሞተሩ ፍሪሲዮን እንዲሞከር ተጠይቆ በተመሳሳይ ሁኔታ እንደማይሠራ የተገለጸ ቢሆንም፣ የቴክኒክ ኮሚቴው ግን በደረጃ አንድ መንገድ ላይ ባይሠራም በደረጃ ሁለትና ሦስት ላይ እንደሚሠራ በመግለጽ ሪፖርት ማቅረቡን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

የቴክኒክ ኮሚቴው ‹‹ሞተሩ ይሠራል›› የሚል ሪፖርት ቢያቀርብም፣ በማኔጅመንት በተደረገ ስብሰባ ሞተሩ እንደማይሠራ ተገልጾ እያለና ምንም ዓይነት ጥናት ሳይደረግ፣ ከግብፁ ኩባንያ ጋር በሦስት ዙር ግዢው እንዲፈጸም በመስማማት ስምምነት ማድረጋቸውን አስረድቷል፡፡

ነገር ግን ተጠርጣዎቹ ውሉን በመጣስ በአንድ ጊዜ የ49 ዳፍ አውቶብሶች ሞተር ከኩባንያው በ33 ሚሊዮን ብር የግዢ ሥርዓት በመፈጸም፣ በሕዝብና በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አስታውቋል፡፡

እንደማይሠሩ እየተገለጸ የተገዙት ሞተሮች በዳፍ አውቶብሶች ላይ የተገጠሙ ቢሆንም፣ ባለመሥራታቸው ቆመው እንደሚገኙ መርማሪ ቡድኑ አስረድቶ ለጊዜው ለምርመራ መነሻ ያገኘው የምርመራ ግኝት ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑንና ብዙ እንደሚቀረው በማስረዳት ለተጨማሪ ምርመራ የ14 ቀናት ጊዜ ጠይቋል፡፡

በሚደረገው ምርመራ ላይ ተቃውሞ እንደሌላቸው በመግለጽ ምላሽ የሰጡት የቀድሞ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በድሉ አሰፋ ናቸው፡፡ አቶ በድሉ እንደገለጹት፣ ከግብፅ ኩባንያ ጋር ተመሳጥረው እየተባለ የሚቀርበው ክስ ትክክል አይደለም፡፡ እሳቸው ከሁለት ዓመት በፊት በጡረታ በክብር ተሸልመው መሰናበታቸውን፣ ባለቤታቸው፣ ልጆቻቸውና እሳቸውም ሕመምተኛ መሆናቸውን አስረድተው፣ ጡረታ ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ በዕውቀታቸው ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ በመሥራት ቤተሰቦቻቸውን እያስተዳደሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሙስናን ለመከላከል በተቋሙ ብዙ መሥራታቸውን አስረድተዋል፡፡ ለትምህርት እንዲሆን በማለት ለግላቸው የተሰጣቸውን ስጦታ እንኳን ለድርጅቱ ማበርከታቸውንና ይኼ አንዱ ማንነታቸውን የሚገልጽ መሆኑን በማስረዳት ዋስትና እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ሌሎቹም በተመሳሳይ ሁኔታ ዋስትና ጠይቀዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ግን ቀሪ ሥራዎቹን ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት ዋስትናውን ተቃውሟል፡፡ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ፣ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ የአሥር ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ፈቅዶ ለመስከረም 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን በአዲስ ከተማ፣ በጉለሌ ክፍለ ከተማና በአራዳ ክፍለ ከተማ የመሬት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት የተለያየ ኃላፊነት ላይ የነበሩ 18 ተጠርጣሪዎችን አቅርቦ የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀምና በጥቅም በመመሳጠር የመንግሥትን ይዞታና የመንግሥትን ቤቶች በግለሰቦች ስም በማዛወር ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን አስረድቷል፡፡ ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀምና የሞቱ ሰዎችን መጠቀሚያ በማድረግ በመንግሥት ጥቅም ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አስረድቷል፡፡ የሰነድ ማስረጃዎች መሰብሰቡን፣ የምስክሮችን ቃል መቀበሉንና በቀጣይም መረጃ ማሰባሰብና የምስክሮችን ቃል መቀበል እንደሚቀረው በማስረዳት 14 ቀናት እንዲፈቀደለት ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹም የተያዙበት ጉዳይ ከእነሱ ጋር እንደማይገናኝና ሥራ ከለቀቁ ረዘም ያለ ጊዜ እንደሆናቸው፣ የሠሩትም ተገቢና በሕጉ መሠረት መሆኑን፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች መሆናቸውን፣ ሁለት ተጠርጣሪዎች ደግሞ ነፍሰጡር በመሆናቸው በማረፊያ ቤት እንደተቸገሩ፣ የትምህርት ቤት መክፈቻ ወቅት በመሆኑ ልጆቻቸውን ማስመዝገብ እንዳለባቸውና ደመወዝና የባንክ ደብተር ስለተያዘባቸው ቤተሰቦቻቸው በችግር ላይ መሆናቸውን በመግለጽ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ ሰባት ቀናት ብቻ በመፍቀድ ለመስከረም 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ሰባት ተጠርጣሪዎችን በሚመለከት መርማሪ ቡድኑ ሥራውን እያጠናቀቀ መሆኑን ፍርድ ቤቱ እንደተገነዘበ ገልጾ፣ ለጳግሜን 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ እንኳን ፖሊስ ፍርድ ቤትም ደመወዝ የማገድ ሥልጣን የለውም በማለት በአስተዳደር በኩል መፍትሔ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ ቡድን 24 ተጠርጣዎችን ያቀረበው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ነው፡፡ በምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ታደለ ደመቀና የደረቅ ቆሻሻ ሥራ አስኪያጅ አቶ ነጋ ፋንታሁን  የምርመራ መዝገብ እስከ ቢሮ አስተዳደር ጸሐፊ ድረስ የተካተቱበት 24 ተጠርጣሪዎች የቀረቡ ሲሆን፣ የተጠርጠሩትም በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸው፣ በአስተዳደሩ ዋና ኦዲተር በመረጋገጡ መሆኑን አስረድቷል፡፡ በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን ገልጾ፣ ጉዳቱ የደረሰው ተገቢ ያልሆነና የአስተዳደሩን የፋናንስ መመርያ በመጣስ ግዢ በመፈጸም፣ ክፍያ በመፈጸም፣ ለሥልጠናና ለአበል በሚል ተገቢ ያልሆነ ክፍያ በመፈጸምና ሌሎችንም ወጪዎች በማውጣት መሆኑን አስረድቷል፡፡ ቀሪ ሥራዎች እንዳሉት በመግለጽ 14 ቀናት እንዲፈቅድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹም ድርጊቱ በየግላቸው እንዲነገራቸው፣ የሠሩት ጥፋት እንደሌለና የወሰዱት አበል ሕጉን ያልተከተለ ነው ተብለው ተመላሽ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ ዋስትና እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ወገኖች ክርክር ካዳመጠ በኋላ የ53 ሚሊዮን ብር ጉዳት ከፍተኛ ቢሆንም፣ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ ድርሻው ምንና እንዴት እንደሆነ ማሳየት ተገቢ መሆኑን እንዳመነበት ጠቁሞ፣ መርማሪ ቡድኑ ለይቶና ድርሻቸው ምን እንደሆነ ገልጾ ለጳጉሜን 3 ቀን 2009 ዓ.ም.  እንዲያቀርብ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ችሎቱ ከጠዋቱ 4፡50 ሰዓት ጀምሮ ያለማቋረጥ ከቀትር በኋላ 8፡30 ሰዓት ድረስ በመቆየቱ ስምንት ተጠርጣዎችን በአዳሪ ጳጉሜን 1 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት የዕለቱን ችሎት አጠናቋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ ማክሰኞ ምሽት ለመንግሥት መገናኛ ብዙኋን በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ዕጣ ሳይደርሳቸው እንደደረሳቸው በማስመሰል አምስት ባለሦስት መኝታ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ለአምስት ግለሰቦች በማስተላለፍ የተጠረጠሩ ሰባት የጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ ሁለት ኃላፊዎች መታሰራቸውን አስታውቀዋል፡፡ የቤቶቹም ግምትም ከ2.3 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን አክለዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ ሁለት ሥራ አስፈጻሚ፣ ሁለት የሥራ ሒደት መሪዎች፣ ሁለት ባለሙያዎችና አንድ ሠራተኛ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ረቡዕ ጳጉሜን 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉት 63 የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንደሆኑ፣ በመንግሥት ላይ የ170 ሚሊዮን ብር ጉዳት እንዳደረሱ ተገልጿል፡፡ በፌዴራልና በአዲስ አበባ ፖሊስ የተያዙ ተጠርጣሪዎች ቁጥርም 125 መድረሱ ታውቋል፡፡

 

 

 

Standard (Image)

የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ኃላፊዎች ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ተባሉ

$
0
0
  • በአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣናት ላይ ምርመራ ተጠናቀቀ

በከባድ የሙስናና ወንጀል ተጠርጥረው ነሐሴ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው የታሰሩት የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አምስት ኃላፊዎች፣ በድምሩ ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ በሕዝብና በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤት ገለጸ፡፡

መርማሪ ቡድኑ ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ባቀረበው የምርመራ ውጤትና ሒደት አቤቱታ እንዳስረዳው፣ በ2006 ዓ.ም. ከመርከብ የተራገፈና 13.5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ከ656,000 ቶን በላይ ስኳር የት እንደደረሰ አይታወቅም፡፡ ኃላፊዎቹ ክትትል ማድረግ ቢገባቸውም አለማድረጋቸውን ተናግሯል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ቀጥሎ እንዳስረዳው፣ በጂቡቲ ለሚገኘው የባህር ትራንስፖርት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መንግሥት በየዓመቱ አሥር ሚሊዮን ዶላር በጀት የሚመድብ ቢሆንም፣ ኃላፊዎቹ መከታተልና መቆጣጠር ሲገባቸው ይህን ባለማድረጋቸው ሊባክን ችሏል፡፡ የፋብሪካና የግብርና ምርቶች በቃሊቲና በሞጆ ደረቅ ወደቦች ውስጥ እየታሸጉ ይላኩ የነበረ ቢሆንም፣ የማሸግ ሥራው በኃላፊዎቹ ትዕዛዝ ወደ ጅቡቲ እንዲሄድ በመደረጉ መንግሥት 470 ሚሊዮን ብር እንዲያጣ ማድረጋቸውን መርማሪ ቡድኑ አብራርቷል፡፡ በዚህ የተነሳም 1,500 ወጣቶች ሥራ እንዲያጡ መደረጉን አክሏል፡፡

አንዳንድ ባለሀብቶች በድርጅቱ በኩል በዱቤ የሚያስገቡት የተለያዩ ምርቶች እንደነበሩ የጠቆመው መርማሪ ቡድኑ፣ ከድርጅቱ ጋር በተደረገው ውል መሠረት ሊሰበሰብ የሚገባው ገንዘብ ኃላፊዎቹ ከ2006 ዓ.ም. እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ እንዳይሰበሰብ በማድረጋቸው፣ መንግሥት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ እንዲያጣ ማድረጋቸውን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በባለሀብቶችና በድርጅቱ መካከል ባለው ውል መሠረት መሰብሰብ የሚገባው ገንዘብ ሳይሰበሰበ አሥር ዓመታት ካለፈው እንደሚሰረዝ የጠቆመው መርማሪ ቡድኑ፣ ኃላፊዎች ከባለሀብቶች ጋር ተመሳጥረው አሥር ዓመታት ያለፈው ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሰረዝ ጥያቄ እንደቀረበበት የሚያሳይ ማስረጃ ማሰባሰቡንም አክሏል፡፡

ኃላፊዎቹ ያለምንም ጨረታ የደረቅ ወደብ ግንባታ በማድረግም በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን፣ በመርከብ ተጓጉዞ የሚገባ ዕቃ እንዲጓተት በማድረግም ጉዳት መፈጸማቸውን ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበው የምርመራ ውጤት መነሻ ሐሳብ መሆኑንና ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች እንዳሉ፣ ብዙ የምርመራ ሒደት እንደሚቀረው በመግለጽ ተጨመሪ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በሰጡት ምላሽ እንዳስረዱት፣ ‹‹እኛን አይመለከትም፣ መንግሥት ራሱ የመደባቸው ከዕቃ ማሸግና ማንሳት ጋር የሚገናኙ ሠራተኞች አሉ፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት አገራዊ አድርጎ የሚያነሳውን ችግር ወደ እነሱ ማምጣቱ ተገቢ  አለመሆኑን የገለጹት ተጠርጣዎቹ፣ እነሱ ድርጅቱን ለማሳደግ ተግተው ከመሥራታቸው ውጪ ጎጂ ድርጊት አለመፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡

የሺፒንግ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቺፍ ኢንጂነር ዓለሙ አምባዬ እንደተናገሩት፣ ባደረጉት ጥናት መሠረት የደረሱበት የእነሱ ችግር እንዳልሆነ ነው፡፡ ነገር ግን እውነቱ እንዲወጣ ስለሚፈልጉ መርማሪ ቡድኑ የሚጠይቃቸው ነገሮች ከአሠራር ጋር የተገናኙ መሆናቸውን ማስረዳታቸውን አብራርተዋል፡፡ የአሠራር ችግር ባለመሆኑ እነሱ ሊጠየቁ እንደማይገባም አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ እንደጨረሰ በሰጠው ትዕዛዝ ተጠርጣዎቹ የጠየቁትን የዋስትና መብት አልተቀበለውም፡፡ መርማሪ ቡድኑ በቀጣይ ቀጠሮ የእያንዳንዱን ተጠርጣሪ የጥርጣሬ መነሻና የተሳትፎ ድርሻ ምን እንደሆነ በግልጽ እንዲቀርብ በመንገር የተጠየቀውን 14 ቀናት ፈቅዷል፡፡

የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ኃላፊዎች የሺፒንግ አገልግሎት ዘርፍ ቺፍ ኢንጂነር ዓለሙ አምባዬ፣ የኮርፖሬት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲሳይ አባፈርዳ፣ የወደብና ተርሚናል አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደሳለኝ ገብረ ሕይወት፣ የፕላንና ቢዝነስ ልማት መምርያ ኃላፊ አቶ ሲራጅ አብዱላሒና የፋይናንስ መምርያ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል መላኩ መሆናቸውን ባለፈው ዕትም  መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩት ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌና ሦስት ተጠርጣሪዎች፣ እንዲሁም በስኳር ኮርፖሬሽን የተንዳሆ ከስም ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት በእነ አቶ አበበ ተስፋዬ መዝገብ የማነ ግርማይ፣ ዮሴፍ በጋሻው፣ ኪሮስ አለማየሁና ኤፍሬም ደሳለኝ  ላይ የፌዴራል መርማሪ ቡድን ምርመራውን ጨርሶ ለዓቃቤ ሕግ ማስተላለፉን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱም ክስ የመመሥረቻ አሥር ቀናትን ፈቅዷል፡፡: በሌሎቹ በኩራዝ ኦሞ አምስትና የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶች ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ የምርመራ አሥር ቀናትን ፈቅዷል፡፡ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በእነ አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል መዝገብ 12 ተጠርጣሪዎችና በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለማየሁ ጉጆ  መዝገብ 16 ተጠርጣሪዎች ላይ አሥር ተጨማሪ የምርመራ ቀናትን በመፍቀድ ለመስከረም 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

Standard (Image)

የአዲስ አበባ አስተዳደር የቴዲ አፍሮ አልበም ምረቃ ፕሮግራም ወቅቱን የጠበቀ የዕውቅና ጥያቄ አልቀረበለትም አለ

$
0
0
  • ቴዲ አፍሮ ከፍተኛ ሐዘን ተሰምቶኛል ብሏል

እሑድ ነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በይፋ እንደሚመረቅ ቀን የተቆረጠለት የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‹‹ኢትዮጵያ›› የተሰኘ አልበም ምርቃት ፕሮግራም፣ ወቅቱን የጠበቀ የዕውቅና ጥያቄ እንዳልቀረበለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው ረዳትና የሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ ፈቃድ ክፍል ተጠባባቂ ኃላፊ አቶ ተስፋ ዋቅጅራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሒልተን አዲስ ነሐሴ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. የአልበም ምረቃ ለማካሄድ ጥያቄ የያዘውን ደብዳቤ የተመለከቱት ሰኞ ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው፡፡

‹‹ሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. እስከ ቀኑ 9፡30 ድረስ ቢሮ ነበርኩ፡፡ የቀረበ ደብዳቤ የለም፡፡ በነጋታው ዓርብ የኢድ አል አድሃ (ዓረፋ) በዓል ስለነበር ሥራ የለም፡፡ ሰኞ ቢሮ ስገባ ደብዳቤውን አግኝቻለሁ፡፡ አለመታደል ሆኖ ግን ቀኑ አልፏል፤›› ሲሉ ፕሮግራሙን ለማዘጋጀት የቀረበው ጥያቄ ዘግይቶ መድረሱን አቶ ተስፋ ተናግረዋል፡፡

‹‹ጥያቄ ሊቀርብ የሚገባው ከፕሮግራሙ በፊት በሥራ ቀናት ከ24 ሰዓት ቀደም ብሎ መሆን ይኖርበታል፡፡ የአልበም ምረቃው ፕሮግራም ጥያቄ ግን ይህንን አካሄድ ያላገናዘበ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሪፖርተር ለአልበሙ ምረቃ የዕውቅና ጥያቄ ማቅረብ ለምን ያስፈልጋል? በአገሪቱም ሆነ በአዲስ አበባ የሚካሄዱ የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች፣ ልዩ ልዩ ስብሰባዎችና የአልበም ምረቃዎች ጭምር የዕውቅና ጥያቄ ቀርቦላቸው አያውቅም፡፡ ይህንን ምን አዲስ አደረገው? የሚሉ ጥያቄዎችን ለአቶ ተስፋ አቅርቦላቸዋል፡፡

አቶ ተስፋ እንደሚሉት፣ ሠርግና የመሳሰሉት ባህላዊ ሥነ ሥርዓቶች ናቸው፡፡ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ሥነ ሥርዓቶች ግን ጥያቄ ሊቀርብላቸው ይገባል፡፡ ‹‹በከንቲባ ጽሕፈት ቤት ሥር ይህ የሰላማዊ ሠልፍና የሕዝባዊ ስብሰባ ፈቃድ ክፍል የተቋቋመው ለዚህ ዓላማ ነው፡፡ ያለበለዚያ ለምን ክፍሉ ያስፈልጋል?›› ሲሉ አቶ ተስፋ ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል፡፡

የቴዲ አፍሮ የሙዚቃ አልበም ምረቃ ፕሮግራም ያዘጋጁት ጆርካ ኢቨንት፣ ጆይስ ኢቨንትና ዳኒ ዳቪስ ናቸው፡፡ አዘጋጆቹ በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፈው ይህንን ፕሮግራም ለማዘጋጀት ከሒልተን አዲስ ጋር ስምምነት አድርገውና ክፍያ ፈጽመው ቀኑን በመጠባበቅ ላይ ነበሩ፡፡

ነገር ግን የሒልተን አዲስ አበባ የጥበቃ ኃይል የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ለጥበቃና ለትራፊክ እንቅስቃሴው ዕገዛ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ አዘጋጆቹን በመጥራት ሐሙስ ጠዋት ውይይት ማድረጋቸውን፣ በዚህ ውይይት ላይ አዘጋጆቹ የዕውቅና ደብዳቤ እንዳላቸው ሲጠየቁ ፕሮግራሙ የተለየ እንዳልሆነና የዕውቅና ጥያቄ እንደማያስፈልገው መከራከሪያ ማቅረባቸውን ከአዘጋጆቹ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ነገር ግን ፖሊስ የዕውቅና ፈቃድ እንደሚያስፈልግና የዕውቅና ፈቃድና ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል በሌለበት ፕሮግራሙ ሊካሄድ አይችልም በሚለው አቋሙ በመፅናቱ፣ አዘጋጆቹ በመጨረሻው ሰዓት የዕውቅና ደብዳቤያቸውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

የጆርካ ኢቨንት ባለድርሻ አቶ አጋ አባተ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጆርካ ኢቨንት ስምንት ትልልቅ ፕሮግራሞችን ሲያካሂድ ተመሳሳይ የዕውቅና ጥያቄ አልተጠየቀም፡፡

‹‹ነገር ግን ይሁን ብለን ለሥነ ሥርዓቱ (ፎርማሊቲ) ሐሙስ ነሐሴ 25 ቀን ደብዳቤ አስገብተናል፤›› በማለት ገልጸው፣ ይህንን ሁሉ ርቀት ከሄዱ በኋላ ፕሮግራሙ ሳይካሄድ በመቅረቱ የሞራል ስብራት እንደደረሰባቸው አመልክተዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ ትልልቅ ዝግጅቶችን የማዘጋጀት ልምድ ገና አልካበተም፡፡ ጆርካ ኢቨንት ይህንን ለመሙላት ነው የተቋቋመው፡፡ ነገር ግን ውኃ የማያነሱ ምክንያቶችና መሰናክሎች መብዛታቸው ከገንዘብ የበለጠ ሞራል የሚነኩ ናቸው፤›› ሲሉ አቶ አጋ በቅሬታ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ሦስቱ አዘጋጆች ተነጋግረው የሚደርሱበትን ውሳኔ እንሚያሳውቁ አቶ አጋ ተናግረዋል፡፡ ውሳኔውን ግን አሁን ለመተንበይ እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡

ቴዲ አፍሮ ይህ ፕሮግራም መካሄድ አለመቻሉን በተመለከተ በፌስቡክ ገጹ እንዳመለከተው፣ ‹‹ኢትዮጵያ የተሰኘው አልበም ምርቃት አስፈላጊው ዝግጅት ሁሉ ተጠናቆና ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች የመግቢያ ወረቀት ታድሎ ካበቃ በኋላ፣ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ ጉዳዩ ይመለተከኛል የሚለው የመንግሥት አካል መርሐ ግብሩን ለማካሄድ ፈቃድ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ዝግጅቱ እንዳይካሄድ መከልከሉን ለክቡራን ወገኖቻችን ስናሳውቅ የተሰማንን ከፍተኛ ሐዘን በመግለጽ ነው፤›› በማለት የተፈጠረውን ሁኔታ አስረድቷል፡፡ የአልበሙ ምርቃት የመሰረዝ ዜና ከተሰማ በኋላ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮችና ማኅበራዊ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

 

Standard (Image)

የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት በ39 የወንጀል ድርጊቶች ክስ ተመሠረተባቸው

$
0
0
  • የመከላከያ ሚኒስቴርን ሚስጥር አሳልፈው ሰጥተዋል ተብሏል
  • በአሜሪካና በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ገንዘብ ማስቀመጣቸው ተጠቁሟል

አራጣ በማበደር ወንጀል ተጠርጥረው ታስረው የነበሩት የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት አቶ ዓብይ አበራ፣ ተጠርጥረው ከታሰሩበት አራጣ ማበደር ወንጀል በተጨማሪ 38 ክሶች ተመሠረቱባቸው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሐሙስ ጳጉሜን 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ተረኛ ችሎት ያቀረበው ክስ አቶ ዓብይ ሦስት አራጣ ማበደር፣ ሁለት የባንክን ሥራ ተክቶ መሥራት፣ አራት በሕገወጥ የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስስሎ ማቅረብ፣ አራት ከፍተኛ የማታለል፣ ስድስት በሕገወጥ መንገድ ኢትዮጵያውያንን ወደ ውጭ መላክ፣ አምስት ግብር አለመክፈል፣ ሰባት የተሳሳቱና ሐሰተኛ ሰነዶችን ማቅረብ፣ አራት ተጨማሪ እሴት ታክስ አለመክፈልና ሦስት ከባድ የማታለል ወንጀሎችን መፈጸማቸውን አብራርቷል፡፡

ተከሳሹ አቶ ዳዊት ከበደ በተባሉ ግለሰብ የተመዘገበ አዳል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥር የተመዘገበና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 10 ውስጥ የሚገኝ ሚስማር ፋብሪካን በመያዣነት በመያዝና ስምንት በመቶ ወለድ የሚከፈልበት ውል በማዘጋጀት፣ 800,000 ብር ማበደራቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ ተበዳሪው በየወሩ በስምንት በመቶ ሒሳብ 64,000 ብር ለስድስት ወራት 384,000 ብር እንዲከፍሉ ማድረጋቸውንም አክሏል፡፡

ተበዳሪው የወሰዱትን ገንዘብ መክፈል ሲያቅታቸው ተከሳሽ በመያዣነት የወሰዱትን ለንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በተበዳሪው የተጻፈ ደረቅ ቼክ እንደሚያስመቱባቸው በመንገርና በማስፈራራት፣ ‹‹ፋብሪካውን ሸጬልሃለሁ ብለህ ፈርምልኝ›› በማለት ድርሻቸውን ሙሉ በሙሉ መውሰዳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ይገልጻል፡፡ አቶ ዓብይ ፋብሪካውን ከወሰዱ በኋላ፣ አቶ ለማ ለሚባሉ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የአሜሪካ ዜጋ በ380,000 ዶላር በመሸጥ፣ ክፍያውን በአቶ ዓብይ ስም ጀርመን ፍራንክፈርት እንዲተላለፍላቸው ማድረጋቸውንም አክሏል፡፡ ሌሎች ንብረቶችን ለአራጣ ማካካሻ በመውሰድ ለተበዳሪው አቶ ዳዊት ከበደ 23,000 ብር ብቻ በመስጠት ፋብሪካውን ከነማሽነሪውና ሁለት ተሽከርካሪዎች መውሰዳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ በመሆኑም የወንጀል ሕግ አንቀጽ 715(ሐ)ን መተላለፋቸውን ጠቁሟል፡፡ ተመሳሳይ የወንጀል ሕግ አንቀጽ በመጣስ፣ አቶ ዳንኤል ወንድወሰን ኢኤል ጄኔራል ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚባለውን ድርጅታቸውን ቤአኤካ ጠቅላላ የንግድ ሥራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር የእሽሙር ማኅበር በመመሥረት ደልቢ ኮል ማይኒንግ የሚባል ማኅበር መሥርተው የሥራ ውል ከተፈራረሙ በኋላ፣ ለሥራ ማስኬጃ ለአቶ ዳንኤል 2,997,000 ብር በሁለት ወር አበድረው 12 በመቶ ወለድ ጨምረው እንዲመልሱ መስማማታቸውንና ከወለዱ ጋር ያላግባብ 3,017,000 ብር እንዲከፍሉ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

ተከሳሹ ሌላው አራጣ በማበደር ወንጀል ፈጽመዋል የተባለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ በሆኑትና የእንግሊዝ ዜግነት ባላቸው አቶ ደረጀ ተክለ ሚካኤል ላይ ነው፡፡ አቶ ዓብይ በ1998 ዓ.ም. እንግሊዝ አገር በሄዱበት ወቅት ከአቶ ደረጀ ጋር ተገናኝተው ስለቢዝነስ ሲነጋገሩ፣ የመኪና ኪራይ አዋጭ መሆኑን አቶ ዓብይ ሲነግሯቸው ሊሞዚን ገዝተው እንዲልኩ መስማማታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ አቶ ደረጀ መኪናውን በ52,000 ዶላር ገዝተው የላኩ ሲሆን፣ መኪናውን ጂቡቲ ወደብ ሲደርስ ግን አቶ ዓብይ ጂቡቲ ከሚገኝ ነጋዴ እንደተሸጠላቸው በማስመሰል በራሳቸው ስም ኤልሲ ከፍተው ወደ ኢትዮጵያ ማስገባታቸውን ጠቁሟል፡፡ አቶ ደረጀ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሲጠይቋቸው ለቀረጥ ከፍያለሁ ባሉት 900,000 ብር ላይ በየወሩ ስምንት በመቶ ወለድ እንዲከፍሉ እንደጠየቋቸውም ክሱ ይገልጻል፡፡ አቶ ደረጀ ተስፋ ባለመቁረጥ በሽምግልና ሲጠይቋቸው አቶ ዓብይ 250,000 ብር በመስጠት አጠገባቸው እንዳይደርሱ እንዳስጠነቀቋቸውም ክሱ ይገልጻል፡፡ በመሆኑም አቶ ደረጃ ወደ አገር ተመልሰው ለመሥራት የሰነቁትን ተስፋ እንዳጨለሙባቸው ክሱ ያብራራል፡፡

አቶ ዓብይ በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005ን በመተላለፍ፣ ኢትዮጵያውያንን በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገር በመላክ ለግለሰቦች በከፍተኛ ወለድ አራጣ በማበደር በርካታ ገንዘብ ማግኘታቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡ እንዲሁም የመንግሥትን ይዞታ በሕገወጥ መንገድ በመያዝ ፈቃድ ሳይኖራቸው የባንክ ሥራ በመሥራት፣ ግለሰቦችን በማታለል ገንዘብና ንብረት በመውሰድ፣ የመንግሥትን ግብር በማጭበርበር ያገኙትን ገንዘብ ሕጋዊ በማስመሰል፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በራሳቸው፣ በቤተሰባቸውና አዲስ ቪው ጄኔራል ሰርቪስ ኃላነፊቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም ለመኖሪያ፣ ለሆቴል ግንባታ የተለያዩ ስፋት ያላቸው የከተማ ቦታዎችና የአክሲዮን ድርሻዎች በመግዛትና በባንክ በማስቀመጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡

ተከሳሹ በወንጀል ተግባር የተገኘን ገንዘብ ወደ ውጭ አገር በማሸሽ ጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ በሚገኘው ኮሜርስ ባንክ ፍሉካን ቅርንጫፍ፣ አሜሪካ በሚገኙ ፒኤንሲ ባንክ፣ ባንክ ኦፍ አሜሪካ፣ በእንግሊዝና በሌሎች የአውሮፓ አገሮች ማስቀመጣቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡

አቶ ዓብይ በባለቤትነት የሚመሩት አዲስ ቪው ጄኔራል ሰርቪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም ያስመዘገቧቸውን የተለያዩ ተሽከርካሪዎች ሲያከራዩ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ሳይቆርጡ ግብይት በማካሄዳቸውም ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ተከሳሹ ምንም ዓይነት የውጭ አገር ንግድ ወኪልነት ሳይኖራቸው ወይም የኮሚሽን ሠራተኝነት የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው፣ በፖላንድ ዋርሶ ከተማ የተመዘገበውንና ቢፖሮማስ ቢፕሮን ትሬዲንግ የሚባለው የውጭ ድርጅት ውክልና እንደሰጣቸው የገለጹ ቢሆንም፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ አለመረጋገጡን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

በመሆኑም አቶ ዓብይ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር የጦር መሣሪያዎችና መለዋወጫዎች ለመግዛት አውጥቶ የነበረውን ውስን ዓለም አቀፍ ጨረታዎች፣ በድርጅታቸው አዲስ ቪው ጄኔራል ሰርቪስ ስም ለመጫረት የጨረታ ማስከበሪያ ሲፒኦ በማጻፍ በጨረታው በመሳተፍና ወክሎኛል ያሉት ድርጅት ሲያሸንፍ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በመቅረብ የማስረከብ ሥራ መሥራታቸው፣ በተፈቀደ የንግድ ፈቃድ የሚሠራን ሥራ ፈቃድ ሳይኖራቸው መሥራታቸውን አብራርቷል፡፡ የፖላንዱን ኩባንያ ተወዳድሮ ካሸነፈው ጠቅላላ ዋጋ ላይ አምስት በመቶ ኮሚሽን 2,922,163 ብር በውጭ አገር ከሚገኘው ሚስተር ጃርስለው ጋር በመመሳጠር ገንዘቡን በውጭ ምንዛሪ ማሸሻቸውንም አክሏል፡፡ የቀረቡትን መሣሪያዎችንም ፎቶ በማንሳት በግል ሞባይላቸውና አይፓድ ላይ በመጫን ለሕዝብ በግልጽ ያልታወቀ ሚስጥርነት ያለው ጉዳይ፣ ላልተፈቀደላቸው ለተለያዩ ሰዎች ያሳዩና መረጃ የሰጡ መሆናቸውንም ዓቃቤ ሕግ አብራርቷል፡፡

አቶ ዓብይ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 691(1)ን በመተላለፍ የግል ተበዳይ የሆኑትን አቶ ሚኪያስ ጌቱና ወላጅ እናታቸው ወ/ሮ የሺ ግዛው (ሞተዋል) የግል ይዞታ የሆነውንና ስፋቱ 118 ሜትር ካሬ ቦታ የአዲስ ቪው ሆቴል አዋሳኝ መሆኑን በመግለጽ፣ መንግሥት ለልማት ቦታውን እንደፈለገው እንደነገሯቸው ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ነገር ግን መንግሥት የሚከፍላቸው ካሳ ትንሽ ስለሆነ እሳቸው የተሻለ ገንዘብ እንደሚሰጧቸው በማሳመን ቦታውን እንደወሰዱባቸው ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር ገልጿል፡፡ ሟች ቦታውን ያቆዩት ለልጃቸው እንደሆነ ለአቶ ዓብይ ሲነግሯቸው፣ ‹‹እሱን ወደ ውጪ እልከዋለሁ›› ያሏቸው ቢሆንም፣ ልጁን ግን የላኩት ደቡብ ሱዳን መሆኑን አስረድቷል፡፡ ቪዛ አውጥተው ወደ ውጭ እንዲሄድ እንደሚልኩለት አሳምነው ወደ ደቡብ ሱዳን የላኩት ቢሆንም፣ ሳይልኩለት በመቅረታቸው ወደ አገሩ መመለሱን ዓቃቤ ሕግ አስረድቷል፡፡ አቶ ዓብይ ለወ/ሮ የሺ ልጃቸውን ወደ ውጭ እንደላኩላቸው በማሳመንና እሳቸውንም እንደሚረዷቸው በመግለጽ የመኖሪያ ቤት ሽያጭ ውል በማዘጋጀት፣ ባልተከፈላቸው 30,000 ብር የግዢ ውል በማስፈረምና እሳቸውን የራሳቸው እናት ቤት ወስደው እንዳስቀመጧቸው ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ ነገር ግን ወ/ሮ የሺ በነበሩበት ቤት ውስጥ ሞተው መገኘታቸውንም ዓቃቤ ሕግ አክሏል፡፡ በመሆኑም ተከሳሹ ከባድ የማታለል ወንጀል መፈጸማቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተው በአቶ ዓብይ፣ አዲስ ቪው ጄኔራል ሰርቪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሚስተር ጃሮስላው ፋልኮልስኪ (በሌሉበት)፣ ቢፕሮማስ ቢፕሮን ትሬዲንግ ኤስኤ (በሌሉበት) እና በድለላ ሥራ እንደሚተዳደሩ የገለጹት አቶ ዮናታን ቦጋለ በላቸው ላይ ነው፡፡

አቶ ዮናታን ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ቢውሉም በሕጉ መሠረት በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ በነፃ እንዲያሰናብታቸው ጠበቃቸው አቶ ሞላ ዘገየ አመልክተዋል፡፡ ተከሳሹ በድለላ ለአቶ ዓብይ አንድ ተሽከርካሪ በ60,000 ብር ያሸጡ ቢሆንም፣ ሊብሬውን ከሻጭ ወደ አቶ ዓብይ አለመተላለፉን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም መኪናው የአቶ ዓብይ አይደለም ማለታቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ መኪናው አቶ አሚር አህመድ የሚባሉ ግለሰብ መሆኑን በመግለጽ የወንጀል ፍሬ የሆነን መኪና አታለው መውሰዳቸውን ዓቃቤ ሕግ ጠቅሶ፣ በከባድ የማታለል ወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡

ጠበቃቸው በደንበኛቸው ላይ የተጠቀሰው የሕግ አንቀጽ ዋስትና እንደማይከለክል በመጠቆም፣ ዋስትና እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ አቶ ዓብይም ባለሀብት፣ የቤተሰብ ኃላፊና የአደባባይ ሰው መሆናቸውን የተናገሩት ጠበቃ ሞላ ዘገየ፣ እሳቸውም የተጠቀሱባቸው አንቀጾች ዋስትና እንደማይከለክሉ በመግለጽ እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ በሰጠው ትዕዛዝ በአቶ ዓብይ ላይ የቀረቡ ክሶች ዋስትና እንደማይከለክሉ አረጋግጦ፣ ነገር ግን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰጠው አስገዳጅ ውሳኔ፣ ተደራራቢ የወንጀል ክስ የቀረበባቸው ተከሳሾች ዋስትና እንደሚነፈጉ መግለጹን አሳውቋል፡፡ በመሆኑም የጠየቁትን ዋስትና ውድቅ አድርጎታል፡፡ አቶ ዮናታን ግን በ15,000 ብር ዋስ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ የመጀመሪያ የክስ መቃወሚያ ለመቀበል ለጥቅምት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

Standard (Image)

አሥራ ሁለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ ከገዢው ፓርቲ ጋር ለመደራደር ተስማሙ

$
0
0

 

ከገዥው ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እየተደራደሩ የሚገኙ 12 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመደራደሪያ ሐሳባቸውን በጋራ ለማቅረብና ለመደራደር ወሰኑ፡፡

አሥራ ሁለቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ ለመደራደር መወሰናቸውን ያስታወቁት ሐሙስ ጳጉሜን 2 ቀን 2009 ዓ.ም. የየፓርቲዎቹ ተወካዮች፣ በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ዋና ጽሕፈት ቤት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው፡፡

በዚህም መሠረት በዚህ ሳምንት ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው ድርድር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) ከኢዴፓ፣ አቶ ሙሉጌታ አበበ ከመኢአድ፣ እንዲሁም አቶ ትዕግሥቱ አወሉ ከአንድነት ዋና ተናጋሪዎች እንዲሆኑ መመረጣቸውን አስታውቀዋል፡፡

   በሁለተኛው ዙር ድርድር የሚደረግበት አጀንዳ ደግሞ የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ አዋጅ 532/99 ነው፡፡ ድርድሩ ለሕዝብና ለአገር የሚበጅ፣ ለሕዝብ ጥያቄ መልስ የሚሰጥና የዴሞክራሲ ምኅዳሩን የሚያሰፋ፣ እንዲሁም ለውጥ ሊያመጣ የሚችልና ጠብ የሚል ድርድር እንዲከናወን በማሰብ አሥራ ሁለቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መሰበሰባቸውን፣ የመኢአድ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ አመልክተዋል፡፡

‹‹ለሕዝቡም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ሒደት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣና ተፈጻሚ እንዲሆን ለመታገል ነው የተሰባሰብነው፤›› በማለት አክለዋል፡፡

‹‹ለብዙ ወራት ከመንግሥት ጋር ከፍተኛ ድርድር ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ይህ ድርድር በተለያዩ ቡድኖች ተከፍሎ ምናልባትም ለውሳኔ ሰጭነት ወይም ለመግባባት ከፍተኛ ችግር ፈጥሮ የቆየ ነበር፤›› በማለት የገለጹት ደግሞ፣ የኢዴሕ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሐየ ናቸው፡፡

‹‹ምንም እንኳ እኛ አንድ ዓይነት አመለካከት ወይም ሐሳብ ቢኖረንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች በሦስት ወይም በአራት ቡድን መከፋፈላችን ድርድሩ ጎታች ባህሪ እንዲኖረው አድርጎት ነበር፡፡ ስለዚህ እርሱን እንደ ትልቅ ትምህርት ወስደን ተሰባስበንና አንድ ሆነን ሐሳባችንን ጨምቀን፣ በአንድ ድምፅ ማስገባት ይሻላል የሚለው ላይ ተሰማምተናል፤›› ብለዋል፡፡

የተሻለው የኢትዮጵያ ምርጫ ሕግ አዋጅ 111 አንቀጾች ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ችግር አሉባቸው ያሏቸውን 25 አንቀጾች ነቅሰው ማውጣታቸውን አቶ ትዕግሥቱ አስረድተዋል፡፡

በእነዚህ 25 አንቀጾች ውስጥ ደግሞ 45 ንዑስ አንቀጾች እንዲሁ ተለይተው መውጣታቸውን ገልጸው በዚህም መሠረት 28 አንቀጾች እንዲሻሻሉ፣ 9 አንቀጾች እንዲሰረዙ፣ እንዲሁም ስምንት አዳዲስ አንቀጾች በአዋጁ እንዲካተቱ ማስገባታቸውን አስረድተዋል፡፡

ፓርቲዎቹ እንዲሰረዙ የጠየቋቸው አንቀጾች የምርጫ ቦርድ አባላትን፣ የቦርዱ ሥልጣንና ተግባራትን፣ የቦርዱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች አሿሿምና ተጠሪነት፣ የምርጫ ክልሎችን፣ በልዩ ሁኔታ ስለሚቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች፣ ለዕጩነት ስለሚያበቁ መመዘኛዎች፣ የዕጩዎችን ብዛት ስለመለየት፣ የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ የማይደረግባቸው ቦታዎችና የምርጫ ታዛቢዎችን የተመለካቱ እንደሆነ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አሥራ ሁለቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ሆነው በሚያቀርቡት ጥያቄና ድርድር ዴሞክራሲ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ከንድፍ ተላቆ ተግባራዊ እንዲሆን፣ ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር የሕዝቦች ባህል እንዲሆን፣ የፖለቲካ ተሳታፊዎች በነፃነት በአደባባይ እንዲንቀሳቀሱና እንዲታዩ የሕግ ከለላ እንዲደረግ፣ ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንዲተገበር፣ እንዲሁም የታፈኑ ሐሳቦች ያላንዳች መሰናክል በሕዝብ ውስጥ እንዲንሸራሸሩ ለማስቻል ተስፋ አድርገዋል፡፡

ከገዥው ፓርቲ ጋር በጋራ ለመደራደር የወሰኑት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሰያዊ ፓርቲ (መኢዴፓ)፣ የመላው ኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኦሕዴፓ)፣ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (ቅንጅት)፣ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት (ኢዴሕ)፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (ኢዴአን) እና የወለኔ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ወሕዴፓ) ናቸው፡፡

 

 

Standard (Image)
Viewing all 475 articles
Browse latest View live