Quantcast
Channel: እኔ የምለዉ
Viewing all 475 articles
Browse latest View live

የወቅቱን ሁኔታ ብዙም ያልዳሰሰው የጠቅላይ ሚኒስትሩና የወጣቶች ውይይት

$
0
0

ሐሙስ ነሐሴ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ ከአገሪቱ የተለያዩ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ3,000 በላይ ወጣቶች ሞልተውታል፡፡

የወጣቶቹ በሥፍራው መሰባሰብ ይደረጋል ከተባለበት ቀን በሁለት ሳምንታት የተራዘመውን የጠቅላይ ሚኒስትሩንና የወጣቶችን ውይይት ለመታደም ነበር፡፡

ነሐሴ 12 እና 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትሩና የወጣቶች ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለባቸው የሥራ ብዛት ሳቢያ መራዘሙ ይታወሳል፡፡

ሐሙስ ዕለት ከተከናወነው የጠቅላይ ሚኒስትሩና የወጣቶች የፊት ለፊት ውይይትና ጥያቄና መልስ አስቀድሞ ቂሊንጦ በሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት፣ ‹‹የወጣቶች ሚና በኅብረ ብሔራዊነት ላይ›› በሚል ርዕስ የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለብርሃን የመሩት ውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ውይይት ወቅት ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ ወጣቶች ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የጎዳና ተዳዳሪ ወጣቶች፣ የአካል ጉዳተኛ ወጣቶች፣ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ወጣቶች እንዲሁም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲን የወከሉ ወጣቶች ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡

ለተቃዋሚ ፓርቲ ወጣቶች በተዘጋጀው ሥፍራ አብዛኞቹ መቀመጫዎች ባዶ ስለነበሩ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲን ወክሎ የመጣ ወጣት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዕድል በመጠቀም ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ያቀረበው ግን አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የሚጠይቁት ዓይነት ‘አባሎቻቸችን በዚህ በዚህ ሥፍራ ታስረዋል፣ እስራትና ወከባ እየደረሰባቸው ነው፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዋች እኩል አይደለም’ እና የመሳሰሉትን ዓይነት መሠረታዊ ጥያቄዎች አልነበረም፡፡

በአንፃሩ ይህ ከአዲስ ትውልድ ፓርቲ የተወከለው ወጣት ያቀረበው አስተያየት ለአገሪቷ ሰላም ወሳኝ መሆኑን፣ እንዲሁም የአገሪቱ ወጣቶች ሥራ አጥ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ አብዛኛዎቹ ብዙውን ጊዜያቸውን የሚያሰልፉት በየቡና ቤቱ ነው የሚል ነበር፡፡

‹‹ለተለያዩ ሥራዎች ወደ ክልል ስንንቀሳቀስ አንድ ቡና ቤት ውስጥ 30 እና 40 የሚሆኑ ወጣቶች ተቀምጠው ነው የምናየው፡፡ ለምን እንዲህ እንደሚያደርጉ ስንጠይቃቸውም መደበሪያችን ነው በማለት መልሰውልናል፤›› በማለት ወጣቶች ቡና ቤት ቁጭ ብለው መዋላቸውን መንግሥት ተመልክቶ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር ጠይቋል፡፡

ከየክልሎቹ ተወክለው የመጡት ወጣቶች ከየክልሎቻቸው አንፃር ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ የአብዛኛዎቹ ጥያቄዎች ማጠንጠኛም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ እንዲሁም ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ነበር፡፡

በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ ካለችበት አለመረጋጋት አንፃር ወጣቶቹ ጉዳዩን በተመለከተ የተለያዩ ጥያቄዎች ያነሳሉ የሚል ግምት የነበረ ቢሆንም፣ ከአማራ ክልል ተወክሎ ከመጣው ወጣት በስተቀር ስለወቅታዊ ጉዳዮች ጥያቄ ያነሳ የለም፡፡

ለአብነት ያህልም ከሐረሪ ክልል ተወክሎ የመጣው ወጣት የተለያዩ ጥያቄዎችን ሲያቀርብ፣ አንዱ ጥያቄ የነበረው አዲስ አበባ የሚገኙ የሐረሪ ክልል የተለያዩ ቅርሶችን ወደ ሐረሪ መመለስ የሚቻልበትን መንገድ መንግሥት እንዲያፈላልግ የሚጠይቅ ነበር፡፡

ለዚህ ጥያቄም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲመልሱ፣ ‹‹ኢትዮጵያን ለመጐብኘት የሚመጣ አንድ ቱሪስት ሁሉንም ቦታዎች ተዘዋውሮ መመልከት ላይችል ይችላል፡፡ ስለዚህ በአዲስ አበባ የአገሪቱን ሁሉንም ክፍሎች የሚወክል ቅርስ ቢኖር ጉዳት አይኖረውም፤›› ብለዋል፡፡

አዲስ አበባን ወክላ ጥያቄ ያቀረበችው ወጣት ደግሞ ያቀረበቻቸው ጥያቄዎች ከመዝናኛ ሥፍራዎችና የስፖርት ማዘውተሪያዎች ዕጦት፣ ከሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ይገነባል ተብሎ ከአሥር ዓመት በላይ ስለዘገየው የአፍሪካ ወጣቶች ማዕከል ግንባታ ነበር፡፡

በአዲስ አበባ በስፋት የሚታየውን የወጣቶች ሥራ አጥነት፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረጉ ፍልሰቶችና የመሳሰሉ ዓበይት ጉዳዮች እያሉ እነዚህን ጥያቄዎች ማቅረቧ ግርታ የፈጠረባቸው ተስተውለዋል፡፡

ከትግራይ ክልል ተወክሎ የመጣው ወጣት ደግሞ ያነሳቸው ጥያቄዎች ከጥቃቅንና አነስተኛና ከመሬት ይዞታ ባለቤትነት ጋር የተያያዙ ነበሩ፡፡ ‹‹የቤተሰቦቻችን መሬት ወደ ከተማ ክልል በሚካለልበት ጊዜ የመውረስ መብት የማይኖረን ለምንድን ነው?›› የሚል ጥያቄም አቅርቧል፡፡

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጣው ወጣት ደግሞ አሁንም ድረስ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እንዳልተገታ፣ በቤኒሻንጉል በኩል የሚደረጉ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውሮች መኖራቸውን ጠቁሞ፣ መንግሥት ይህን ለመቅረፍ ምን እየሠራ እንደሆነ ጠይቋል፡፡

ከየክልሎቹና ከከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከሌሎች ተቋማት ተወክለው የመጡት ወጣቶች ጥያቄዎቻቸው ከክልላቸው አልያም ከየተወከሉበት ተቋም አንፃር የተቃኙ ነበር፡፡

የወጣቶቹን ጥያቄዎች በጠቅላላ አዳምጠው ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በቀጥታ ጥያቄዎቹን ከመመለሳቸው በፊት፣ ስለአገሪቱ አጠቃላይ የወጣቶች ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የአገሪቱ አብዛኛው ዜጋ ወጣት እንደሆነ በመተንተን ንግግራቸውን የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ጥያቄዎቹን አንድ በአንድ እያነሱ ከመመለስ ይልቅ ስለአገሪቱ አጠቃላይ ሁኔታ በሚሰጡት ትንታኔ ውስጥ እየመለሷቸው ማለፍን መርጠዋል፡፡

‹‹70 በመቶ የሚሆነው የአገራችን ሕዝብ ከ30 ዓመት በታች ነው፡፡ ይህም ማለት ኢትዮጵያ የወጣቶች አገር ናት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ የወጣቶች አገር ከሆነች በሕዝቦች ፈቃድ ወደ ሥልጣን የሚመጣ መንግሥት የወጣቶቹ መንግሥት መሆን አለበት፤›› በማለት ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ ፖሊሲ መንግሥታቸው እንደሚከተል ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ ወደ ጥያቄዎቹ ምላሽ ከመግባታቸው በፊት በሰጡት የኢትዮጵያ ወጣቶች ሁኔታ ትንታኔ ውስጥ የነገሮች ሁሉ ማጠንጠኛ መሆን ያለበት ሕገ መንግሥቱ እንደሆነ አስምረውበታል፡፡

‹‹አሁን ያለው ሥርዓት የተመሠረተው በወጣቶች ነው፡፡ በዚህም መሠረት ለዘመናት ሲጠየቁ የነበሩ ጥያቄዎችን መመለስ የቻለ ሕገ መንግሥት እንዲኖረን አስችሏል፡፡ በዚህ መድረክ ላይ የሕገ መንግሥት ጉዳይ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ይገባል፤›› በማለት ሕገ መንግሥቱ የነገሮች ሁሉ ማጠንጠኛ እንደሆነ ለወጣቶቹ አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም፣ ‹‹ሕገ መንግሥታችን ከዚህ በፊት የነበሩ የተዛቡ ግንኙነቶቻችንን ለማከም የሚያስችል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የተዛቡ ግንኙነቶች ነበሩ፡፡ ነገር ግን የዛሬ 20 ዓመት ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ እነዚህ የተዛቡ ልዩነቶች ለሚቀጥለው ትውልድና ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የማይተላለፉ ሆነው አልፈዋል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በሥራ ፈጠራ፣ የሥራ አጥ ቁጥርን ከመቀነስ፣ እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንፃር የተሠሩ ሥራዎች ቢኖሩም ሙሉ በሙሉ ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ አግኝተዋል ማለት እንዳልሆነም ጠቅሰዋል፡፡

ሥራ አጥነትን ለመዋጋት ወጣቶች ራሳቸው ሥራ ፈጣሪ መሆን እንደሚገባቸው ጠቁመው፣ ለአብነትም ከታች ተነስተው ዛሬ የዓለማችን ታላላቅ ስለሆኑት የሳምንሰንግና የቶዮታ ኩባንያዎች ባለቤቶች የሥራ ስኬት ለወጣቶቹ ሐሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

መንግሥታቸው የወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ብዙ ሥራዎችን እንደሠራ ገልጸው፣ ከዚህ በተጨማሪ ግን ማኅበራዊ ግንኙነታቸውንም ለማሻሻል እየሠራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

‹‹የሰው ልጅ ማኅበራዊ እንስሳ ነው፡፡ ስለዚህ ማኅበራዊ ተጠቃሚነታችንና ትስስራችን መጐልበት አለበት፡፡ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ብቻውን በቂ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

የመልካም አስተዳደር ጥያቄን በተመለከተ ወጣቶች በቻሉት መጠን ሁሉ የመልካም አስተዳደር ችግር ያለባቸውን አመራሮች በማጋለጥ ሚናቸውን መጫወት ይኖርባቸዋል በማለት ተናግረዋል፡፡

ወጣቶች ተስፋ ሳይቆርጡ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ጥያቄዎቻቸውን በማቅረብ፣ በአገሪቱ አሉ የተባሉ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ጥያቄዎችን ለማስመለስ መንቀሳቀስ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በቅርቡ በተለያዩ የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች የተከሰቱትን አለመረጋጋቶች አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ ጥያቄ ያላቸው ወጣቶች ጥያቄያቸውን በሕገ መንግሥቱ መሠረት ማቅረብ ሲችሉ ድንጋይ በመወርወርና በሌሎች እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ መሆናቸው ማንንም እንደማይጠቅም አብራርተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወጣቶች የተነሱትን ጥያቄዎች ከመለሱና አጠቃላይ ማብራሪያ መስጠታቸውን ከአጠናቀቁ በኋላ ለማመስገን ወደ መድረኩ የወጣው የዕለቱ የፕሮግራም መሪ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በማለት ፈንታ ‘ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ’ ብሎ የጀመረው የምሥጋና ንግግር አዳራሹ ውስጥ የነበሩትን ታዳሚዎች በሙሉ አስደንግጦ ነበር፡፡    

 

Standard (Image)

የኢሕአዴግ አንጋፋ አመራሮች ምን እያሉ ነው?

$
0
0

በኦሮሚያና በአማራ ብሔራዊ ክልሎች ዓመቱን ሙሉ ማለት ይቻላል የተለያዩ ተቃውሞዎችና የአመጽ እንቅስቃሴዎች ተከስተዋል፡፡ በሒደቱ የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ የአካል ጉዳት ተከስቷል፣ ንብረት ወድሟል፡፡ በዜጎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይም ተፅዕኖ ተፈጥሯል፡፡

በአገሪቱ በሁለቱ ትልልቅ ክልሎች ይህን መሰል ክስተት መፈጠሩ ምን ያመለክታል? የሥርዓቱ ዕጣ ፈንታን ይወስናል? ምን ዓይነት ጊዜያዊና ዘላቂ ተፅዕኖ ይፈጥራል? በሚል ጉዳዩ ይመለከተናል ያሉ የአገር ውስጥና የውጭ ኃይሎች የውይይት አጀንዳ ከፈጠሩ ሰነባብተዋል፡፡

ዜጎች፣ ቡድኖችና የተለያዩ ተቋማት በጉዳዩ ላይ የራሳቸውን ትንታኔ በማቅረቡ ላይም ይገኛሉ፡፡ መንግሥትም ለጉዳዩ እየሰጠ ካለው ምላሽ በተጨማሪ የራሱን ማብራሪያ ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ መንግሥት መሥርቶ አገሪቱን መምራት ከጀመረ 25 ዓመታት ያለፉት ኢሕአዴግም፣ በቅርቡ ጉዳዩን ገምግሜ የመፍትሔ አቅጣጫ አስቀምጫለሁ ማለቱ ይታወቃል፡፡

ከቀናት በፊት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የሕወሓት፣ የብአዴን፣ የኦሕዴድና የዴኢሕዴግ አንጋፋ አመራሮች የሆኑት አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ አቶ በረከት ስምኦን፣ አቶ አባዱላ ገመዳና ዶ/ር ካሱ ኢላላ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሸን (ኢቢሲ) ጋር ባደረጉት ሰፋ ያለ ውይይት በእነዚሁ ጉዳዮች ላይ የበኩላቸውን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

እነዚህ አንጋፋ የኢሕአዴግ አመራሮች የተቃውሞዎቹና የአመፅ እንቅስቃሴዎቹ የመንግሥት የልማትና የዕድገት ስኬቶች የወለዷቸው እንደሆኑ በመግለጽ፣ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ምክር ቤት የተሰጡ መግለጫዎች ላይ የተቀመጠውን ጭብጥ ደግመውታል፡፡

በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ችግሮቹ በሥርዓቱ ላይ ያሉ ክፍተቶችን ያጋለጡና ማሻሻያ አስፈላጊ እንደሆነ ያሳዩ ናቸው በማለት ይገልጻሉ፡፡ ኢሕአዴግ በኪራይ ሰብሳቢነት፣ በዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ይዞታ እንዲሁም የጠባብነትና የትምህክተኝነት አመለካከቶች ላይ ክፍተቶች እንደተከሰቱ በመግለጽ ጉዳዩ የመልካም አስተዳደርና የአፈጻጸም ክፍተት እንጂ ከፖሊሲና ከሥርዓቱ መሠረታዊ መርሆች ጋር የተያያዘ አይደለም በማለት ራሱን ይከላከላል፡፡

የአንጋፋዎቹ ማብራሪያም በዚሁ መንፈስ የተሰጠ ነው፡፡ አቶ በረከት ኢትዮጵያ በኢሕአዴግ አመራር በመነሳት ላይ ያለችና የቆዩ ችግሮቹን እየፈታች ያለች አገር እንደሆነች ገልጸዋል፡፡ በአቶ በረከት ገለጻ እነዚህ የቆዩ ችግሮች ብዝኃነትን በአግባቡ ማስተናገድ፣ የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ ይዞታ፣ የኢኮኖሚ ዕድገትና የሰላም መረጋገጥ ናቸው፡፡ ‹‹ብዝኃነትን በአግባቡ ማስተናገድ ጀምረናል፡፡ ዴሞክራሲን ተግባራዊ ማድረግና ማስፋት ችለናል፡፡ አሁን የአገሪቱ ፀጋዎችን በደንብ ማልማትና ሀብት ማፍራት ጀምራለች፡፡ ግጭቶችን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በመከተል እየፈታን በመሆኑ ውጫያዊና ውስጣዊ ሰላም ተከብሯል፤›› ብለዋል፡፡

በአገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ የተቃውሞና የአመፅ እንቅስቃሴዎች ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱና የፌዴራል ሥርዓቱ በአግባቡ እየዋለ አይደለም በማለት ተቃውሞ ያቀረቡበት አጋጣሚን አስተናግደዋል፡፡ አቶ ዓባይ ግን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱም ሆነ የፌዴራል ሥርዓቱ በአግባቡ እየተተረጎመ መሆኑን በመግለጽ ተከራክረዋል፡፡ አሁን በኢሕአዴግ የተመዘገበው ስኬት ከቀደመው ሥርዓት ችግሮች አንፃር ቢቃኝ ልዩነቱን በግልጽ ማየት እንደሚቻልም አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ያስወገደው የፖለቲካ ሥርዓት ልዩነትን በኃይል የሚጨፈልቅ፣ የፖለቲካ ልዩነትን እንደ ወንጀልና ኃጢያት የሚወስድ ነበር፡፡ አሁን የሥልጣን ክፍፍልና የመንግሥት ተቋማት ሚዛናዊ የሆነ የቁጥጥር ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ ራሳቸውን የቻሉ ገለልተኛ የፌዴራልና የክልል ምክር ቤቶችና ፍርድ ቤቶች ተቋቁመዋል፡፡ በሕግ የሚመራ አስፈጻሚ አካላትም አሉ፤›› ብለዋል፡፡

ኢሕአዴግ የሐሳብ ልዩነትን እንደማይቀበልና ተቃዋሚዎቹን በኃይል ለማጥፋት ይጥራል በሚል በተደጋጋሚ እንደሚተች ይታወቃል፡፡ አቶ ዓባይ  ግን ክፍተት ካለ የሥርዓቱ መለያ ሳይሆን በበቂ ሁኔታ ያለመተግበር ችግር እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ‹‹ሥርዓቱ ሕገ መንግሥቱን በአጥጋቢ ደረጃ ቢተገብርም ያልዳበሩና የሚፈቱ ጉዳዮች አሉ፤›› ብለዋል፡፡

አቶ አባዱላም ከአቶ ዓባይ ጋር ይስማማሉ፡፡ የአገሪቱ የ25 ዓመታት ጉዞ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ የሚሠራ መሆኑን በተግባር እንዳረጋገጠም አመልክተዋል፡፡ ‹‹የፌዴራል ሥርዓቶችን የሚሠራ፣ ምንም እንከን የሌለውና ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው፤›› ብለዋል፡፡

አሁን አገሪቱ የዕድገት ተምሳሌት እንደሆነች ያመለከቱት አቶ አባዱላ ልማቱ የፈጠረውን ኃይል ፍላጎት ማሟላት ከባድ ፈተና መፍጠሩ ግን አምነዋል፡፡ ችግሩም በማስፈጸም አቅም ውስንነትና በገንዘብ እጦት የሚገለጽ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ዶ/ር ካሱ በበኩላቸው የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ዴሞክራሲያዊ ሰላም ማምጣቱን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ድሮ ድርቅ ሲኖር ሕዝብ ይረግፍ ነበር፤›› ያሉት ዶ/ር ካሱ፣ አሁን ይህን የመቋቋም አቅም መዳበሩ አገሪቱ በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ እንደምትገኝ አመላካች እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ወደ መካከለኛ ገቢ ለመግባት አስተማማኝ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው፤›› ብለዋል፡፡

የሕዝቡ ከድህነት የመውጣት ፍላጎት በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ልማታዊ ባለሀብት እያፈራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ኅብረተሰቡም ሞጋችና መብቱን ጠያቂ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

አቶ በረከት ኢትዮጵያ የጀመረችው ዕድገት ዘላቂነት እንዳለው ማሳያው በልማቱ እየመጣ ያለው ከአገር ውስጥ ሀብት መሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ዛሬ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት ከራሳችን አገራዊ ምንጮች እያገኘን ነው፡፡ ከግብርናችን፣ ከአገልግሎት ዘርፍ፣ ከኢንዱስትሪው ሀብት እየፈጠርን ነው፡፡ የማንኛውም አገር ኢንዱስትሪ ልማት፣ የግብርና መስፋፋት፣ የአገልግሎት ዘርፍ መጠናከር የሚወሰነው የአገር ዕድገቱን ሊያፋጥንለት የሚችል ካፒታል ከራሱ ምንጮች ማግኘት ከቻለ ብቻ ነው፡፡ እኛ በሚሊዮን የሚቆጠር ጉልበት ያለው አርሶ አደር አለን፡፡ የሰሜን ምሥራቅ እስያ አገሮች ተሞክሮ የሚያሳየው በመሬት የተከፈለ፣ በጥሩ ፖሊሲዎች የሚደገፍ፣ መንግሥት የቴክኖሎጂና የብድር አቅርቦት የሚያሟላለት አነስተኛ አርሶ አደር በጣም ሰፊ አገራዊ ሀብት የመፍጠር አቅም ይኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የ1980ዎቹን ቻይና ትመስላለች፡፡ ቻይና ትልቁን ዕድገት ለማምጣት በተዘጋጀችበት ጊዜ የነበረችበት ደረጃ ላይ እንደደረስን አኃዛዊ መረጃዎች ያሳያሉ፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

በመንግሥት ጥረት ፍላጎቱን በደንብ የሚያውቅና የሚራመድ ኅብረተሰብ መፍጠሩን ያመለከቱት አቶ በረከት፣ መንግሥት አቅሙን አዲስ ከፈጠረው ኃይል ፍላጎት ጋር ለማጣጣም አቅሙን ሊያሳድግ ይገባል ብለዋል፡፡ ‹‹ከጊዜ ወደ ጊዜ የተማረ ኅብረተሰብ እየፈጠርን ነው የመጣነው፡፡ ይኼን የተማረና በዴሞክራሲውም የዳበረ አመለካከት ያለው ኅብረተሰብ ማስተዳደር ከመንግሥት በኩል የማያቋርጥ ብቃትና መሻሻል ይጠይቃል፡፡ ሕዝቡ አዳዲስ ፍላጎቶች ይዞ ይመጣል፡፡ ወጣቶችም አዳዲስ ፍላጎት ይዘው ይንቀሳቀሳሉ፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡

ዕድገቱ የወለዳቸው ካሏቸው ፈተናዎች በተጨማሪ በመንግሥት በኩል አላግባብ የመጠቀም ዝንባሌም ሌላ ፈተና መሆኑን አቶ በረከት አምነዋል፡፡ ለሕዝብ የቆመ መንግሥት ግንባታ ላይ ግድፈት ቀጠለ ማለት ወደ ኋላ የመመለስ አደጋ የሚደቅን እንደሆነም አክለዋል፡፡

አቶ ዓባይ የተቃውሞና የአመፅ እንቅስቃሴው አንዱ መነሻ ምክንያት የገበሬዎች መፈናቀልም ቢሆን የልማቱ ውጤት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ‹‹በበርካታ አካባቢዎች ተገቢ ካሳ ተከፍሏል፡፡ መልሶ ማቋቋም ተከናውኗል፡፡ በሌሎች አንዳንድ አካባቢዎች ግን በአመራርና በአስተዳደር ክፍተት ይህ ሳይከናወን ቀርቷል፤›› ብለዋል፡፡

በፓርቲም ሆነ በመንግሥት ደረጃ የአመራር ድክመትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መነሳታቸውን ያስታወሱ አቶ ዓባይ፣ የፍትሕ አካላት ራሳቸው የብቃት፣ የተጠያቂነትና የውጤታማነት ችግር ያለባቸው መሆኑ ነገሮችን እንዳባባሰ አመልክተዋል፡፡ ከእነዚህ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ተገቢ በመሆናቸው ምላሽ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ተገቢ ያልሆኑ ጥያቄዎችም አሉ፤›› ብለዋል፡፡

በተቃዋሚዎቹ የሕወሓት የበላይነት አንዱ ጥያቄ ነበር፡፡ የሕወሓት መሥራች የሆኑት አቶ ዓባይ ግን ይህን ጉዳይ አጣጥለውታል፡፡ ‹‹አንዱ ብሔር የበላይ፣ ሌላው የበታች አይደለም፡፡ ፖሊሲውም ሆነ ትግበራው ፍትሐዊና ተመጣጣኝ ልማት ነው፡፡ የጎደለ ነገር ካለ ሁሉም ጋር ነው የጎደለው፤›› ብለዋል፡፡ ዶ/ር ካሱም የትግራይ የበላይነት እውነትነት የሌለው ነው ብለዋል፡፡ መከላከያውም በአንድ ብሔር የበላይነት ነው መባሉ ስህተትና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ የሁሉም ብሔረሰቦች ተዋጽኦ የተንፀባረቀበት ነው ብለዋል፡፡

አንጋፋዎቹ አመራሮች ሙስና በግለሰብ ደረጃ ቢታይም የሥርዓቱ መገለጫ አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ አቶ አባዱላ ‹‹አሁን የተፈጠረው ነገር የመንግሥትን ድክመት የሚያሳይ አይደለም፡፡ መንግሥታዊ ሙስና አይደለም ያለው፡፡ ፖሊሲዎችንና ተቋሞችን ለሙስና የሚመቹ አይደሉም፡፡ ለሙስና የማይመቹ አደረጃቶችና አሠራሮች አሉን፡፡ አሁን የተከሰተው ነገር እዚህ አገር ሙሰኛ ሆኖ መቀጠል እንደማይቻል ማሳያ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል የተነሳው ተቃውሞ መነሻ ምክንያት የወልቃይት የማንነት ጥያቄ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በጉዳዩ ላይ አቶ ዓባይ ሲናገሩ፣ ‹‹ኢሕአዴግ ከመጣ በኋላ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሌሎች ክልሎችም ሲካለሉ በድሮው አከላለል ትግራይ ውስጥ የነበረ ወደ አማራ ክልል የሄደ፣ ወደ አፋር ክልል የሄደ፣ ወደ ትግራይ ክልል ደግሞ የመጣ፣ ወደ ኦሮሚያ የሄደ ቦታ አለ፡፡ ሽግሽጎች ተደርገዋል፡፡ መስፈርቱን መሠረት በማድረግ በሕዝብ አሰፋፈርና በቋንቋ ነው የተወሰነው፡፡ ወልቃይት በትግራይ ክልል የተከለለው በዚያ መሠረት ነው፤›› ብለዋል፡፡ አሁን ጥያቄ ካለ ለትግራይ ክልል መቅረብና መታየት እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያ በተመሳሳይ ተቃውሞ የጀመረው የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም ነበር፡፡ ተቃውሞው እየበረታ መጥቶ መንግሥት ማስተር ፕላኑ እንደቀረ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ የኢሕአዴግ አንጋፋ አመራሮች ግን ማስተር ፕላኑ ቀረ ከማለት ይልቅ ‹እንዲዘገይ የተደረገው› የሚል ገለጻ ተጠቅመዋል፡፡ አቶ ዓባይ ‹‹ማስተር ፕላኑ አዲስ አበባንና በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለውን የልዩ ዞን ሕዝብ የሚጠቅም ነው፡፡ ገበያው፣ ትራንስፖርቱ፣ መሠረተ ልማቱ ተጠቃሚ የሚያደርገው ክፍተት ነው፡፡ የአመራር ችግር ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ እስኪረዳው ድረስ ይቆይ የተባለው ለዚህ ነው፡፡ እንጂ ስህተት ስለሆነ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ክፍተት የፈጠረው በመንግሥትና በገዥው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን በሕዝቡና በዴሞክራሲ ተቋማት ጭምር እንደሆነ አቶ ዓባይ ተከራክረዋል፡፡ ‹‹ጥያቄዎችን ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መልኩ የመጠየቅና የማስተናገድ ልምድ ተቋማዊና ባህል ልናደርገው እንችል ነበር፡፡ ከአሁን በኋላም ልናደርገው ይገባል፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማት በአግባቡ ቢሠሩ ኖሮ መንግሥት ጥያቄዎችን በአግባቡና በወቅቱ እንዲፈታ ጫና ያደርጉ ነበር፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

አቶ ዓባይ ተቃውሞዎቹንና የአመፅ እንቅስቃሴዎቹን ‹የህዳሴ ጉዞ ማዕቀፍ ውስጥ የተፈጠሩ ጊዜያዊ ችግሮች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ሌሎቹ አመራሮችም ችግሮቹ የአገር ህልውና ይፈታተናሉ በሚል የቀሪውን ትንታኔ በመቃወም በቀላሉ የሚፈቱ ናቸው ሲሉ ደምድመዋል፡፡

 

 

 

Standard (Image)

የተቃውሞ ዓመት

$
0
0

2008 ዓ.ም. በገባ በሦስተኛው ወር በኦሮሚያ የተነሳው ተቃውሞ እየተቀጣጠለ በርካታ የክልሉን አካባቢዎች አዳረሰ፡፡ በተለያዩ የክልሉ ከተሞችና ዩኒቨርሲቲዎች በሰላማዊ መንገድ የተጀመረው ተቃውሞ መልኩን በመቀየር ወደ ደም መፋሰስ፣ የበርካታ ነዋሪዎችንና የፀጥታ ኃይሎችን ሕይወት እስከ መቅጠፍ ተሸጋገረ፡፡ በተመሳሳይ ወቅት በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞን ለዓመታት ሲንከባለል በቆየው የቅማንት ብሔረሰብ የማንነት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ማጣት ከሰላማዊ መንገድ እንዲወጣ በመገደዱ፣ ደም አፋሳሽ ግጭትን አስከተለ፡፡ የበርካቶችንም ሕይወት ቀጠፈ፡፡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተነሱት የሕዝብ ጥያቄዎች ለተወሰኑ ወራት ጋብ ያሉ ቢመስልም ተዳፍነው ሲግሉ ቆይተው መልካቸውን ቀይረው በድጋሚ ገነፈሉ፡፡ በኦሮሚያ ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ መልኩን ቀይሮ ፖለቲካዊ ይዘትን ተላበሰ፡፡ በትግራይ ክልል በወልቃይት ማንነት ጋር የተገናኘ የወሰን ጥያቄ፣ በተለያዩ ተፅዕኖዎች ከትግራይ ክልል ተገፍቶ ወጥቶ በሰሜን ጎንደር በመክተም ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ ማቅረቡን ቀጠለ፡፡ በአዲስ አበባ አዲስ የትራፊክ ሥነ ሥርዓት ደንብ ፀድቆ ወደ ተግባር መግባቱና ደንቡ የያዛቸው ተደራራቢና ጥብቅ ቅጣቶችን በመቃወም የታክሲ አሽከርካሪዎች የአንድ ቀን የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ በመንግሥት ላይ ጫናቸውን አሳረፉ፡፡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተነሱት ተቃውሞዎች ሙሉ በሙሉ ፖለቲካዊ ይዘትን ተላብሰው መንግሥትና ገዥው ፓርቲን አጣብቂኝ ውስጥ በመክተት ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዓመት በግራ መጋባት ውስጥ እየተቀበሉት ይገኛሉ፡፡ ተቃውሞ ወደ ገነፈለበትና በአገሪቱ በስፋት የተስፋፋበትን የ2008 ዓ.ም. ሕዝባዊ የተቃውሞ ክስተቶችን ዮሐንስ አንበርብርእንደሚከተለው ቃኝቷቸዋል፡፡    

 

ቅድመ 2008 ዓ.ም.

 

በ2007 ዓ.ም. በኅዳር ወር ውስጥ የአዲስ አበባና የዙሪያዋ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን ለውይይት ይፋ መሆኑን ተከትሎ፣ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ማስተር ፕላኑን በመቃወም የጀመሩት እንቅስቃሴ ወደ ኅብረተሰቡ ውስጥ ዘልቆ እንደገባ ይታወሳል፡፡ ለተወሰኑ ወራት የቀጠለው ተቃውሞ በፀጥታ ኃይሎች በአጭሩ ለመግታት በመቻሉ ገዥው ፓርቲና መንግሥት ዕፎይታን አገኙ፡፡ የተቃውሞው መነሻ የሆነው የአዲስ አበባና የዙሪያው የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን የአዲስ አበባ ይዞታ ወደ ኦሮሚያ ክልል ድንበሮች ለማስፋፋት ያቀደ ነው የሚለው የተማሪዎችና የክልሉ ነዋሪዎች ተቃውሞ፣ በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ውስጥ ቢወድቅም ጥያቄው ግን ሙሉ ምላሽን ወይም መግባባትን አላገኘም፡፡

በዚህ ጊዜያዊ መረጋጋት ፋታ ያገኙት ገዥው ፓርቲና መንግሥት አምስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በግንቦት ወር 2007 ዓ.ም. ውስጥ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲካሄድ አስቻላቸው፡፡ በውጤቱም ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ላለፉት ዓመታት የመንግሥትን ሥልጣን ከያዘበት ውጤት የተለየና መነጋገሪያ ያደረገውን መቶ በመቶ ውጤት ማግኘቱ ይፋ ሆነ፡፡ ገዥው ፓርቲ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 547 መቀመጫዎች በሙሉ ማሸነፋቸው በአገሪቱ ምርጫ ቦርድ ይፋ ሆነ፡፡

ገዥው ፓርቲ በውጤቱ ግራ የተጋባ ቢመስልም የሕዝብ ፍላጎት የተገለጸበት ትልቅ ኃላፊነት እንደሆነ በመቀበል አሥረኛውን አጠቃላይ ጉባዔውን በመቀሌ ከተማ ማካሄዱ ይታወሳል፡፡ የዚህ ጉባዔ ዋነኛ ማጠንጠኛም መልካም አስተዳደርን በማስፈን ሕዝቡ ለፓርቲው ያሸከመውን ትልቅ ኃላፊነት መወጣት ትልቁና ቀዳሚው ዕርምጃ መሆኑን ፓርቲው ይፋ አደረገ፡፡

2008 ዓ.ም.

ኢትዮጵያውያን 2008 ዓ.ም. በተቀበሉበት በመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት፣ ኢሕአዴግና አጋሮቹ በፓርላማው 547 ወንበሮች ላይ ተቀምጠው ለቀጣይ አምስት ዓመታት አገሪቱን የሚመራውን መንግሥት መሠረቱ፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሕልፈት ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሾሙት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለቀጣይ አምስት ዓመታት አገሪቱን እንዲያስተዳድሩ በድጋሚ ተሾሙ፡፡

በጥቅምት ወር መጀመሪያ ሳምንት ላይ የመንግሥትን የ2008 ዓ.ም. ዕቅድ ለመግለጽ በፓርላማ ተገኝተው የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ የዓመቱ ቁልፍ ተግባር እንደሚሆን አወጁ፡፡

ይህ የመልካም አስተዳደር አገር አቀፍ ንቅናቄ ከውጥን አልፎ መሬት ከመንካቱ በፊት፣ በኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. የኦሮሚያ ተቃውሞ በድጋሚ ፈነዳ፡፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን ጊንጪ ከተማ የምትገኝ አንድ ትምህርት ቤት ይዞታ ያለ አግባብ ለባሀብት ተሰጠ በሚል በተማሪዎች የተቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ የተዳፈነውን ‹‹የአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ መስፋፋት›› ጉዳይ በድጋሚ እንዲቀጣጠል አደረገ፡፡ ተቃውሞው ከሰላማዊ መንገድ በመውጣት ከመንግሥትና ከገዥው ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የንግድ ተቋማትንና የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ወደማውደም ተሸጋገረ፡፡ በርካታ የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት መዋቅር ቢሮዎች በተቃዋሚዎቹ እንዲወድሙ ተደረገ፡፡

በኦሮሚያ የተነሳው ተቃውሞ ከሰላማዊ መንገድ እንዲወጣ ያደረገው መንግሥት ለሕዝቡ ጥያቄ ወቅታዊ ምላሽ ባለመስጠቱ ነው የሚል ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞች ትችታቸውን በስፋት ሰነዘሩ፡፡

ተቃውሞው ወደ ግጭት ተቀይሮ የበርካቶችን ሕይወት ከቀጠፈ በኋላ፣ የኦሮሚያ ክልል የተቀናጀ ማስተር ፕላኑን  በሕዝብ ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን አሳወቀ፡፡

መንግሥት በራሱ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በግጭቱ የሞቱን ሰዎች በአጠቃላይ 173 መሆናቸውን ቢገልጽም፣ መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ሒውማን ራይትስ ዎች በኦሮሚያ ግጭት ከ400 በላይ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ይፋ አድርጓል፡፡ በዚሁ ተመሳሳይ ወቅት የቅማንት ሕዝብ የማንነት ጥያቄን የክልሉ መንግሥት በፍጥነት መመለስ ባለመቻሉ ወደ ግጭት አመራ፡፡ በዚህም የበርካታ ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡ በመንግሥት መረጃ መሠረት የ95 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በሁለቱም ክልሎች የተቀሰቀሱት ደም አፋሳሽ ግጭቶችና ተቃውሞዎች ከተረጋጉ በኋላ በአካባቢዎቹ መርማሪዎችን በመላክ መረጃ የሰበሰበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ፀጥታ ኃይሎች በአማራ ክልል ከመጠን በላይ ኃይል መጠቀማቸውን ሲገልጽ፣ በኦሮሚያ ግን ተመጣጣኝ ኃይል እንደተጠቀሙ ሪፖርት አደረገ፡፡ ነገር ግን ሪፖርቱን በርካቶች አልተቀበሉትም፡፡ አጠቃላይ የሪፖርቱ ይዘትም እስካሁን ለሕዝብ ይፋ አልሆነም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በመጋቢት ወር

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የመንግሥታቸውን የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በመጋቢት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ለፓርላማው ባቀረቡበት ወቅት ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተነሳው ግጭት መንስዔና ወዴት ሊያመራ እንደሚችል የተመለከተ ይገኝበታል፡፡

በሰጡት ምላሽም፣ ‹‹ጣታችንን በሌላ አካል ላይ ከመቀሰር ችግሩ የራሳችን እንደሆነ አስምረን መሄድ አለብን፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ባለፉት 12 ዓመታት የአገሪቱ አርሶ አደሮችም ሆነ የከተማ ነዋሪዎች ኢትዮጵያ ተስፋ ያላት አገር እንደሆነች ቢገነዘቡም፣ የሕዝቡን ጥያቄ በፍጥነት መንግሥትና ገዥው ፓርቲ መመለስ ባለመቻሉ ምክንያት ከሕዝብ ጋር ቅራኔ ውስጥ መግባታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

‹‹ይህ ቅራኔ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ወደ ግጭት አምርቷል፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ግጭት ስላለ ሌላ ቦታ ይኼ ግጭት የለም ማለት አይደለም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ከትግራይ ጀምሮ እስከ ደቡብ ጫፍ ይኼ ችግር ያውና ተመሳሳይ ነው፤›› በማለት የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

አገሪቱ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገቧ ምክንያት የአገሪቱ ሕዝቦች ዓይን መከፈቱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ እንዲቀጥል ኅብረተሰቡ እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ በሚፈልገው ፍጥነት ገዥው ፓርቲ መፍጠን ባለመቻሉ የተፈጠረው ቅራኔ እየተስፋፋ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

‹‹ከፊት ለፊት ደንቃራ ስንሆንበት ዞር በሉ ብሎ መግፋቱ አይቀርም፡፡ ዞር በሉ ሲል አንዳንዴ በእጁ ይላል አንዳንዴ በቃሉ ይላል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ አሁን በእጁ ነው ዞር በሉ ያለው፤›› ሲሉ ችግሩ ከመልካም አስተዳደርና ከኢኮኖሚ ጥያቄዎች ጋር የተገናኘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአማራ ከቅማንት ጋር በተገናኘ ለተፈጠረው ችግርም የክልሉ መንግሥት ጥያቄውን በፍጥነት ባለመመለሱ ወደ ግጭት እንዳመራ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ጥያቄው ሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ ሊመለስ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

የማንነት ጥያቄ ግጭት ሊያስከትል የሚገባ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ይህንን ጉድለት የክልሉ መንግሥትና ፓርቲ ተገንዝቦ ጥያቄው ዕውቅና እንዲያገኝ መደረጉን የተናገሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ከዚህ በኋላ ጥያቄው ከቀጠለ ሌላ ጉዳይ እንደሚሆን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ በማከልም በኢትዮጵያ ውስጥ የማንነት ጉዳይ በተሳሳተ መንገድ እየተተረጐመ እንጂ ያልተመለሰ የማንነት ጥያቄ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

በአንድ ብሔር ውስጥ የሚኖር ጐሳ ተነጥሎ ራሱን የቻለ ብሔር ይሁን የሚል የተሳሳተ ጥያቄ እየተነሳ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

‹‹ከአሁን በኋላ የማንነት ጥያቄ ተመልሶ አልቋል የሚል ምላሽ መሰጠት አለበት፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ሕዝቡን የባህል ልብስ እያስለበሱና እያሠለፉ የማንነት ጥያቄ የሚያነሱ ጥገኞችም ማረፍ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

ወልቃይት

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የማንነት ጥያቄ በኢትዮጵያ ተመልሶ አልቋል ቢሉም በትግራይ ክልል ከወልቃይት ማንነት ጋር የተያያዘ የወሰን ለውጥ ጥያቄውን ይዞ የተነሳው በዚያው ወር ውስጥ ነበር፡፡

የወልቃይት የማንነት ጉዳይ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ጥያቄውን ለትግራይ ክልል ምክር ቤት ሳያስገባ የጥያቄ አቀራረብ አካሄዱን በመዝለል ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርቧል፡፡ ነገር ግን ምክር ቤቱ የሰጠው ምላሽ በመጀመሪያ ለትግራይ ክልል እንዲቀርብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴው ከወልቃይት ማንነት ጋር የተያያዘ የወሰን ለውጥ ጥያቄ በሐምሌ ወር መጀመሪያ በሰሜን ጎንደር ጐዳናዎች ላይ ይዞ ወጥቷል፡፡   

ኮሚቴው ጥያቄውን በትግራይ ክልል ለማቅረብ ወይም ጥያቄውን በወልቃይት ጐዳናዎች ይዞ እንዳይወጣ፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ሊወስዱት የሚችሉት ዕርምጃን ምክንያት በማድረግ ወደ አጐራባች ሰሜን ጎንደር እንዲሄድ መገደዱን የሚገልጹ አሉ፡፡

በሰሜን ጎንደር እጅግ ሰፊ የሆነ ሕዝብ የወልቃይት ጥያቄን በማንሳት ሰላማዊ ሠልፎችን በሰላማዊ መንገድ አከናወነ፡፡

የአማራ ክልል መንግሥት ወልቃይትን የሚጠይቁ ሰላማዊ ሠልፎች የተካሄዱት በሕገወጥ መንገድ ነው ቢልም ሠልፉ ሰላማዊ በመሆኑ በማንም ላይ ዕርምጃ አልወሰደም፡፡ ነገር ግን የፌዴራል መንግሥት የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል የወልቃይት መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን በሽብር ወንጀል እንደሚፈልጋቸው በመግለጽ፣ በሰሜን ጎንደር አባላቱ የሚገኙበትን አካባቢ በመክበብ ለመያዝ ያደረገው እንቅስቃሴ ደም መፋሰስን ብሎም የሕይወት መጥፋትን አስከተለ፡፡

የፌዴራል መንግሥት የወልቃይትን ጥያቄ ለማፈን አይደለም ቢልም ተዓማኒነትን ማግኘት አልቻለም፡፡

ከዚህ በኋላ የወልቃይት ጉዳይ መነሻ እንጂ የተቃውሞው መስፋፋት ምክንያት አልሆነም፡፡

ከሰሜን ጎንደር ወደ ባህር ዳርና የተያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ተንሰራፋ፡፡ የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ የንብረት ማውደም እንቅስቃሴም የተቃውሞው መገለጫ ሆነ፡፡  

በአማራ ክልል በተደረጉ ሠልፎች ላይም የኦሮሞ ሕዝብ መብት እንዲከበር የሚጠይቁ መፈክሮች ተስተጋቡ፡፡

በሰላማዊ ሠልፍ የተጀመው ተቃውሞ በቤት ውስጥ መቀመጥ ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው ባለሀብቶችንና የሕዝብ መገልገያዎችን በማውደም ከመስፋፋቱ በተጨማሪ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ተቃውሞ ዳግም እንዲነሳ አድርጓል፡፡ በመሆኑም የአገሪቱን አጠቃላይ ሕዝብ 60 በመቶ በሚወክሉት ሁለቱ ክልሎች የተነሳው ተቃውሞ ተመሳሳይ የተቃውሞ ቴክኒክ በመጠቀም፣ አንዴ በሰላማዊ ሠልፍ አንዴ በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ አገልግሎት በማቋረጥና መንገድ በመዝጋት የፖለቲካ ሥርዓቱን አጣብቂኝ ውስጥ ከተውታል፡፡

በእነዚህ ተቃውሞዎች መሀል በየካቲት ወር መጨረሻ በአዲስ አበባ ለአንድ ቀን የታክሲዎች የሥራ ማቆም አድማ መደረጉ አይዘነጋም፡፡  በከተማዋ አዲስ የትራፊክ ሥነ ሥርዓት ደንብ ተግባራዊ መደረጉን በመቃወም ነበር የታክሲ አሽከርካሪዎች የሥራ ማቆም አድማውን ያካሄዱት፡፡

ይህ ክስተት ገዥውን ፓርቲና መንግሥትን የበለጠ አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ በመሆኑ፣ የትራፊክ ሥነ ሥርዓት ደንቡ በአስቸኳይ እንዲነሳ በመደረጉ በተለያዩ ክልሎች የተነሳው ተቃውሞ አዲስ አበባን መያዝ አልቻለም፡፡ የተለያዩ የሠልፍ ጥሪዎች ለአዲስ አበባ ቢተላለፉም ውጤታማ አልነበሩም፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች እየተቀጣጠሉ ያሉት ተቃውሞዎች ማንነት ተኮር በመሆናቸው አዲስ አበባን መያዝ እንዳልቻሉ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

ይህንን ትንታኔ የማይቀበሉት ደግሞ የፀጥታ ኃይሉ የአዲስ አበባ ሕዝብ እንዳይነሳ በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ መሆኑን በምክንያትነት ያነሳሉ፡፡

ኢሕአዴግ

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ አሁን ያለውን ሁኔታ በቀድሞው ዕይታው እየተመለከተ ይገኛል፡፡ በነሐሴ ወር መገባደጃ አካባቢ የተሰበሰበው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም ማዕከላዊ ኮሚቴው ተቃውሞውን ከመልካም አስተዳደርና ከኢኮኖሚ ጥያቄ ጋር አሁንም አያይዞታል፡፡

ሥልጣንን ለግል ጥቅም መገልገያ የሚል አዲስ አገላለጽ ከመጨመሩ ውጪ፣ ለሕዝብ የተገለጸው ግምገማ ተመሳሳይ ይዘት ያለው ነው፡፡

በ2007 ዓ.ም. በኦሮሚያ የተጀመረው ተቃውሞ በ2008 ዓመቱን ሙሉ ተቀጣጥሎና ከአማራ የሕዝብ ተቃውሞ ጋር አብሮ 2009 ዓ.ም. እየተቀበለ ይገኛል፡፡

አዲሱ 2009 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ምን ይዞ ይመጣል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፡፡

     

Standard (Image)

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንትና የቀድሞ ምክትላቸው ከጦርነት አትራፊ መሆናቸው በሪፖርት ይፋ ሆነ

$
0
0

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና የቀድሞ ምክትላቸው ዶ/ር ሪክ ማቻር ከሥልጣን ጋር በተያያዘ ምክንያት ከተጋጩ፣ ግጭቱም ብሔርን መሠረት ካደረገ ሁለት ዓመት አልፎታል፡፡

በዚህ ከሁለት ዓመት በላይ በተደረገው ውጊያ በአሥር ሺሕ የሚቆጠር ሰላማዊ ሕዝብ አልቋል፡፡ ሚሊዮኖች ቆስለዋል፣ ተገርፈዋል፣ ተደፍረዋል እንዲሁም ተርበዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተሰደዋል፡፡ በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሀብት፣ ንብረትና የሰብል ውድመት እንደደረሰም በተለያዩ ወቅት የወጡ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡

አገሪቱ ከገባችበት ቀውስ ትወጣ ዘንድ የአካባቢው አገሮች፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የመሩዋቸው በርካታ ድርድሮችና ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ የውይይቶቹ ውጤቶች ግን ፍሬ ያፈሩ አይደሉም፡፡

ከበርካታ ወራት ድርድር በኋላ ወደ ርዕሰ መዲናዋ ጁባ ተመልሰው የምክትል ፕሬዚዳንትነት ሥልጣኑን ዳግም ይዘው የነበሩት ዶ/ር ሪክ ማቻር ዳግም አገሪቷን ለቀው ወጥተዋል፡፡ በምትካቸውም ጄኔራል ታባን ዴንግ የምክትል ፕሬዚዳንትነት መንበሩን ተቆናጠዋል፡፡

በመከራዎችና በሕዝቡ እንግልት የተሞላችው ደቡብ ሱዳን ካላት ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ ክምችትና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብት አንፃር፣ የመሪዎቿ መከፋፈልና አለመስማማት ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በቅጡ እንዳትጠቀም አድርጓታል፡፡

ምንም እንኳን አብዛኛው የአገሪቱ ዜጋ ከአገሪቱ የተፈጥሮ ሀብትና ነዳጅ ከሚገኘው ጥቅም ተጠቃሚና ተቋዳሽ ባይሆንም፣ መሪዎቹ ለግል ጥቅማቸው የአገሪቷን ሀብት እንዳዋሉ የሚጠቅሱ በርካታ ሪፖርቶች ወጥተዋል፡፡

በታዋቂው አሜሪካዊ የፊልም ባለሙያ ጆርጁ ክሉኒና አጋሮቹ ድጋፍ የተከናወነ የጥናት ሪፖርት በዚህ ሳምንት ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ በሪፖርቱም የአገሪቱ ፕሬዚዳንትና የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት የጦርነቱ ዋነኛ ተጠቃሚ እንደሆኑ ይፋ አድርጓል፡፡

‹‹ምንም እንኳን አገሪቷና ዜጐቿ እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ተጐጂዎችና የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሾች ቢሆኑም፣ የደቡብ ሱዳን የፖለቲካና የመከላከያ ልሂቃን ግን በጦርነቱ ራሳቸውን ሀብታም አድርገዋል፤›› ይላል ሪፖርቱ፡፡

ጆርጅ ክሉኒ በጋራ በመሠረተው ዘ ሴንቸሪ በተሰኘ የምርመራ ቡድን የተከናወነው ጥናት ለሁለት ዓመታት ያህል የተካሄደ ሲሆን፣ በርካታ ማስረጃዎችንና የምስክርነት ቃል መሰብሰቡን ገልጿል፡፡

ሪፖርቱ ከወጣ በኋላ በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ተቆርቋሪ እንደሆነ የሚነገርለት ጆርጅ ክሉኒ፣ ‹‹ማስረጃዎቹ የተብራሩና ሊካዱ የማይችሉ ናቸው፤›› በማለት የሪፖርቱን ጥንካሬ ገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በዚህ ዓመታት በፈጀው ጦርነት ተጠቃሚ የሆኑት የአገሪቷ መሪዎች በሕገወጥ መንገድ ሀብት ለማጋበስ በሚያደርጉት ጥረት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ባንኮች፣ ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች፣ እንዲሁም የሪል ስቴት ተቋማት ተሳትፎ እንደነበራቸውም ጆርጅ ክሉኒ አስረድቷል፡፡

መሪዎቿ ከአገሪቷ የመዘበሩትን ገንዘብ ተከታዮቻቸውን ለማስታጠቅ እንደሚጠቀሙበትም ተመልክቷል፡፡ ‹‹ከአሁኑ ዕርምጃ መውሰድ አለብን፡፡ ይህን ካላደረግን በመጪዎቹ አሠርት ዓመታት የሚፈጠረውን ችግር ማዳፈን ላይ እንሠራለን፤›› በማለት ክሉኒ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

የሪፖርቱ ግኝቶች

“War Crimes Shouldn’t Pay” በሚል ርዕስ ይፋ የተደረገው ሪፖርት የአገሪቷ መሪዎችና የጦር ጄኔራሎች በአገሪቷ ለተፈጠረው የሕዝብ ዕልቂትና ውድቀት ተጠያቂ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ ከሚያገኙት መካከለኛ የመንግሥት ደመወዝ አንፃር ከፍተኛ የሆነ ሀብት ከአገሪቷ ጦርነት በትርፍ አጋብሰዋል በማለት ይኮንናል፡፡

የአገሪቷ የፖለቲካና የመከላከያ ልሂቃን ከእርስ በርሱ ጦርነት ተጠቃሚ የሆኑት የተወሰኑት ራሳቸው ከፍተኛ የንግድ ድርድር ውስጥ በመግባት በንግድ በመሰማራት ሲሆን፣ የተወሰኑት ደግሞ መቀመጫቸውን ደቡብ ሱዳን ካደረጉና የተለያዩ ሥራዎችን ከሚሠሩ ኩባንያዎች በሚፈጸምላቸው ክፍያ አማካይነት እንደሆነ ሪፖርቱ ይፋ ያደርጋል፡፡

ሥልጣናቸውን መከታ አድርገው የአገሪቱን ሀብት እየዘረፉ ነው የሚለው ሪፖርቱ፣ የአገሪቷን ከፍተኛ የሆነ ሀብት ለመቆጣጠርና ለግል ጥቅም ለማዋል የሚደረገው ሽኩቻ የአገሪቷን የእርስ በርስ ጦርነት ለማፋፋም ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሆነም ይገልጻል፡፡

ከፍተኛ የሆነ የሀብት ትስስር (ኔትወርክ) እንደተፈጠረ የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ ሁለቱ ተቃራኒ መሪዎች ከጀርባቸው የብሔር ማንነትን መጠጊያ በማድረግና የጦር ነጋሪት በመጐሰም ለሥርዓቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የጦር ጄኔራሎች የገቢ ምንጭ አድርገውታል በማለት ይፋ አድርጓል፡፡

አብዛኛዎቹ የባለሥልጣናቱ ሀብቶች ምንጭ በውጭ አገር የሚገኙ ውድ ዋጋ የሚያወጡ ንብረቶች፣ የግልና የመንግሥት ንብረት የሆኑ በርካታ ተቋማትን በባለቤትነት መያዝና ከነዳጅ ሽያጭ ውል የሚገኙ እንደሆነ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና የዶ/ር ሪክ ማቻር ቤተሰቦች የሚኖሩት ከደቡብ ሱዳን ውጪ እንደሆነ በመግለጽ፣ ሁለቱ ተፃራሪ ወገኖች በኬንያ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ አፕማርኬት በተባለ የመኖሪያ ሠፈር ውስጥ የሚኖሩበት ቅንጡ የመኖሪያ ቤቶች እንዳሉዋቸው ያትታል፡፡    

የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የ12 ዓመት ወንድ ልጅ በአንድ የአክሲዮን ድርጅት ውስጥ የ25 በመቶ ድርሻ እንዳለው፣ ሌሎች ሰባት የፕሬዚዳንቱ ልጆችና ባለቤታቸው ቀዳማዊ እመቤት ሜሪ አየን ማያርዲት በበርካታ ዘርፎች የንግድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንደሚሳተፉና ጠቀም ያለ ድርሻ እንዳላቸው ይኼው ሪፖርት ይገልጻል፡፡

ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች ይህን ሥልጣንን መሠረት ያደረገውን የአገሪቷን ሀብትና ንብረት መቀራመት ሥርዓት በማደራጀት መሳተፋቸው በሪፖርቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ሌሎቹ ዓለም አቀፍ ተዋናዮችም እየተካሄደ ካለው የደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ግጭት ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ይፋ አድርጓል፡፡

‹‹ጥቂት ግለሰቦች የደቡብ ሱዳንን ኢኮኖሚ ተቆጣጥረውት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ጥቂት ሰዎች ደግሞ በአገሪቷ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እየተሳተፉ የሚገኙና ዋነኛ ተዋናዮች ናቸው፤›› በማለት የሪፖርቱ ጸሐፊ ጅንየር ማይሌይ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሪክ ማቻር በሩሲያ ደላሎች አማካይነት ከዩክሬን መሣሪያ አምራቾች ጋር መደራደራቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡

‹‹ከዶ/ር ሪክ ማቻር ጋር በተያያዘ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ነዳጅ በመሸጥ መሣሪያ ለመግዛት ተደራድረዋል፤›› በማለት ጸሐፊው ይፋ አድርገዋል፡፡

በሪፖርቱ ከተካተቱት ዝርዝር ማስረጃዎች ውስጥ ከሚገኙ ፎቶግራፎች ውስጥ የፖለቲከኞቹና የጄኔራሎቹ መኖሪያዎች እንደሆኑ የሚያሳዩ በኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በኡጋንዳና በአውስትራሊያ የሚገኙ ቅንጡ ቪላዎች ይገኛሉ፡፡

የአገሮቹ መሪዎችና የጦር ጄኔራሎች የአገሪቷን ሀብትና ንብረት ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው በተደጋጋሚ እየተገለጸ ባለበት ወቅት፣ በተመድ የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) አገሪቷ ለአስከፊ የምግብ እጥረት የተጋለጠች መሆኗን አስታውቋል፡፡

እንደ ድርጅቱ አኃዝ ከሆነ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ አምስት ሚሊዮን ዜጐች ለከፋ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ካልተረጋጋና ግጭቶች የሚቀጥሉ ከሆነ ለምግብ እጥረት የሚጋለጡ ዜጐች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡

በእንቅርት ላይ … እንዲሉ በአገሪቱ ዳግም በተቀሰቀሰው ጦርነት በመንግሥትና በተቃዋሚዎች መካከል በተከሰተው ግጭት በግምት 30 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የዕርዳታ እህል፣ ከሁለት የተመድ ተቋማት መዘረፉን ድርጅቱ በተጨማሪ አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከ12,000 በላይ የሰላም አስከባሪ ኃይል በደቡብ ሱዳን የተሰማራ ሲሆን፣ በቅርቡ ዳግም ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ተመድ ተጨማሪ 4,000 ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲሰማራ ወስኗል፡፡

ምንም እንኳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር መጀመሪያ ላይ ውሳኔው ሉዓላዊነትን መጣስ ነው በማለት ተጨማሪ ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ደቡብ ሱዳን እንደማይገባ ተቃውመው የነበሩ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ግን ስምምነታቸውን በመግለጻቸው ተጨማሪ 4,000 ሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ አገሪቱ እንደሚገባ መተማመኛ ተገኝቷል፡፡

ተመድ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው በአገሪቱ ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት እያደረሰ ካለውና ሊያደርስ ከሚችለው የከፋ ቀውስ ለመታደግ እንደሆነ አስታውቋል፡፡       

Standard (Image)

የኢሕአዴግ የማሻሻያ ሐሳቦች ዘላቂነት

$
0
0

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ዜጎቿንም ሆነ አጋር ምዕራባውያን አገሮችን እያስጨነቀ ይገኛል፡፡ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን ያነገቡ ኢትዮጵያውያን ከሰሜን እስከ ደቡብ ጥያቄያቸውን ይዘው አደባባይ ወጥተዋል፡፡ ኢሕአዴግ ወደዚህ አጣብቂኝ ውስጥ እንዴት ገባ? የሕዝብ ተቃውሞ ገዢውን ፓርቲ ኢሕአዴግ ወዴት እየገፋው ነው? ከዚህ ለመውጣት መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ያሰቧቸው የለውጥ ዕቅዶችስ ምን ያህል ያዋጣሉ?

ምርጫ 97 እና 2002 እንደ መነሻ

      በ1983 ዓ.ም. የተፈጠረውን የሥርዓት ለውጥ ተከትሎ የመንግሥት ሥልጣንን በሕዝብ ምርጫ ለማግኘት ላለፉት 20 ዓመታት ከተካሄዱት አምስት ጠቅላላ ምርጫዎች፣ በ1997 ዓ.ም. የተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በአንፃራዊነት የተሻለ እንደነበር የውጭ ታዛቢዎችና በፖለቲካ ፉክክሩ ያለፉ ይመሰክሩለታል፡፡ ከምንጊዜውም የተሻለ የፖለቲካ ምኅዳር፣ ግልጽና የቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ያገኘ የፖለቲካ ክርክር፣ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ የሲቪክ ማኅበራት የመራጩን ንቃተ ህሊና በማጎልበት ረገድ በነፃነት ሚናቸውን የተጫወቱበት፣ እንዲሁም በገዢው ፓርቲ በኩልም አንፃራዊ ዴሞክራሲያዊነት የታየበት እንደነበር ያለ ልዩነት በርካቶች ይስማሙበታል፡፡

በምርጫው ውድድር የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተበታትነው የሕዝብ ድምፅን እንዲበታተን ከማድረግ ይልቅ፣ በጥምረት በመሳተፋቸው ከአሥር ዓመት በላይ ሥልጣን ላይ የቆየውን ገዢውን ፓርቲ ኢሕአዴግን አጣብቂኝ ውስጥ የከተቱበት ወቅት ነበር፡፡ ምርጫውን በሚያስፈጽመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በይፋ የተገለጸው ውጤት በጥምረት ገዢውን ፓርቲ የተወዳደሩት ተቃዋሚዎች አስገራሚ ውጤት ለመጀመሪያ ጊዜ ቢያገኙም፣ ፓርቲዎቹ እርግጠኛ በነበሩበት ውጤትና በይፋ በተገለጸው ውጤት መካከል የነበረውን ሰፊ ልዩነት ለመቀበል በመቸገራቸው ከውጤቱ በኋላ መንግሥት በወሰዳቸው አንዳንድ ጤነኛ በማይመስሉ ዕርምጃዎች ምክንያት ፓርላማውን እንደማይቀላቀሉ መግለጻቸው ነገሮችን ሙሉ በሙሉ ቀያይሯል፡፡

የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓቱ እንደተጠናቀቀ የቀድሞ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሰላማዊ ሠልፍና ስብሰባ ማድረግ ለአንድ ወር መከልከሉን ገለጹ፡፡ በአዲስ አበባ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ዕዝ ተቋቋመ፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት ላይ ወከባና ጫና ስለመድረሱ ሪፖርቶች መውጣት ጀመሩ፡፡ በወቅቱ አዲስ አበባ ላይ ሙሉ በሙሉ ያሸነፈው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ አዲስ አበባን መረከብ አለመረከቡ ሳይታወቅ፣ በአዲስ አበባ ሥር የነበሩ አንዳንድ ቢሮዎች ተጠሪነት ወደ ፌዴራል መንግሥት እንዲዘዋወሩ ተደረገ፡፡

በሕገ መንግሥቱ ላይ በተደነገገው መሠረት ኦሮሚያ አዲስ አበባ ላይ ያላት ልዩ ጥቅም በሕግ እንዲወሰን እንቅስቃሴዎች ተጀመሩ፡፡ በመቀጠልም ሕዝቡን ለአመፅ አነሳስተዋል እንዲሁም ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል በሚል ክስ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ለእስር ተዳረጉ፡፡

ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ መንግሥት መሥርቶ ሥልጣኑን ካረጋጋ በኋላም ቢሆን፣ ቀድሞ የፈቀደውን ዴሞክራሲ ያህል መክፈት እንዳልቻለ ይተቻል፡፡ የአባላት ቁጥሩን በአንድ ጊዜ በአራት ሚሊዮን እንዲጨምር በማድረግ የአንድ ለአምስት አደረጃጀትን ለፖለቲካና ማኅበራዊ ፋይዳዎች መጠቀም ጀመረ፡፡ የምርጫ አዋጁ ማሻሻያ አሁንም የምርጫ ቦርድን ገለልተኝነት ማስጠበቅ አልቻለም በሚል ትችት ተጠናክሮ ቀረበበት፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ በአገሪቱ የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ጉልህ ሚና የነበራቸውን ሲቪክ ማኅበራት አንኮታኮተ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለፉት አምስት ዓመታት ተጠናቀው ምርጫ 2002 ዓ.ም. ገባ፡፡ በዚህ ወቅት የተሻለ ተፅዕኖ የነበረው አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ የተባለው ፓርቲ ቢሆንም፣ የፓርቲው አመራር የነበሩት ወይዘሮ ብርቱካን ሚደቅሳ ቀደም ሲል የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በይቅርታ የተለቀቁበትን ሥርዓት ‹‹ይቅርታ አላልኩም ብለው ክደዋል›› በሚል ክስ በድጋሚ ወደ ወህኒ ተወረወሩ፡፡ ይህም በውጤቱ አንድነት ፓርቲ መሠረቱ እንዲፈራርስ እንዳደረገው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የተካሄደው የ2002 ዓ.ም. ምርጫን ኢሕአዴግ ከሁለት ወንበሮች ውጪ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረው፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ የምርጫ 97 አጣብቂኝ ውስጥ እንዳይገባ እንጂ ምርጫ 2002 በዚህ ሁኔታ የማሸነፍ ዕቅድ እንዳልነበረው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሕአዴግ የንድፈ ሐሳብ መጽሔት ዋና አዘጋጅ እንደነበሩ በሚነገርላቸው አቶ መለስ ዜናዊ እንደጻፉት የሚታመነው ጽሑፍ፣ ምርጫ 2002 ትልቅ ድል የተገኘበት እንደሆነ ይከራከራል፡፡ በአዲስ ራዕይ መጽሔት ላይ የታተመው ይኼው ትንታኔ በርካታ ሌሎች ነጥቦችንም ይዳስሳል፡፡

በምርጫ 2002 የተገኙት ድሎች ሁለት መሆናቸውን ይኼው ጽሑፍ ይገልጻል፡፡ አንደኛው በጥላቻና ቂም በቀል የተመሠረቱና ይህንኑ የሚያራምዱ ፓርቲዎች ለሕገ መንግሥቱ አደጋ የማይሆኑበት ደረጃ ላይ መድረሳቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል የአውራ ፓርቲ ሥርዓትን አገሪቱ ውስጥ የፈጠረ በመሆኑ የተረጋጋ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አገሪቱ ውስጥ ለመፍጠር ምቹ ሁኔታን እንዳበጀ ይተነትናል፡፡

ኢሕአዴግ ለአራት ተከታታይ ጊዜያት በምርጫ እንዳሸነፈ የሚያስታውሰው ይኼው ጽሑፍ፣ ኢሕአዴግ በምርጫ 2002 አስገራሚ ድል ያስገኙለትን መሠረታዊ ባህሪዎችን ጠብቆ ከቀጠለ የሚቀጥሉትን አንድ ሁለት ምርጫዎች ምናልባትም ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ ሊያሸንፍ እንደሚችል ይተነብያል፡፡ ስለሆነም በተግባር በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለው ሥርዓት በስዊድንና በጃፓን ታይቶ እንደነበረው ዓይነት የአውራ ፓርቲ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ነው ብሎ መከራከር እንደሚቻል ይጠቅሳል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ኢሕአዴግ በምርጫ 2002 አስገራሚ ድል ቢያገኝም፣ ይህንን ድል ያረጋገጠበትን ጠንካራ ጎኖች ካጣ በሚቀጥለውም ምርጫ ሊዘረር እንደሚችል ጽሑፉ ያስረዳል፡፡ ‹‹ይልቁንም እነዚህን ጠንካራ ባህሪያቱን ካጣ ሕዝቡ አንቅሮ የተፋቸው ፀረ ሕገ መንግሥት ፓርቲዎች ሳይቀሩ ሊያንሠራሩና የምርጫ 97 ሁኔታ ሊደገም ይችላል፤›› ሲልም ያክላል፡፡ ከዚህም ባሻገር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከውድቀታቸው ተምረው ጉድለቶቻቸውን አስተካክለው ከመጡ፣ በአጭር ጊዜ ተጠናክረው ኢሕአዴግን ሊያሸንፉት ይችላሉ ብሎ መከራከር እንደሚቻልም በትንታኔው ተመልክቷል፡፡

ሁለቱም መከራከሪያዎች ጠንካራ ጎን እንዳላቸው የሚጠቅሰው ይህ ጽሑፍ ዞሮ ዞሮ ልዩነቱ የሚያጠነጥነው በሁለት ጉዳዮች ላይ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ጠንካራ ጎኖቹን ጠብቆ ማቆየት ይችላል ወይስ አይችልም በሚለው ጉዳይ ላይና ተቃዋሚዎች ራሳቸውን ከጥላቻና ከቂም በቀል ፖለቲካ ነፃ አውጥተው በምን ያህል ፍጥነት ተጠናክረው ይወጣሉ በሚለው ጉዳይ ላይ ነው ልዩነቱ፤›› የሚለው ይኼው ጽሑፍ፣ ‹‹ሁለቱም አስተያየቶች ስለመጪው ሁኔታ መላምት የሚያስቀምጡ ስለሆኑ ወደፊት የሚሆነውን ማንም ሰው በእርግጠኝነት ማወቅና ያ ነው ትክክል ያ ደግሞ ስህተት ነው ማለት አስቸጋሪ ይሆናል፤›› በማለት ይገልጻል፡፡ የሚኖረው አማራጭ እስካሁን ድረስ ያሉት አዝማሚያዎች ላይ በመመሥረት የተሻለ የሚመስለውን መላምት ማስቀመጥ የሚበጅ መሆኑን በማስረገጥ አዝማሚያዎቹን ወደ መገምገም ይሻገራል፡፡

‹‹ከዚህ በመነሳት ስንገመግመው ምንም እንኳን ኢሕአዴግ ጠንካራ ጎኖቹን ጠብቆ እንዲቀጥል ምንም ዓይነት ዋስትና የሌለው ቢሆንም፣ አዝማሚያው ባህሪውን ጠብቆ ለመቀጠልና ይበልጥም ለማጠናከር ከፍተኛ ትግል እንደሚያካሂድ የሚያመለክት ነው፡፡ ስለሆነም ኢሕአዴግ በአጭር ጊዜ ውስጥ አሁን ሊገመት በማይችል መልኩ ይበላሻል ብሎ ከመተንበይ ይልቅ፣ በተፃራሪ ረዘም ላለ ጊዜ ባህሪውን እንደጠበቀ ይቆያል ብሎ መተንበይ ይበልጥ አሳማኝ ይሆናል፤›› በማለት ጽሑፉ ይደመድማል፡፡ በተመሳሳይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ከጥላቻና ከቂም በቀል ፖለቲካ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ አፅድተው ኢሕአዴግ የሕዝብ ይሁንታ ያገኘባቸውን መስመሮችና ስትራቴጂዎች የራሳቸው አድርገው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናክረው፣ ከኢሕአዴግ ከራሱ የበለጡ ኢሕአዴጎች ሆነው ይወጣሉ ብሎ ከመተንበይ ይልቅ ይህ ሒደት በተነፃፃሪ ረዘም ያለ ጊዜ ይጠይቃል ብሎ መተንበይ ይበልጥ አሳማኝ እንደሚሆን በአዝማሚያ ትንተና የደረሰበት ሁለተኛው ነጥብ ነው፡፡ ‹‹በመሆኑም ኢሕአዴግ በቀጣዮቹ የተወሰኑ ምርጫዎችም አሸናፊ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው ማለት ይቻላል፤›› በማለት የወደፊት ሁኔታዎችን ለመመልከት ሞክሯል፡፡

ምርጫ 2007ን ተከትሎ

ከምርጫ 2002 በኋላም ቢሆን ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ የቀጣይ ዓመታት ሥልጣኑንና የልማታዊ ዴሞክራሲን እንጂ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ፍላጎት የማረጋገጥ ፍላጎት እንደሌለው ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በተለያዩ ጊዜያት ገልጸዋል፡፡ ለዚህ የሚሰጡት ምክንያትም በርካታ ጋዜጠኞች ሥራቸውን በመሥራታቸው ብቻ በፀረ ሽብር ሕጉ አዋጅ ወደ ወህኒ ቤት መወርወራቸውን፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይም የወጣቶች ስብሰብ እንደሆነ የሚነገርለት ሰማያዊ ፓርቲ በኢትዮጵያ በየትኛውም አካባቢ በነፃነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻሉ በተለያዩ ሁኔታዎች ተገልጿል፡፡

በዚህ ሁኔታ የተካሄደው ምርጫ 2007 በዓለም የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አስገራሚ ሊሆን የሚችለውን የመቶ በመቶ ድል አስመዘገበ፡፡ ኢሕአዴግ 547 መቀጫዎች ያሉትን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአጋሮቹ ጋር በመሆን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ፡፡ ይሁን እንጂ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ በ2007 ምርጫ ያገኘውን ውጤት ይዞ መንግሥት ቢመሠርትም በወሩ በኦሮሚያ ክልል በርካታ አካባቢዎች የሕዝብ ተቃውሞ ገነፈለ፡፡ የዚህ ተቃውሞ መነሻ የአዲስ አበባና የዙሪያዋ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን አዲስ አበባን ወደ ኦሮሚያ የማስፋፋት ውጥን አለው በሚል የተቀሰቀሰ ነው፡፡ ተቃውሞው ወደ ደም መፋሰስ ሲያመራና የበርካቶችን ሕይወት ሲቀጥፍ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ማስተር ፕላኑን መሰረዙን ገለጸ፡፡ ሁኔታዎች ለተወሰነ ጊዜ በረድ ያሉ ቢመስልም በአማራ ክልል ከወልቃይት የወሰን ጥያቄ ጋር ተያይዞ ከተነሳው ተቃውሞ ጋር ተገናኝቶ የኦሮሚያ ተቃውሞው ዳግም ፈነዳ፡፡

በአሁኑ ወቅት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ በደቡብ ክልል የኮንሶ ሕዝብ ከሰገን ሕዝብ በመነጠል ራሱን ችሎ የመተዳደር ጥያቄ አንስቷል፡፡ በመሆኑም አገሪቱ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ዓይታ የማታውቀው ቀውስ ውስጥ ገብታለች፡፡ የተቃውሞ መነሻ የሆኑ ምክንያቶች እየጠፉ የኢሕአዴግ አገዛዝ ‹‹በቃኝ›› ወደሚል ጥያቄ ተሸጋግሯል፡፡

የሕዝብ ተቃውሞ ኢሕአዴግን ወዴት እየገፋ ነው?

ከላይ የተገለጸውና አቶ መለስ ዜናዊ እንደጻፉት የሚታመነው ጽሑፍ በ2002 ዓ.ም. ምርጫ ውጤት ማግሥት የተጻፈ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የአውራ ፓርቲ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት እየተመሠረተ መሆኑንና ይህም ለተተኪ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት ምቹ ሁኔታን እንዳበጀ ገምቷል፡፡ ኢሕአዴግ በወቅቱ የነበሩትን ጥንካሬዎችን ይዞ ሊቀጥል የሚችል እንደሆነ ከአዝማሚያዎች በመነሳት የደመደመው ይህ ጽሑፍ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ከጉድለታቸው ተምረውና ከቂም በቀል ፖለቲካ ፀድተው ኢሕአዴግን ይጥሉታል የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ እንደሚሆን በመጠቆም፣ ኢሕአዴግ ረዘም ላለ ጊዜ ሥልጣን ላይ እንደሚቆይ አዝማሚያን መሠረት ያደረገ ድምዳሜ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ትንታኔ በሕዝብ ውስጥ ያለን አዝማሚያ መመልከት እንዳልቻለ መረዳት ይቻላል፡፡

በዚህ ወቅት ከሰሜን እስከ ደቡብ በተቀጣጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ የተፈተነው ኢሕአዴግና የኢሕአዴግ መንግሥት የተቃውሞው መነሻ ምክንያትና ተገቢ ናቸው ያላቸውን ምላሾች መመለስ ጀምሯል፡፡ በኢሕአዴግ ትንተኔ መሠረት የተቃውሞው መነሻ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ እንዲሁም አመራሩ ሥልጣንን ለግል ጥቅምና ብልፅግና ማዋል የሚሉት ምክንያቶች ናቸው፡፡

ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር ተይዞ የተነሳውን የወሰን ለውጥ ጥያቄም የአማራና የትግራይ ክልል አመራሮች በወቅቱ መመለስ ባለመቻላቸው የፈነዳ እንደሆነ የፓርቲው ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ገልጸዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያነጣጠረ ማሻሻያ እንደሚያደርግም በይፋ አስታውቋል፡፡ አንደኛው የአገሪቱን የምርጫ ሕግ ማሻሻል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከገዢው ፓርቲ ነፃ የሆኑ ልሂቃን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ ነው፡፡ ሦስተኛ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላትን ጥቅም መመለስ ነው፡፡

እንደሚሻሻሉ የተገለጹት ነጥቦች ከምርጫ 97 በኋላ ፓርቲው ከመጣበት መንገድ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ የምርጫ ሕጉ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ ማሻሻያ የተደረገለት ሲሆን፣ በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ 30 የሚሆኑ የማሻሻያ ሐሳቦችን አቅርቦ ነበረ፡፡ መሠረታዊ የመሻሻያ ነጥቦቹ የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነትን ጨምሮ ቢያቀርቡም ተቀባይነትን አላገኙም፡፡ የምርጫ 97 ውጤት አዲስ አበባ ላይ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ሙሉ በሙሉ ማሸነፉን ተከትሎ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላት ልዩ ጥቅምን የመመለስ ጥያቄ በሕግ ለመመለስ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ለአሥር ዓመታት አዳፍኖ የቆየው ገዢው ፓርቲ፣ አሁን ጥያቄውን ለመመለስ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡

በተጨማሪም የመንግሥት መዋቅሮች የግድ በኢሕአዴግ ፖለቲከኞች ብቻ መሞላት የለባቸውም የሚሉ የተቃዋሚዎችም ሆነ የምሁራን ምክርን ወደ ጎን ሲል እስከ መጋቢት 2008 ዓ.ም. ድረስ ቆይቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በመጋቢት ወር 2008 ዓ.ም. በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምሁራን ጋር ባደረጉት ውይይት ይኸው ጥያቄ ተነስቶላቸው፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ዝግጁ አይደለንም፤›› የሚል ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ተንታኞችም ኢሕአዴግ ከምርጫ 97 በኋላ የመጣበትን የተበላሸ መንገድ እያረመ ይመስላል ብለዋል፡፡

ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኝና የቀድሞው የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ፣ ለመለወጥ መሞከር ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አሁን ላለው ተቃውሞ ምን ፋይዳ አለው? የሕዝቡ ጥያቄ ምንድነው? በሚለው ላይ መግባባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

‹‹በአገሪቱ ላለው ችግር ራሳቸው ትርጉም ሰጥተው መልሱንም ራሳቸው ለመመለስ እየሞከሩ ነው፤›› የሚሉት አቶ ሙሼ፣ ‹‹በዚህ መንገድ ፋታ ሊገኝ ቢችል እንኳ እንደገና እንደማይገነፍል ማረጋገጫ የለም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ወደ መንግሥት መዋቅር ይገባሉ የሚባሉት ከፖለቲካ ነፃ የሆኑ ግለሰቦች እነማን ናቸው?›› ብለው የሚጠይቁት አቶ ሙሼ፣ ምርጫ 97ን ተከትሎ ኢሕአዴግ ያቋቋመው ባለአደራ አስተዳደር ውስጥ እነማን እንደተካተቱ ይታወቃል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሌላው የገቨርናንስና ዴቨሎፕመንት መምህር በበኩላቸው፣ የችግሩ ምንጭ ይኼ ነው ብሎ አንጥሮ መለየት እንደሚያስፈልግ በተመሳሳይ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በእኔ እምነት በዚህ መንገድ የሚገለሉ የገዢው ፓርቲ ልሂቃንን ያስቆጣል፡፡ በቡድን ተደራጅተው ሥርዓቱን ወደ መገዝገዝ እንዳይገቡ ሥጋት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

የምርጫ ሕጉን ማሻሻል ጥሩ ቢሆንም አሁን ላለው ተቃውሞ መፍትሔ ይሆናል ብለው እንደማያምኑ የገለጹት አቶ ሙሼ፣ ‹‹ምርጫ የሚደረገው በሚቀጥለው ዓመት ቢሆን ኖሮ ያስኬዳል፡፡ ነገር ግን ገና አራት ዓመታት ለሚቀሩት ምርጫ አዋጁን ማሻሻልና አሁን ካለው ተቃውሞ ጋር የማገናኘት ተገቢነቱ አይታየኝም፤›› ብለዋል፡፡

በሜልቦርን ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት ዶ/ር ፀጋዬ ረጋሳ በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ንቅናቄ አቀንቃኝ ሲሆኑ፣ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላትን ልዩ ጥቅም አስመልክተው፣ “The Special Interest: The Affirmation of Denial” በሚል ባቀረቡት ጽሑፍ ላይ አዲስ አበባ ኦሮሚያ ውስጥ ብትሆንም የኦሮሚያ እንዳትሆን ተደርጋለች የሚል መሠረታዊ ነጥብ በማንሳት ይከራከራሉ፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49(5) መሠረት ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላት ልዩ ጥቅም የማኅበራዊ አገልግሎቶች፣ የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚነት፣ የጋራ አስተዳደርና ሌሎች በሕግ የሚወሰኑ ተብለው ነው የተቀመጡት፡፡

ማኅበራዊ አገልግሎትን በተመለከተ በኦሮሚያ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶችን በአዲስ አበባ እንዲቋቋሙ ማድረግ፣ የኦሮሞ ባህልን በአዲስ አበባ ማጎልበት የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት እንደሚገባ፣ የኦሮሚኛ ቋንቋ በአዲስ አበባ የአማርኛ አቻ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ማድረግና ሌሎችንም መመለስ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡

ሌላኛው መሠረታዊ ጥያቄ የጋራ አስተዳደርን የተመለከተ ፖለቲካዊ መብት በመሆኑ፣ መንግሥትና ገዢው ፓርቲ ጥያቄውን ለመመለስ የጋራ የመሬት አስተዳደር እንዲኖር መፍቀድ፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ተጠሪነት ለፌዴራል መንግሥት ብቻ ሳይሆን ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም ተጠሪ እንዲሆን ማድረግና ሌሎቹንም ነጥቦች ያነሳሉ፡፡

ነገር ግን የፕሬስና የኢንፎርሜሽን ነፃነትን ለማጎልበት የወጣው ሕግ እንዴት የፕሬስ ነፃነት ላይ ገደብ እንዳደረገ፣ የምርጫ መብቶችን ለማስፋት በሚል የወጣው ሕግ እንዴት ነፃና ፍትሐዊ ምርጫን በኢትዮጵያ እንዳቀጨጨ፣ የሲቪክ ማኅበራት እንዴት በሕግ እንዲንኮታኮቱ እንደተደረጉ የተመለከተ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም በሕግ ይመለሳል ብሎ ተስፋ ለማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

Standard (Image)

መንግሥት ከዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር በጀመረው ውይይት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቃውሞ ገጠመው

$
0
0

-  ‹‹ይች አገር እንድትቀጥል ከተፈለገ እኛ አድማጭ እናንተ ተናጋሪ የምትሆኑበት አካሄድ ማክተም አለበት››  አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር

-  በሐሮማያና በባህር ዳር መምህራን ከተሳትፎ ታቅበዋል

 -  በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ውይይቱ አልተጀመረም

መንግሥትና ገዥው ፓርቲ በትምህርት ዘርፍና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ አባላት ጋር የጀመረው ውይይት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር አባላት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው፡፡

በአገሪቱ በሚገኙ 35 ዩኒቨርሲቲዎች ውይይቱ የተጀመረው ባለፈው ሳምንት ውስጥ ሲሆን፣ በአዲስ አበባና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች ውይይቱ የተጀመረው መስከረም 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውይይቱ በአምስት ቦታዎች ተከፍሎ የተካሄደ ቢሆንም፣ ዋናውና በዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ካሣ ተክለብርሃን የተመራው ውይይት የተካሄደው በብሔራዊ ስብሰባ ማዕከል ነው፡፡

በዚህ ውይይት ላይ በርካታ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ አባላት ተገኝተዋል፡፡ ውይይቱን የሚመሩት የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሊቀመንበርና የፌዴራልና የአርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ካሣ ተክለብርሃንና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት በቀጥታ ወደ ውይይቱ አጀንዳዎች ለመግባት በሞከሩበት ወቅት፣ ከፍተኛ ተቃውሞ ከዩኒቨርሲቲው መምህራን ገጥሟቸዋል፡፡

‹‹እናንተ ውረዱና ከእኛ ጋር ተቀመጡ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይምጡና ያወያዩን፤›› ሲሉ አንድ መምህር ጠይቀዋል፡፡

‹‹የዛሬ ዓመት በተመሳሳይ የውይይት መድረክ ብዙ ቁም ነገሮች ተነስተው ነበር፡፡ ነገር ግን አንዳቸውም ሳይተገበሩ ዛሬ ደግመን ተገናኘን፤›› ሲሉ ውይይቱ ፋይዳ ቢስ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ በቀጥታ በአወያዮቹ ላይ ያነጣጠረ ትችት ሰንዝረዋል፡፡

‹‹አቶ ካሣ እርስዎ ሚኒስትር ነዎት፡፡ በዚያ ላይ የዩኒቨርሲቲዎችን ቦርድ ሊቀመንበርም ነዎት፡፡ በዚህ ሁሉ ኃላፊነት ውስጥ ሆኖ በዩኒቨርሲቲው የዶክትሬት ተማሪ መሆን አይቻልም፡፡ ስለዚህ ሥራዎትን ይልቀቁ፤›› ሲሉ አንድ መምህር ጠይቀዋል፡፡

ሌላው መምህር በበኩላቸው፣ ‹‹የመንግሥት ሥልጣን ይዘው ለግል ጥቅም በማዋል የዩኒቨርሲቲውን ሕግ ጥሰው የዶክትሬት ተማሪ ሆነዋል፤›› ሲሉ ተችተዋል፡፡

ለተነሱባቸው ትችቶችና ተቃውሞዎች ምላሽ የሰጡት አቶ ካሣ፣ መንግሥት ወክሏቸው በኃላፊነት ውይይቱን ለመምራት መምጣታቸውን፣ ይህ ማለት ግን ከተወያዮቹ የተሻሉ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹እኔ ብማር ክፋቱ ምንድነው? እኔም እኮ አንድ ዜጋ ነኝ፡፡ ከዚህ ቀደም እኔም ትምህርት የመጀመሩን ዕድል አግኝቼው ነበር፤›› ሲሉ ተረጋግተው መልሰዋል፡፡

ከዚህ በኋላ የተሻለ መረጋጋት የተስተዋለ በመሆኑ ወደ ውይይቱ አጀንዳዎች ለመግባት ሲሞከር አንድ መምህር በማሳሰቢያ መልክ፣ ‹‹በመጀመሪያ ይኼ ስብሰባ ሲጀመር በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላና በኮንሶ ለተገደሉ ንፁኃን ዜጎች የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ሊደረግ ይገባል፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ይህንኑ ተከትሎም መድረኩን የሚመሩት አወያዮች የህሊና ፀሎት አስደርገዋል፡፡ በመቀጠል የውይይቱ የመጀመሪያ አጀንዳ የሆነው፣ ‹‹የማሽቆልቆል ምዕራፍ ተዘግቶ የዕድገት ምዕራፍ በተከፈተበት የሃያ አምስት ዓመታት ጉዞ ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት ሚናና ለቀጣይ ተልዕኮ ሊኖረው የሚገባ ቁመና›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ሰነድ ቀርቧል፡፡

ይሁን እንጂ በዚህ ሰነድ ላይም ለመወያየት ፍላጐት አልታየም፡፡ ‹‹ሰው እየሞተና ሕዝብ ለተቃውሞ እየወጣ አገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ገብታ ስለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት መወያየት ያሳፍረኛል፤›› ሲሉ አንድ መምህር ተናግረዋል፡፡

ሌላ ተናጋሪ በበኩላቸው አቶ ካሣን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ብቁ አይደሉም በመሆኑም ይልቀቁ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ሰነዱ ‹‹ትምህርትና የኢትዮጵያ ሁኔታ፣ ያለፉት 25 ዓመታት በአገሪቱ የተመዘገቡ አንኳር ለውጦች፣ የማሽቆልቆል ጉዞን በገታ ሩብ ምዕተ ዓመት የልማት፣ የሰላምና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አገራዊ ስኬት ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት ሚና›› የሚሉና ሌሎች ንዑስ ርዕሶችን ያካተተ ነው፡፡

በርካታ መምህራን ውይይቱን በመሰልቸት ጥለው ወጥተዋል፡፡ በማግሥቱ የተወያዮች ቁጥር በእጅጉ በመሳሳቱ ወደ ቡድን ውይይት በዲፓርትመንት እንዲካሄድ ተወስኖም ውይይቱ ተበትኗል፡፡

በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረው ውይይት ቀናትን ያሳለፈ ቢሆንም፣ መምህራን በአካል ከመገኘት ባለፈ ተሳትፎ እያደረጉ አለመሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በዚህ የተነሳም ውይይቱን እንዲመሩ የተወከሉት የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ስለሺ ጌታሁንና አቶ ሴኮቱሬ ጌታቸው፣ የመምህራኑ ዝምታ እንዲጠና ሲሉ ሐሳብ አቅርበው ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡

በተመሳሳይ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መስከረም 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ቢጀመርም መጠነኛ ተሳትፎ ብቻ ታይቷል፡፡ መስከረም 10 ቀን በነበረው ውሎ አንድም አስተማሪ ጥያቄ አለማቅረቡን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ውይይቱን የመሩት የቦርድ ሰብሳቢው አቶ አለምነው መኮንን፣ በዩኒቨርሲቲው መምህራን በተደጋጋሚ በቀረበው ማጉረምረምና ዝምታ ደስተኛ ሳይሆኑ ስብሰባውን እየመሩ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መጀመር የነበረበት ውይይት እስከ ማክሰኞ መስከረም 11 ቀን 2009 ዓ.ም. አለመጀመሩን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ውይይትን እንዲመሩ የተመደቡት የቦርድ ሊቀመንበሩ ዶ/ር ስንታየሁ ወልደ ሚካኤል ሲሆኑ፣ ዶ/ር አምባቸው መኮንንና ሌሎች አምስት የኢሕአዴግ አባላትም ተወክለዋል፡፡

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲም የመምህራኑ ውይይት የተጀመረው ባለፈው ሐሙስ ሲሆን፣ ውይይቱን የመሩት የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንትና የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ አባል ዶ/ር አዲስዓለም ባሌማ ናቸው፡፡ በውይይቱ ወቅትም አንድ መምህር፣ በመገናኛ ብዙኃን መንግሥት የሚናገረው ምንም ረብ የሌለውና አሰልቺ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አወያዩ ምንም አዲስ ነገር እንደማይናገሩም ገልጸው፣ ምሁራንን አዳምጠው ማስታወሻ በመያዝ ከመንግሥት ጋር እንዲወያዩበት ጠይቀዋል፡፡

በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲ ለአገሪቱ ህዳሴ ያለውን ወሳኝ አስተዋጽኦ ሁሉም ወገን ተረድቶ ብዝኃነትን ለማስተናገድ ለብሔራዊ መግባባት መሠረት መፍጠር የውይይቱ ዓላማ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በውይይቱ ማጠናቀቂያ ላይ የዩኒቨርሲቲ አመራሮችና ፈጻሚዎች ሚና በዝርዝር የሚገመገምበት ሂስና ግለሂስ እንደሚደረግም ለዩኒቨርሲቲዎቹ ከተላከው ሰነድ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

አዲስ ገቢ ተማሪዎች ብቻ ደግሞ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎችና ሰላማዊ የትግል ሥልት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት›› በሚል ርዕስ ውይይት እንደሚያካሂዱ ታውቋል፡፡

በአጠቃላይ የተጀመረውን ውይይትና ሥልጠናውን የሚከታተል ከኢሕአዴግ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤትና ከትምህርት ሚኒስቴር የተውጣጣ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል፡፡

በየዩኒቨርሲቲው የተደራጁ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ዕለታዊ የመገምገሚያ ነጥቦች መሠረት ውሎአቸውንና ሳምንታዊ እንቅስቃሴያቸውን ገምግመው ለክልል በየዕለቱ የስልክ ሪፖርትና በየሳምንቱ የጽሑፍ ሪፖርት እንዲያደርጉ መታዘዛቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ክልሎች በበኩላቸው ከየዩኒቨርሲቲዎቹ የሚደርሷቸውን ሪፖርቶች አደራጅተው በየዕለቱ በስልክ እንዲሁም በየሳምንቱ በጽሑፍ ወደ ማዕከል ሪፖርት እንዲያደርጉ መታዘዛቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአጠቃላይ ትምህርት የሚጀመረው ከጥቅምት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በኋላ እንደሆነም ሰነዱ ይገልጻል፡፡      

Standard (Image)

በሕግ ሳይሆን በፖለቲካ የሚፈቱት የማንነት ጥያቄዎች

$
0
0

በ1960ዎቹ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ተማሪዎች የፖለቲካ ንቅናቄ ማዕከል ያደረገው ለኢትዮጵያ ተስማሚ የሆነ የፖለቲካዊ ሥርዓትን በክርክር አንጥሮ ለማውጣት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይገልጻሉ፡፡

በኢትዮጵያ የተጨፈለቁ ማንነቶችን ከጭቆና በማውጣት ሁሉንም የአገሪቱ ብሔረሰቦች ነፃነት የሚያጐናጽፍ ሥርዓትን ለማበጀት ያለመ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ የተማሪዎቹ ንቅናቄ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሶ ሊፈጥሩት የነበረው ፖለቲካዊ ሥርዓት በወታደራዊ ኃይል ተቀልብሶ ወታደራዊ መንግሥት ቢመሠረትም የወጣቶቹ እምነት አልሞተም፡፡ ይሁን እንጂ እንደ አጀማመራቸው በሰላማዊ ትግል ሊቀጥል አልቻለም፡፡ ይህንኑ የተማሪዎችን መሠረታዊ ዓላማ በማንገብ ትጥቅ ትግል ከጀመሩት ድርጅቶች መካከልም ስኬትን የተቀዳጁት ሕወሓትና ኢሕዴን የመሠረቱት ኢሕአዴግ በ1983 ዓ.ም. ወታደራዊ አገዛዙን በማስወገድ አገሪቱን ሲቆጣጠርም፣ ይኸው መሠረታዊ የትግሉ መርህ አልሞተም ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ከግንቦት ወር 1983 ዓ.ም. በኋላ የመሠረተው የሽግግር መንግሥት ቋሚ መርህም ተጨፍልቀው ለዘመናት የኖሩ የብሔሮች ማንነትን ነፃነት ማጐናፀፍ ነበር፡፡

የሽግግር መንግሥቱ ቻርተር ፖለቲካዊ አስተዳደር ምሰሶ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን መሠረት ያደረገ ያልተማከለ አስተዳደርን በወቅቱ ፈጥሯል፡፡ በዚሁ ቻርተር መሠረት በወቅቱ ተቋቁሞ የነበረው የሕዝቦች ምክር ቤት የደነገገው አዋጅ ቁጥር 7/1984 የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ የራሳቸውን አስተዳደር መመሥረት እንዲችሉ ፈቅዷል፡፡ በዚሁ መሠረት የራሳቸው ክልላዊ ወሰን ያላቸውን 63 ብሔር ብሔረሰቦችን እንደለየና ከእነዚህ ውስጥ 47ቱ የራሳቸውን አስተዳደር እንዲመሠርቱ ዕውቅና መስጠቱንም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በዚሁ መሠረትም ብሔርን መሠረት ያደረጉ 14 ክልላዊ አስተዳደሮችና በርካታ ንዑስ የአካባቢ አስተዳደሮች ተመሥርተው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ብሔርን መሠረት በማድረግና በሽግግር መንግሥት ወቅት የተመሠረቱትን ክልላዊ አስተዳደሮች በመቀበል በ1987 ዓ.ም. የፀደቀውና በሥራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ለመጀመሪያ ጊዜ ብሔራዊ ማንነትን መሠረት ያደረገ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን በኢትዮጵያ አወጀ፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 የብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች መብት በሚል ንዑስ ሥር ‹‹ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው፤›› የሚል ድንጋጌን አስቀምጧል፡፡

በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ሦስት ላይ ደግሞ ‹‹ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት አለው፡፡ ይህ መብት ብሔር ብሔረሰቡ ሕዝቡ በሠፈረበት መልክዓ ምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግሥታዊ ተቋም የማቋቋም፣ እንዲሁም በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መበትን ያጠቃልላል፤›› የሚል ፖለቲካዊ መብቶችን ያዘለ ድንጋጌ ተቀምጧል፡፡

ይህ ሕገ መንግሥት ከመፅደቁ በፊትም ሆነ በኋላ በርካታ የፖለቲካ ልሂቃን የተጠቀሰውን ድንጋጌ ኢትዮጵያን ለመበታተን ያለመ እንደሆነ ሲተቹት የነበረ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ወደ ተግባር ከገባ 20ኛ ዓመቱ ቢያልፍም ራስን ከማስተዳደር ጋር በተያያዙ ጥያቄዎች አገሪቱ በየቦታው በግጭቶች እየታመሰች ትገኛለች፡፡ ሕገ መንግሥቱን ያመነጨውና አገሪቱን ላለፉት 25 ዓመታት እያስተዳደረ የሚገኘው ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን በሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ ድንጋጌ አንቀጽ 39 መሠረት እያኖረ ነው? የሚለው ጥያቄ አሁንም ተደጋግሞ ይነሳል፡፡

ኮንሶ እንደ ማሳያ

በደቡብ ክልል የኮንሶ ብሔረሰብ ለዓመታት ያልተመለሰለትን ራስን በራስ የማስተዳደር ሰላማዊ ጥያቄው አሁን ወደ ግጭት ተቀይሯል፡፡ ሰሞኑን በተቀሰቀሰው አመፅም ከሰባት ሺሕ በላይ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ ከ12 ሺሕ በላይ ሰዎች ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፣ በርካታ ሰዎችም መሞታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ማዕከል መምህር የሆኑት አቶ ናሁሰናይ በላይ በግጭቱ ወቅት በኮንሶ ለጥናታዊ ጉዞ ተዘጋጅተው የነበሩ ሲሆን፣ በግጭቱ ምክንያት ጉዟቸውን ለመሰረዝ ተገደዋል፡፡

‹‹የኮንሶ ጥናታዊ ጉዞዬን እንድሰርዝ ያስገደደኝን ግጭት ምንነት ለማወቅ የአካባቢው ሰዎችን አነጋግሬ ያገኘሁት መረጃ›› በማለት ባስነበቡት ጽሑፍ፣ ሁኔታው ከአሁኑ ካልተገታ ወደማያባራ ግጭትና መተራረድ ሊያመራ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

የኮንሶ ሕዝብ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግሥት እስከ 2004 ዓ.ም. በልዩ ወረዳ መዋቅር ራሱን ሲያስተዳድር ቆይቷል፡፡ ከመጋቢት ወር 2004 ዓ.ም. በኋላ ግን የኮንሶ ልዩ ወረዳ ከቡርጂ፣ ከአማሮ፣ ከአሌ እና ከደራሼ ሕዝቦችን በመጨመር የሰገን አካባቢ ዞን ተደርጐ ተዋቅሯል፡፡

አቶ ናሁስናይ የሰገን ዞን ምሥረታ በባህሪው ራስ ገዝ አስተዳደር የነበሩ ወረዳዎችን በማሰባሰብ የተዋቀረ ሲሆን፣ ሕዝቦች መክረውበትና ፈቅደው የተዋሀዱበት አለመሆኑን፣ ይልቁንም የክልሉ አመራሮች ባቀዱት መሠረት ብቻ የተመሠረተ ዞን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኮንሶ ልዩ ወረዳ ፈርሶ የሰገን ሕዝቦች ዞን ምሥረታ ከተካሄደበት ማግሥት አንስቶ በተፈጠረው የዞን መዋቅር ደስተኛ አለመሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡

ፍትሐዊ የበጀት፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የግብርና እንዲሁም ማኅበራዊ ጥቅሞች እንደተጓደሉበት እየገለጸ ይገኛል፡፡ ከዞኑ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የኮንሶን ብሔረሰብ ተወላጆች መገለል እየደረሰባቸው መሆኑን እየገለጹ ናቸው፡፡

እነዚህንና ሌሎች ያልተገለጹ በደሎችን ምክንያት በማድረግ የኮንሶ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ እንዲመለስና ራሱን ችሎ የብሔረሰብ ዞን ሆኖ እንዲደራጅ፣ እንዲሁም ያለ ኮንሶ ሕዝብ ዕውቅና ከኮንሶ ወረዳ የተቆረጡ ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ እንዲመለሱለት ለክልሉም ሆነ ለፌዴራል መንግሥት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ይህ ባለመሆኑም ሰላማዊና ሕገ መንግሥታዊ የነበረው የኮንሶ ብሔር ጥያቄ ወደ ግጭት አምርቶ ደም እያፋሰሰ ይገኛል፡፡

‹‹የተጠየቀው ጥያቄ ሕጋዊነቱንና ሕገ መንግሥታዊ አካሄድን የጠበቀ እስከሆነ ድረስ ሕጋዊ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፣ ይህ ጥያቄ ለምን ተጠየቀ ተብሎ የኃይል ዕርምጃ መውሰድ ዘላቂና ተገቢ መፍትሔ ፈጽሞ አይሆንም፡፡ የአካባቢው አመራሮች እየፈጸሙት ያለው ወንጀል ልክ የለውም፡፡ በሰሞኑ ግርግርም ወደ ሦስት መንደር የሚሆኑ የሣር ጐጆዎች መቃጠላቸውንና ነፍሳቸውን ለማዳን ሲሉም በርከት ያሉ ኮንሶዎች ለመሰደድ መገደዳቸውን ለመረዳት ችያለሁ፤›› በማለት ሁኔታውን አቶ ናሁሰናይ ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ክልል ከሌሎቹ ክልሎች በተለየ ሁኔታ ነገር ግን ከፌዴራል መንግሥቱ አወቃቀር ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ሁለት አወቃቀሮች አሉት፡፡ የደቡብ ክልል ምክር ቤትና የደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት በሚል የተዋቀረ ነው፡፡ የደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት በፌዴራል መንግሥቱ አወቃቀር መሠረት ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

በመሆኑም የኮንሶን ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ የሚመልሰው የደቡብ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ነው፡፡ የኮንሶን ጉዳይ የተጠየቁት የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ለማ ገዙሜ የዞን፣ የልዩ ወረዳና የወረዳ አወቃቀር የአስተዳደር ቅልጥፍናን አመቺነትንና የሕዝቡን የልማት ጥያቄ ታሳቢ በማድረግ ነው የሚመለስ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

በመሆኑም የኮንሶ ወረዳ በሰገን ሕዝቦች ዞን እንዲካተት የተደረገው ይህንን ታሳቢ በማድረግ መሆኑን አፈ ጉባዔው አቶ ለማ ያስረዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ጉዳዮችና አካባቢያዊ አስተዳደሮች ላይ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ዘመላክ አየለ አይተነው፣ የክልሉ መንግሥት ውሳኔ የኮንሶ ሕዝብን ሕገ መንግሥታዊ መብት የረገጠ የፖለቲካ ውሳኔ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የአገሪቱ ሕገ መንግሥትም ሆነ የደቡብ ክልል ሕገ መንግሥት በሚፈቅደው መሠረት የኮንሶ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱ ተከብሮለት ልዩ ወረዳ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ኮንሶ ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ወቅት ከኮንሶ ጋር በመሆን የሰገን ዞንን የመሠረቱት አማሮ፣ ቡርጂና ደራሼ ልዩ ወረዳ እንደነበሩ የሚገልጹት ዶ/ር ዘመላክ፣ የክልሉ ገዥ ፓርቲ ዴኢሕዴን በ2004 ዓ.ም. በወሰደው ፖለቲካዊ ዕርምጃ ሁሉንም ልዩ ወረዳዎች በማፍረስና እንዲዋሀዱ በማድረግ የሰገን ሕዝቦች ዞን ሆነው እንዲዋቀሩ ማድረጉን ይገልጻሉ፡፡

የሰገን ዞን የብሔረሰቦች ጥርቅም የሆነ የአስተዳደር አካል እንጂ ራስ ገዝ የሆነ የአካባቢያዊ መንግሥት መዋቅር አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም ከልዩ ወረዳ ጋር ሲነፃፀር የዞን አወቃቀር እዚህ ግባ የማይባል አነስተኛ የፖለቲካ ሥልጣን ብቻ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡

ኮንሶን ጨምሮ አራቱ ልዩ ወረዳዎች ፈርሰው የሰገን ሕዝቦች ዞን ሆነው በአንድ እንዲዋቀሩ መደረጉ የኮንሶ ብሔረሰብን ራስን በራስ የማስተዳደር ፖለቲካዊ ሥልጣንን እንዳሳጣ ዶ/ር ዘመላክ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከአንቀጽ 39 ጋር የሚላተመው ኢሕአዴግ

በሥራ ላይ የሚገኘው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 የደነገገው የብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች መብት ጠቅላላ ድንጋጌ በኢትዮጵያ አጠቃላይ ፖለቲካዊ መብት ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ሳይሆን ለብሔሮች የተሰጠ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

በዚህ ድንጋጌ መሠረት የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት ራስን ከማስተዳደር ሙሉ መብት ባለፈ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠልንም አጐናፅፏል፡፡

ይህ የብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ፖለቲካዊ መብት ተግባራዊ ይሆን ዘንድም የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 50 (4) ላይ ክልሎች አስፈላጊ ሆኖ በሚያገኙት ሁኔታ መሠረት የራሳቸውን አስተዳደራዊ መዋቅሮች ሊያቋቁሙ እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ ማንኛውም ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራስን የማስተዳደር ሙሉ መብት እንዳላቸው ቢገለጽም፣ የአስተዳደር መዋቅሩን ክልሎች በሚመቻቸው መሠረት እንዲፈቅዱ ደንግጓል፡፡

‹‹The Politics of Sub-national Constitutions and Local Government in Ethiopia›› በሚል ርዕስ የጥናት ጽሑፋቸውን ያሳተሙት ዶ/ር ዘመላክ፣ በአሁኒቷ ኢትዮጵያ 670 ወረዳዎችና 98 የከተማ አስተዳደሮች መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡     

ወረዳዎች በክልሎች ሕገ መንግሥት መሠረት የሚመሠረቱ መሆናቸውን የሚያስታውሱት ዶ/ር ዘመላክ፣ በልዩ ወረዳና በብሔረሰብ ዞን የሚዋቀሩ የአስተዳደር መዋቅሮች ደግሞ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 የሚሰጠውን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተግባራዊ የሚሆንበት አወቃቀር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ልዩ ወረዳ የተባለው ከወረዳ የተለየ በመሆኑና ልዩነቱም የልዩ ወረዳ አስተዳደራዊ ክልል የሚወሰነው በብሔረሰቡ አሰፋፈር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የብሔረሰብ ዞን አወቃቀር ዓላማው ከልዩ ወረዳ ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም፣ ክልላዊ ወሰኑ ወይም የቆዳ ሽፋኑ ሰፋ ያለ በመሆኑና በውስጡ ከሁለት በላይ ወረዳዎችን ሊይዝ የሚችል ስለሆነ ከልዩ ወረዳ የተለየ ስያሜ እንዲይዝ እንዳደረገው ይገልጻሉ፡፡

በዚህም መሠረት በአምስት ክልላዊ መንግሥቶች ውስጥ የልዩ ወረዳ አወቃቀር መኖሩን እነርሱም ደቡብ፣ አማራ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና አፋር ናቸው፡፡ በእነዚህ ክልላዊ መንግሥታት ውስጥም የብሔረሰብ ዞኖች አደረጃጀት መኖሩን ይገልጻሉ፡፡ ለአብነት ያህል በአማራ ክልል የኦሮሞ፣ ሕምራና አዊ ብሔረሰብ ዞኖችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

የመጀመሪያው የአካባቢ መንግሥት አወቃቀር የተጀመረው በሽግግር መንግሥት ወቅት መሆኑን በጥናታዊ ጽሑፋቸው የገለጹት ዶ/ር ዘመላክ፣ ክልሎች ሕገ መንግሥቶቻቸውን ካፀደቁ በኋላ የነበሩትን አካባቢያዊ አስተዳደሮች እንዳለ እንደተቀበሏቸው ያስረዳሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ፀድቆ ተግባራዊ መሆን በጀመረባቸው ዓመታት አገሪቱን የሚያስተዳድረው ኢሕአዴግ ማንኛውንም የብሔረሰብ መብት ጥያቄ ለማስተናገድ ፈቃደኛ ብቻ ሳይሆን፣ በተግባር ረገድም ችግር እንዳልነበረበት ያስታውሳሉ፡፡

ኢሕአዴግ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ይህንን ያደርግ የነበረው የብሔረሰቦች ግጭትን ለማብረድ እንደሆነ በመጥቀስ፣ በማሳያነት በሰሜን ኦሞ የብሔረሰብ ዞን አወቃቀር ተነስቶ የነበረውን ግጭት ያስታውሳሉ፡፡ ለምሳሌ ወላይታ፣ ጋሞ ጐፋና ዳውሮ ብሔረሰቦችን በማጣመር የሰሜን ኦሞ የብሔረሰብ ዞን መፈጠሩን ይጠቅሳሉ፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ወላይታ ራሱን የቻለ የብሔረሰብ ዞን እንዲኖረውና ከሰሜን ኦሞ ዞን መለየት መፈለጉ በመሀላቸው ግጭትን እንደቀሰቀሰ፣ በመሆኑም የክልሉ መንግሥት በፍጥነት የወላይታን ጥያቄ መቀበሉን ይገልጻሉ፡፡

በዚህ የተነሳም የሰሜን ኦሞ ብሔረሰብ ዞን ለሦስት ራሳቸውን የቻሉ የብሔረሰብ ዞኖች (ዳውሮ፣ ጋሞጐፋና ወላይታ) እና ሁለት ልዩ ወረዳዎች (ባስኬቶና ኮንታ) አወቃቀሮች መፈጠራቸውን ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ. ከ2000 በኋላ ኢሕአዴግ የብሔረሰቦችን ራስን በራስ ማስተዳደር ጥያቄ የሕዝቦችን የአገልግሎት አቅርቦትና የልማት ጥያቄ ለመመለስ እንዳላስቻለው በመጥቀስ፣ የልዩ ወረዳና የብሔረሰብ ዞን አስተዳደራዊ መዋቅር ጥያቄዎችን መንፈግ መጀመሩን ያብራራሉ፡፡

እነዚህ የልዩ ወረዳና የብሔረሰብ ዞን ጥያቄዎች መቆሚያ ያጡት የማኅበረሰቡ ልሂቃን የሥልጣንና የሀብት ማስገኛ መንገድ አድርገው በመቁጠራቸው እንደሆነ በገዥው ፓርቲ መታመኑን ያስረዳሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ከገዥው ፓርቲ ማዕከል ወደታች የወረደ በሚመስል መልኩ ክልሎች ሕገ መንግሥቶቻቸውን በማሻሻል አስተዳደራዊ መዋቅር ብቻ ለሆኑት ወረዳዎች የተሻለ ሥልጣንና ሀብት በመልቀቅ፣ የልዩ ወረዳና የብሔረሰብ ዞን ጥያቄዎችን ማዳከም መጀመራቸውን ያስረዳሉ፡፡

ከላይ በወረዳው የኢሕአዴግ ትዕዛዝ ክልሎች ሕገ መንግሥታቸውን በማሻሻል ቀደም ሲል የክልል ፕሬዚዳንቶች በወረዳዎች ላይ የነበራቸውን ፍፁማዊ ሥልጣን እንዲያጡ መደረጋቸውን ያትታሉ፡፡ ለዚህ የሚሰጠው ሁለተኛው ምክንያት የመንግሥት የልማት ፖሊሲ አቅጣጫ የነበረው ዘላቂ የድህነት ቅነሳ ፕሮግራም ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም መሠረት ያደረገው ወረዳዎች ላይ ነበር፡፡ መንግሥት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (GTP) የተባለውን የልማት ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምር ደግሞ፣ ወረዳዎች መረሳታቸውንና ከተሞች ላይ ትኩረት ያደረገ የልማት እንቅስቃሴ መጀመሩን ይገልጻሉ፡፡

በመሆኑም ኢሕአዴግ በመጀመሪያ የብሔረሰቦችን ግጭት በማስወገድ መረጋጋትን ለመፍጠር ሕገ መንግሥታዊ የሆነውን ብሔርን መሠረት ያደረገ አካባቢያዊ አስተዳደርን መፍቀድ ከጀመረ በኋላ፣ የልማትና ተመጣጣኝ የአገልግሎት አቅርቦትን ለሕዝቦች ለማድረስ በሚል ልማታዊ ምክንያት የብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን ማፈኑን ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም በአንድ ወቅት ብሔር ተኮር የነበሩ ወረዳዎችን ማጥፋት ብቻ ሳይሆን ማዋሀድ ድረስ በመሄድ፣ በኋላ የልማት አቅጣጫው ከተማ ተኮር ሲሆን ወረዳዎችን በመርሳት ክልሎች ከራሳቸው ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን የሚመልስ አካባቢያዊ የመንግሥት መዋቅር እንዳይፈጥሩ በማድረግ፣ ግጭቶች በየቦታው እንዲስፋፉ ማድረጉን ይገልጻሉ፡፡

አንድ ወጥ አካባቢያዊ የአስተዳደር መዋቅር በሁሉም ክልላዊ መንግሥቶች የሚሠራ ባለመሆኑ፣ ለክልሎቹ ነፃነት በመሰጠት ተገቢ የሆነውን አደረጃጀት በራሳቸው እንዲወስኑ ማድረግ ይገባል ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ

የአካባቢያዊ አስተዳደሮች በክልሎች ሕገ መንግሥትና ነባራዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብ መወሰኑ ቀርቶ፣ ከኢሕአዴግ በሚመጣ ውሳኔ የልማት አቅጣጫን መሠረት ያደረጉ ውሳኔዎችን ክልሎች እንዲከተሉ በመደረጉ በየቦታው ግጭት እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ የግጭት ስፋቱ በዋናነት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ያይል እንጂ በአማራ ክልል የቅማንት ጥያቄ፣ እንዲሁም በትግራይ ክልል የወልቃይት ጥያቄ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ቢሆንም ማጠንጠኛቸው ራስን ማስተዳደር ነው፡፡

እነዚህን ጥያቄዎች በሕገ መንግሥታዊ መርህ መሠረት ከመመለስ ይልቅ ለማዳፈን መሞከር የግጭቱ መሠረታዊ ችግር መሆኑን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የሰላምና ደኅንነት ባለሙያ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ጉዳዩ ሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡ ስለዚህ በሕግና በቴክኒክ መመለስ ሲገባው በፖለቲካ ነው እየተመለሰ ያለው፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ለተመሳሳይ ጉዳይ የተለያዩ ምላሾችን መስጠት ያመጣል፡፡ ለአላባ የፈቀድከውን ለኮንሶ ትከለክላለህ፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ ወጥ የሆነ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት መስፈን አለበት የሚሉት እኚሁ ባለሙያ፣ ‹‹ሕዝብ አንቀሳቅሰህ መንግሥትን ስታስጨንቅ የሚሰጥ መብት እየሆነ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ይህ ሕገ መንግሥታዊ መብት በአገሪቱ ውስጥ ወጥ ሆኖ ሊተገበር አልቻለም፤›› ይላሉ፡፡

ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጣቸው መርሆዎች እያሉ ኢሕአዴግ ተግባራዊ እያደረገ ያለው በተለየ መንገድ መሆኑን ያስረዱት እኚሁ ባለሙያ፣ የሁለቱ ግጭት አገሪቱን እየበጠበጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ በሕገ መንግሥቱ ላይ እስከሆነ ድረስ፣ ለዚህ ሕገ መንግሥት ዜጐች ብቻ ሳይሆኑ ኢሕአዴግም ሊገዛ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

የሕገ መንግሥቱን መርህ በመከተል እያንዳንዱን የራስ ገዝ አስተዳደር ጥያቄ መመለስ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል የሚያምኑት ዶ/ር ዘመላክ፣ ጥያቄውን መከልከል ግን ፀረ ሕገ መንግሥት ከመሆንም ባሻገር የግጭት ምንጭ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

ሁሉም የራስ ገዝ አስተዳደሮች የማኅበረሰብ ወይም የብሔረሰቡ ሙሉ ፍላጎት ነው ብሎ መደምደም ባይቻልም፣ መከልከሉ ግን ሕገ መንግሥታዊ እንደማያደርገው ዶ/ር ዘመላክ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎቹን በጥብቅ ተግባራዊ ለማድረግ ባለ ችግርና በተለያዩ የብሔር ማኅበረሰቦች ሊቀጥል የሚችለው የራስ ገዝ አስተዳደር ጥያቄ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ውዝግብና የግጭት ምንጭ ሆኖ እንደሚቀጥል የዶ/ር ዘመላክ እምነት ነው፡፡

  

         

 

Standard (Image)

ኤችአር 2016 - ለወቅታዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያለው ፋይዳ

$
0
0

የኢትዮጵያ መንግሥትን የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታን በተመለከተ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖችና አገሮች፣ በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ይዘት ያላቸውን ሪፖርቶች ይፋ ያደርጋሉ፡፡

በተለይ ከምርጫ 97 ወዲህ ባሉት ዓመታት የየተቋማቱ ሪፖርቶችና መንግሥት ለሪፖርቶቹ የሚሰጠው ምላሽ በተለያዩ ወቅቶች የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ስቦ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ከእነዚህ በተደጋጋሚ ከወጡ ሪፖርቶች መካከል ግን ኤችአር 2003 የተባለውና በአሜሪካ የኮንግሬስ አባል በነበሩት ዶናልድ ፔይንና ክሪስ ስሚዝ ተረቆ ለአሜሪካ ሕግ አውጭ ምክር ቤት ቀርቦ የነበረው ረቂቅ፣ ረዥም ሒደቶችን ያለፈና በኢትዮጵያ መንግሥትም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ሕግ ሆኖ እንዳይፀድቅ ከፍተኛ ሥራ የሠራበት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2007 ቀርቦ የነበረው ይህ ረቂቅ ሕግ ‹‹Ethiopia Democracy and Accountability Act of 2007›› የሚባል ሲሆን፣ በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት እንዲስፋፋና እንዲጠናከር፣ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲጠናከሩ ግፊት ለማድረግ የቀረበ ረቂቅ ነበር፡፡

እነዚህንም ነገሮች ለማሳካት ይቻለው ዘንድ ረቂቁ የአሜሪካ ኮንግረስ ከደኅንነት ጋር የተያያዙ ድጋፎችን እንዲቆጣጠርና በወቅቱ ተፈጥሮ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር እጃቸው ያለበት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚጠይቅ ረቂቅ ነበር፡፡

የእዚህን ረቂቅ ሕግ ለመቃወምና ከታለመለት ግብ እንዳይደርስም የኢትዮጵያ መንግሥት መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገውን ዲኤልኤ ፓይፐር የተሰኘ ዓለም አቀፍ የሕግ ተቋም በመቅጠር፣ ረቂቁ ከግቡ እንዳይደርስና የተዘጋጁት ማዕቀቦች ተፈጻሚ እንደሆኑ ማድረግ ችሎ ነበር፡፡

በተመሳሳይ በቅርቡ ለአሜሪካ ሕግ አውጪ ምክር ቤት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝና ዴሞክራሲ ዙሪያ የሚያጠነጥን አዲስ ረቂቅ ቀርቧል፡፡

ይህን ረቂቅ ሐሳብ የቀረበው በአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበርና ኤችአር 2003ን ካቀረቡትና እንዲፀድቅ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ከነበሩት መካከል ክሪስ ስሚዝ አማካይነት ነው፡፡

ይህ ኤችአር 2016 የተባለው ረቂቅ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት እንዲከበር የሚጠይቅና በእስር ላይ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ተማሪዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ የሚጠይቅ ነው፡፡

ይህ ረቂቅ ሕግ ዋነኛ ዓላማው ለሰብዓዊ መብት መከበር የሚሠራና ሁሉን አቀፍ የሆነ መንግሥት ምሥረታን መደገፍና ማበረታታት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በአገሪቱ ተቃውሞ የሚያደርጉ ዜጎች ላይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የሚወስዱትን የኃይል ዕርምጃ በፅኑ ይኮንናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በፀጥታ ኃይሎች ስለተገደሉት ሰዎች ተዓማኒነት ያለው ምርመራ እንዲካሄድና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ ምርመራ አድርጐ ሪፖርት እንዲያቀርብ የሚጠይቅ ነው፡፡

የረቂቁ አጠቃላይ ይዘት

አዲሱ ረቂቅ እ.ኤ.አ. በመጋቢት 2016 በአዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ፊት ለፊት ተቃውሞ ያሰሙ 20 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መታሰራቸውን፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች 21 የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና አባላት በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ መከሰሳቸውና መታሰራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታን ችግር የሚያሳይ ነው ይላል፡፡

በተጨማሪም በዚህ ያላግባብ ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሚገኝ በገለጸው የአገሪቱ የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ አማካይነት የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ዮናታን ተስፋዬ የፌስቡክ ገጻቸው ላይ የጻፉዋቸው ጽሑፎች እንደ ማስረጃ ተመዝግበው መታሰራቸው፣ የፓርቲው ልሳን የነገረ ኢትዮጵያ ድረ ገጽ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበሩት አቶ ጌታቸው ሽፈራው፣ የኦሮሚያ ቴሌቪዥን የዜና አዘጋጅ የነበሩት አቶ ፍቃዱ ሚርካና እንዲሁም አቶ ዘላለም ወርቅ አገኘሁ የተባሉ ብሎገር መታሰራቸው ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማሳያ እንደሆነ ያትታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ይህ አዲሱ ረቂቅ የቀድሞው አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የሕዝብ ግንኙነት የነበሩት አቶ ሀብታሙ አያሌው የሚያስፈልጋቸውን ሕክምና በጊዜው እንዳያገኙ መከልከላቸው፣ የመንግሥትን በሃይማኖት ጣልቃ መግባትን የተቃወሙ የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን ማሰሩና ከሰባት እስከ ሃያ አምስት ዓመታት ድረስ በሚደርስ የእስር ቅጣት መቅጣቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መበራከቱን እንደሚያሳይ አስረጅ ሆነው ቀርበዋል፡፡

ሰብዓዊ መብትን መደገፍና ሁሉን አቀፍ የሆነ መንግሥትን ማበረታታት ተገቢ እንደሆነ የሚገልጸው ረቂቁ፣ በኢትዮጵያ በ2007 ዓ.ም. ከተደረገው ጠቅላላ ምርጫ በኋላ ግን የአገሪቱ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ መመናመኑን ያትታል፡፡

ለዚህም የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታና የዴሞክራሲ መመናመን በረቂቁ የሚቀርበው አንዱ ምክንያት ደግሞ፣ አገሪቱን እየመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን መቶ በመቶ መቆጣጠሩን ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከምርጫው በኋላ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመደራጀት መብት መገደቡ፣ በርካታ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው እስራቶች መፈጸማቸው፣ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ላይ እስራቶች፣ ወከባና ማስፈራራት መድረሱ ሌሎች ማስረጃዎች እንደሆኑ ረቂቁ ይዘረዝራል፡፡

በአማራ ክልልና በኦሮሚያ ክልል አለመረጋጋት ከተከሰተ በኋላ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሟቾች ቁጥር 120 ነው ማለቱን የሚገልጸው ረቂቁ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች የሟቾችን ቁጥር 400 እንደሚያደርሱት ጠቁሞ ቁጥሩ ግን ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችል አስታውቋል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የሚነሱ አለመረጋጋቶችንና ግጭቶችን ለመቆጣጠርና ለማረጋጋት መንግሥት በሚወስደው ዕርምጃ፣ በመሠረታዊነት የአገሪቱን ሕገ መንግሥት የሚጥስ መሆኑንም ረቂቁ ያትታል፡፡

ረቂቁ በቅርቡ በቂሊንጦ እስር ቤት የደረሰው ቃጠሎ ተመርምሮ ለሕዝብ እንዲገለጽ የሚጠይቅ ሲሆን፣ በተጨማሪም በአገሪቱ የሚገኙ እስር ቤቶች በጣም የተጣበቡና የተጨናነቁ ከመሆናቸው ባሻገር የፅዳት ሁኔታቸውም ችግር እንዳለበት ይገልጻል፡፡

በተጨማሪም በአገሪቱ እስር ቤቶች የንፁህ የመጠጥ ውኃ እጥረት መኖሩን፣ እንዲሁም እስረኞች የሕክምና አገልግሎት እንዳያገኙ ማድረግና ተገቢውን የሕግ ምክር አገልግሎት እንዳያገኙና እንዳይጐበኙ ማድረግ፣ ሌሎች ከእስር ቤቶች ጋር በተያያዘ በረቂቁ የተዘረዘሩ ችግሮች ናቸው፡፡

እነዚህን ከላይ የተዘረዘሩትን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ጥሰቶችን አስመልክቶ ጉዳዮቹን የዘረዘረው ረቂቅ፣ የንፁኃን ዜጐችን ሞትና የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተጠቀሙትን ከመጠን ያለፈ ዕርምጃ አውግዟል፡፡

በተጨማሪም ጋዜጠኞች፣ ተማሪዎች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የመሰብሰብና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን በመጠቀማቸው የደረሰባቸውን እስራትና እንግልት እንዲሁ አውግዟል፡፡

የአገሪቱን ፀረ ሽብርተኝነት ሕግ መንግሥት በተለጠጠ ማዕቀፍ በመጠቀም የተለየና የተቃውሞ ድምጾችን ለማፈን ከማዋል እንዲቆጠብና ሌሎች የዜጐችን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚያፍኑ ሕጐችና አዋጆች እንዲሻሩ ይጠይቃል፡፡

በመጨረሻም በአገሪቱ እየተካሄዱ ያሉ ተቃውሞዎች በሰላማዊ መንገድ፣ እንዲሁም ከግጭቶች ፀድተው እንዲካሄዱ ለሕዝቡ መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን፣ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችም ከመጠን ያለፈ ኃይል መጠቀምን እንዲያቆሙ ጠይቋል፡፡

የመንግሥት ምላሽ

ኤችአር 2003 በረቂቅ ደረጃ እያለ ሕግ ሆኖ እንዳይፀድቅ ከፍተኛ ጥረት ያደረገውና ዓለም አቀፍ የሕግ ተቋምን በወትዋችነት ቀጥሮ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ አሁን ግን እንደዚያ ዓይነት ዕርምጃ እንደማይወስድ ገልጿል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ‹‹ለአዲሱ ረቂቅ ምንም ዓይነት ወትዋች ቡድን አይቀጠርም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትን የሚደግፉ በርካታ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ስላሉ መንግሥት ተጨማሪ ወትዋች አያስፈልገውም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሕጐች ጊዜ ጠብቀው እንደሚወጡ የገለጹት አቶ ጌታቸው ይህንንም ሕግ፣ ‹‹ይህ እንደ ኢንፍሉዌንዛ ጊዜ እየጠበቀ የሚወጣና ዴሞክራሲ ከአሜሪካ ብቻ ነው የሚመጣው የሚል አመለካከትን የሚያንፀባርቅ ነው፤›› በማለት አዲሱን ረቂቅ ተችተውታል፡፡

ኤችአር 2003 በርካታ ደረጃዎችን አልፎ የበርካታ ፖለቲከኞችና የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖቹ መወያያ ሆኖ ነበር፡፡ አሁን የቀረበው ረቂቅ ኤችአር 2016 ምን ያህል እንደሚጓዝና የሚፈጥረው ተፅዕኖ በጊዜ ሒደት የሚታይ ይሆናል የሚሉም አሉ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች አተያይ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ጥናትና ምርምር ኃላፊ የሆኑት አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ ረቂቁን መመልከታቸውን ገልጸው፣ በዋናነት ለረጅም ጊዜ የአገሪቱ የፖለቲካ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲጠይቁት የነበረ ጥያቄ በረቂቁ መካተቱን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የተነሱት ጥያቄዎች እኛ ስናነሳቸውና ስንጠይንቀቸው የነበሩ ናቸው፡፡ በዋናነት አሁንም ቢሆን ተቃዋሚዎች ናቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የዴሞክራሲም ሆነ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ኃላፊነት መውሰድ ያለባቸው፡፡ እነዚህን ረቂቅ ሕጐች የምንመለከታቸው ድጋፍ ይሆናሉ በሚል እንጂ፣ በዋናነት ከዚያ በኩል የሚነሳ ጥያቄ የኢትዮጵያን መንግሥት ጫና ውስጥ ከትቶ የእኛንም ጥያቄዎች ያስመልሳል የሚል ግምት የለንም፡፡ የመፅደቅ ዕድሉም ተስፋ የሚጣልበት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት ይህን ረቂቅ መሠረት አድርጐ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የተለያዩ ጫናዎች ይፈጥራል የሚል እምነት እንደሌላቸውም አቶ ዋስይሁን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ብዙ ነገሮች ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄዱ የአሜሪካ መንግሥት ምንም ሲያደርግ አላየንም፡፡ ምርጫ 2007 በተካሄደ ማግሥት ፕሬዚዳንቱ ስለኢትዮጵያ ምርጫ የሰጡትን አስተያየት ማንሳቱ በቂ ነው፤›› በማለት አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና የማድረግ ፍላጎት እንደሌላት አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ረቂቁ ብቻውን ለኢትዮጵያ ፖለቲካ መልስ ይሰጣል ብለው እንደማያምኑ አመልክተዋል፡፡  ‹‹አሜሪካኖች ብዙ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ነገር ሲያጋጥም የሕዝቡን ትኩረት ለመያዝና ከሕዝብ ጎን የቆሙ ለማስመሰል የሚያደርጉት ነው፤›› በማለት ረቂቁን ተችተዋል፡፡

በምርጫ 97 የወጣውን ኤችአር 2003 ያስታወሱት ኢንጂነር ይልቃል፣ ‹‹ነገሩ ውኃ በልቶት ነው የቀረው፤›› ብለዋል፡፡ ይኼኛውም ከዚያ የተለየ ዕጣ ፈንታ ይኖረዋል ብለው እንደማይገምቱ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የዚህ ዓይነቱን በተግባር ያልተደገፈ የፖለቲካ አፍዓዊ አስተያየት አልቀበለውም፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ናቸው እንጂ ውጤት የሚያመጡት፣ እንዲህ ያለ ነገር ዳር ደርሶ ውጤታማ ሲሆን አላይም፤›› በማለት በረቂቁ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ገልጸዋል፡፡

‹‹እንደ አንድ ፖለቲከኛ ጓደኞቼ ከእስር ቢፈቱና አፋኝ አዋጆች ቢሰረዙ እውነት ከሆነ ደስ ይለኛል፡፡ እኛም ደጋግመን የምንጠይቃቸው ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር በረቂቁ የተነሱት ጥያቄዎች ትክክል ናቸው፡፡ ነገር ግን እንደ ፖለቲካ አሜሪካኖች ቁርጠኝነት እንደሚያንሳቸውና ጉዳዩን ከምር እንዳልያዙት የሚታይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከረቂቁ መፅደቅ አንፃር ሊፀድቅ እንደሚችል የገመቱ ቢሆንም፣ ‹‹ነገር ግን ወደ ተግባር ለመለወጥ ምን ያህል እርግጠኞች ናቸው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ኤችአር 2003 ለምን ሳይፀድቅ ቀረ? የኢትዮጵያ መንግሥት ተሻሽሎ ነው? ከዚያ ወዲህ ነው እነዚህ አፋኝ ሕጎች የወጡት፡፡ ነገሮች እዚህ ደረጃ ላይ ሳይደርሱ ያን ሕግ ለማፅደቅ ብዙ ምክንያቶች ነበራቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ከሕዝብ ግንኙነት ሥራ አልፎ አሜሪካኖች ለፖለቲካ ቆርጠው ይህን መንግሥት ለመቆንጠጥና ነገሮች እንዲለወጡ ሄደዋል በሚለው ጉዳይ ጥርጣሬ አለኝ፤›› በማለት ደምድመዋል፡፡ 

           

Standard (Image)

የአቶ ኃይለ ማርያም መንገድ

$
0
0

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ መስከረም 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ድፍን አራት ዓመት ሞላቸው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ካረፉ ጀምሮ ዓለም የቀጣዩን መሪ አፈጻጸም ለማየት በጉጉት ነበር የጠበቀው፡፡ በሥልጣን ማማ ላይ ለአራት ዓመታት የዘለቁት አቶ ኃይለ ማርያም እንዴት እንደተወጡ ለመገምገም ተገቢ ጊዜ ይመስላል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም ወደ ሥልጣን ሲመጡ መንግሥት ያስመዘገበውን ጥሩ ውጤት ከማስቀጠል ባሻገር አዲስ የአመራር ዘይቤ እንደሚያስተዋውቁም ተጠብቆ ነበር፡፡ ይህም በዋነኛነት ከሌሎች የኢሕአዴግ አመራሮች በተለየ ባሏቸው የኋላ ታሪኮች የተነሳ ነበር፡፡ የአቶ ኃይለ ማርያም ብሔር፣ ሃይማኖትና ባህል ከተለመደው የኢትዮጵያ የአመራር ባህርያት የተለዩ ናቸው፡፡ የአቶ ኃይለ ማርያም ብሔር ወላይታና ሃይማኖታቸው አፓስቶሊክ ፕሮቴስታንት ክርስቲያን ከዚህ ቀደም ለከባድ ሥልጣን የሚታጩ አልነበሩም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትጥቅ ትግሉም የተሳተፉ አልነበሩም፡፡ በሲቪል ኢንጂነሪንግ የተመረቁትና የማስተርስ ትምህርታቸውን ፊንላንድ ከሚገኘው ታምፐር ዩኒቨርሲቲ በኃይድሮሎጂ ያጠናቀቁት አቶ ኃይለ ማርያም፣ የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዲን በመሆንም አገልግለዋል፡፡

በአቶ ኃይለ ማርያም ተስፋ ያደረጉ እንዳሉ ሁሉ የተወሳሰበ ግንኙነት ያለውን የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ለመምራት ተገቢ ሰው አይደሉም በሚል ከመነሻው ጥርጣሬያቸውን የገለጹም አልጠፉም፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑትና ለተተኪነት የታጩት በአቶ መለስ በጎ ፈቃድ እንደነበር ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ እርግጥ ነው አቶ ኃይለ ማርያም ለአስተዳደሩ አዲስ ሰው አልነበሩም፡፡ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አስተዳዳሪና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ነበሩ፡፡ አዲሱ ሥራቸውን ከመጀመራቸው በፊትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል፡፡

ከአራት ዓመታት በፊት ለበዓለ ሲመታቸው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የመንግሥታቸውን የትኩረት አቅጣጫ አመላክተዋል፡፡ በዚህም ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሽግግር እንቅፋት በሆኑት የሙስና ተግባራት ላይና በኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካ ኢኮኖማሚ ላይ ቀዳሚ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ገልጸው ነበር፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በአሸናፊነት ለመውጣት የሕዝቡን ተሳትፎ የሚያረጋግጡ አስቻይ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥሩም ቃል ገብተው ነበር፡፡

የፍትሕ ሥርዓቱ ለመሠረታዊ ነፃነቶችና ለነፃ የገበያ ሥርዓት ጥበቃ ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ ማሻሻያ እንደሚደረግበትም አስታውቀው ነበር፡፡ ይህም የፖሊስ፣ የዓቃቤ ሕግና የፍርድ ቤትን አሠራር የተሻለ የሚያደርጉ መሠረታዊ የሕግ ማሻሻያዎች በማድረግ የሚፈጸም መሆኑ ተገልጾ ነበር፡፡

በተመሳሳይ ቀን መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ላይ የሚሠሩና የዴሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከር የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ሒደቱን አንድ እርከን ለማሳደግም ቃል ገብተው ነበር፡፡ በተለይ ከሚዲያ፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከነፃና ገለልተኛ ሲቪክ ተቋማት፣ ከሙያ ማኅበራትና ከሕዝባዊ ድርጅቶች ጋር ተባብረው ለመሥራትም ቃል ገብተው ነበር፡፡ ይህ ግንኙነትም ከወገንተኝነትና ከጣልቃ ገብነት በፀዳ መንገድ የሚፈጸም እንደሚሆን ተናግረው ነበር፡፡

ይህን ባሉ ልክ በአራት ዓመታቸው መስከረም 11 ቀን 2009 ዓ.ም. አሜሪካ ኒውዮርክ ለ71ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ባደረጉት ንግግር፣ ማኅበራዊ ሚዲያ በርካታ ጠቀሜታዎች ቢኖሩትም ጉዳቶቹ ዝም ሊባሉ አይገባም ሲሉ ተከራከሩ፡፡ አክራሪ ኃይሎች የሕዝቡን ትክክለኛ ሥጋቶች ከዓውድ በማውጣት ያለ ገደብ የጥላቻና የመገለል መልዕክቶች እያስተላለፉ እንደሚገኙ፣ በዚህም ወጣቶች ተጠቂ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ፀብ የሌላቸው፣ እንዲያውም ወዳጅ የሚባሉ አገሮች ለእነዚህ አካላት መጠለያ መስጠታቸውና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸው ኢትዮጵያን እንደሚያሳስባትም አመለከቱ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ዓመት ለሚሆን ጊዜ ያህል በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተስተዋለውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለማነሳሳት ማኅበራዊ ሚዲያ ስለፈጠረው ተፅዕኖ እየተናገሩ ነበር፡፡ መንግሥታቸው ሕዝባዊ ተቃውሞዎቹ ተገቢ ጥያቄዎችን እንደያዙ ያለ ሙሉ ልብ የሚቀበል ቢሆንም ዋነኛው ምክንያት የውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ነው በማለት ይከራከራል፡፡ በአጠቃላይ በሚዲያ ላይ በተለይ ደግሞ በኢንተርኔት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርግ በመሆኑ፣ ለተከሰተው ችግር ይህን በማለታቸው ብዙዎች መገረማቸውን ገልጸዋል፡፡

በእነዚህ ሁለት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሮች መሀል ባሉ አራት ዓመታት ውስጥ አገሪቱ ብዙ ነገሮችን አስተናግዳለች፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም በእነዚህ ዓመታት ምን ተግዳሮት ገጠማቸው? ምን ስኬት አስመዘገቡ? ስለመጪው ጊዜያቸውስ ዜጎች ምን ይላሉ?

የኃይለ ማርያም የአመራር ዘይቤ

ከላይ እንደተገለጸው በመጀመሪያ የሥራ ቀናቸው እንዳደረጉት ሁሉ ባለፉት አራት ዓመታት በበርካታ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ቃል ቢገቡም፣ ቃላቸውን የመተግበር ከፍተኛ ፈተና ገጥሟቸዋል፡፡ በትኩረት እሠራበታለሁ ያሉት የሙስና ትግል፣ የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር፣ የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ ይዞታ ማሻሻያ፣ ከነፃና ገለልተኛ ተቋማት ጋር በሚኖረው መልካም ግንኙነት ላይ ለውጥ ከማየት ይልቅ ነገሮች ተባብሰው ሲጓዙ ነው የታየው፡፡

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሕዝባዊ ተቀውሞዎች ከታዩ በኋላ መንግሥት በይፋ እንደገለጸው አቶ ኃይለ ማርያም እንዲሻሻሉ በትኩረት እሠራለሁ ያሏቸው ጉዳዮች የአገሪቱን ህልውና እየተፈታተኑ ነው፡፡ ከገዥው ፓርቲም ሆነ ከአቶ ኃይለ ማርያም የግል ሰብዕና ጋር የተያያዙ ችግሮች ነገሮች እየተባባሱ እንዲሄዱ አድርገዋል፡፡

የአቶ ኃይለ ማርያም አድናቂዎች ሲገልጿቸው ለስላሳ፣ ትሁት፣ ታማኝና ታታሪ ይሏቸዋል፡፡ እነዚህ ባህርያትም ያረጀ ያፈጀውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ለመቀየር ተፈላጊ እንደሆኑ ይከራከራሉ፡፡

ታዋቂው ፈላስፋና የፖለቲካ ተንተኝ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ አቶ ኃይለ ማርያም አዲሰ ዘመን ይዘው እንደሚመጡ ተስፋ አድርገው ከነበሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን አንዱ ናቸው፡፡ ‹‹ከኋላ ታሪካቸው በመነሳት ብዙ ነገር ጠብቄ ነበር፡፡ አንዳቸውም አልተሳኩም፡፡ ወደ ሥልጣን ሲመጡ በአገሪቱ ሁሉም አቅጣጫዎች የሚገኝ ሕዝብ ተቀብሏቸው ስለነበር እሱ ላይ ተመሥርተው ቢሠሩ መልካም ዕድል ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ይሁንና የኃይለ ማርያምን የአመራር ዘይቤ በተግባር ለማየት መቸገራቸውን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ‹‹አራት ዓመታት የአንድን መሪ ሰብዕና ለመገምገም በቂ አይደሉም፡፡ የአመራር ባህርያቸውን፣ ፊርማቸውን፣ ቀለማቸውንና ዘይቤያቸውን መለየት አልቻልኩም፡፡ በዚህ ቢሮ ራሳቸውን ማግኘት የቻሉ አልመሰለኝም፡፡ እንዴት እየሠሩ እንደሆነ ከአራት ዓመት በኋላ ቢያንስ ምልክትና አዝማሚያ ማየት ነበረብን፡፡ እኔ ግን የኃይለ ማርያምን መንገድ ማየት አልቻልኩም፡፡ ካላቸውም ድብቅ ነው፤›› ሲሉ ዶ/ር ዳኛቸው ሞግተዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የሕገ መንግሥት ኤክስፐርት በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ይዘውት የመጡትን አዲስ ነገር ማየት እንዳልቻሉ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹መሠረታዊ የሆነ አዲስ አቀራረብ፣ አቅጣጫና መንገድ አላየሁም፡፡ አዲሰ ፖሊሲ ለመቅረፅ ተነሳሽነት ሲወስዱ አልያም አዳዲስ ተግዳሮቶችን ለመወጣት የቀድሞ ፖሊሲዎችን አተገባበር ሲለውጡ አላየሁም፤›› ብለዋል፡፡

ኤክስፐርቱ አዲስ የአመራር ዘይቤ ማምጣት ይቅርና በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ ሥልጠናቸውን አስረግጠው ለመጠቀም ሲሞክሩም እንዳልታዩ ያመላክታሉ፡፡ ‹‹በመንግሥት ጉዳዮች ላይ ሙሉ ቁጥጥር የላቸውም የሚለውን የሕዝቡን አመለካከት ከአራት ዓመታት በኋላ አላስቀየሩም፡፡ ወደዚህ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት አገር ለመምራት የሚያስችሉ ከታሪክ፣ ከፖለቲካ፣ ከፍልስፍናና ከሕግ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ የትምህርትም ሆነ የንባብ ዝግጅት ያደረጉ አልመለኝም፡፡ ይህን ከሚሰጧቸው ቃለ ምልልሶች መረዳት ይቻላል፡፡ እርግጥ ነው በእነዚህ ጉዳዮች ላይ እንደ አንድ አባል ፓርቲው በሚሰጣቸው ሥልጠናዎች በመሳተፍ ልምድ ይቀስማሉ፡፡ ይህ ግን ነገሮችን ገለልተኛ ሆኖ ለመገምገም የሚያስችል አይሆንም፤›› ብለዋል፡፡

ከፓርቲው ባህል በተጨማሪ አስተያየት ሰጪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የራሳቸውን የአመራር ዘይቤ እንዳያወጡ ከልክለዋቸዋል የሚሏቸውን ተግዳሮቶች ይጠቅሳሉ፡፡ የመጀመሪያ ተግዳሮት ሆኖ የሚጠቀሰው ከአቶ መለስ ባህርያት ጋር የመጣጣም ክፍተት ነው፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የፖለቲካ ሳይንቲስት አቶ ኃይለ ማርያምን ከአቶ መለስ ጋር ማነፃፀር አግባብ እንዳልሆነ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹መለስ የሥርዓቱ እምብርት ለመሆን ጊዜ፣ ልምድ፣ እውቀት፣ ፈተናዎችን የማለፍ ዕድል፣ ተፈጥሯዊ ክህሎትና ሰብዕና ነበራቸው፡፡ የውስጥ ፓርቲ ችግሮችን፣ የውጭና የፀጥታ ሥጋቶች፣ ከተቃዋሚ ፓርቲ ጋር ያሉ ችግሮች፣ ኢኮኖሚው የነበሩበት ችግሮችን ለመፍታት አቶ መለስ ሁሌም ሕገ መንግሥቱንና ዝርዝር ሕጎችን አይከተሉም ነበር፡፡ ይልቁንም የራሳቸውን ንድፈ ሐሳቦች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም ማመቻመቾች መጠቀም ይመርጡ ነበር፡፡ ስለዚህ አቶ ኃይለ ማርያም የተኩት ቦታ በጣም ቁልፍ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ታዋቂው የሕግ ባለሙያና የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አብዱ ዓሊ ሂጅራም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ ‹‹አቶ መለስ በጣም ጠንካራ ሰው ነበሩ፡፡ እሳቸውን መተካት ከፍተኛ መፍጨርጨር ይጠይቃል፡፡ ለአቶ ኃይለ ማርያም ትልቁ ፈተና አዲስ ለውጥ ማምጣት ሳይሆን፣ ኢሕአዴግ አምጥቸዋለሁ የሚለውን ለውጥ ማስቀጠል ነው፤›› ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉት ጠበቃና የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ፣ ከአቶ መለስ ጋር ሲነፃፀሩ የአቶ ኃይለ ማርያም የኋላ ታሪክ ሥራቸውን ይበልጥ ፈታኝ የሚያደርግ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የመንግሥት መሪ ናቸው፡፡ ነገር ግን የተመረጡት በፓርቲው ነው፡፡ ስለዚህ የፓርቲውን ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ መከተል አለባቸው፡፡ እያስፈጸሙ ያሉት የፓርቲውን ትዕዛዞች ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እንደ አቶ መለስ ያልተገደበ ሥልጣን ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ከ1993 ዓ.ም. በኋላ አቶ መለስ አገር ነበሩ፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ተመሳሳይ የታሪክ፣ የተቋማትና የአደረጃጀት መሠረት የላቸውም፡፡ በአቶ መለስ በጎ ፈቃድ ብቻ ወደ ሥልጣን የመጡ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም ራሳቸው አቶ መለስን መተካት ከባድ ነገር መሆኑን ይቀበላሉ፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት በሰጡት ቃለ ምልልስ ሥራው በጣም ከባድ ቢሆንም፣ ፓርቲው ግልጽ ፖሊሲና ስትራቴጂ ስላለው ከሌሎች ጓዶች ጋር በቡድን እየሠሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በብዙ ተንታኞች አተያይ ከአቶ መለስ ጥላ ወጥተው ራሳቸውን መሆን ለአቶ ኃይለ ማርያም ከሌሎች ሁሉ የላቀ ተግዳሮት ነው፡፡

የአቶ ኃይለ ማርያም ሁለተኛው ፈተና ተደርጎ የሚቆጠረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣንና ቦታ ነው፡፡ ለፖለቲካ ሳይንቲስቱ ቦታው ፈተና የሆነው ሥልጣንና ተግባሩ በግልጽ የሚታወቅ ባለመሆኑ ነው፡፡ ‹‹የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቢሮ የተመለከቱ ግልጽ ያልሆኑ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ የቦታው ኃላፊነት በግልጽ ቢታወቅ ኖሮ አቶ ኃይለ ማርያም ብዙ ይቸገራሉ ብዬ አልገምትም፡፡ ስለ ቁርጠኝነታቸው ጥርጥር የለኝም፡፡ በዚያ ላይ እውነተኛና ታማኝ ናቸው፡፡ ያመኑበትን ነገር ለመፈጸም ቁርጠኛ ናቸው፡፡ ይሁንና ቦታው በሥርዓት የተደገፈ ስላልሆነ ጠንካራ ሰብዕና ይጠይቃል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ጠንካራ ሰብዕና አላቸው ብዬ አላስብም፤›› ሲሉ ጉዳዩን በንፅፅር አስቀምጠውታል፡፡

አቶ ሙሉጌታ፣ አቶ ኃይለ ማርያም በውሳኔ አሰጣጣቸው ቁርጠኛ ባለመሆናቸው በሥራቸው ያሉ ባለሥልጣናት እንዳይታዘዙዋቸው ማድረጉን ያምናሉ፡፡ ‹‹በእኔ እምነት በፓርቲው ውስጥ እንደ ዋና ባለሥልጣን እሳቸውን ተቀብሎ ውሳኔያቸውን ማስፈጸም ፈቃደኛ ያለመሆን አዝማሚያ ያለ ይመስለኛል፡፡ በቅርቡ ሕወሓትና ብአዴን ትልቅ ችግሮች እንዳሉባቸው ሰምተናል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም የሁለቱ ክልሎች ኃላፊዎች ተጠያቂ ናቸው ካሉ በኋላ ችግራቸውን ራሳቸው ይፈታሉ ብለውናል፡፡ ይኼ በአቶ መለስ ዘመን የሚታሰብ አይመስለኝም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ችግሩ እዚህ ደረጃ ላይ አይደርስም፡፡ ቢደርስ እንኳን በአስቸኳይ የማረሚያ ዕርምጃዎች ይወስዱ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም የገጠማቸው ሌላኛው ተግዳሮት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ከተነሱት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ጋር የተያያዙ ከዚህ ቀደም ታይተው የማያውቁ የፖለቲካ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ የፖለቲካ ሳይንቲስቱ እነዚህን ሁኔታዎች መቆጣጠር ለማንም ቢሆን አስቸጋሪ መሆኑን፣ ይሁንና የአቶ ኃይለ ማርያም ጥረቶች ተስፋ ሰጪ ሆነው እንዳላገኟቸው አመልክተዋል፡፡ ‹‹አሁን የፌዴራል ሥርዓቱ እየጎለበተ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የፖለቲካና የሕዝብ አመራር ብልህነትን ይጠይቃል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ጊዜ ደጋፊን ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚንም ጭምር ለመሳብና ለማሳመን ፍላጎት ማሳየት አለብህ፡፡ ከዚህ አንፃር ጊዜው የሚጠይቀውን አመራር አቶ ኃይለ ማርያም ስለመስጠታቸው እርግጠኛ አይደለሁም፤›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ይሁንና በእነዚህ ተግዳሮት መሀል አቶ ኃይለ ማርያም ያሳዩት አፈጻጸም የሚመሰገን እንደሆነ የፖለቲካ ሳይንቲስቱ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹አቶ ኃይለ ማርያም የኢኮኖሚ ዕድገቱ እንዲቀጥል አድርገዋል፣ መንግሥትንም በተገቢ መንገድ አስተዳድረዋል፡፡ ነገር ግን ዘለቄታ ያለው የፖለቲካ አመራር ስለመስጠታቸው እጠራጠራለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ኃይለ ማርያም አንድ የኢሕአዴግ አባል ናቸው

ከኢሕአዴግ ባህሪ በመነሳት አቶ ኃይለ ማርያም የተለየ ነገር ይፈጥራሉ ብለው እንዳልጠበቁ አቶ ሙሉጌታ ይናገራሉ፡፡ ‹‹አቶ ኃይለ ማርያም ኢትዮጵያን በፖለቲካውም ሆነ በማኅበራዊ ጉዳይ ወደ ከፍታ ይወስዷታል ብዬ አልገመትኩም፡፡ ለኢሕአዴግ የውስጥ ሰው ሳይሆኑ መጤ ናቸው፡፡ የኢሕአዴግ ሥርዓት የተመቻቸው በትጥቅ ትግሉ የተሳተፉ ሰዎች በበላይነት እንዲመሩት ነው፡፡ የቀድሞ አመራሮች በአዳዲስ ፊቶች ቢቀየሩም አሠራሩ አልተቀየረም፡፡ የኢሕአዴግ ርዕዮተ ዓለም፣ አሠራርና ተቋማት ከመንግሥት ሥርዓት በላይ ናቸው፡፡ የምትመራው በሕግ ሳይሆን በፓርቲው ድንጋጌዎች ነው፡፡ ፓርቲው ከሕግ በላይ ነው፡፡ በመንግሥትና በፓርቲው መካከል ልዩነት ስለሌለ መንግሥት በነፃነት ሊንቀሳቀስ አይችልም፤›› ብለዋል፡፡

የአቶ አብዱም አመለካከት ተመሳሳይ ነው፡፡ ‹‹የኢሕአዴግ ፖሊሲና አቅጣጫ የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ መሪን መለወጥ የማሽኑን መለዋወጫ ዕቃ እንደ መቀየር ነው፡፡ ጥያቄው ትክክለኛ መለዋወጫ ዕቃ አግኝተናል ወይ ነው፡፡ አለዚያ ማሽኑ ተመሳሳይ አገልግሎቱን መስጠት ይቀጥላል፤›› ሲሉ ጉዳዩን በምሳሌ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ አንፃር አቶ ኃይለ ማርያም የኢሕአዴግን አፈጣጠር እንዲቀይሩ መጠበቅ ያልተገባ ፍረጃ ነው በሚል የሚከራከሩ አሉ፡፡ ይሁንና አቶ መለስ በከፍተኛ ፍጥነት እየተቀያየረ ባለው ዓለም ኢሕአዴግ የያዛቸውን ተለዋዋጭ አቋሞች በመቅረፅ፣ በፓርቲውና በእሳቸው እምነት መካከል ልዩነት እስኪጠፋ ድረስ ተፅዕኖ ማድረጋቸው በሩ ለአቶ ኃይለ ማርያምም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ላለመዘጋቱ ማሳያ ነው፡፡

ለብዙ ተንታኞች የኢሕአዴግ ንድፈ ሐሳብና ተግባር አራምባና ቆቦ ነው፡፡ ስለዚህም እንደ ቅዱስ መርሆዎች የሚሰብካቸውን ጉዳዮች ሲድጣቸው መመልከት ብርቅ አይደለም፡፡ በኢሕአዴግ ላይ ሰፊ ጥናት ያደረጉ እንደ ጅያን ኒኮላስ ባች፣ ሳራ ቮሃን፣ ቶቢያስ ሃግማንና ጆን አቢኒክ ያሉ ተመራማሪዎች ከኢሕአዴግ ባህርያት በመነሳት ለተቃርኖው ማብራሪያ ለመስጠት ይሞክራሉ፡፡

ሕወሓትና ብአዴን (ያኔ ኢሕዴን) ኢሕአዴግን በ1981 ዓ.ም. ሲመሠርቱ የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም መውደቅ ጀምሮ ነበር፡፡ በ1983 ዓ.ም. ደርግን በጦርነት አሸንፈው ሥልጣን ሲይዙ ደግሞ የካፒታሊዝምን ተፅዕኖ ተቋቁሞ በሶሻሊዝም መቀጠል እጅግ ፈታኝ ጊዜ ነበር፡፡

በዚህም የተነሳ በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው የሊበራል መርሆዎችን ሳይወድ በግድ ለመቀበል ኢሕአዴግ ተገዷል፡፡ በዋነኛነት ይህን ለውጥ የተቀበለው በኪሳራ ላይ የነበረውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለመታደግ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

በ1987 ዓ.ም. ፀድቆ አሁንም በሥራ ላይ ያለው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በሊበራል አስተሳሰብ ላይ የተቀረፀውም ኢሕአዴግ ከዚህ ጫና ባልወጣበት ዘመን በመረቀቁ እንደሆነ አጥኚዎች ይከራከራሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኙ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ሁሉ ያቀፈ ነው፡፡ የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት ከመሠረታዊ መርሆዎች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ነገር ግን በሕዝቡ ውስጥ ያለው አመለካከት የኢሕአዴግ አመራሮች ጥቅማቸውን ከሕገ መንግሥቱም በላይ ያስቀድማሉ የሚል ነው፡፡ ለብዙ አስተያየት ሰጪዎች በኢሕአዴግ ንድፈ ሐሳብና ተግባር መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት መገለጫ በትጥቅ ትግሉ ዘመን የተቀረፀው የፓርቲው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ ርዕዮተ ዓለሙ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ከተመሠረተም በኋላ የቀጠለ ነው፡፡ በ1986 ዓ.ም. በመቀሌ ከተማ በተካሄደው የሐወሓት ጉበዔ አቶ መለስ ኢትዮጵያ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት አብዮታዊ ዴሞክራሲን መከተሏ የግድ ነው ብለው ነበር፡፡

የኢሕአዴግ ተቺዎች የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለምን ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ጀርባ ያለ ሌላ ሕገ መንግሥት ነው ይሉታል፡፡ ይሁንና የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ትርጉም አባላቱ ራሱ እንዳልገባቸው የሚያሳዩ በርካታ ጥናቶች አሉ፡፡ ጂያን ኒኮላስ ባች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ኮሌኒኒዝም፣ ማርክሲዝም፣ ማኦይዝምና ሊበራሊዝም ተቀላቅሎ የተቀረፀ ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን ተምሳሌታዊ የሆነ የፖለቲካ መሣሪያ እንጂ ትክክለኛ አብዮታዊ ፕሮግራምን አያመለክትም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ላይ ያለው የትርጉም ውዝግብ እንዳለ ሆኖ የርዕዮተ ዓለም መገለጫ የሆኑ ባህርያት ግን አሉ፡፡ አንድ መሪ ፓርቲ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና በማኅበረሰቡ ላይ አውራ ሚና ያለው በፓርቲ የሚመራ መንግሥት፣ እንዲሁም የሰፊውን ሕዝብ ንቃተ ህሊና በማሳደግ ለአብዮት የሚያዘጋጁ ልሂቃን ዋነኛ መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ በእነዚህ ባህርያቱም የጠቅላይነት ሚና የተላበሰ ነው፡፡

ርዕዮተ ዓለሙ የመሪ ፓርቲው የውሳኔ አሰጣጥ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ እንዲመራም ያስቀምጣል፡፡ ይህም ውስጣዊ መሰነጣጠቅን ለማስወገድ ወሳኝ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በዚህም የተነሳ በኢሕአዴግ ሥር ያሉ ሁሉም ድርጅቶች በዚሁ መርህ ይሠራሉ፡፡

ርዕዮተ ዓለሙ በፓርቲና በመንግሥት መካከል ልዩነት እንዳይኖር አድርጓል ተብሎም ይተቻል፡፡ በዚህም የመንግሥት አስተዳደርና ሲቪል ሰርቪስ ከፓርቲ ተፅዕኖ ውጪ እንዳይሆኑ ማድረጉም ይወሳል፡፡

የኢሕአዴግ ርዕዮተ ዓለም ለመሪ ድርጅት ባለው ልዩ ቦታ ራሱ ኢሕአዴግ ያስተዋወቀው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ቀስ በቀስ እየሞተ ለጊዜም ወረቀት ላይ መቅረቱ፣ ኢሕአዴግ ሥልጣን በመጋራት ስለማያምን የፖለቲካ ብዝኃነትንና የሲቪልና የፖለቲካ መብቶችን እንደሚገፉም ብዙዎች ያምናሉ፡፡ በዚህም ሒደት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ነፃና ገለልተኛ መንግሥታት ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሲቪል ማኅበራት፣ ተቺዎች፣ ነፃ ሚዲያ፣ ነፃና ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና የንግድ ማኅበራት ተጠያቂዎች መሆናቸውን የተለያዩ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡

ከእነዚህ የኢሕአዴግ ባህርያት አንፃር ኃይለ ማርያም እንዲያመጡ የተጠበቁትን ለውጥ ለማምጣት እንደሚቸገሩ የሚከራከሩ በርካታዎች ናቸው፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ግን የኢሕአዴግ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ይዞታ ትክክለኛ መስመር ይዟል ባይ ናቸው፡፡ ‹‹የዴሞክራሲ ባህል መገንባት ጊዜ ይወስዳል፡፡ ነገር ግን እኛ ትክክለኛ ጎዳና ላይ ነን፤›› ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ላይ መንግሥታቸው የፈጠረው ጫና የለም ሲሉም ይከራከራሉ፡፡ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ሌሎች ድርጅቶች በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ ከአመፅ ውጪ ተቃውሞ ማሰማት፣ የፈለጉትን መናገር፣ ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግና መንግሥት ላይ ጫና ማሳደር ይችላሉ፡፡ ሁሌም ቢሆን ልዩነቶች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፈታት የሚችሉ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ከቃላቸው ውጪ ያሉትን ነገር በተግባር ማሳየት እንደሚሳናቸው በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ፡፡

በአቶ መለስ ዘመን የኢሕአዴግ ድርጅታዊ ታክቲኮች ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን የሚያስተናግዱ ነበሩ፡፡ የሕገ መንግሥቱ ኤክስፐርት አቶ ኃይለ ማርያም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንደሚችሉ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹የኢሕአዴግ አሠራሮች አመራርን አስቸጋሪ ማድረጋቸው አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን ለውጥ ማምጣትን የማይቻል አያደርጉም፡፡ አሁን ሁኔታዎች ተቀይረዋል፡፡ አገሪቱ ፈተናዎች ገጥመዋታል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ለጠንካራ መሪዎች መልካም አጋጣሚ ይፈጥራሉ፡፡ በተለመደው ጊዜ የማይታሰቡ ነገሮችን ለመምከር ያስችላሉ፡፡ አሁን አገሪቱ ሁኔታዎችን ገምግሞና ተንትኖ አሳማኝ ትርክት የሚያቀርብ መሪ ትፈልጋለች፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም የራሳቸውን አዲስ ራዕይ ለማምጣት ልዩ አጋጣሚ ተፈጥሮላቸው ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ኤክስፐርቱ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ግልጽነት የጎደለው መሆን ለተለዋዋጭ ሁኔታዎች በር ይከፍታል ብለዋል፡፡ ርዕዮተ ዓለሙ ላይ አሳማኝ ለውጥ ለማምጣት የፓርቲውን የ15 ዓመታት ጉዞ ባደረጉ ወቅት አጋጣሚ ተፈጥሮ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ግምገማው ጥልቀት አልነበረውም፤›› በማለት እንዳልተጠቀሙበት አመልክተዋል፡፡

ለፖለቲካ ሳይንቲስቱ አቶ ኃይለ ማርያም በመጪዎቹ ዓመታት የተሻለ አመራር ለማሳየት ሁለት አማራጮች አሉዋቸው፡፡ እነዚህም ጠንካራ ሰብዕና መገንባት ወይም ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ናቸው፡፡ ‹‹አቶ ኃይለ ማርያም ሥርዓትና ተቋማትን መገንባት ይችላሉ፡፡ ይህ ከሆነ የአገሪቱ ደኅንነት በግለሰቦችና በመሪዎች የፖለቲካ ብስለትና ብቃት ላይ አይመሠረትም፡፡ አሁን የፓርቲዎች እርስ በርስ ግንኙነት እየተቀየረ ነው፡፡ ኢሕአዴግን ያለ ፖለቲካ ስሌት መምራት አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ሳይንቲስቱ የአቶ ኃይለ ማርያም የለውጥ ፍላጎት እውነተኛ ቢሆንም፣ ይህን የሚያስችሉ በርካታ አጋጣሚዎችን ሳይጠቀሙ በማሳለፋቸው ግን ይተቿቸዋል፡፡ ‹‹በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሹመት፣ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ሹመትና በፀረ ሙስና ሹመትና አሠራር ለውጥ ላይ የተሻለ ነገር መሥራት ነበረባቸው፤›› ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ ግምገማ ያካሄደው ኢሕአዴግ አመራሮቹ በሙስና ተግባራት መሠለፋቸውን ማረጋገጡ ይታወሳል፡፡ ኤክስፐርቱ፣ ‹‹ይህ በመሪው ላይም ተፅዕኖ አለው፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም የፓርቲው ሊቀ መንበርና መሪ ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ እየበሰበሰ ያለው በእሳቸው አመራር ነው፡፡ በግላቸው በሙስና ላይሳተፉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ለሌሎችም ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠራቸውም ተጠያቂ ናቸው፡፡ በሕገ መንግሥቱ ለተቀመጠው ሥልጣንና ኃላፊነታቸው ዜጎች ተጠያቂ ማድረግ የሚችሉት እሳቸውን ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቅምን መሠረት ያደረገ ሹመት የኃይለ ማርያም ትሩፋት ይሆን?

ሕዝቡ ነገሮች እየሄዱ ባለበት ሁኔታ ላይ መሠረታዊ ቅሬታ እንዳለው በተለያዩ መድረኮች ገልጿል፡፡ ብቃት የሌለው አመራር ከእነዚህ የቅሬታ ምንጮች አንዱ ነው፡፡ መንግሥትም ለችግሩ አሉኝ ካላቸው የመፍትሔ ሐሳቦች አንዱ በመጪዎቹ ሳምንታት አቅምን መሠረት አድርጌ እንደገና አዋቅረዋለሁ ያለው ካቢኔ ነው፡፡ ይህ በፖለቲካ ታማኝነት ብቻ ተመሥርቶ ተዋቅሯል፣ በዚህም ተገቢ አገልግሎት እየተሰጠ አይደለም ለሚለው ትችት መልስ ከሆነ የሚበረታታ እንደሆነ ብዙዎች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

ዶ/ር ዳኛቸው ከልምድ አንፃር የኢሕአዴግ ሹመቶች ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ ለፓርቲው የሥልጣን ፍላጎት ቅድሚያ የሚሰጡ እንደሆኑ ተከራክረዋል፡፡ በተመሳሳይ አቶ አብዱም የሒደቱን ከልብ መሆን ተጠራጥረዋል፡፡ አቅምን መሠረት ያደረገ ቢሮክራሲ መገንባት ጊዜ እንደሚጠይቅም ሞግተዋል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ በጉዳዩ ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ ቃል የገባው በሐምሌ ወር 2008 ዓ.ም. ነው፡፡ አሁን በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ለውጦችን አስታውቃለሁ ብሏል፡፡ ይኼ ጊዜ እንኳን መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንኳን ለመመካከር አያስችልም፤›› ብለዋል፡፡

ኢሕአዴግ አቅምን መሠረት ያደረገ ቢሮክራሲ ከመፍጠር በተጨማሪ፣ ከኢሕአዴግ አባል ያልሆኑ ነፃና ገለልተኛ ኤክስፐርቶችንም የማካተት ዕቅድ እንዳለው ገልጿል፡፡ አቶ አብዱ፣ ‹‹ነፃና ገለልተኛ ቢሮክራቶች የኢሕአዴግን አቅጣጫ፣ መስመርና ቋንቋ ካልተረዱ ሊቆዩ አይችሉም፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት በመሥራትና የኢሕአዴግን አሠራር በመከተል መካከል ግጭት መኖሩም አይቀርም፤›› በማለት አክለዋል፡፡

የፖለቲካ ሳይንቲስቱ፣ ‹‹ይኼ ለጊዜው የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተስፈኛ ያደርግ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሥርዓቱ በተመሳሳይ መንገድ ከተጓዘ የሰዎች ለውጥ ረጅም ርቀት አይወስደንም፤›› ብለዋል፡፡                

  አቶ ሙሉጌታ ግን ለውጡ የመጣበት ጊዜ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ‹‹ከሌሎች የለውጥ ፕሮግራሞች ጋር ከመጣ ጥሩ ነው፡፡ ኢሕአዴግ የፖለቲካና የሕግ ተቋማትና ሥርዓት ላይ ለውጥ ለማድረግ ምን ያህል ዝግጁ ነው? የፓርቲ አሠራሮች ከሕግ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ከሆነ የዓለም ምርጥ ብሩህ አእምሮዎች ካቢኔያችንን ቢሞሉትም ለውጥ አናመጣም፡፡ ለቴክኖክራቶች አስቻይ ሁኔታዎች ቀድመው ሊዘጋጁ ይገባል፡፡ ከዚያ ውጪ አንድ ኃላፊ ወይም ሚኒስትር ከኃላፊነት ሲነሳ አማካሪ በመሆን የሚሾምበትን አሠራር መንግሥት ሊያጤነው ይገባል፤›› በማለት ሒደቱ ላይ ብዙም ተስፋ እንዳልጣሉ ገልጸዋል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም ለአመራር እጅግ ጠቃሚው ነገር የሕዝብ አመኔታ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ በእርሳቸው ላይ የነበረው አመኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መሆኑን በተለያዩ መንገዶች ይገልጻል፡፡ በሚገቧቸው በርካታ ቃሎች ላይ ተግባር የማይታከል ከሆነ የግል ሰብዕናቸው መጠለያ የማይሆንበት ቀን መምጣቱ አይቀርም ይላሉ፡፡ 

Standard (Image)

በኢሬቻ ክብረ በዓል ለደረሰው የንፁኃን ዜጎች ሕልፈት ተጠያቂው ማነው?

$
0
0

የምሥራቅ ኦሮሚያዋ ከተማ ቢሾፍቱ ቅዳሜ ምሽት ላይ አሸብርቃ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበትን የኢሬቻ ክብረ በዓል ለማስተናገድ ተዘጋጅታለች፡፡

ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የመጡ በኦሮሞ ባህላዊ ልብሶች ያጌጡ ወጣቶች እየተዘዋወሩ ብሔሩን የሚያሞግሱ ዜማዎችን ሲያሰሙ ነበር፡፡

በከተማዋ አመሻሹ ላይ የደረሰ እንግዳ በጭራሽ መኝታ አልጋ ሊያገኝ አይችልም ነበር፡፡

ማምሻውን ሁሉም መዝናኛ ቤቶች በደስታና በጭፈራ ተሞልተዋል፡፡ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ባያቸው የምሽት መዝናኛ ቤቶች ዓመታዊውን የኢሬቻ በዓል ለማክበር ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የመጡ ወጣቶች ብሔሩን የሚያወድሱ ዘፈኖች፣ እንዲሁም ስለደረሱ ጭቆናዎች የተዜሙ ዜማዎች በሚከፈቱበት ወቅት ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው በኅብረት ያዜሙ ነበር፡፡

ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች ሌሊቱን ሙሉ ሲደሰቱ ያሳለፉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ለእሑድ አጥቢያ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ ካረፉባቸው ሆቴሎችና ሌሎች ማረፊያ ቤቶች ወጥተው በቡድን በቡድን እየዘመሩ ክብረ በዓሉ ወደሚከናወንበት ሆራ አርሰዲ ሲተሙ ተስተውሏል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል በሁሉም የበዓሉ ታዳሚ ወጣቶች ላይ ፍተሻ እያደረገ ነበር ወደ ክብረ በዓሉ እንዲገቡ የሚፈቅደው፡፡ በዋዜማው ምሽት መዝናኛ ቤቶች ከነበሩ ጭፈራዎች አዝማሚያ በመነሳት በበዓሉ ላይ ተቃውሞ ሊኖር እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡

ለእሑድ አጥቢያ ከንጋቱ 11 ሰዓት በኋላ እጃቸውን በማጣመር የኦሮሞ ሕዝብ የተቃውሞ ምልክት የሆነውን “X” የሚያሳዩ ወጣቶችን አልፎ አልፎ ለመመልከት ተችሏል፡፡

ባህላዊውን የምሥጋና ሥነ ሥርዓት የሆራ ሐይቅን በመባረክና ቄጤማ ወደ ሐይቁ በመንከር የብሔሩ ባህላዊ አመራሮች አባ ገዳዎች ቢያስጀምሩም፣ ጥቂት በዕድሜ ገፋ ካሉት በስተቀር የተከተላቸው አልነበረም፡፡

በአካባቢው የተገኙት ወጣቶች እጃቸውን በማጣመር ተቃውሟቸውን ክልሉን በሚያስተዳድረው የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ላይ ሲያሰሙ ነበር፡፡ እንዲሁም ʻወያኔ በቃን፣ ነፃነት እንፈልጋለን፣ የኦሮሞ ሕዝብ የተከበረ ነው፣ ራሱን ማስተዳደር አለበት…ʼ የሚሉ መፈክሮችን በተደጋጋሚ ያሰሙ ነበር፡፡

እጅግ በጣም በርካታ የሚባሉት ተቃውሟቸውን እያሰሙ ጐን ለጐን በሞባይል ስልኮች ተቃውሟቸውን፣ እንዲሁም ሌሎች ቡድኖች የሚያደርጉትን ተቃውሞ ሲቀርፁ ተስተውሏል፡፡

በዚሁ በሐይቁ አካባቢ ተቃውሞው ድምቅ ብሎ መቀጠሉ ያሳሰባቸው የልዩ ኃይሉ ፀጥታ አስከባሪዎች ሐይቁን ወደከበቡት ተራራማ ቦታዎች ላይ በመቅረብ መታየታቸው የበለጠ ተቃውሞው እንዲጋጋል አድርጐታል፡፡

አባ ገዳዎች በሐይቁ ዳርቻ ባህላዊ ሥርዓቶችን አከናውነው ወደተዘጋጀላቸው መድረክ ሲመለሱ በዚሁ አካባቢ የልዩ ኃይሉ ፖሊሶች በረድፍ በመቆም ባበጁት የተከለለ ቦታ ላይ፣ ታዳሚዎች በተመሳሳይ ግለት ከንጋቱ 12 ሰዓት የጀመረውን ተቃውሞ በዚህ ሥፍራም ቀጥለውበታል፡፡

‹‹ወያኔ አይበጀንም››፣ ‹‹ኦፒዲዮ በቃን››፣ ‹‹ኦሮሞን የሚያስተዳድረው ኦሮሞ ብቻ ነው…›› የሚሉ መፈክሮችን በኦሮሚኛ ያሰሙ ነበር፡፡

አልፎ አልፎ በአማርኛ ‹‹ወያኔ ሌባ›› ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ በኦሮሚኛ ቋንቋ ‹‹ዲʼኔ - ዲኔ ዲኔ››፣ “ኑገʼኤራ”፣ ‹‹ቢሊሱማ›› የሚሉ መፈክሮችን ያሰሙ ነበር፡፡ የእነዚህ መፈክሮች ትርጓሜም ‹‹እምቢ››፣ ‹‹በቅቶናል›› እና ‹‹ነፃነት እንፈልጋለን›› የሚሉ ናቸው፡፡

አንዳንድ ቡድኖች ወጣት ሴቶችን እንኮኮ አድርገው ሴቶቹ ወጣቶች አባ ገዳዎቹ እንደማይወክሏቸው የሚያሰሙትን መፈክር ይደግሙ ነበር፡፡ በመድረኩ ላይ ከተሰበሰቡት አባ ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች መካከል የቀድሞ አባ ገዳ አሁን ደግሞ ‹‹ዮባ›› ተብለው የሚጠሩትን በዕድሜ ከሁሉም ገፋ ያሉትን ዮባ ስለሺ ዳባ ቱሉ እየሆነ ስላለው ሪፖርተር ጥያቄ አቅርቦላቸዋል፡፡

ዮባ ስለሺ ዳባ ለጥያቄው ምላሽ መስጠት የጀመሩት ስለኢሬቻ በዓል ታሪካዊ ትርጓሜና ፋይዳ በማብራራት ቢሆንም፣ ‹‹ዛሬ እየሆነ ያለው ከየት መጣ? መልዕክቱ ምንድነው? የሚለውን መንግሥት መመርመር አለበት፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኢሬቻ ማለት የተጣላው የሚታረቅበት፣ ለተጋደለው ጉማ (ካሣ) ተከፍሎ ለዕርቅ ‹‹መልካ›› የሚወጣበት ቀን መሆኑን የገለጹት አቶ ስለሺ፣ ‹‹መልካ ማለት የፍቅር፣ የመታረቂያ፣ የወደፊት ሰላማችንን መለመኛ ቀን ነው፡፡ ምክንያቱም ታንክና መድፍ፣ ጄት አይደለም ያለን፡፡ ስለዚህ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ሰጥተኸናልና እሷኑ ያዝልን፣ ድንበሯን ጠብቅልን ብለን የምንለምንበት ቀን ነው፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት የአገር ሽማግሌዎችንና የእምነት አባቶችን አሰባስቦ ምንድን ነው ይኼ መልዕክት ብሎ መፍትሔ መስጠት እንዳለበት ያሳሰቡት ዮባ ስለሺ፣ ‹‹መፍትሔ ቶሎ ካልተሰጠው ሌላ መልክ የሚያመጣ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ጠጋ ብሎ ተነጋግሮ መፍትሔ መምጣት አለበት፤›› ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

ሪፖርተር ዮባ ስለሺ ዳባን እያነጋገረ በነበረበት ወቅት የታዳሚዎቹ ተቃውሞም ያለማቋረጥ ተጋግሎ እንደቀጠለ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ እየተከናወነ መሆኑን እንጂ ስለሚፈጠረው መገመት ያልቻሉት አዛውንቱ አቶ ስለሺ፣ ‹‹በዚህ በዓል እንደዚህ ዓይነት ነገር ታይቶ አያውቅም፡፡ ቢሆንም ግን ከመታፈን ይሻላል፡፡ ከታፈነ መርዝ ነው የሚሆነው፡፡ አሁን ግን ወጥቷል፡፡ ከወጣ ደግሞ ቶሎ ብሎ መፍትሔ መፈለግ ግድ ይላል፡፡ እኛም አንተኛም፤›› ብለዋል፡፡

ተቃውሞው አሁንም ቀጥሏል፡፡ አንዳንድ የቡድን መሪዎች በልዩ ኃይሉ ከታጠረው ክልል ውስጥ ፖሊሶቹን እያስፈቀዱ ለውጭ የሚዲያ ተቋማት ስለተቃውሟቸው ለመግለጽ ወደ መድረኩ እየተጠጉ ይመለሳሉ፡፡

ከየት አካባቢ እንደመጡ የሚገልጽ ‹‹ባነር›› የያዙ ሁለት ወጣቶች ወደ መድረኩ ወጥተው ሲመለሱም የልዩ ኃይሉ ፖሊሶች በትህትና በኦሮሚኛ በማነጋገር እንዳይደግሙት ከማሳሰብ ውጪ፣ ነገሮችን በጣም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሲመሩ ነበር፡፡

በዚህ ሁሉ ሒደት ውስጥ ባህላዊው የኢሬቻ ሥነ ሥርዓት መከበር አልተጀመረም፡፡ አባ ገዳዎቹ ለምን ሥርዓቱን ለማስጀመር እንደማይሞክሩ ሪፖርተር አንድ የአካባቢውን ተወላጅ ሲጠይቅ ዋናው አባ ገዳ ሰንበቶ የተባሉት አልተገኙም የሚል ምላሽ ተሰጥቶታል፡፡

በነገሮች መራዘም እንዲሁም የሚጠበቁ አባ ገዳዎች ወይም ባለሥልጣናት መገኘት አለመቻል የተሰላቹት በመድረኩ የተገኙት አባ ገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች፣ እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች መድረኩን ጥለው ለመውረድ ሲሞክሩ የበዓሉ አስተባባሪዎች እንዲቀመጡ አድርገዋቸዋል፡፡

በዚህ ወቅት የበለጠ ተቃውሞው ተቀጣጥሏል፡፡ አባ ገዳዎቹ በበዓሉ ሥነ ሥርዓት መሠረት ምርቃት እንዲካሄድ እንዲጠይቁ በሥነ ሥርዓቱ አስተባባሪዎች በተመከሩት መሠረት፣ ድምፅ ማጉያ ይዘው ድምፅ ማሰማት ቢጀምሩም የሚያዳምጣቸው ሊያገኙ አልቻሉም፡፡

በልመና እንዲያዳምጧቸው ቢጠየቁም ማንም ሊሰማቸው አልቻለም፡፡ አንድ የፕሮግራሙ አስተባባሪ ማይክራፎን ተቀብሎ ታዳሚዎች እንዲረጋጉ ቢጠይቅም የሚሰማው አልተገኘም፡፡ ከታዳሚዎች መካከል ቀስ ብሎ መድረኩን የተቀላቀለ አንድ ወጣት ማይክራፎኑን ከሌላው ወጣት አስተናባሪ ሲቀበል ተመሳሳይ የማረጋጋት ሥራ ለመሥራት እንጂ ቀጥሎ ያደረገውን የገመተ ያለ አይመስልም፡፡

‹‹Down Down Weyane›› (ውድቀት ለወያኔ) ‹‹Down Down TPLF›› (ውድቀት ለሕወሓት) የሚል መፈክሮችን በማይክራፎን ማሰማት ሲጀምር፣ ሁሉም ታዳሚዎች በአንድነት ተቀብለው ያስተጋቡ ጀመር፡፡ ይህ ክስተት ሁሉንም አንድ አድርጐ የበለጠ ተቃውሞው ተቀጣጠለ፡፡

ከወጣቱ ላይ ማይክራፎኑን ለመንጠቅ አስተናባሪዎችና ፖሊሶች ተረባረቡ፡፡ አንዳንድ ወጣቶች ይህንን ድርጊት የውኃ ላስቲክ በመወርወር ለመቃወም ሲሞክሩ ሌሎቹ የሚወረውሩትን ሲገስጹ ተስተውሏል፡፡

ነገሮች አስቸጋሪ ሆነው እየተለወጡ መምጣታቸውን ያስተዋለው የልዩ ኃይሉ ኮማንደር፣ ‹‹ባለቤት አብጁለት ባለቤቱ ማነው?›› በማለት ከሌላ ሲቪል ከለበሰ ባልደረባው ጋር በአማርኛ ሲነጋገር ተሰምቷል፡፡

አባ ገዳዎቹና ሽማግሌዎቹ እንዲሁም የእምነት አባቶቹ መድረኩን ለቀው ወጡ፡፡ ከዚህ በኋላ በርከት ያሉ ወጣቶች መድረኩን ተቆጣጠሩ፡፡ ይሁን እንጂ የልዩ ኃይሉ ፖሊሶች በሰላማዊ መንገድ አስወርደዋቸዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሌላ በርከት ያሉ ወጣቶችን የያዘ ቡድን ከስብስቡ ጀርባ በመነሳት አባላትን እያበዛ ሰላማዊ የሆነውን የተቃውሞ መፈክር እያሰማ ዳግም ወደ መድረኩ አመራ፡፡ ይህ ቡድን እጅግ ብዙ ቁጥር ያለው ነው፡፡

ከዚህ በኋላ ነገሮች በዚህ መልኩ እንዲቀጥሉ ባልፈቀዱት የልዩ ኃይሉ ኃላፊዎች ትዕዛዝ መሠረት ፖሊሶቹ አስለቃሽ ጭስ መፈናፈኛ ወዳልነበረበት የሕዝብ ስብስብ ተኮሱ፡፡

በበርካታ መቶ ሺዎች የሚቆጠረውን ታዳሚ የያዘው የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል ማክበሪያ ቦታ በሁለት አቅጣጫዎች ጥልቅ ተፈጥሯዊ ገደሎች እንዳሉት ቢታወቅም በአጥር አልተከለሉም፡፡

በተተኮሰው አስለቃሽ ጭስ ድምፅ ተደናግጦ ራሱን ለማዳን የተነቃነቀው ታዳሚ የፈጠረው ግፊት በገደሎቹ ጠርዝ አቅራቢያ ለነበሩት የበዓሉ ታዳሚዎች አሳዛኝ አጋጣሚን ፈጠረ፡፡ በበርካታ መቶዎች የሚቆጠሩት ድንጋያማ ከሆኑት የገደሎቹ ግድግዳዎች እየተጋጩ ቁልቁል ወረዱ፡፡   

እርስ በርስ በመደራረባቸውና በመተፋፈጋቸው መተንፈሻ ያጡት በሕይወት መውጣት አልቻሉም፡፡

ከላይ ያሉት ራሳቸውን ለማዳን ሲሞክሩ ጥቂት ተረጋግተው በአካባቢው የቀሩ ወጣቶችንና የልዩ ኃይሉን እጆች ዕርዳታ አግኝተው ለመትረፍ ችለዋል፡፡

ዕርዳታ ለመስጠት የነበሩት ጥቂት የቀይ መስቀል አምቡላንሶች ቅድሚያ በሕይወት ያሉትን እያስቀደሙ ወደ ሕክምና መስጫ ጣቢያዎች ተራወጡ፡፡ በርካታ አስከሬኖች ከጉድጓዶቹ ወጥተው ሜዳ ላይ ተዘርረዋል፡፡

በተተኮሰው አስለቃሽ ጭስ ተደናግጠው የሮጡት አብዛኛዎቹ ታዳሚዎች ወደ ሥፍራው ዳግም አልተመለሱም፡፡ ይልቁንም ራሳቸውን አረጋግተው ተቃውሞአቸውን ዳግም እያሰሙ ወደ ከተማው መዝለቃቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተለምዶ ‹‹ሠርክል›› ተብሎ በሚጠራው የቢሾፍቱ ዋና አደባባይ አካባቢ የልዩ ኃይሉ ፖሊሶች በድጋሚ በአስለቃሽ ጭስ እንደበተኗቸው የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ወደዚህ አደባባይ ሪፖርተር በደረሰበት ወቅት የፌዴራል ፖሊስ አድማ በታኝ ፖሊስ አባላት በክፍት መኪና ተጭነው ቅኝት ሲያደርጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ታዝቧል፡፡      

ከተማው ውስጥ የነበረው አብዛኛው ሕዝብ በኢሬቻ ክብረ በዓል ቦታ ስለተፈጠረው አደጋ አያውቁም ነበር፡፡ በየምግብ ቤቱ ደስታና ጭፈራ ይታያል፡፡

ሪፖርተር ቢሾፍቱ ሆስፒታል በደረሰበት ወቅት የሚታየው ነገር ዘግናኝ ነበር፡፡ በሁለት የዩኒሴፍ ድንኳኖች ቤተሰቦቻቸው እንዲለዩዋቸው የተንጋለሉ ከፈን ያልለበሱ በርካታ አስከሬኖች ይታያሉ፡፡ ሪፖርተር ባደረገው አጭር ቅኝት በርካታ አስከሬኖችን ለማየት ችሏል፡፡ አስከሬኖቹ ምንም ዓይነት ጉዳት አይታይባቸውም፡፡ አንድ ወጣት ላይ ብቻ ከአፉ ጐን የደረቀ ደም ይታያል፡፡

ሕይወታቸውን ያጡት ተሳታፊዎች ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ በመሆናቸው ጓደኛው የቀረበት ወይም የተጠፋፋ ወደዚህ ሆስፒታል ይመጣል፡፡ እየመጡ ያዩትን ለማመን ከብዷቸው እንዲሁም አቅም ከድቷቸው መሬት ይቀመጣሉ፡፡ አንዳንዶች የተረጋጉት አስከሬኖችን ሲገንዙና ትራንስፖርት ሲኮናተሩ ታይቷል፡፡   

ከቢሾፍቱ ሆስፒታል ውጪ ወደተለያዩ የሕክምና ተቋማት ያመሩ መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በበኩሉ 110 ተጐጂዎችን ማመላለሱን አስታውቋል፡፡

በተፈጠረው አሳዛኝ አጋጣሚ በእጅጉ ማዘኑን የገለጸው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሟቾች ቁጥር 55 መሆኑንና ከ100 በላይ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሕክምና ማግኘታቸውን ገልጿል፡፡

ለዕልቂቱ ተጠያቂው ማነው?

አሳዛኝ የዜጐች ሕልፈት በተከሰተበት መስከረም 22 ቀን 2009 ምሽት ላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በመንግሥት ቴሌቪዥን በኩል መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተቃውሞውን ያነሳሱ ባሏቸው ጥቂት ኃይሎች ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል፡፡ በክልሉ መንግሥት በኩልም ሆነ በፌዴራል መንግሥት በኩል ከፍተኛ የፀጥታ ዝግጅት ስለመደረጉ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ የፀጥታ ኃይሉ አንዲትም ጥይት አለመተኮሱንና በተሰጠው መመርያ መሠረት ዝግጅት አድርጐ የክብረ በዓሉ ሒደት ሰላማዊ እንዲሆን በማድረጉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ የተከሰተው የሰዎች ሕልፈትም በመረጋገጥና በመተፋፈግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ተቃውሞውን በመበተን የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ውጤታቸው ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን በወቅቱ የፀጥታ ኃይሉን የሚመሩት ኃላፊዎች ያጤኑት አይመስልም፡፡

በፖሊሶች የተተኮሰው አስለቃሽ ጭስ ቢሆንም ከፍተኛ ፍንዳታ የሚያሰማና በመጀመሪያም ከጭሱ ይልቅ ድንጋጤን የሚፈጥረው ድምፁ መሆኑን በዚህ የተነሳ ምን ይከሰታል የሚለውን በአግባቡ ኃላፊዎቹ የተረዱት አይመስልም፡፡ በዚህ ቅጽበት ውስጥ ለማድረግ የሞከሩትም ስህተታቸውን ተረድተውት የሚመስል ነበር፡፡

በተሽከርካሪዎቻቸው በፍጥነት በመንዳት ‹‹ተረጋጉ በዓላችን ነው ተረጋጉ›› እያሉ ለማረጋጋት ሞክረዋል፡፡ ይህ ሙከራቸው ግን የንፁኃንን ሕልፈት ወደኋላ ተመልሶ ሊታደግ አልቻለም፡፡    

 

     

 

Standard (Image)

የሥልጣን ሽግሽግና ሹም ሽር ለወቅታዊው የፖለቲካ ቀውስ ምን ፋይዳ አለው?

$
0
0

የአዲስ አበባና የዙርያው የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው የኦሮሞ ሕዝብ ተቃውሞ አሁን መልኩን ቀይሯል፡፡

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በወልቃይት የማንነትና የወሰን ለውጥ ጥያቄ ጋር ተያይዞ ከ2008 ዓ.ም. አጋማሽ በኋላ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ የበርካቶችን ሕይወት ከቀጠፈ በኋላ መልኩን ቀይሮ፣ የተለያዩ የአማራ ከተሞችና አካባቢዎች በመንግሥትና በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሟቸው ተሰምቷል፡፡

ከ60 በመቶ በላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚወክሉት እነዚህ ሁለት ክልሎች የተቃውሞ አንድነት በመፍጠር አንዱ ጋ ጋብ ሲል በሌላው በኩል እየተቀጣጠለ ተቃውሞው እየተሰማ ይገኛል፡፡

በበርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎች አንፃራዊ መረጋጋት በሚስተዋልበት በአሁኑ ወቅት፣ በኦሮሚያ በርካታ ከተሞች የተቀሰቀሰው ግጭትና ተቃውሞ ማሳያ ነው፡፡

ባለፈው እሑድ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ የኦሮሞ ሕዝብ ፈጣሪውን በሚያመሰግንበት የኢሬቻ በዓል ላይ የተገኙ ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች በስፋት ያስተጋቡት ተቃውሞን ተከትሎ፣ የደረሰው አሳዛኝ የወጣቶች ሕይወት ሕልፈት በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች የንብረት ውድመትን እያደረሰ ያለ ሌላ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡

በኢሬቻ በዓል ላይ ለመታደም የተገኙ በአንድ ድምፅ ‹‹ወያኔ በቃን››፣ ‹‹ኦሕዴድ በቃን›› እያሉ በአንድነት በማስተጋባት ጥያቄያቸው ምን እንደሆነ በትክክል ለማስገንዘብ ሞክረዋል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ ባህላዊ ሥርዓትን ተጠቅመው ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩ በበርካታ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ታዳሚዎች ለመበተን የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ በተኮሰው አስለቃሽ ጭስ በመደናገጥ በተፈጠረው መገፋፋት፣ በርካቶች ገደል ውስጥ ገብተው መሞታቸው በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች የበለጠ ቁጣ ቀስቅሷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በዚህ ቁጣ ወደ አደባባይ የወጡ ወጣቶች የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮችን ንብረት ከማውደም በላይ ብሔር ተኮር ጥቃቶች እየደረሱ ነው፡፡

ተቃውሞው ከተቀሰቀሰ ከዓመት በላይ ያስቆጠረ ከመሆኑ ባሻገርም ስፋቱ እየገዘፈ ይገኛል፡፡

የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ተቃውሞዎች በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በተቀጣጠለበት በነሐሴ ወር ላይ ተሰብስቦ የችግሩ መንስዔ ናቸው ያላቸውን መለየቱ ይታወሳል፡፡

ማዕከላዊ ኮሚቴው ነሐሴ 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫም፣ ‹‹ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ከሚፈታተኑት ችግሮች መካከል አንዱ የመንግሥትን ሥልጣን የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ከማዋል ይልቅ፣ የግል ኑሮን መሠረት አድርጐ የመመልከትና በአንዳንዶችም ዘንድ የግል ጥቅምን ማስቀደም ይታያል፤›› ብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የሕዝብ ፍላጎትና የሥራ አጥነት ችግርን በፍጥነት አለመፍታት፣ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለተንሰራፋው የሕዝብ ተቃውሞ ምክንያቶች መሆናቸውን ገምግሟል፡፡

በተጨማሪም ከሥራ አስፈጻሚው ጀምሮ የትምክህተኝነትና የጠባብነት አስተሳሰብና ጥገኝነት መኖራቸውን፣ እነዚህንም በጥብቅ በመታገል እንዲተጉ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝርዝር ዕቅዶችን ማዘጋጀቱን በመግለጫው መግለጹ ይታወሳል፡፡

‹‹እነሆ ዛሬ ድርጅታችን በዚህ ችግር ምክንያት የተፈጠረውን አደጋ መሠረታዊ መንስዔዎች በሌላ በማንም ሳያሳብብ በመንግሥትና በድርጅት ማዕቀፍ የሚታይ ቀዳሚ ችግር እንደሆነ ተገንዝቧል፤›› የሚለው ይኸው መግለጫ፣ ‹‹ችግሩን ለመፍታት የሚደረገው እንቅስቃሴ በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ላይ በሚጠበቁ የለውጥ ፕሮግራሞች ተጠናክሮ ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል፤›› ብሏል፡፡

ችግሩን ለመፍታት ትኩረት የተደረገው በገዥው ፓርቲ ላይም ሆነ በመንግሥት መዋቅር አስፈጻሚዎች ላይ ሹም ሽርና የሽግሽግ ለውጥ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ለውጥ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ብቃት ላይ መሠረት ያደረገ ምደባ ማድረግን፣ ለዚህም የፓርቲ አባልነት ቦታ እንደማይኖረው ተገልጿል፡፡

ይህ ሹመትና ሽግሽግ ሰኞ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ፓርላማው ሥራ ከጀመረ በኋላ በቀጣዮቹ የፓርላማው መደበኛ ስብሰባዎች የሚጠበቅ ነው፡፡

ኢሕአዴግ የሕዝቡን ጥያቄ ተረድቶታል?

ብሉምበርግ (Bloomberg) የተባለው የአሜሪካ ሚዲያ የኢትዮጵያ ወኪል ጋዜጠኛ በመሆን ከአምስት ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ሲከታተልና ሲዘግብ የቆየው በዜግነቱ እንግሊዛዊ የሆነው ዊሊያም ዴቪሰን፣ በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ የሚዲያ ተቋማት በተሻለ ተቃውሞ በተካሄባቸው አካባቢዎች በመገኘት እንቅስቃሴዎችን በገለልተኝነት ተከታትሏል፡፡

ከሙያው ጋር በተገናኘ በተጓዘባቸው አካባቢዎች የተነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችን እንዴት እንደተረዳቸው ሪፖርተር ላቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ፣ ‹‹ደካማ የሕዝብ አገልግሎት፣ መልስ የማይሰጥ የተኛ ቢሮክራሲ፣ በአግባቡ የማይሠሩ ፍርድ ቤቶች፣ የባለሥልጣናት ሙሰኛ መሆን፣ ያልተመጣጠነ የካሳ ክፍያና በመናር ላይ የሚገኝ የኑሮ ዋጋ (ግሽበት) ሕዝቡን በከፍተኛ ደረጃ አማረውታል፤›› ብሏል፡፡

ከዚህ የሕዝብ ምሬት ጋር የተቀላቀሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮች መኖራቸውን እንደታዘበ የሚገልጸው ጋዜጠኛ ዊሊያም የዴሞክራሲ ዕጦት፣ የትግራይ (የሕወሓት) የበላይነትን አስመልክቶ የተፈጠረ እምነት (Perception)፣ የኦሮሞ ሕዝብ መገለል፣ የአማራ ወሰን ለትግራይ ተላልፏል የሚል ክስ ከላይ ከተጠቀሱት ጋር ተዋህደው በኢትዮጵያ አሁን ያለውን የፖለቲካ ቀውስ ፈጥረውታል የሚል አረዳድ እንዳለው ጠቁሟል፡፡    

መንግሥት የገጠመውን ቀውስ ለመፍታት የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ሙስናን መታገልና ባለሥልጣናትን የማንሳት እንቅስቃሴና የአገልግሎት አሰጣጥና አስተዳደር ላይ ያሉትን ችግሮች ለማሻሻል ዕቅድ ቢኖረውም፣ በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ፈጣንና ትልቅ ለውጥ ማምጣት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻል፡፡ ለዚህ የሚሰጠው ምክንያት እነዚህ ጉዳዮች ላለፉት በርካታ ዓመታት የመንግሥት ትኩረት አቅጣጫ የነበሩና ያልተሳኩ በመሆናቸው፣ የሕዝብ ተቃውሞን በመቀነስ ረገድ ጉልህ ድርሻ ይኖራቸዋል ብሎ እንደማያምን ይገልጻል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አቶ ናሁሰናይ በላይ፣ መንግሥት የሕዝብ ተቃውሞን አስመልክቶ ያደረገው ግምገማ ቁንፅል ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ እንዲሁም የፓርቲው አባላት በተናጠል ባደረጉት ውይይት፣ የተቃውሞዎቹ መነሻ መሠረታዊ ምክንያቶችን አስመልክቶ የደረሱባቸው ድምዳሜዎች የችግሩ አካል ይሁኑ እንጂ ፓርቲው ሕመሙን አልተረዳውም ይላሉ፡፡

‹‹የችግሩ አረዳድ ላይ ነው ችግሩ፤›› የሚሉት አቶ ናሁሰናይ፣ ‹‹ፓርቲው የገጠመው የቅቡልነት ቀውስ (Legitmacy Crisis) ነው፤›› ብለዋል፡፡

ነፃ ፍርድ ቤት፣ ጤነኛ ፓርላማ፣ በቅጡ የሚሠሩ ኮሚሽኖች ተፈጥረው ሥራ አስፈጻሚውን ሥርዓት ማስያዝ ሲገባቸው የተገላቢጦሽ ሙሉ በሙሉ አንድ ፓርቲ ለሚቆጣጠረው መንግሥት ተገዥ እንደሆኑ፣ ይህም የሥልጣን መባለግ መፍጠሩን አቶ ናሁሰናይ ገልጸዋል፡፡

‹‹በአጠቃላይ አገሪቱ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ሥርዓት ሕገ መንግሥቱን ባለመምሰሉ ፓርቲው ሕዝባዊ ቅቡልነቱን አጥቷል፤›› ብለዋል፡፡

የሚጠበቀው ሹም ሽርና ሽግሽግ መፍትሔ ይሆናል?

ሰኞ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በ2009 ዓ.ም. ሊከናወኑ ስለሚገባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ለመንግሥት በሚሰጡት አቅጣጫ መደበኛ ጉባዔውን የሚጀምረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በቀጣዮቹ ቀናት በሚያካሂደው መደበኛ ስብሰባዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቀውን የካቢኔ አባላት ሹም ሽርና ሽግሽግ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ይህ የካቢኔ ሹም ሽርና ሽግሽግ ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውሱን ለመፍታት ገዥው ፓርቲና መንግሥት ቃል ከገቡት መሠረታዊ ከሚባሉት መፍትሔዎች መካከል ዋነኛው ነው፡፡ ይህ ሹም ሽርና ሽግሽግ፣ እንዲሁም በብቃት ላይ የተመሠረተ እንጂ የኢሕአዴግ አባልነት ላይ ያላተኮረ የካቢኔ ምሥረታ ፋይዳው ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡

ሪፖርተር በዚህ አዲስ የካቢኔ አወቃቀር ፋይዳ ዙሪያ ያነጋገራቸው መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉት የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያና ጠበቃ አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ ሌሎች መሠረታዊ የፖለቲካና የሕግ ማሻሻያዎች አብረው ካልተደረጉ፣ ‹‹የዓለም ምርጥ ብሩህ አዕምሮዎች ካቢኔውን ቢሞሉትም ለውጥ አይመጣም፡፡ አስቀድሞ ለቴክኖክራቶች አስቻይ ሁኔታዎች ሊዘጋጁ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ካልተፈጠረ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ካልተረጋገጠ፣ ሕግ ከፓርቲ አሠራር የበላይ ካልሆነ፣ በፖለቲካዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ መሠረታዊ ማሻሻያዎች ካልተደረጉ ለቀውሱ መፍትሔ ይመጣል የሚል እምነት የላቸውም፡፡

አቶ ናሁሰናይም ተመሳሳይ አቋም ያንፀባርቃሉ፡፡ የችግሩ መሠረታዊ መነሻ በአገሪቱ ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ ሥርዓት ሕገ መንግሥቱን አለመምሰሉ መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ናሁሰናይ፣ መልሱም ሕገ መንግሥቱን የሚመስል ፖለቲካዊ ሥርዓት መፍጠር መሆኑን ያሳስባሉ፡፡

ሹም ሽርና ሽግሽግ እንዲሁም ብቃት ላይ የተመሠረተ የካቢኔ አወቃቀር መፍጠር ቁንፅል መፍትሔ እንደሚሆን ይጠቁማሉ፡፡

ከሁሉም በላይ ገዥው ፓርቲም ሆነ መንግሥት ያጣውን ሕዝባዊ ተቀባይነት በድጋሚ ለማግኘት መሥራት እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡

ይህም ማለት የዜጐችን ተቋማዊ አቅም መገንባት፣ የፖለቲካ መብታቸውን ያለ ገደብ እንዲተገብሩ ማድረግ፣ እንዲሁም መተማመንን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ይጠቅሳሉ፡፡

እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች በፍጥነት እየመለሱ መሄድ ካልተቻለ ግን ማንኛውም ዓይነት ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡  

Standard (Image)

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ የአዋጅ

$
0
0

ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚ መሆን የጀመረውና ለሕዝብ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው በኢቢሲ የተነበበው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

  1. ይህ አዋጅ የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
  2. ትርጉም፡-ለዚህ አዋጅ አፈጻጸም ሲባል
  1. የሕግ አስከባሪ አካል ማለት የአገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ የመረጃና የደኅንነት አገልግሎት፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የክልል ፖሊስና ሌሎች የፀጥታ አካላት ናቸው፡፡
  2.  የመርማሪ ቦርድ ማለት በሕገ መንግሥት አንቀጽ 93(5) የተመለከተው የአስቸኳይ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ማለት ነው፡፡
  3. የአስቸኳይ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ማለት፣ ይህን አዋጅ ለማስፈጸም በአንቀጽ 6 መሠረት የተቋቋመ የአስቸኳይ ጊዜ አስፈጻሚ ኮማንድ ፖስት ማለት ነው፡፡
  4. ሕግ ማለት የፌዴራል ሕገ መንግሥት፣ እንደ አግባብነቱ በፌዴራል ወይም በክልል መንግሥታት ሕግ አውጭ ወይም ሥልጣን ባለው አስፈጻሚ አካል የወጣ የክልል ሕገ መንግሥት አዋጅ ደንብና መመርያ ማለት ነው፡፡
  5. ሰው ማለት የተፈጥሮ ወይም የሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ማለት ነው፡፡
  6.  በዚህ አዋጅ በወንድ አነጋገር የተገለጸው ሴትንም ይጨምራል፡፡
  1. የተፈጻሚነት ወሰን
  1. ይህ አዋጅ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተፈጻሚ ይሆናል፡፡
  2. በአዋጁ መሠረት የሚወሰድ ዕርምጃ ተግባራዊ ወይም ቀሪ የሚሆንበት አካባቢ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ይወስናል፡፡ ይህንኑ ለሕዝብ ያሳውቃል፡፡
  1. በአስቸኳይ ጊዜ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች

የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማስከበርና የሕዝብና የዜጐች ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን፣

  1. ማንኛውም ሁከት፣ ብጥብጥና በሕዝቦች መካከል መጠራጠርና መቃቃር የሚፈጥር ይፋዊም ሆነ የድብቅ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ጽሑፍ ማዘጋጀት፣ ማሳተምና ማሠራጨት፣ ትዕይንት ማሳየት፣ በምልክት መግለጽ፣ ወይም መልዕክትን በማናቸውም መንገድ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ሊከለክል ይችላል፡፡
  2. ማናቸውም የመገናኛ ዘዴ እንዲዘጋ ወይም እንዲቋረጥ ሊያደርግ ይችላል፡፡
  3. የሕዝብና የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሲባል ስብሰባና ሠልፍ ማድረግ፣ መደራጀት፣ በቡድን ሆኖ መንቀሳቀስም ሊከለክል ይችላል፡፡
  4. የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ በማደፍረስ ተግባር ላይ ተሳትፏል ብሎ የሚጠረጥረውን ማናቸውም ሰው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር ለማድረግ፣ እያጣራ ወይም እያስተማረ ለመልቀቅ፣ ይህ አዋጅ ተፈጻሚ መሆን እስካለበት ጊዜ ድረስ ይዞ ለማቆየት ወይም በመደበኛ ሕግ ተጠያቂ እንዲሆን ለማድረግ ይችላል፡፡
  5. ወንጀል የተፈጸመባቸውን ወይም ሊፈጸምባቸው የሚችሉ ዕቃዎችን ለመያዝ ሲባል ማናቸውም ቤት፣ ቦታ፣ መጓጓዣ ለመበርበር እንዲሁም ማናቸውንም ሰው ለማስቆም፣ ማንነቱን ለመጠየቅ፣ ለመፈተሽ ይችላል፡፡ በብርበራ ወይም በፍተሻ የተያዙ ዕቃዎችን በማስረጃነት ለፍርድ ቤት የማቅረብ፣ እንደተጠበቀውም አጣርቶ ለባለመብቱ ይመልሳል፡፡
  6. የሰዓት ዕላፊ ተፈጻሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ይወስናል፡፡
  7. በተወሰነ ጊዜ አንድን መንገድ፣ አገልግሎት መስጫ ተቋም ለመዝጋት እንዲሁም ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ፣ ወደተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡ፣ ከተወሰነ ቦታ እንዲለቁ ማዘዝ ይችላል፡፡
  8. የተቋማትና የመሠረተ ልማቶች ጥበቃ ሁኔታንም ይወስናል፡፡
  9. የሕዝብና የዜጎች ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሲባል የጦር መሣሪያ፣ ስለት ወይም እሳት የሚያስነሱ ነገሮችን ይዞ መንቀሳቀስ የማይቻልባቸውን ቦታዎች ለይቶ ሊወስን ይችላል፡፡
  10.  በሰላም መደፍረስ ምክንያት የፈረሱ የተለያዩ የአስተዳደር እርከኖች ከክልሉና ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር በመተባበር መልሶ እንዲቋቋሙ ያደርጋል፡፡
  11.  ሕዝብ የሚጠቀምባቸው ወይም ፈቃድ የወጣባቸው የንግድ ሥራዎች የመንግሥት ተቋማት እንዳይዘጉ፣ አገልግሎት እንዲሰጡ ወይም የሥራ ማቆም እንዳይደረግ ሊያዝ ይችላል፡፡
  12.  በዚህ አዋጅ የተመለከቱ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርምጃዎችን ለማስፈጸም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ተመጣጣኝ ኃይል ለመጠቀም ይችላል፡፡  ኃላፊነቱን ለመፈጸም ሌሎች አስፈላጊ ተግባራትን ይፈጽማል፡፡
  1. የማይፈቀዱ ተግባራት

ማናቸውም የሕግ አስከባሪ አካልና አባል ለዚህ አዋጅ አፈጻጸም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ አንድ የተመለከተውን የመንግሥት ስያሜ መቀየር፣ በአንቀጽ 18 የተመለከተውን ኢሰብዓዊ አያያዝ የመፈጸም፣ በአንቀጽ 25 የተመለከተውን የሰዎችን የእኩልነት መብት የሚጥስ ተግባር መፈጸም፣ በአንቀጽ 39(1)ና (2) የተመለከተውን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን መብቶችን መጣስ የተከለከለ ነው፡፡ 

  1. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት መቋቋምና ኃላፊነት

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ አግባብነት ካላቸው አካላት የተውጣጡ አባላትን የያዘ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት አባላትን ይመርጣል፡፡ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4 የተመለከቱ ተግባራትን በበላይነት ይመራል፣ ያስፈጽማል፡፡ የሕግ አስከባሪ አካላትን በአንድ ዕዝ አድርጐ ሥራ ይመራል፣ ያዛል፡፡

  1. የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ ግዴታ

የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ በቁጥጥር ሥር የተደረጉ ሰዎችንና የሚቆዩበትን ቦታ ለመርማሪ ቦርዱ ያስታውቃል፡፡

  1. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል፡፡ የመርማሪ ቦርዱ ሰባት አባላት የሚኖሩት ሲሆን፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ከሕግ ባለሙያዎች የተውጣጡ ሆነው በምክር ቤቱ ይመደባሉ፡፡

  1. የመርማሪ ቦርድ ሥልጣንና ተግባር
  • በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የታሰሩትን ሰዎች ስም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይፋ ያደርጋል፣ የታሰሩበትን ምክንያት ይገልጻል፡፡ 
  • በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሚወሰዱት ዕርምጃዎች በማናቸውም ረገድ ኢሰብዓዊ እንዳይሆኑ ይቆጣጠራል፣ ይከታተላል፡፡
  • ማንኛውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕርምጃ ኢሰብዓዊ መሆኑን ሲያምንበት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዕርምጃውን እንዲያስተካክል ሐሳብ ይሰጣል፡፡
  • በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕርምጃዎች ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጽሙትን ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ያደርጋል፡፡
  • የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲቀጥል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ሲቀርብ ያለውን አስተያየት ለምክር ቤቱ ያቀርባል፡፡
  1.  ተፈጻሚነታቸው የታገዱ ሕጐች

በቪየና ኮንቬንሽን የተመለከተው የዲፕሎማቲክ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረን የፍሬ ነገርና የሥነ ሥርዓት ሕጐች ለዚህ አዋጅ አፈጻጸም ይህ አዋጅ በሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜያት ተፈጻሚነታቸው ታግዶ ይቆያል፡፡

  1.  የመተባበር ግዴታ

ማንኛውም ሰው የዚህን አዋጅ አፈጻጸም፣ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስትና የሕግ አስከባሪ አካላት ይህን አዋጅ በማስፈጸም የሚወስዷቸውን የአስቸኳይ ጊዜ ዕርምጃዎች የማክበርና የመተባበር ግዴታ አለበት፡፡

  1.  የወንጀል ተጠያቂነት

በዚህ አዋጅ የተመለከቱት አስቸኳይ ጊዜ ዕርምጃዎች ጋር የተያያዙ ግዴታዎችን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት ይቀጣል፡፡

በዚህ አዋጅ አንቀጽ 11 የተመለከተውን የመተባበር ግዴታ የጣሰ ማንኛውም ሰው እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ይቀጣል፡፡

  1.  ደንብና መመርያ የማውጣት ሥልጣን

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህን አዋጅ ለማስፈጸም ደንብና መመርያ ያወጣል፡፡

  1.  አዋጁ የሚጸናበት ጊዜ
  • ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ለስድስት ወራት የፀና ይሆናል፡፡
  • የስድስት ወራት የጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስቱ የአዋጁ ተፈጻሚነት ቀሪ የሚሆንበትን ጊዜ ሊወስን ይችላል፡፡
  • ይህ አዋጅ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93(2)(ለ) መሠረት በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ በተወካዮች ምክር ቤት ተቀባይነት እንዲያገኝ መቅረብ ይኖርበታል፡፡
  • የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድስት ወራት ጊዜ ገደቡ ሲጠናቀቅና አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የጊዜ ገደቡ በየአራት ወራት እንዲታደስ ሊያደርግ ይችላል፡፡
  • ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን በሚዲያ ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል፡፡

አዲስ አበባ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም.

ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር

Standard (Image)

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና ተጠባቂ ለውጦች

$
0
0

አገሪቱ መደበኛ ሕይወቷ ከታወከ ዓመት ሊሞላ ነው፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተቃውሞዎች እየተከሰቱ በተቃውሞ አቅራቢዎቹና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መካከል ግጭት እየተፈጠረ የሰው ሕይወት ሲያልፍ፣ በሰውና በንብረት ላይም ጉዳትና ውድመት ሲከሰት ማየት አዲስ ነገር መሆኑ እየቀረ መጥቶ ነበር፡፡

መንግሥት የችግሩን መሠረታዊ ምንጭ ገምግሞ መለየቱን፣ በዚህም የመልካም አስተዳደር ክፍተት፣ የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች፣ የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ ይዞታ ክፍተቶች ሕዝቡ በመንግሥት እንዲከፋ ማድረጉን አምኖ መፍትሔ ለመስጠትም ቃል ገብቶ ነበር፡፡ እነዚህ የመፍትሔ ዕርምጃዎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ሥራ ከጀመረ በኋላ በሒደት ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረጉ ተገልጾ ስለነበር ብዙዎች በጥርጣሬ የተመለከቱት ቢሆንም፣ የዕርምጃዎቹን ዓይነትና ጥልቀት ለማየት ግን መጓጓታቸው አልቀረም፡፡

ይህ ቀን ደርሶ ለማየት ጥቂት ቀናት ሲቀሩ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ሆራ ሐይቅ ከኢሬቻ በዓል አከባበር ጋር በተያያዘ የሰዎች ሕይወት በሚያሳዝን አደጋ መጥፋቱ ግን ነገሮችን ሙሉ በሙሉ የቀየረ ነው የሚመስለው፡፡ ለወራት ጋብ ብሎ የነበረው የኦሮሞ ተቃውሞ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ ያስከተለውም ጉዳት አስደንጋጭ ነበር፡፡ ከመስከረም 23 እስከ መስከረም 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ውስጥ ባሉት አምስት ቀናት ብቻ 130 ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በኦሮሚያ ወድመዋል፡፡ በቅርብ ጊዜያት በአማራ ክልልና በደቡብ ክልል ኮንሶና ዲላ አካባቢዎች ተመሳሳይ ውድመቶች መፈጸማቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴሬሽንን ከመሠረቱት ዘጠኝ ክልሎች መካከል በቆዳ ስፋትም ሆነ በሕዝብ ብዛት ትልልቅ በሆኑት እነዚህ ክልሎች የተነሳው ተቃውሞ ሕዝባዊ መሠረት እንዳለው የሚያምነው መንግሥት በውጭ ድርጅቶች፣ በግለሰቦችና በመንግሥት ድርጅቶች ላይ የደረሰው ውድመት ከተቃውሞው ጀርባ ሌሎች የውጭ ኃይሎች የማቀጣጠል ሚና እየተጫወቱ ነው በሚል ያቀርብ የነበረውን ክርክር የሚያረጋግጥ ነው ብሎታል፡፡

ይህ ከክልል የፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ውጭ ሆኖ በስንት ጉትጎታና ልመና ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ለእንዲህ መሰል ጥፋት መንግሥት ዋስትና የሰጣቸው የውጭ ተቋማትን ጨምሮ በበርካታ ድርጅቶች ላይ ውድመቱ ባልተቋረጠበት ወቅት፣ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. የተሰበሰበው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አሁን ማውጣት ያስፈለገበትን ምክንያት አስመልክተው ሲናገሩ፣ ‹‹በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የሰላምና የመረጋጋት፣ እንደዚሁም የሕዝብ ደኅንነት ጉዳይ አደጋ ውስጥ መውደቁን አይቷል፡፡ የተለያዩ ቡድኖች በማሰማራትና በመምራት ሥጋት የሚጭሩ ሁከቶችና ብጥብጦች እየተካሄዱ ነው ያሉት፡፡ እነዚህ ሥጋቶችና ብጥብጦች በመደበኛው መንገድ ለማስታገስ የሚደረጉ ሙከራዎች ጊዜ እየጠየቁ በመሆናቸው፣ የዜጎች ሕይወትም በስፋት እየተቀጠፈ በመሆኑ፣ የውጭ ዜጎች ሕይወት ጭምር እየጠፋ መሆኑን በመገንዘብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ እነዚህን ችግሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ በማስወገድ ወደ ሰላማችንና መረጋጋታችን እንድንመለስ ማድረግ አስፈላጊና በጣም ተገቢ ነው ብሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በማመኑ ይህ አዋጅ ታውጇል፤›› ብለዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በሰጡት ማብራሪያ፣ በተመሳሳይ በደረሰው አደጋ የሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ በሥጋት ውሰጥ መግባቱ፣ የበርካታ መቶዎች ዜጎች ሕልፈት ምክንያት መሆኑ፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎች የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ እጅግ ከፍተኛ አደጋ መከሰቱ፣ ይህም በመደበኛ የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ ሊፈታ ይችላል ተብሎ ስላልታመነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁን ተናግረዋል፡፡

የሚጣሉት ገደቦች ሕዝቡ ሙሉ እንቅስቃሴውን በተረጋጋ መልኩ ማከናወን የሚያስችለው ሰላም ለማግኘት ያለሙና መደበኛ ሕይወትን ለመመለስ ያቀዱ እንደሆኑም አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹የሕዝቡ መደበኛ እንቅስቃሴ ተገድቧል፡፡ የተደራጁ ትንንሽ ቡድኖች ግለሰቦችን ያጠቃሉ፣ ሱቆችን ያዘጋሉ፣ ፋብሪካዎችን ያወድማሉ፣ መንገዶችን ይዘጋሉ፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ አዋጁ እነዚህን አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ለመገደብ ያሰበ ነው ብለዋል፡፡

መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለበጎ ዓላማ የሚውልና ችግሮችን ለመቅረፍ ብቻ የሚውል መሆኑን ቃል ቢገባም፣ ብዙዎች አስቀድሞም በቋፍ ላይ የሚገኘውን የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ይዞታ ላይ የማይቀለበስ ጉዳት እንዳያስከትልና በቀውስ ውስጥ የሚገኘውን ፖለቲካ እንዳያባብስ መሥጋታቸው አልቀረም፡፡ ይሁንና የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላልተፈለገ ዓላማ እንዳይውል የሚያደርጉ ያላቸውን ቅድመ ሁኔታዎችና የቁጥጥር ሥርዓቶችን ይዘረጋል፡፡

ሕገ መንግሥትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93 ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚደነገግባቸውን ቅድመ ሁኔታዎችና የሚፈጸምበትን ዝርዝር ሥነ ሥርዓት ያስቀምጣል፡፡ አዋጁ በሥራ ላይ በሚቆይበት ጊዜ የማይገሰሱ መብቶችም እንዲሁ ተለይተው ተደንግገዋል፡፡  

በሕገ መንግሥቱ የውጭ መረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፣ ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን እንዳለው ተደንግጓል፡፡ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የክልል መስተዳድሮች በክልላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጁ እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡

ከፌዴራል መንግሥቱ መግለጫ ለመረዳት እንደሚቻለው ለአዋጁ መታወጅ ምክንያት የሆነው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ መውደቁና ይህንንም በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም አይቻልም ተብሎ መታመኑ ነው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ እያለ ወይም ባልሆነበት ወቅት ሊታወጅ ይችላል፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት አዋጁ ምክር ቤቱ በሥራ ላይ እያለ ከታወጀ በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ለምክር ቤቱ ሊቀርብ ይገባል፡፡ ነገር ግን በሥራ ላይ ካልሆነ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ሊቀርብ ይገባል፡፡ የአሁኑ አዋጅ ምክር ቤቱ ሥራ ከመጀመሩ በፊት የታወጀ በመሆኑ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ሊቀርብ የሚችል ነው፡፡ እርግጥ ነው አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች ምክር ቤቱ በመሀል ሥራ ሲጀምር በሁለት ቀናት ውስጥ ሊቀርብ ይገባል ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

አዋጁ ለምክር ቤቱ ሲቀርብ የሚፀድቀው የአባላቱን ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ካገኘ ብቻ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ወዲያውኑ ይሻራል፡፡ ተፈላጊውን ድምፅ ያገኘ አዋጅ በሥራ ላይ እስከ ስድስት ወራት ሊቆይ ይችላል፡፡ ችግሩ አልተቀረፈ ምክር ቤቱ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ በየአራት ወሩ በተደጋጋሚ እንዲታደስ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በአንዳንድ አገሮች ዝቅተኛውና ከፍተኛው ቀነ ገደብ የተቀመጠ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ግን ምክር ቤቱ ለማደስ ፈቃደኛ እስከሆነ ድረስ ሳይቋረጥ ሊቀጥል ይችላል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣቸው ደንቦች መሠረት የአገርን ሰላምና ህልውና፣ የሕዝብን ደኅንነት፣ ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሥልጣን ይኖረዋል፡፡ ይህን ሥልጣን ተግባራዊ በሚያደርግበት ወቅትም በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን መሠረታዊ የፖለቲካና የዴሞክራሲ መብቶችን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለማስወገድ ተፈላጊ ሆኖ በተገኘው ደረጃ እስከ ማገድ ሊደርስ እንደሚችልም ተደንግጓል፡፡

ነገር ግን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊገደቡ የማይችሉ መብቶች ተለይተው ተቀምጠዋል፡፡ በዚህም መሠረት ኢሰብዓዊ አያያዝ (አንቀጽ 18)፣ የእኩልነት መብት (አንቀጽ 25) እና የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብት (አንቀጽ 39(1) እና (2)) ገደብ ከማይደረግባቸው መብቶች መካከል ናቸው፡፡ እንደ መብት ባይቆጠርም የኢትዮጵያ መንግሥት ስያሜ (የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ) (አንቀጽ 1) በተመሳሳይ ሊቀየር እንደማይችል ተደንግጓል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአባላቱና ከሕግ ባለሙያዎች መርጦ የሚመድባቸው ሰባት አባላት ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ይቋቋማል፡፡ ቦርዱ አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚፀድቅበት ጊዜ ይቋቋማል፡፡

ከመርማሪ ቦርዱ ሥልጣንና ኃላፊነቶች መካከል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የታሰሩትን ግለሰቦች ስም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይፋ ማድረግና የታሰሩበትን ምክንያት መግለጽ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሚወስዱትን ዕርምጃዎች በማናቸውም ረገድ ኢሰብዓዊ አለመሆናቸውን መቆጣጠርና መከታተል፣ ማናቸውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕርምጃ ኢሰብዓዊ መሆኑን ሲያምንበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዕርምጃውን እንዲያስተካክል ሐሳብ መስጠት፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕርምጃዎች ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጽሙትን ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ፣ እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲቀጥል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ሲቀርብ ያለውን አስተያየት ለምክር ቤቱ ማቅረብ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የመጀመሪያው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ወደ ሥራ ከገባበት ከነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም. በኋላ ሕጉን በተከተለ መንገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲታወጅ ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም. ከተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ተፈጥሮ የነበረውን አለመረጋጋት ለማብረድ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የሰዓት እላፊ ገደብና የፖለቲካ ስብሰባ ክልከላ መደረጉን ማስታወቃቸው፣ እንደ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚወስዱት በርካቶች ናቸው፡፡

ይህ አዋጅ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተፈጻሚ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ በአዋጁ መሠረት የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ተግባራዊ ወይም ቀሪ የሚሆንበት አካባቢ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት እንደሚወሰንና ለሕዝብ እንደሚያሳውቅ ተደንግጓል፡፡

አዋጁ በአንቀጽ 4 የሚወሰዱ ዕርምጃዎችን ይዘረዝራል፡፡ በዚህም መሠረት ኮማንድ ፖስቱ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማስከበርና የሕዝብና የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን ማንኛውም ሁከት፣ ብጥብጥና በሕዝቦች መካከል መጠራጠር፣ መቃቃር የሚፈጥር ይፋዊም ሆነ የድብቅ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ጽሑፍ ማዘጋጀት፣ ማሳተምና ማሰራጨት፣ ትዕይንት ማሳየት፣ በምልክት መግለጽ ወይም መልዕክትን በማናቸውም መንገድ ለሕዝቡ ይፋ ማድረግ ሊከለክል ይችላል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ማናቸውም የመገናኛ ዘዴ እንዲዘጋ ወይም እንዲቋረጥ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ኮማንድ ፖስቱ የሕዝብና የዜጐች ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሲባል ስብሰባና ሠልፍ ማድረግ፣ መደራጀት፣ በቡድን ሆኖ መንቀሳቀስም ሊከለክል ይችላል፡፡

ኮማንድ ፖስቱ የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ በማደፍረስ ተግባር ላይ ተሳትፏል ብሎ የሚጠረጥረውን ማንኛውንም ሰው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር ለማድረግ፣ እያጣራ ወይም እያስተማረ ለመልቀቅ፣ አዋጁ ተፈጻሚ መሆን እስካለበት ጊዜ ድረስ ይዞ ለማቆየት ወይም በመደበኛ ሕግ ተጠያቂ የማድረግ ሥልጣንም ተሰጥቶታል፡፡

ወንጀል የተፈጸመባቸውን ወይም ሊፈጸምባቸው የሚችሉ ዕቃዎችን ለመያዝ ሲባል ማናቸውም ቤት፣ ቦታ፣ መጓጓዣ ለመበርበር እንዲሁም ማናቸውንም ሰው ለማስቆም፣ ማንነቱን ለመጠየቅና ለመፈተሽ እንደሚችልም ተደንግጓል፡፡ ኮማንድ ፖስቱ የሰዓት እላፊ ተፈጻሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ይወስናል፡፡ ሌሎች ከተከሰተው አደጋ ጋር ተያያዥ የሆኑ በርካታ ኃላፊነቶችም ተሰጥተውታል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ

አዋጁ ለአስፈጻሚው አካል ሰፊ የሆነ የመመርመር፣ የመክሰስና የማስቀጣት ሥልጣን የሰጠ በመሆኑ፣ በሰብዓዊ መብቶች ላይ ያልተፈለገ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ሥጋት አለ፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አማካይነት አስቀድሞ ደካማ ይዞታ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ይበልጥ ሊባባስ ይችላል የሚለው ሥጋትን በርካቶች ይጋሩታል፡፡ ፒያትሮ ቶጊያ የተባሉ ተመራማሪ “The State of Emergency: Police and Cararal Regimes in Modern Ethiopia” በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጽሑፍ፣ ኢሕአዴግም ሆነ ከእሱ በፊት የነበሩት የደርግና የኃይለ ሥላሴ አገዛዞች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተቃዋሚዎቻቸውን ለማጥቃትና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በስፋትና በብዛት ለመፈጸም ይጠቀሙበታል ሲሉ ይደመድማሉ፡፡  

አቶ ይኼነው ፀጋዬ “State of Emergency and Human Rights under the 1995 Ethiopian Constitution” በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጽሑፍም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰብዓዊ መብቶችን ያላግባብ እንዳይጥስ መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች በዝርዝር ተንትነዋል፡፡

አቶ ይኼነው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ወቅት በመንግሥት ፀጥታ የማስክበር ኃላፊነትና በግለሰቦች መብቶችና ነፃነቶች መካከል ሚዛን መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ መርህ እንደሆነ አስምረውበታል፡፡ መንግሥት ይህን መርህ ሲፈጽም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ያስገደደ ልዩ የደኅንነት ሥጋት መፈጠሩን ለሕዝቡ የማስረዳት፣ ከተከሰተው አደጋ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ዕርምጃ እንደሚወስድ የማረጋገጥ፣ በማንኛውም ሁኔታ የማይገረሰሱ መብቶች እንዳይጣሱ የማረጋገጥ፣ የሚወሰዱት ዕርምጃዎች በአድልኦነት እንደማይፈጸሙ የማረጋገጥና ሁሉም ዕርምጃዎች አገሪቱ ከገባቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር ተጣጥመው እንዲፈጸሙ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ተመራማሪው አቶ ይኼነው በአስቸኳይ ጊዜ የሚወሰደው ዕርምጃ የተፈጠረውን አደጋ ለማስወገድ ብቻ ያለመ መሆን አለበት ሲባል ከዚህ ጋር ባልተገናኙ ጉዳዮች ላይ የመብት ገደብ ማድረግንና አደጋው በሌለባቸው ቦታዎች የመብት ገደብ እንዳያደርግ መከላከልን ይጨምራል ብለዋል፡፡ በርካታ ዜጐች በኦሮሚያ የተከሰተው አደጋ ሌሎች ከችግሩ የራቁ አካባቢዎችን ይጨምራል ወይ የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ይደመጣል፡፡ ነገር ግን አዋጁ በመላው አገሪቱ ተፈጻሚ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጭምር የማይገረሰሱ መብቶች በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የተዘረዘሩ ቢሆንም፣ የዝርዝሮቹ ብዛት ከሌሎች ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አንፃር ልዩነት አለው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸውና የአገሪቱ ሕግ አድርጋ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መካከል አንዱ የሆነው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን በአንቀጽ 4(2) ላይ በሕይወት የመኖር መብት፣ ከኢሰብዓዊ አያያዝ የመጠበቅ መብት፣ በባርነት ያለመያዝ መብት፣ የፍትሐ ብሔር ግዴታን ባለመወጣት ያለመታሰር መብት፣ የወንጀል ሕግ ወደ ኋላ ሄዶ ተግባራዊ እንዳይሆን የመጠበቅ መብት፣ በሕግ ፊት በእኩልነት የመታወቅ መብት፣ የአመለካከት፣ በነፃነት የማሰብና የሃይማኖት መብት በማንኛውም ሁኔታ ሊገሰሱ የማይችሉ መብቶች ናቸው ይላል፡፡ በኢትዮጵያ ግን በሕይወት የመኖርና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ጨምሮ የሚገሰሱ መብቶች እንደሆኑ መረዳት ይቻላል፡፡ ለአብነት አዋጁ ማንኛውንም መገናኛ ዘዴ መዝጋት እንደሚቻል በግልጽ ያስቀምጣል፡፡

በዓለም አቀፍ ሕግ ከተቀመጡ መርሆዎች አንዱ የአስችኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈጻሚ ከመሆኑ በፊት ለሕዝብ ይፋ መደረግ እንዳለበት ይገልጻል፡፡ ይህ አዋጅ ተፈጻሚ የሚሆነው ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሆነ የተገለጸ ቢሆንም፣ ለሕዝቡ ይፋ የተደረገው ግን መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው፡፡ ኮማንድ ፖስቱ የት ቦታ፣ የትኛው መብት እንደሚገደብ እንደሚያስታውቅ የተደነገገ ቢሆንም እስካሁን በዝርዝር ሁኔታ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ አዋጁ ተፈጻሚ መሆን ጀምሯል ማለት ምን ማለት ነው በማለት እየጠየቁ ያሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያ ግን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ አደጋ አምጥተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ተጠያቂ ለማድረግ መደበኛውን የሕግ ማስከበር አካሄድ ለመከተል መንግሥት እንዳይገደድ ያደርጋል እንጂ፣ በግልጽና በዝርዝር አስቀድሞ ካልተገለጸ በዜጐች መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ላይ ገደብ ማድረግ አሁንም ቢሆን አይቻልም፡፡

የሕግ ባለሙያው አዋጁ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን እንዳይጋብዝ የማድረግ ዋና ኃላፊነት የሚወድቀው በመርማሪ ቦርዱ ላይ መሆኑን አስታውሰው የቦርዱ አባላት ነፃና ገለልተኛ የሆኑ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸውና በሕግ እውቀታቸውና ልምዳቸው የላቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡    

 

Standard (Image)

ኢትዮጵያን ከግብፅ ጋር ዳግም እሰጥ አገባ ውስጥ የከተታት ክስተት

$
0
0

የአዲስ አበባና የዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላንን በመቃወም በ2007 ዓ.ም. በኦሮሚያ ከተሞችና ዩኒቨርሲቲዎች የተጀመረው ተቃውሞ ለተወሰኑ ወራት የተረጋጋ ቢመስልም በ2008 ዓ.ም. በኅዳር ወር ተቀስቅሷል፡፡

በኦሮሚያ ዳግም ላገረሸው ተቃውሞ በምዕራብ ኦሮሚያ ጊንጪ ከተማ የሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይዞታ በከፊል ለባለሀብት መሸጡን በመቃወም ተማሪዎቹ ያነሱት ተቃውሞ መነሻ ምክንያት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ መነሻው ይህ ቢሆንም፣ የአዲስ አበባና የዙሪያው ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን ላይ የነበረው ተቃውሞ በርካታ አካባቢዎችን ያደረሰ ግጭት አዘል ተቃውሞ መቀስቀሱ ይታወቃል፡፡

በዚህም የበርካታ ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተመሳሳይ ወቅት የተነሳው ግጭት ከቅማንት ብሔረሰብ ማንነት ጋር የተያያዘ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የቅማንት ብሔረሰብ ማንነትን የክልሉ መንግሥት ዕውቅና ሊሰጥ አልቻለም በሚል መነሻ የተቀሰቀሰው ግጭት የበርካቶች ሕይወት ቀጥፏል፡፡ ንብረቶች ወድመዋል፡፡ አንድ ብሔር ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ተሰንዝረዋል፡፡

በሰሜን ጐንደር ከቅማንት ጋር ተያይዞ የተነሳው ግጭት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ካገኘ በኋላ መረጋጋትን አሳይቷል፡፡ ይሁን እንጂ በዚያው በሰሜን ጎንደር ዞን ከወልቃይት ማንነትና የወሰን ለውጥ ጥያቄ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ተቀስቅሷል፡፡

በትግራይ ክልል ውስጥ የተካለለው የወልቃይት ፀገዴ ሕዝብ አማራ ነው መተዳደር ያለበትም በአማራ ክልል ውስጥ ነው በሚል የተነሳው ጥያቄ ይዘቱን ቀይሮ፣ በአማራ ክልል በጎንደርና በጐጃም ዞኖች በመንግሥት ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ሠልፎችና አድማዎች፣ እንዲሁም ባህሪው ተቀይሮ ወደ ንብረት ማውደም ተቀይሯል፡፡

በእነዚህ ሁለት የአገሪቱ አካባቢዎች የተነሳው የፖለቲካ ቀውሶች በማኅበራዊ ሚዲያ እየተመሩ በርካታ አካባቢዎችን ከማዳረሳቸውም በላይ የጋራ ዓላማ ያላቸው መስለዋል፡፡

መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ ስለተነሱበት ጥያቄዎች ራሱን ተጠያቂ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

ባለፈው ሳምንት ሰኞ የተወካዮች ምክር ቤትንና የፌዴሬሽን ምክር ቤትን የጋራ ጉባዔ በንግግር የከፈቱት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተሾመ ሙላቱ በአብዛኛው ያነሱትም፣ መንግሥት ሊመልሳቸው የሚገቡ ጥያቄዎች በፍጥነት ባለመመለሳቸውና ከፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ከግምት ያላከተተ የካሳ ክፍያ በመክፈል አርሶ አደሩን ከመሬቱ ማፈናቀል፣ እንዲሁም የማንነት ጥያቄዎችን በአግባቡ አለመመለስ መሠረታዊ የኅብረተሰቡ ጥያቄዎች መሆናቸውን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ባለመቻሉ በተለያዩ የውጭ ኃይሎችና በጽንፈኛ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች መጠለፉን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ቀን ለውጭ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ኢትዮጵያውያን ፍትሐዊ ጥያቄዎችን ቢያነሱም የግብፅ መንግሥት ተቋማትና የኤርትራ መንግሥት ይህንን የሕዝብ ጥያቄ ለራሳቸው ዓላማ በመጥለፍ ኢትዮጵያን ለመበታተን ሲያጠነጥኑ፣ በገንዘብ ሲደግፉና ሲያስታጥቁ እንደተደረሰባቸው ለዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት አሳማኝ ማስረጃ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በንግግራቸው፣ ‹‹በቅርቡ በአንዳንድ የአገራችን ክልሎች ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ሲካሄዱ የቆዩ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን መሠረታዊ ባህርይና አንድምታ በትክክል መገንዘብ ተገቢ ነው፤›› በማለት፣ የአገሪቱ ሕዝቦች በሰላማዊ መንገድ ያቀረቡት ቅሬታን በመጥለፍ ወደ ሁከትና አውዳሚ እንቅስቃሴ ለመቀየር የተረባረቡ የውጭ ኃይሎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በትንሳኤ ላይ መሆኗን የማይቀበሉ አገሮችና ‹‹የኒዮሊብራል›› አጀንዳቸውን ለመጫን የሚፈልጉ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማተራመስ በስፋት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን፣ ፕሬዚዳንቱ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ባደረጉት ንግግር ጠቁመዋል፡፡

‹‹ከጽንፈኛ ዳያስፖራዎች ጀምሮ በአባይ ወንዛችን ላይ የተጠቃሚነት መብታችንን ለማረጋገጥ የጀመርነውን እንቅስቃሴ ለማኮላሸት የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ወገኖች፣ በቅርቡ ታላቁን የኢሬቻ በዓል ከማወክ ጀምሮ በልዩ ልዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ያካሄዱት ውድመትና ቃጠሎ በማንኛውም ሚዛን ፍትሐዊነት የሌለው ነው፡፡ በመሆኑም መንግሥት ይህን የመሰለው አፍራሽና ከባድ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ታዝሎ የመጣ ፀረ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ እንዲመከትና ወንጀለኞቹም በጥብቅ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ በቃጠሎ የወደሙ ንብረቶች በተለይ ደግሞ የምርት ተቋማት አገራችንና ሕዝቦቿ ከውጭ የልማት አጋሮቻችን ጋር በመተባበር በአፋጣኝ መልሰው እንዲገነቡና ለላቀ ምርታማነት እንዲበቁ ጠንካራ ርብርብ ይደረጋል፡፡ በመሆኑም መላ የአገራችን ሕዝቦች ኢትዮጵያን እንደፈራረሱት የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ለማተራመስ የሚደረገውን ይህን አፍራሽና አሳፋሪ ሙከራ መንግሥትና ሕዝብ በጀመሩት መንገድ በጋራ ይፋለሙታል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በተለይ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የማንንም እጅ ሳንጠብቅ በመላ የአገሪቱ ሕዝቦች ተሳትፎና በአገራዊ አቅም በመተማመን መገንባት መጀመራችን ያስቆጣቸው አገሮች፣ ረዘም ላሉ ዓመታት ውስጥ ውስጡን ሲዘጋጁ ከርመው በአሁኑ ጊዜ ጽንፈኛ የዳያስፖራ ኃይሎች ከቀሰቀሱት ነውጥ ጋር በመመጋገብ አገሪቱን ለማተራመስ በቀጥታ እየተረባረቡ ይገኛሉ፤›› ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ እንደተናገሩት በቀላሉ ሊነሱ የሚችሉ ወጣቶችን የጥፋት ሐሳብ፣ ክብሪትና ነዳጅ እያስታጠቁ ለአገሪቱ ቁልፍ የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ያላቸውን ፋብሪካዎች፣ የአበባ እርሻዎችና ሌሎች ተቋማት በማጋየት ከፍተኛ ውድመት እንዳስከተሉ ተናግረዋል፡፡

‹‹የኦነግና የግንቦት ሰባት መሪዎች ከግብፅ መንግሥት ተቋማት ጋር እጅና ጓንት በመሆን ባቀነባበሩት የጥፋት እንቅስቃሴ በርካታ አገራዊና የውጭ ባለሀብቶችና ሠራተኞቻቸውን ለአደጋ ያጋለጠ የታሰበበት ከፍተኛ ውድመት ፈጽመዋል፤›› ብለዋል፡፡

ይህንን ተከትሎ የፌዴራል ፖሊስ ከኦነግ ጋር ግንኙነት በመፍጠርና አመራር በመቀበል የጥፋት ተግባር ተሰማርተዋል በሚል የጠረጠራቸውን 17 ወጣቶች በቁጥጥር ሥር አውሎ ሰሞኑን ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡

እነዚህ ወጣቶች ከኦነግ አመራሮችና የሽብር ቡድን አባላት ጋር የስልክ ግንኙነት በማድረግ በአገር ውስጥ አባላትን ሲመለምሉ እንደነበር፣ ዓላማቸውም የኢትዮጵያን መንግሥት በኃይል የመለወጥ የፖለቲካ ዓላማ እንደነበራቸው በክሱ ገልጿል፡፡

እነዚህ ወጣቶች መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ፣ በቢሾፍቱ፣ በጅግጅጋና በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች በማድረግ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የክስ መዝገቡ ያስረዳል፡፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን የዕርዳታ እህል የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ያቃጠሉ፣ በመንገድ ሥራ ላይ የነበሩ ማሽነሪዎች፣ ሆቴሎችና የአስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች ላይ ጉዳት ያደረሱ ተጠርጣሪዎች በነዋሪዎች ጥቆማ በፖሊስ እየተያዙ መሆናቸውን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደረጀ ሙላት ተናግረዋል፡፡

በአርሲ ነገሌ የውኃ ፕሮጀክቶች ላይ ጉዳት ያደረሱና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን ያቃጠሉ በርከት ያሉ ወጣቶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የዞኑ መስተዳደር አካላት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ታማኝ ማስረጃ እንዳላቸው በመግለጽ የግብፅ ተቋማትን እየወነጀሉ ሲሆን፣ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ መንግሥታቸው በኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት እጁ እንደሌለበት በመግለጽ እያስተባበሉ ይገኛሉ፡፡

የግብፅ ፕሬዚዳንት ለአገራቸው የመከላከያ ሠራዊት ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ግብፅ ከማንም አገር ጀርባ አታሴርም፤›› ማለታቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

‹‹ለኢትዮጵያውያን ወንድሞቼ ማረጋገጥ የምፈልገው ግብፅ ምንም ዓይነት ድጋፍ ለኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች አላደረገችም፡፡ መቼም አታደርግም፤›› ማለታቸውም ተሰምቷል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ይህንን ይበሉ እንጂ የግብፅ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተለያዩ ጊዜያት ከቀጣናቸው በመውጣት አለመረጋጋት የሚታይባቸውን የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በድብቅ በመጎብኘት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡

ከእነዚህም አገሮች መካከል ኤርትራ አንዷ ስትሆን በዚህች አገር የግብፅ ፍላጐት እንደተሟላ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን በማስጠለል ሲተባበር፣ ግብፅ አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ እያደረገች መሆኑን መንግሥት ይገልጻል፡፡

ይህንኑ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ በሶማሌላንድና በደቡብ ሱዳን ለመድገም እንቅስቃሴ የተደረገ ቢሆንም፣ የሶማሌላንድ መንግሥት አለመቀበሉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በሶማሌላንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መድረክ ዋና ዳይሬክተር ሞሐመድ አህመድ ባርዋኒ፣ የግብፅ መንግሥት ኃላፊዎች ከጥቂት ወራት በፊት በሶማሌላንድ ያደረጉት ጉብኝት ዓላማው፣ በአገሪቱ ጦራቸውን ለማስፈር የሚያስችላቸውን ስምምነት ለመፍጠር ቢሆንም አልተሳካላቸውም የሚል ምላሻቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ዓላማቸውን እውን ለማድረግ ከየመን ጋር የተያያዙ ምክንያቶችን ያቅርቡ እንጂ፣ ጉዳያቸው ኢትዮጵያ ነች የሚል እምነት እንዳላቸው ባርዋኒ ተናግረዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የደቡብ ሱዳንን ችግር እንዲፈታ ኃላፊነት የሰጠው ለምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (IGAD) ቢሆንም፣ ግብፅ በዚህ አካባቢ ጦሯን ለማሰማራት ከፍተኛ ፍላጐት እንዳላት እየገለጸች ትገኛለች፡፡ በግብፅ ለረጅም ዓመታት ግብፅ የቆዩ አንድ ኢትዮጵያዊ ዲፕሎማት እንደገለጹት ከሆነ ደግሞ የግብፅ መንግሥት ሁለት እጆች እንዳሉት ይናገራሉ፡፡

አንደኛው ውስጥ ለውስጥ የሚንቀሳቀስበት ከመንግሥት ጋር ንክኪ የሌላቸው ተደርገው የሚቆጠሩ ተቋማት፣ ነገር ግን ሙሉ የበጀት ድጋፍ በግብፅ መንግሥት የሚደረግላቸው መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ሌላው ግን ራሱ የግብፅ መንግሥት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚፈጽመው ሴራ ነው፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሸን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ባለፈው ዓርብ ባወጣው መግለጫ፣ ባለፉት ዓመታት አገሪቱ ያስመዘገበችውን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማደናቀፍ፣ የወጣቶችን ሕጋዊ የተጠቃሚነት ጥያቄ ጠልፈው መሠረተ ልማቶችን ወደ ማውደም የተሸጋገሩ ኃይሎች ተልዕኮ፣ ወደ ድህነት የተመለሰችና የፈራረሰች አገር መፍጠር ነው ብሏል፡፡

በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች ለዚሁ ዓላማ የተደራጁና በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሚደገፉ የሁከት ኃይሎች የሞከሩት ይህንኑ ነበር ያለው መግለጫው፣ እነዚህ ኃይሎች በተቀናጀ መንገድ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንና የሕዝብ ደኅንነትን አደጋ ላይ ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል በማለት አክሏል፡፡

    

Standard (Image)

በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ችግሮች ላይ የተሰነዘሩ ምልከታዎች

$
0
0

ቅዳሜ ጥቅምት 5 ቀን 2009 ዓ.ም. የሸራተን አዲስ ላሊበላ አዳራሽ ከ250 በላይ በሚሆኑ አንጋፋና ወጣት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፣ በአንጋፋ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት፣ በንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ በሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች፣ በምሁራንና በታዋቂ ግለሰቦች ተሞልቶ ነበር፡፡

በወቅቱ የተሰበሰቡት እነዚህ ግለሰቦች ያሰባሰባቸው ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው፣ ‹‹የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከየት ወዴት? ፈተናዎችና መልካም ዕድሎች›› በሚል ርዕስ በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ የሚሰማቸውን ስሜት ለመግለጽ ነበር፡፡

በዚህ ሙሉ ቀን በተከናወነው የውይይት መድረክ ላይ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ይወክላሉ በተባሉ ተወያዮች አማካይነት ለውይይት መነሻ የሚሆኑ አራት ጽሑፎች ቀርበው ነበር፡፡

በዕለቱ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሑፎች ያቀረቡት ደግሞ አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ፣ የፍሊንትስቶን ሆምስ ባለቤት ኢንጂነር ፀደቀ ይሁኔ፣ የኢዴፓ መሥራችና የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌውና ኢሕአዴግን የወከሉት የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ምክትል ኃላፊ አቶ በረከት ስምኦን ነበሩ፡፡

አራቱ የውይይት መነሻ ሐሳብ አቅራቢዎች ሐሳቦቻቸውን ከማቅረባቸው በፊት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔና የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ አባዱላ ገመዳ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወልዱ ይመስል ስለመድረኩ ጠቀሜታና አስፈላጊነት የመግቢያ ንግግር አድርገዋል፡፡

የመጀመርያ የውይይት መነሻ ሐሳብ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ዶ/ር ካሳሁን ናቸው፡፡ በመነሻ ጽሑፋቸውም የአገሪቷን ያለፉትን 25 ዓመታት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በወፍ በረር ለመቃኘት ሞክረዋል፡፡

የአሁኑ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ አንፃራዊ ሰላም ተገኝቷል በማለት የሚገልጹት ዶ/ር ካሳሁን፣ ‹‹ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም መንገድ ተከፍቷል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ለብሔሮች እንጂ ለአገር ስሜት ብዙም ቦታ አልሰጠም ከሚሉ ሥጋቶች ውጪ ብዙ ይዘቶቹ ተቀባይነት ያገኙ ናቸው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መንገድ ቢከፈትም ቅሉ፣ አሁን የሚታዩት በመንግሥት የታመኑት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሰፊ መሆን ለሒደቱ ተግዳሮት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ለግልም ሆነ ለቡድን ጥቅም የመንበርከክ አዝማሚያ፣ በመንግሥት ተቋማት ላይ የቁጥጥር ማነስ፣ በመንግሥትና በፓርቲ መካከል ልዩነት እየጠፋ መምጣት ሌሎች የሚታዩ ችግሮች ናቸው በማለት፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ሒደት እየገጠመው ያለውን ፈተና ገልጸዋል፡፡

እዚህ ተግዳሮቶች ደግሞ ለብቻቸውም እንኳን ባይሆን በከፊል በቅርቡ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ለተነሳው ተቃውሞ እንደ ምክንያትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ ብለዋል፡፡

የዴሞክራሲ ተቋማትና የሲቪክ ማኅበራት አቅምና አደረጃጀትን በተመለከተ፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን ማንነት በኢትዮጵያ ሁኔታ ስንመዝን መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ እያልን መክፈል እንችላለን በማለት ያስገነዝባሉ፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ግን በአገራችን ባለው ሁኔታ የተነሳ በአብዛኛው የዴሞክራሲ ተቋማት የመንግሥት ተቋማት ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የዴሞክራሲ ተቋማት የመንግሥት መሆናቸው፣ እንዲሁም ከእነዚህ ተቋማት አንፃር ሕጎች መውጣታቸው ችግር ባይኖረውም በአፈጻጸም በኩል የሚታው ክፍተት ግን ችግር ነው፤›› ብለዋል፡፡  ከዚህ አንፃር ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ ሥራቸውን በትክክል እስከሠሩ ድረስ እንደ ዴሞክራሲ ተቋም ሊቆጠሩ እንደሚችሉም አስረድተዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የእንባ ጠባቂ ተቋምን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ደግሞ፣ ‹‹እነዚህ ተቋማት በቂ ሥልጣን ቢሰጣቸውና በቂ አቅም ቢገነባላቸው ሥራቸውን ሊሠሩና ለአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ በቂ ሥልጣን፣ በቂ ጥርስና ጥፍር ያላቸው አይመስለኝም፤››  ብለዋል፡፡

ከአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሚና አንፃር የተመለከቱት ሌላኛው ዘርፍ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃንን ነው፡፡ በዚህም መሠረት፣ ‹‹ምንም እንኳን ሁሉም ነው ለማለት ባልችልም በእኔ ድምዳሜ የመንግሥት ሚዲያ አወዳሽ፣ አሞጋሽና ሚዛናዊ ያልሆነ ነው፤›› በማለት ገልጸውታል፡፡

በተጨማሪም የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያ የአገር ስምምነትና ሚዛናዊነት ማጣት በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሒደት ላይ ብዙ ጫና እያሳደረ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ‹‹ሚዲያዎች ወደ አንድ ወይም ወደ ሌላ ጫፍ የማዘንበል አዝማሚያዎች አሏቸው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡

የግል ሚዲያን በተለከተም፣ ‹‹የግል ሚዲያ ተቋማት በከፊል በራሳቸው ውስንነት በከፊል ደግሞ በመንግሥት ባለሥልጣናትና በደጋፊዎቻቸው ተፅዕኖ አንድ ወይም ሌላ ጫፍ ውስጥ ሲገቡ እናያቸዋለን፤›› በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡

የምሁራን ተግባርና ኃላፊነት ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አንፃር ከየት ተነስቶ የት ደረሰ የሚለውን ክፍል ከመግለጻቸው በፊት፣ ‹‹በአገራችን ትንሽ ከተምታቱ ጽንሰ ሐሳቦች መካከል ምሁር የሚለው ነው፤›› በማለት ምሁር ማን ነው የሚለውን ጥያቄ ሰንዝረው አልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምሁራን ጥናትና ምርምር በማድረግ ስለዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ፣ ስለተግባሩና ስለሌሎች አገሮች ልምድ በርካታ ነገሮችን እንደጻፉ የሚያወሱት ዶ/ር ካሳሁን፣ የአገሪቱን ምሁራን በሁለት ከፍለው አቅርበዋቸዋል፡፡

በዚህም በፖለቲካ አደረጃጀት ረገድ ሕዝቡን በፖለቲካ አደራጅተው በፖለቲካ፣ በመብትና በዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳቦች ንቃተ ህሊናው እንዲያድግ የሞከሩ እንወክለዋለን የሚሉትን የኅብረተሰብ ክፍል ድምፅ ለማሰማት የሕይወት ፋና ወጊዎች በመሆን ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሙከራ መስዋዕትነት የከፈሉ በማለት የገለጿቸው የመጀመርያውን ቡድን ይወክላሉ፡፡

በአንፃሩ ደግሞ አፍራሽ ሚና የተጫወቱ፣ በአልባሌነትና ምን አገባኝ በሚል ስሜት አድፍጠው የተቀመጡ ወይም የሚኖሩ በማለት የገለጿቸው ሌላኛው ቡድን ውስጥ ተካተዋል፡፡

በአጠቃላይ ግን ምሁራን መሆን የሚገባቸው በሚዛናዊነትና በማስረጃ የተደገፉ ድምዳሜ ላይ መድረስ፣ ጥላቻና ፍጥጫን ወደ ጐን አድርገው ስለአገርም ሆነ ስለወገን ጥቅም መሥራትና መታገል፣ አስፈላጊም ከሆነ መስዋዕትነት መክፈል ነው በማለት ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

ሌላው በዕለቱ የመወያያ ሐሳብ ያቀረቡት ደግሞ ኢሕአዴግን ወክለው በመድረኩ የተገኙት አቶ በረከት ስምኦን ናቸው፡፡

አቶ በረከት የ25 ዓመቱን የዴሞክራሲ ግንባታ ጉዞ በተለያዩ ክፍሎች ከፍለው ገለጻ የሰጡ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተፈጠሩት ችግሮች ላይም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ አንፃርም ግጭቶቹ አገሪቱን የማፍረስ አቅም አላቸው ብዬ አላምንም በማለት ተናግረዋል፡፡

ከዚህም በላይ፣ ‹‹አሁን በአገሪቱ አንዳንድ ሥፍራዎች የተከሰቱት ግጭቶች ጠያቂ ኅብረተሰብ በመፍጠራችን የመጣ ነው፤›› በማለት በመንግሥት ባለሥልጣናት የሚሰጠውን ምላሽ አጠናክረው መልሰዋል፡፡ በተጨማሪም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከመገንባት አንፃር ሕዝቡ በፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ላይ ችግር የለበትም በማለት ተከራክረዋል፡፡

ያለፉትን ሁለት ምርጫዎች በኢሕአዴግ ሙሉ የበላይነት መጠናቀቁ ኢሕአዴግ ራሱም አምኖ የምርጫ ሥርዓቱን ለማስተካከል እየሠራ እንደሆነ የገለጹት አቶ በረከት፣ ይሁንና ተቃዋሚዎች ማሸነፍ ያልቻሉትና ምክር ቤቱም በኢሕአዴግና በአጋሮቹ ብቻ የተያዘው ሕዝቡ በድርጅቱ ላይ ፅኑ እምነት ስላሳደረ መሆኑን በመግለጽ፣ ይህም የሕዝብ ድምፅ መከበር እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

ኢሕአዴግ ከ25 ዓመታት በፊት የተረከባት ኢትዮጵያ በመሠረታዊነት አራት መገለጫዎች እንደነበሩት ያብራሩት አቶ በረከት፣ መገለጫዎቹንም በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

ከእነዚህ የአገሪቱ መገለጫዎች መካከል የመጀመሪያው ኢሕአዴግ ከደርግ የተቀበላት ኢትዮጵያ ነፃነቷን ለዘመናት ጠብቃ የቆየች አገር መሆኗ ነው ካሉ በኋላ ‹‹በዚህ ሁላችንም የምንስማማ ይመስለኛል፤›› ብለዋል፡፡

ሁለተኛው የአገሪቱ መገለጫ እንደ አቶ በረከት አገላለጽ ደግሞ ከገናና ሥልጣኔ ወደ ማሽቆልቆል በተራዘመ ሒደት የገባች መሆኗ ነው፡፡ ‹‹ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የምናመጣው ዴሞክራሲ ከማሽቆልቆል ሒደት አውጥቶ ወደ ሥልጣኔ የሚያመራ መሆን ነበረበት፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

ሦስተኛው ከ25 ዓመታት በፊት የነበረው መገለጫ ደግሞ ብዝኃነት ያላቸው ማኅበረሰቦች ያሉባት አገር ሆና ይህን ብዝኃነት በአግባቡ ማስተናገድ ተስኗት የቆየች አገር መሆኗ ነው፡፡

አራተኛውና የመጨረሻው መገለጫ ደግሞ ሕዝቦቿ ለዘመናት ለመብትና ለጥቅም የታገሉ መሆናቸው ሲሆን፣ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገነባው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሕዝቦችን መብትና ጥቅም የሚያስከብር መሆን አለበት በማለት አስረድተዋል፡፡

ከዚህ አንፃር በኢሕአዴግ አማካይነት ከሽግግር መንግሥቱ ጊዜ ጀምሮ ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ ሥርዓት እንዲሰፍን በተደረገው ሁሉን አቀፍና እልህ አስጨራሽ ትግል፣ ፈጣን ዕድገት ከሚያስመዘግቡ አገሮች ተርታ መሠለፍ መቻሏን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ድሎች እንደተጠበቁ ሆነው አሁን በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ለተፈጠሩት ችግሮች ዋነኛ ምክንያቶች ደግሞ፣ ‹‹ዕድገቱ የፈጠረውን ፍላጎት ማርካት ያለመቻልና ይህንን ሊመልስ የሚችል ብቃት ያለው አመራር ያለመኖሩ ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹በየአካባቢው የታዩት ግጭቶች የብሔርና የማንነት ጥያቄ የፈጠራቸውና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ያለማግኘታቸው የፈጠረው ጫና ውጤትም ናቸው፤›› በማለት ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

ሌላው ጽሑፍ አቅራቢ ባለሀብቶችን የወከሉት የፍሊንትስቶን ሆምስ ባለቤት ኢንጂነር ፀደቀ ይሁኔ ናቸው፡፡ እርሳቸውም በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሒደቱ ላይ ‹‹የንግድ ማኅበረሰቡና የግል ባለሀብቱ ሚና ከየት ወዴት? ጥንካሬና ድክመት፣ ቀጣይ አቅጣጫዎች›› በሚል ርዕስ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ አጓጊ የሆነው ምንድነው የሚለውን ጥያቄ በመመለስ ጽሑፋቸውን የሚጀምሩት ኢንጂነር ፀደቀ፣ ለግልና ለወል መብት መከበር የተመቻቸው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ ብዝኃዊ በሉዓላዊነቱና በማንነቱ የሚኮራ ጭቆናን መሸከም የማይችል ሞጋች ኅብረተሰብ፣ በመቶ ቢሊዮኖቹ የሚገመት፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የከተማ መሬት መኖርያ ቤትና የቤት ቁሳቁስ ሀብት በየክልሉ በከተማ ቤተሰቦች እጅ መከማቸቱና መሰል ሁኔታዎች በአገሪቱ ያለው ሁኔታ አጓጊ እንዲሆን አድርጐታል ይላሉ፡፡

አሥጊ የሚሏቸውንም የአገሪቷን ሁኔታ ኢንጂነሩ በጽሑፋቸው መጀመርያ ላይ ይገልጻሉ፡፡ በዚህም መሠረት ያለመቻቻልና ያለመነጋገር ለብሔራዊ መግባባት እንቅፋት መሆናቸው፣ ቀዳሚ ተጠቃሚዎች አድሎዓዊ በሆነ ጥገኝነት መዘፈቃቸው፣ በዋና ከተሞች የተከማቸው ሀብትና የንግድ እንቅስቃሴ ለፍትሐዊ ዕድገት እንቅፋት መሆኑና መልካም አስተዳደርና ልማትን ከማመጣጠን ልማትን ለፀረ ዴሞክራሲያዊነት ምክንያት ማድረግ ሥጋቶች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመሥረት በተካሄደው የሽግግር መንግሥት ዓመታትና ባለፉት ከሕገ መንግሥቱ መፅደቅ በኋላ በነበሩት አሠርት ዓመታት ውስጥ፣ በንግድ ሥርዓቱ ሒደትና በሀብት ክምችት እንቅስቃሴው ላይ የታዩ ጥንካሬንና ድክመቶችን በጽሑፋቸው ዳሰዋል፡፡

በመጨረሻም ‹‹የአዲሲቷ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ቀጣይነት ዛሬ ላይ ቆመን ስናየው ከኢሕአዴግ ህልውና ጋር ምን ያህል ቁርኝት አለው?›› የሚለው ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በዚህም መሠረት፣ ‹‹በፌዴራላዊ ሥርዓቱ ግንባታ ሒደት እያደግን፣ እየበሰልንና እየከበርን የመጣነው የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለይም አርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩና ባለሀብቱ በአብዛኛው የኢሕአዴግን ህልውና፣ የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋትና ብልፅግና ሳንነጣጥል ለዛሬው ማንነታችን ኢሕአዴግን እያወደስን ለነገ ተስፋችንም በኢሕአዴግ ላይ ተንጠልጥለን መጪው ጊዜ ከኢሕአዴግ ጋር ብሩህ ነው እንላለን፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ይህን አመለካከት ከየት አመጣነው? እንዴትስ አዳበርነው? ብለን ጠለቅ ብለን ብንመረምር ምክንያቶቹ ሦስት ናቸው በማለት ያስረዳሉ፡፡

እነዚህም ምክንያቶች ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ብቻ ተጠቅመው በጋራ ጉዳዮች ላይ እየተግባቡ ሕዝቡን አታግለው ራሳቸውም ለመታገል የተዘጋጁ ጽኑ የሰላማዊ ትግል ተቃዋሚዎች የተመናመኑ መሆን፣ የማያቋርጠው የኢሕአዴግ መጠነ ሰፊ ፕሮፓጋንዳ፣ እንዲሁም በጣም አሥጊ የሆነው ጉዳይ ደግሞ ኢሕአዴግን የሚያክል ግንባር የራሱ ውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ ልዩነትን የማይፈቅድ መሆኑ ናቸው ብለዋል፡፡

በማጠቃለያ ነጥባቸውም፣ ‹‹ምን ቢበዛ ምን ቢሰፋ ምን ሥርዓት ቢሆን ያው መሪ እንጂ ሕዝብ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ ሕዝቡስ? የሕዝቡንስ ድርሻ ማን ይዘምርለት? ማን ስለትዕግሥቱና ስለሰቆቃው፣ ስለአሸናፊነቱስ ውዳሴውን ማን ይናገርለት? ሰላማዊው ሕዝብ ሆይ፣ ታጋሽ ሸማች ሆይ፣ ብርቱው አምራች ሆይ፣ ትሁቱ ነጋዴ ሆይ እያለ ማን ያወድሰው?›› በማለት በጥያቄ ጽሑፋቸውን ቋጭተዋል፡፡

ሌላው ጽሑፍ አቅራቢ አቶ ልደቱ አያሌው ሲሆኑ፣ በሽግግር መንግሥቱ ወቅት አሁን በአገሪቱ ካለው ሁኔታ አንፃር የተሻለ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንደነበር በመግለጽ ንግግራቸውን ጀምረዋል፡፡ ነገር ግን ከሽግግር መንግሥቱ የሥልጣን ዘመን አጋማሽ ጀምሮ በተከሰቱ አንዳንድ ፖለቲካዊ ሁነቶች ኢሕአዴግ እውነተኛ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት በአገሪቱ እንዲጠናከር ሳይሆን፣ የራሱን የፖለቲካ የበላይነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ ባልሆኑ መንገዶች ተቆጣጥሮታል በማለት ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት፣ ‹‹በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የሚታዩት ቀውሶች በብዙ ችግሮች ተባብሰው ዛሬ ላይ ከፍተኛ ደረጃ ቢደርሱም፣ የችግሩ መሠረቶች ግን በሽግግር መንግሥቱ ወቅት ከተፈጸሙት ስህተቶች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የወቅቱ የሕዝብ ትግል ትክክለኛ መነሻ ምክንያት ከሥርዓቱ የተሳሳተ ፖሊሲ፣ የመፈጸም ብቃት ማነስ፣ ፀረ ዴሞክራሲና ትምክህተኛ አመለካከትና ድርጊት የመነጨ ነው ብለዋል፡፡ ትግሉ ግልጽ፣ ራዕይና አመለካከት ባለው አካል እየተካሄደ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ‹‹የፖለቲካ ምኅዳሩ እየጠበበ ብቻ ሳይሆን እየተዳፈነ በመምጣቱና የአስተሳሰብ ብዝኃነት በአገሪቱ ቦታ አጥቷል፤›› ያሉት አቶ ልደቱ፣ ይኼም መሠረታዊ የተቃውሞ መነሻ እንደሆነ ሞግተዋል፡፡

‹‹ኢሕአዴግ ለዚህ ሁሉ ድክመት ተጋላጭ ያደረገው ዋናው ምክንያት የሥልጣን የበላይነቱን ያላግባብ አስጠብቆ ለመቀጠል ሲል ሆን ብሎ የፖለቲካ ሙስና ውስጥ የተዘፈቀ ድርጅት መሆኑ ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

የኢሕአዴግን ድክመትና ስህተት ከመንቀስ ባለፈ በአገሪቱ በሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በኩልም ያለውን ችግርና ጥንካሬ አንስተዋል፡፡

‹‹ኮረንቲና ፖለቲካን አንድ አድርጐ በማየት በፖለቲካ ፓርቲዎች ዙርያ ተደራጅቶ የመታገል ባህል በሌለው ሕዝብና ተቃዋሚነትን በጠላትነት ፈርጆ የአፈና ድርጊት በሚፈጽም ሥርዓት ውስጥ ሆነው ሥርዓቱን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ እየታገሉ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገራችን መኖራቸው በራሱ እንደ ጥንካሬ ይቆጠራል፤›› ብለዋል፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሠረታዊ ድክመት የሚመነጨው በዋናነት ከሦስት አቅጣጫ ነው በማለት የሚያስረዱት አቶ ልደቱ፣ እነዚህም የሕዝቡንና የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በአግባቡ ያገናዘበ ጥራት ያለው አማራጭ ሐሳብ ተንትኖ አለማቅረብ፣ ከተሳሳተ የትግል ሥልትና አቀራረብ እንዲሁም ጠንካራ ድርጅት ለመፍጠር የሚያስችል ሁለንተናዊ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ካለመሆን የሚመነጭ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በአገሪቱ ያሉትን ችግሮች የመፍትሔ አቅጣጫን በተመለከተም፣ ‹‹የችግሩ ምንጭ ሙስናና የአፈጻጸም ብቃት ማነስ ብቻ ሳይሆን በዋናነት በፖሊሲ ስህተትና የፀረ ዴሞክራሲ አመለካከት ጭምር መሆኑን ችግሩን ለመፍታት የሚቻለውም በኢሕአዴግ ውስጥ ጥልቅ ተሃድሶ በማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ከሕዝቡና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከሚወክሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሲቪል ማኅበራት ጋር በመምከርና በመተባበር መሆኑን ከልቡ አምኖ መቀበል አለበት፤›› በማለት ከኢሕአዴግ የሚጠበቀውን በመግለጽ አጠናቀዋል፡፡   

    

Standard (Image)

የምርጫ ማሻሻያው የተለዩ ድምፆችን ይታደግ ይሆን?

$
0
0

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በ1987 ዓ.ም. ከፀደቀ ጀምሮ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ለመምረጥ ሥራ ላይ የሚውለው የአንደኛ አላፊ የምርጫ ሥርዓት ተገቢነት ላይ፣ ምሁራንና ፖለቲከኞች ጥያቄ ሲያቀርቡ መስማት የተለመደ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 54(2) ላይ ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች መካከል አብላጫ ድምፅ ያገኘ ተወዳዳሪ አሸናፊ በሚሆንበት የምርጫ ሥርዓት ይመረጣሉ፤›› ሲል ይደነግጋል፡፡ በአብዛኛው የምርጫ ሥርዓት በሕገ መንግሥቶች አይወሰንም፡፡

በምርጫ ሥርዓቱ ላይ ጥያቄዎች መነሳታቸው አዲስ ነገር ባይሆንም፣ በምርጫ 2007 የተገኘው ውጤት ግን ጠንካራ ክርክሮች እንዲነሱ ለማድረግ በቂ ነበር፡፡ በውጤቱ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና አጋሮቹ በፌዴራልና በክልል ያሉ ሁሉንም መቀመጫዎች ማሸነፋቸው መገለጹ ይታወሳል፡፡ ለዚህ የመቶ ፐርሰንት ውጤት የምርጫ ሥርዓቱ አስተዋጽኦ አድርጓል ወይስ አላደረገም የሚለው አጀንዳ ክርክሮቹን አስነስቷል፡፡ በኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያለባቸውን ፈተና የማባባስ አዝማሚያ አለው ወይስ የለውም የሚል ጥያቄም አስነስቷል፡፡ በእነዚህ አንኳር ጉዳዮች ላይ የሕገ መንግሥት ኤክስፐርቶች በሪፖርተር ላይ የሐሳብ ልውውጥ ማድረጋቸውም ይታወሳል፡፡

አንዳንዶች በምርጫ 2002 እና 2007 የተገኘው ውጤት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትርጉም ያለው ሚና እንደሌላቸው ካረጋገጠ በኋላ አገሪቱ የምርጫ ሥርዓቷን ወደ ተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓት መቀየር አለባት ብለው ተከራክረዋል፡፡

በተጨማሪም የመቶ ፐርሰንት ውጤት ተፅዕኖ መገለጫዎች ምን ሊሆኑ ይችላሉ በሚለው ጉዳይ ላይ በርካታ ትንታኔዎች ቀርበዋል፡፡ በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መቶ ፐርሰንት ውጤት እጅግም ያልተለመደ ውጤት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላለ የብዝኃነት አገር ደግሞ ይበልጥ የሚያስደንቅ ያደርገዋል፡፡ በፓርላማ ውስጥ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች መቀመጫ የሌለው አገር ጤናማና የተረጋጋ ዴሞክራሲ ሊኖረው አይችልም ሲሉ ብዙዎች ይከራከራሉ፡፡ አንዳንዶች ገዥው ፓርቲን የሚቃወሙ ድምፆች በፓርላማ ካልተስተናገዱ ሰላማዊና ገንቢ ያልሆኑ የተቃውሞ መንገዶችን ሊከተሉ ይችላሉ ሲሉም አስጠንቅቀው ነበር፡፡ ይህ ነጥብ ምናልባትም አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተነሱትን ተቃውሞዎች ከምርጫ ውጤቱ ጋር ለምን እንደሚያገናኙት አንድ ማሳያ ይሆናል፡፡

የአካባቢያዊ አስተዳደሮች ኤክስፐርት የሆኑት ዶ/ር ዘመላክ አይተነው፣ ‹‹የምርጫ ሥርዓቱ ላይ ለውጥ ለማድረግ መነሻ ሆኗል ብዬ የማምነው የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት የፈጠራቸው የማይፈለጉ ውጤቶችን ነው፡፡ በተለይ ኢሕአዴግና አጋሮቹ የሕግ አውጪውን አካል ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸው አሁን በአገሪቱ የተፈጠረውን ቀውስ ቀስቅሷል ብለው የሚከራከሩም አሉ፤›› ብለዋል፡፡

በርካቶች ገዥው ፓርቲ ከዋነኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማግለሉ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል በማለት ሲመክሩም ነበር፡፡ በዋነኛነት ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ድምፁን የሰጠው ሕዝብ ቅሬታ በሒደት ወደ ግጭት ሊያመራ እንደሚችልም ይገልጻሉ፡፡ መንግሥት የተቃዋሚዎች ሚና መቀነስ ጉዳይን ብዙም ትኩረት ባይሰጠው፣ በሕግ አውጭ አካላት ያልተወከሉ ድምፆች የሚሰሙባቸው አማራጮችን ግን እንደሚፈልግ ቃል ይገባ ነበር፡፡

ነገር ግን አንድ መስተዋል ያለበት ጉዳይ በምርጫ 2002 እና 2007 መካከል ያለው ብቸኛ ልዩነት የአቶ ግርማ ሰይፉ መኖርና አለመኖር ነው፡፡ እርግጥ ነው አንዳንዶች ተቃውሞዎች የተቀሰቀሱት ባለፉት አሠርት በተከሰቱ አሉታዊ ዕርምጃዎች ድምር ውጤት ነው በማለት ይከራከራሉ፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ብዙ ተስፋ ተጥሎበት ከነበረው ምርጫ 97 በኋላ በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳርና የዴሞክራሲ የሽግግር ሒደቱ ወደኋላ እየተጓዘ ነው ሲሉም ይገልጻሉ፡፡

የሕዝቡን ብዝኃነት ያላቸው ፍላጎቶች በተቀናጀ መልኩ ለመወከል ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተሻለ ተመራጭ መድረክ ማግኘት ይከብዳል፡፡ ይሁንና ባለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህን እያደረጉ ስለመሆኑ ማሳያ ለማቅረብ አዳጋች ነው፡፡

በአንዳንዶች ይህን ይቀርፋል ተብሎ ተስፋ የተደረገበትን ማሻሻያ እንደሚያደርግ መንግሥት በቅርቡ አስታውቋል፡፡ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. 5ኛው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ ‹‹ባለፉት ሁለት ምርጫዎች በምክር ቤቶቻችን የገዥው ፓርቲ ሙሉ የበላይነት ተስተውሏል፡፡ ይህ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በተካሄደ ምርጫ የሕዝብ ድምፅ ያስገኘው ውጤት እንደሆነ ባያጠያይቅም፣ ተቃዋሚዎችን የመረጡ የኅብረተሰብ ድምፆች በመኖራቸውና በአብላጫ ድምፅ ወንበር የማግኘት የምርጫ ሥርዓታችን መሠረት በአገራችን ወሳኙ የሥልጣን አካል በሆነው ምክር ቤት የማይወክሉ ድምፆች እንዲኖሩ አድርጓል፡፡ በመሆኑም ከገዥው ፓርቲ በተለዩ ፓርቲዎች የሚወከል ጥቅምና ፍላጎት ያላቸው ማኅረሰቦችን የሚወክሉ ፓርቲዎች በምክር ቤቶቻችን ውስጥ የመሳተፍ ዕድል ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡ ስለሆነም ይህን የመሰለው ሁኔታ ሥርዓታችን ተረጋግቶ እንዲቀጥል ከማድረግ አኳያ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያስከትል በመሆኑ፣ በተቻለ መጠን ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ዴሞክራሲያዊ መድረኮችን በማስፋትና በቀጣዩ ምርጫም በሕግ ማዕቀፍ በተደገፈ አኳኋን የሕዝብ ምክር ቤቶች የተለያዩ ድምፆች የሚሰሙባቸውና የሚፎካከሩባቸው መድረኮች እንዲሆኑ በማድረግ ማስተካከል ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

ተቃዋሚዎች በፓርላማው አለመወከላቸው ለአገር አለመረጋጋት የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው በርካቶች ለዓመታት የመከሩ ቢሆንም፣ ይህን መንግሥት መቀበሉ ድንገተኛ ለውጥ ሆኗል፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ከምርጫ 2007 መጠናቀቅ ሁለት ሳምንታት በኋላ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የምርጫ ሥርዓቱ ላይ ለውጥ እንዲደረግ ስለሚቀርበው ሐሳብ ሲጠየቁ፣ ‹‹የአንደኛ አላፊ የምርጫ ሥርዓት በጣም ዴሞክራሲያዊና አሳታፊነቱ በዓለም ደረጃ የተረጋገጠ ነው፡፡ በተለይ እንደኛ ባሉ ብዝኃነት ባላቸው አገሮች አናሳ ማኅበረሰቦች በሕግ አውጪው ለመወከል ይህ የምርጫ ሥርዓት ምቹ ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

ይሁንና አቶ ጌታቸው የምርጫ ሥርዓቱ ለውጥ ያስፈልገዋል ወይስ አያስፈልገውም በሚለው ጉዳይ ላይ መንግሥት ጥናት አጥንቶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በ2004 ዓ.ም. የተደረገው ጥናት አስፈላጊ ከሆነ በድጋሚ ሊጤን እንደሚችልም ገልጸው ነበር፡፡

ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ተቃውሞዎች በተለየዩ የአገሪቱ ክፍሎች መስማት የጀመሩ ሲሆን፣ መንግሥት ከተቃውሞዎቹ ትክክለኛ የሆኑ የሕዝብ ጥያቄዎችን በተለይም ከመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙትን እንደሚቀበልም ገልጾ ነበር፡፡ መንግሥት ሊወስድ ስላሰባቸው ዕርምጃዎች አራት የኢሕአዴግ አንጋፋ አመራሮች በኢቢሲ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር፡፡

ከእነዚህም አመራሮች አንዱ የቀድሞው የማስታወቂያ ሚኒስትርና ከኢሕአዴግ ጥቂት የሐሳብ አፍላቂዎች አንዱ የሆኑት አቶ በረከት ስምኦን፣ ‹‹የኅብረተሰቡ ብዝኃነት ያለው ፍላጎት በአንድ ፓርቲ ብቻ ሊወከል እንደማይችል ኢሕአዴግ በጥብቅ ያምናል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንድ ፓርቲ ብቻ ተወካዮች ሊኖሩት አይገባም፡፡ ባለፉት ሁለት ምርጫዎች ገዥው ፓርቲ ከሞላ ጎደል ሁሉንም ወንበሮች አሸንፏል፡፡ ይኼ ፓርቲው ፈለገውም አልፈለገው፣ በሕጋዊ መንገድ ተረጋግጦ የመጣ ውጤት ነው፡፡ በውጤቱ ላይ ኢሕአዴግ ውስጥ ክርክር ሲደረግ ነበር፡፡ የምርጫ ሕጉን ለማሻሻል ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር እንመክራለን፤›› ብለዋል፡፡

ከአቶ ጌታቸውና ከአቶ በረከት ሐሳቦች ለመረዳት እንደሚቻለው የምርጫ ሥርዓቱን የማሻሻል ውሳኔ በድንገት የመጣ አይደለም፡፡ ምናልባትም ተቃውሞዎቹ ውሳኔው እንዲፈጥን አድርገዋል ብሎ መረዳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ቁጥራቸው ቀላል የማይባል አስተያየት ሰጪዎች ለውጡ እውነተኛ ነው ብለው አልተቀበሉትም፡፡ ለውጡን ያስገደደው የሕዝብ ተቃውሞና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምክር እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ከዚሁ ጋር በተገናኘ በቅርቡ ኢትዮጵያን የጎበኙት የጀርመኗ መራሒተ መንግሥት አንገላ መርከል በኢትዮጵያ ፓርላማ ንግግር እንዲያደርጉ ሲጋበዙ ያልተቀበሉት ከመቶ ፐርሰንት ውጤቱ ጋር በተገናኘ መሆኑ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም መንግሥታቸው የምርጫ ሥርዓቱን እንደሚያሻሽል የገለጹት ከመርከል ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው፡፡

አሁን ዋናው ጥያቄ የምርጫ ማሻሻያው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱን ችግሮች የመቅረፍ ተፅዕኖ ይኖረዋል ወይ ነው፡፡

ምርጫዎቹ ሲመዘኑ

በኢትዮጵያ የምርጫ ሥርዓት ላይ ንፅፅራዊ ጥናት የሠሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ፣ በዓለም ላይ ሦስት ዋና ዋና የምርጫ ሥርዓቶች እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡

የመጀመሪያው የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት (Plurality/Majority)፣ ሁለተኛው የተመጣጣኝ ውክልና (Proportional representation)፣ ሦስተኛው ደግሞ ቅልቅል (Hybrid/Mixed) ተብለው እንደሚታወቁም ያስረዳሉ፡፡ በሦስቱ የምርጫ ሥርዓቶች ሥር የሚወድቁ ሌሎች በርካታ ንዑስ የምርጫ ሥርዓቶች በተለያዩ አገሮች ተግባራዊ እንደሚደረጉም ያስገነዝባሉ፡፡

‹‹የምርጫ ሥርዓቱን ለማሻሻል ስናስብ ከግምት ውስጥ ማስገባት ያሉብን ነገሮች አሉ፡፡ የነበረው ችግር ምንድን ነው? ምን ችግር ነው ማስወገድ የምንፈልገው? የሚለው ከግምት ውስጥ ገብቶ ከተለያዩ የምርጫ ሥርዓቶች ውስጥ ያሉብንን ችግሮች የበለጠ የሚቀርፈውን የምርጫ ሥርዓት ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ በዋነኛነት ሁለት ነገሮች ከግምት ውስጥ ሊገቡ ይገባል፡፡ አንደኛው መራጭ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በኑሮ ደረጃ በምክር ቤት ውክልና እንዲያገኝ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛ ጠንካራ መንግሥት፣ ፖሊሲና ሕግ ማውጣትና መተግበር የሚችል ማድረግ ደግሞ ሌላው ዓላማ ነው፡፡ ሁለቱን ማጣመር ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር ጌታቸው አሁን በሥራ ላይ ያለው የምርጫ ሥርዓት አንደኛ አላፊ፣ የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት አካል መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ከዚህ ሥርዓት ጥቅሞች መካከል ጠንካራ ፓርቲዎችን (በብዛት ሁለት ወይም ሦስት) የሚፈጥር መሆኑ፣ ጠንካራ መንግሥት የሚፈጥር መሆኑ፣ አፍራሽ ዓላማ ላላቸው ትናንሽ ፓርቲዎች ቦታ የማይሰጥ መሆኑ፣ በወኪሎቹና በሕዝቡ መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት የሚፈጥር መሆኑ ተጠቃሾች መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡

የዚህ የምርጫ ሥርዓት ደካማ ጎኖች በማለት ደግሞ የለዩት ትንንሽ ፓርቲዎች ውክልና እንዲያገኙ ማድረጉ፣ ድምፆችን የሚያባክን መሆኑና የድምፅ መከፋፈልን መጋበዙ መሆናቸውን ነው፡፡

ሁለተኛው ዋነኛ የምርጫ ሥርዓት የተመጣጠነ ውክልና ጠንካራ ጎኖች ደግሞ ድምፆች እንዳይባክኑ የሚያደርግ፣ ፓርቲዎች በክልል ብቻ ተወስነው እንዳይቀሩ ይልቁንም ትንሽ ድጋፍ ባላቸው ቦታዎች ጭምር ሄደው ዘመቻ እንዲያደርጉ ዕድል የሚፈጥር መሆኑ፣ የፖሊሲና የሕግ ቀጣይነትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑና ለሥልጣን ክፍፍል የተመቸ መሆኑ ናቸው፡፡

የዚህ ምርጫ ሥርዓት ደካማ ጎኖች ደግሞ ጠንካራ መንግሥት እንዳይኖር የሚያደርግ መሆኑ፣ የፖሊሲ ግጭትና ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ተግዳሮት የሚፈጥር መሆኑ፣ ብዙ ፓርቲዎች እንዲኖሩና አንዳንዴም በጥምር መንግሥት እንዲካተቱ ማድረጉ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የሕገ መንግሥት ኤክስፐርት ተመራማሪው ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቴዎስ በአንደኛ አላፊ የምርጫ ሥርዓት አሸናፊው የተሻለ ድምፅ ያለው እንጂ፣ የአብዛኛውን መራጭ ይሁንታ ሊያገኝ እንደሚችል አስታውሰው፣ ይህ ባህሪ ፓርቲዎችን ከመከፋፈል ይልቅ አንድነት ለመፍጠር እንደሚያስገድድ ተከራክረዋል፡፡

በተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት አፍራሽ ሚና ያላቸው ትንንሽ ፓርቲዎች ፓርላማና ጥምር መንግሥት ውስጥ ገብተው እንዳይበጠብጡ ለማድረግ፣ ከአጠቃላይ ምርጫ ማግኘት ያለባቸውን የድምፅ ፐርሰንት በሕግ የመደንገግ አሠራር አለ፡፡ ለምሳሌ በጀርመን ከአጠቃላይ መራጩ አምስት በመቶ ያላገኘ ፓርቲ ፓርላማ ወንበር አይሰጠውም፡፡

ለኢትዮጵያ የቱ ይሻላል?

ዶ/ር ጌድዮን ከአንደኛ አላፊና ከተመጣጣኝ ውክልና ውጪ ያሉት የምርጫ ሥርዓቶች እጅግ የተወሳሰቡ ስለሆኑ ለኢትዮጵያ ተገቢ አይደሉም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹በርካታ ማንበብና መጻፍ የማይችል ሕዝብ ባለበት አገር ቀላል የምርጫ ሥርዓት ተፈላጊ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የተለያዩ የምርጫ ሥርዓቶችን ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማነፃፀር አሁን በሥራ ላይ ያለው የተሻለ እንደሆነ የሚከራከሩ አሉ፡፡ በተለይ ጠንካራና የተረጋጋ መንግሥት መፍጠር የሚያስችል የምርጫ ሥርዓት መሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል ሲሉም ይገልጻሉ፡፡

ዶ/ር ጌድዮንም እዚህ ሐሳብ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ‹‹ከድህነታችን፣ ከአካባቢያዊ ፀጥታ ሁኔታችንና ከብሔር ፖለቲካ ትኩሳቱ የተነሳ የተረጋጋና ጠንካራ መንግሥት እጅግ አስፈላጊያችን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሌሎች ግን የአንደኛ አላፊ የምርጫ ሥርዓት አግላይና የአንድን ፓርቲ ፍፁም የበላይነት የሚጋብዝ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ወደ ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት መሸጋገር አለበት ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ የፖለቲካ ተንተኝና የሕግ ባለሙያው የ‹‹አንቀጽ 39›› መጽሐፍ ደራሲ አቶ ውብሸት ሙላት ከዚህ አንፃር ለድምፆች ተመጣጣኝ ወንበር የሚያደላድለው የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ለኢትዮጵያ እጅግ የተሻለ ምርጫ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹መድረክና ሰማያዊ በየቦታው ያገኙት ድምፅ ቢደመርላቸው ኖሮ የተወሰኑ መቀመጫዎች ሊያገኙ ይችሉ ነበር፡፡ ለሚቀጥሉት ዓመታት ሐሳባቸውን በፓርላማው አማካይነት ስለሚያንፀባርቁ እየታወቀ፣ እየተጠናከሩና ደጋፊዎችም እያፈሩ ይሄዱ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

የተመጣጣኝ ውክልና እንደ ኢትዮጵያ ላለ ብዝኃነት ላለው አገር ተመራጭ ነው ሲሉ ሌሎችም ይከራከራሉ፡፡ ዶ/ር ጌታቸው፣ ‹‹የዓለም አገሮችን የዴሞክራሲ ታሪክ ስንመለከት ብዝኃነት ያላቸው አገሮች የምርጫ ሥርዓታቸው የአንደኛ አላፊ ባይሆን የበለጠ የተሳካ አንድነትና የሕዝብ ውክልና ሊያመጡ ይችላሉ ተብሎ በምሁራን የተገመገመ ነው፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የዴሞክራሲ ሽግግር ያደረጉ አገሮች የምርጫ ሥርዓታቸውን ከአንደኛ አላፊ ወደ ተመጣጣኝ ውክልና ወይም ቅልቅል ቀይረዋል፡፡ ለአብነት ኒውዚላንድ፣ ጃፓንና ጀርመንን መጥቀስ ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡

ይሁንና የምርጫ 2007 ውጤቶች ሲታዩ የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ተግባራዊ ቢደረግም፣ የኢሕአዴግ ፍፁም የበላይነትን ለመለወጥ አያስችልም ነበር በማለት የሚከራከሩም አሉ፡፡ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በምርጫው 33 ሚሊዮን ሕዝብ ተሳትፏል፡፡ ይህም መምረጥ ከሚችለው 90 በመቶ ማለት ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል 95 በመቶ የሚያህሉት ለኢሕአዴግና ለአጋሮቹ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ ይህ ማለት አጠቃላይ የተቃዋሚዎች ድርሻ አምስት በመቶ አካባቢ ነው ማለት ነው፡፡ ፓርላማ ለመግባት ዝቅተኛውን ድምፅ ኢትዮጵያ ብትወስን ለምሳሌ እንደ ጀርመን አምስት በመቶ ብታደርግ ወንበር የሚያገኝ ተቃዋሚ አይኖርም ማለት ነው፡፡

ነገር ግን ኢትዮጵያ ከሁለት አንዱን ከመምረጥ ድብልቅ ብታደርግ የተሻለ ነው የሚሉም በርካቶች ናቸው፡፡ መቀመጫቸውን ሆላንድ ያደረጉት የሰብዓዊ መብት የሕግ ባለሙያና ተመራማሪው ዶ/ር አደም ካሴ፣ ኢትዮጵያ ድብልቅ የምርጫ ሥርዓት በመከተል የሁለቱን የምርጫ ሥርዓቶች ድክመት ለመቅረፍና ጠንካራ ጎናቸውን ለማጉላት እንደምትችል ይመክራሉ፡፡ ዶ/ር ጌታቸውና የሕገ መንግሥት ኤክስፐርቱ ዶ/ር ያሬድ ለገሠም ቅልቅል የምርጫ ሥርዓት ለኢትዮጵያ ተመራጭ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡

የምርጫ ሥርዓቱ ጋ ችግር የለም

በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ጠበቃውና የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ ስለምርጫ ሥርዓቱ ማሻሻያ ሲጠየቁ፣ ‹‹ይኼ የቅንጦት ጥያቄ ነው፤›› ነበር ምላሻቸው፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ አሸናፊውን እንዴት እንለይ የሚለው ላይ ከመከራከር በፊት ቅድሚያ በአገሪቱ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ማካሄዳችንን እርግጠኛ እንሁን የሚል ነበር፡፡

ከዚሁ ክርክር ጋር አብሮ በሚሄድ መልኩ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ያሉበት በርካታ ችግሮች ባልተቀረፉበት ሁኔታ የምርጫ ሥርዓቱ ቢለወጥ ምንም ዓይነት ለውጥ አይመጣም ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ዶ/ር ጌድዮን፣ ‹‹የአንደኛ አላፊ የምርጫ ሥርዓት ተቃዋሚዎች ፓርላማ እንዳይገቡ አላደረገም፡፡ የፖለቲካ ነፃነት እጦት ነው ዋናው ችግር፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነፃ የፖለቲካ ምኅዳር አግኝተው እንዲደራጁ፣ ገንዘብ እንዲያሰባስቡ፣ ድጋፍ እንዲያገኙ፣ ሐሳቦቻቸው ለሕዝቡ እንዲሸጡ፣ ሰላማዊ ሠልፍ እንዲያደርጉና ስብሰባ እንዲጠሩ ባለመደረጉ ነው የምርጫ 2007 ውጤት የመጣው፤›› ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ነፃነት በመንግሥትና በተለያየ መንገድ ተቃዋሚዎች እንዲዳከሙ ኢሕአዴግና መንግሥት አስተዋጽኦ አድርገዋል ቢባልም ተቃዋሚዎቹም ከትችት የፀዱ አይደሉም፡፡ የተለያዩ አማራጭ ፖሊሲዎችን የመቅረፅና የኢሕአዴግን ጫና ለመቋቋም የሚያስችል አደረጃጀትና አሠራር አልተከተሉም የሚል ወቀሳ ከተለያዩ አካላት ይሰነዘርባቸዋል፡፡

በተለይ በሥራ ላይ ያለው የምርጫ ሥርዓት ተቃዋሚዎች እንዲቀናጁና እንዲጣመሩ የሚያስገድድ ቢሆንም፣ በተግባር ሲሰነጣጠቁና እርስ በርስ ሲወቃቀሱ የሚስተዋሉ መሆኑ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር እነዚህን ችግሮች በቅድሚያ ሳይፈቱ የምርጫ ሥርዓቱን ከመቀየር ጎን ለጎን እነዚህ ችግሮች ላይ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች መሥራት እንዳለባቸው በርካቶች ይመክራሉ፡፡  

ከዚሁ ጎን ለጎን ሌላ የሚነሳው ጉዳይ የምርጫ ሥርዓቱ ለውጥ በፌዴራል መንግሥቱ ብቻ የተገደበ ነው ወይስ ክልሎችንም ያጠቃልላል የሚለው ነው፡፡ ዶ/ር ጌታቸው፣ ‹‹ለክልሎች የምርጫ ሥርዓት ማውጣት የሚችለው ፌዴራል መንግሥቱ ነው፡፡ ክልሎች የምርጫ ሕግ ማውጣት አይችሉም፡፡ የፌዴራል መንግሥት የሚያወጣው ሕግ የክልሎችን የምርጫ ሥርዓት የተለየ ሊያደርገው ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

ዶ/ር አደም ግን ክልሎች የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ዴሞግራፊክ (የሕዝብ ስብጥር)፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ስላላቸው ወጥ የምርጫ ሥርዓት እንዲከተሉ ሊጫንባቸው እንደማይገባ ይከራከራሉ፡፡

በተመሳሳይ ዶ/ር ዘመላክ ለፌዴራል መንግሥቱ የምርጫ ሥርዓቱን ማሻሻል ማለት ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ማለት ቢሆንም፣ ለክልሎች ግን ይህን ማሻሻያ ለማድረግ ሕገ መንግሥቱ መሻሻሉ ቅድመ ሁኔታ አለመሆኑ ጉዳዩን በተሻለ ቀላል እንደሚያደርገው አስገንዝበዋል፡፡ የምርጫ ሕጉ (አዋጅ ቁጥር 532/1999) የክልሎችና የአካባቢያዊ አስተዳደሮች ምርጫ ከፌዴራሉ በተመሳሳይ በአንደኛ አላፊ የምርጫ ሥርዓት እንዲደረግ ይደነግጋል፡፡ ይህን ሕግ በማሻሻል የተለያዩ ሕጎችን ማውጣት እንደሚቻል አስታውሰዋል፡፡

በ2007 ዓ.ም. የፌዴራልና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ቀጣዩ ምርጫ በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደው በአካባቢያዊ አስተዳደሮች ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ነው፡፡ ‹‹የምርጫ ሥርዓቱ ማሻሻያ ከአካባቢያዊ ምርጫ በፊት መጠናቀቅ አለበት፡፡ ይህም በ2012 ዓ.ም. ለሚካሄደው ምርጫ አዲሱን ሥርዓት ምን ይዞ እንደሚመጣ በአካባቢያዊ ምርጫ ለመሞከር ይጠቅማል፡፡ በተጨማሪም በአብዛኛው በአካባቢያዊ ምርጫዎች ለመሳተፍ በማቅማማት ለሚታወቁት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለመሳተፍ ማትጊያ ሆኖም ያገለግላል፤›› በማለት ዶ/ር ዘመላክ አብራርተዋል፡፡

የምርጫ ሥርዓቱ ማሻሻያ ሒደት ሲጠናቀቅ አገሪቱ ሕገ መንግሥቷን ለመጀመሪያ ጊዜም ታሻሽላለች፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 105 ላይ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል የሚያስፈልገውን ዝርዝር ሥነ ሥርዓት ያስቀምጣል፡፡ ይሁንና ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል መሞከር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ከማፍረስ ያለመለየት አዝማሚያ በኢሕአዴግ ዘንድ ይስተዋላል፡፡ ይህ ጽንፍ የያዘ አቋም በከፊል ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የኢሕአዴግ ተቺዎች አዲስ ሕገ መንግሥት ለማርቀቅ አልያም ያለው ሕገ መንግሥት መሠረታዊ የሆነ ማሻሻያ እንዲደረግበት ለሚያቀርቡት ተደጋጋሚ ጥሪ የተሰጠ ምላሽ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥቱ አንዴ ከተሻሻለ መሰል ጥያቄዎች በብዛት ይመጣሉ በማለት እንዲፈራ ሆኗል ሲሉም የሚገልጹ አሉ፡፡

ዶ/ር ጌታቸው ሕገ መንግሥቶች ከሌሎች ሕጎች የሚለዩት ዋና ምክንያት ለረጅም ጊዜ እንዲያገለግሉ ሆነው የሚሠሩ ሰነዶች በመሆናቸው ቢሆንም፣ ከጊዜው ጋር ለመራመድ ግን ለውጥ እንዲደረግባቸው አስገዳጅ ሁኔታዎች እንደሚኖሩ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ተፈጥሯዊና ጤናማ የሆነ የሕገ መንግሥት ተግባር ነው፡፡ በዓለም ላይ ለረጂም ጊዜ ያገለገሉት ሕገ መንግሥቶች እየተሻሻሉ ባይመጡ ኖሮ፣ አስፈላጊ ሆነው ለረጅም ጊዜ ባልቆዩ ነበር፡፡ የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት የፀደቀው የእኛ ሕገ መንግሥት ከወጣ ከአንድ ዓመት በኋላ ነው፡፡ ነገር ግን ባለኝ መረጃ እስካሁን 17 ጊዜ ተሻሽሏል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ እውነት አንፃር የምርጫ ሥርዓት ማሻሻያው በር ከፋች ዕርምጃ እንደሆነ ዶ/ር ጌታቸው አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹በተመሳሳይ ሁኔታ ሌሎች ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው አንቀጾችም እንዲሻሻሉ ማድረግ ሕገ መንግሥቱ ይበልጥ ቅቡልነት ያለውና ለዜጎች ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥ ያደርገዋል፡፡ ተጨባጭ ሁኔታዎች የሚጠይቋቸውን ለውጦች ማስተናገድ አለበት፤›› በማለትም ጠቀሜታውን አብራርተዋል፡፡               

 

Standard (Image)

ሹመትን በብቃት - የጨፌ ኦሮሚያ ፈለግ

$
0
0

ኢሕአዴግ ደርግን በነፍጥ አሸንፎ ሥልጣን በያዘባቸው 25 ዓመታት ውስጥ የመሠረተው ሥርዓት እንደ ዘንድሮ እንደ ብረት የጠነከረ ፈተና ተደቅኖበት የሚያውቅ አይመስልም፡፡

ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ያፀደቀው በብዙዎች እምብዛም እንከን የማይወጣለት ፌዴራላዊ ሕገ መንግሥት፣ በተለይ እዚህ አገር በነበሩ ተከታታይ ሥርዓቶች የማንነት ጭቆና የደረሰባቸው ሕዝቦች ተቀባይነት እንደነበረው ብዙዎችን የሚያስማማ ነው፡፡ ሆኖም ኢሕአዴግ በሕዝቦች ዘንድ ያገኘውን ተቀባይነት ያህል በተለይ ‹‹የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎች›› የሚላቸው ተቃዋሚዎች በተለያዩ ግንባሮች የተቃወሙት ቢሆንም፣ ሥርዓቱን ለአደጋ የጣሉበት ጊዜ አልነበረም፡፡

እንደ በር ከፋች ተደርጎ የሚታየው የ1997 ዓ.ም. ምርጫም ቢሆንም ተንታኞች እንደሚሉት፣ በኢሕአዴግ በድርቅና የተሞላ ፖለቲካና በተቃዋሚዎች ኃላፊነት የጎደለው ቅስቀሳ ምክንያት መጨረሻው የማያምር ሆኖ ተጠናቋል፡፡

ይህን ክስተት ተከትሎ መንግሥት የወሰዳቸው ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች በብዙዎች የተተቹ ነበሩ፡፡ የተከፈተውን የዴሞክራሲ በር የሚዘጉ በሚል፡፡ ከእነዚህም መካከል የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን ጨምሮ በግል ሚዲያና በሲቪክ ማኅበረሰቦች ላይ የወጡ አዋጆች ተቃዋሚዎችን ‹‹ማፈናፈኛ አሳጥተዋል›› ተብለው የተተቹ ሲሆን፣ እንደተገመተው ቀጥሎ በተካሄደው አራተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ያላንዳች ተቃውሞ ኢሕአዴግ ከሁለት መቀመጫዎች በስተቀር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ተቆጣጥሮታል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት የተካሄደው አምስተኛው ዙር ምርጫ ደግሞ ይባስ ብሎ መቶ በመቶ በኢሕአዴግና በአጋሮቹ ሙሉ ቁጥጥር የወደቀበት አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡

በኢሕአዴግ ዘመን ይህ ክስተት የመጀመርያው ሲሆን፣ በፓርቲው እንደ አጠቃላይ ድል ነበር የተከበረው፡፡ ሆኖም ክስተቱን ከገለልተኛ ታዛቢዎችና ከተቃዋሚዎቹ በተቃራኒ የተነተነው ኢሕአዴግ፣ መንግሥት በመሠረተበት ሰሞን በተለይ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰው ሁከት ተቃርኖውን አመላካች ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በመጀመርያ መንግሥት ችግሩን የሥርዓት ቀውስ ሳይሆን የቢሮክራሲ በማድረግ ቀላል አድርጎ ቢገነዘብም፣ በታችኛው የአስተዳደር እርከን የተወሰዱ የማባረር ዕርምጃዎች አልመለሱትም፡፡

መንግሥት አረጋገጥኩት ባለው ማስረጃ መሠረት ከሁከቱና ከአመፁ ጀርባ እንደ ግብፅና ኤርትራ የመሳሰሉ የአገሪቱ ቁጥር አንድ ጠላቶች ነዳጅ ያርከፈከፉ ቢሆንም፣ የአገር ውስጥ ችግር በኦሮሚያ ወጣቶች ሁከት አላበቃም፡፡ በሁለተኛው ትልቁ ክልል በአማራ ክልልም፣ የገዥው ፓርቲ የትጥቅ ትግል መናኸርያ በሆነው በትግራይ ክልልም (አምባስነይቲ) ሳይቀር ተቃውሞ ተሰምቷል፡፡

በተለይ በኦሮሚያና በአማራ አካባቢዎች በዚህ የተነሳ የዜጎች ሕይወት አልፏል፣ በርካታ የአገር ንብረቶችና የልማት አውታሮችም ወድመዋል፡፡ መንግሥትም በቅርቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከማወጅም በቅቷል፡፡ ኢሕአዴግም በጥልቀት ለመታደስ ቃል ገብቷል፡፡

ቀደም ሲል ከገለልተኛ አካላትና ተንታኞች ጥምር ጥያቄ ሲነሳባቸው የቆዩ የሕግ ማዕቀፎች (ለምሳሌ የምርጫ ሕግ)፣ የፓርላማ ብዙኃነት፣ የሦስቱ የመንግሥት አካላት የቁጥጥር ሥርዓት፣ እንዲሁም ደግሞ ሹመት በብቃት ሳይሆን በፖለቲካ ታማኝነት መሆኑን በተመለከተ ለመፈተሽና ለመከለስ ድርጅቱ ቃል ገብቷል፡፡

ኢሕአዴግ ዘግይቶም ቢሆን የሥርዓት ቀውስ መከሰቱን አምኗል፡፡ ከፓርቲ አባላት ውስጥም ሥልጣንን ተጠቅመው ከግንባሩ መንፈስ ውጪ መንቀሳቀሳቸውንና ሥልጣንን ለግል ጥቅም መዋሉን በግላጭ ሊቀመንበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አምነዋል፡፡

ሁለተኛ ህዳሴ?

የግንባሩ አባል ፓርቲ (ሕወሓት) ለሁለት ተሰንጥቆ የድርጅቱ ነባር አመራሮች በ‹‹አንጃነት›› የተባረሩበት 1993 ዓ.ም. የመጀመርያው የህዳሴ ዘመን ተደርጎ ይወስዳል፡፡ እሱን ተከትሎ በፓርቲም ሆነ በመንግሥት የማይነቃነቅ ሥልጣን ነበራቸው የሚባሉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የቀየሱት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ‹‹ልማታዊ›› መንግሥት አስተሳሰብ ላለፉት አምስት ዓመታት ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ያመጣ ቢሆንም፣ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት አደጋ እንደሚሆን አሜሪካዊው ፕሮፌሰር አሌክስ ዲዋል ለሪፖርተር ተናግረው ነበር፡፡ ሌሎችም እንዲሁ ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡

ኢሕአዴግ በተለይ ‹‹አውራ ፓርቲ›› እያለ የሚጠራው አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ መሞከሩ አሁን ለተከሰተው ቀውስ ምክንያት ይሁን አይሁን ባይገልጽም፣ በጥልቀት ለመታደስ መወሰኑን ግን በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡ ለትግበራውም ከሥራ አስፈጻሚ ጀምሮ እስከ ማዕከላዊ ኮሚቴና ታች የአመራር እርከኖች ድረስ እየገመገመ ይገኛል፡፡

የኢሬቻ በዓል ክስተት ከመፈጠሩ በፊት ግምገማዎች በማካሄድ ላይ የነበረው ኢሕአዴግ፣ አራቱ አባል ድርጅቶቹ በየፊናቸው ውስጣቸውን እንዲፈትሹ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡

የሚያስተዳድሩዋቸው ክልሎች ክፉኛ የሁከት መናኸሪያ ከሆኑት ከብአዴንና ከኦሕዴድ ከፍተኛ ዕርምጃ ሲጠበቅ ነበር፡፡ ከመሥራች ድርጅቱ ከሕወሓትም ቢሆን እንደዚሁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሊቀመንበርነት የሚመሩት ደኢሕዴንን ጨምሮ አራቱ አባል ድርጅቶች ከየአቅጣጫቸው ተጠያቂዎችን ከአመራር ለማውረድ፣ ሙሰኞችን ለሕግ ለማቅረብ፣ እንዲሁም አዳዲስ አመራሮች ወደ ላይ ለማምጣት መግለጫ ቢያወጡም፣ እስካሁን በተግባር የታየው የኦሮሚያን ክልል በሚያስተዳድረው በኦሕዴድ ብቻ ይመስላል፡፡    

ቃሉን ያከበረው ኦሕዴድ ነው?

የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ ያደረጉት ንግግር፣ ሁከቱ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ በመንግሥት ከሚሰጡ መግለጫዎች የሕዝቡን ቀልብ የሳበ ይመስላል፡፡

በአሳዛኙ የኢሬቻ በዓል ማግሥት የመጣው የፕሬዚዳንቱ ሰፊ ንግግር አገሪቱ የገባችበትን ቀውስ በጥልቀት የዳሰሰ ነበር፡፡

‹‹መላ የአገራችን ሕዝቦች በየአካባቢው ሲመለከተው የቆየውን በሥልጣን ያለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌና የሕዝብ አገልጋይነት መጓደል መነሻ በማድረግ ሲታገሉ ቆይተዋል፡፡ እነሆ ይህን የሕዝብ ትግል መነሻ በማድረግና ጉዳዩን ከልብ በመቀበል መንግሥት ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ ራሱን ከዚህ ዝንባሌ ለማፅዳት ቁርጠኛ እንቅስቃሴ ማካሄድ ጀምሯል፤›› የሚለው ይገኝበታል፡፡ በግግራቸው መቋጫ ቀደም ሲል በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተነገረውን የ15 ዓመታት የህዳሴ ዘመቻ በሚያብራራ አገላለጽ፣ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የአመራር ሥርዓት በአዲስ መልክና ቅኝት ለማዋቀር ተግባራዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድ መንግሥትን ወክለው ቃል ገብተዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱን ንግግር ተከትሎ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጣ ሲሆን፣ አንፃራዊ የፖለቲካ መረጋጋት መጥቷል፡፡ ሕዝቡ በፕሬዚዳንቱ የተገባውን ሥር ነቀል ለውጥ እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ ከዚህ በፊት ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተቺዎችን ጨምሮ፣ ለብዙዎች እንደ ሥጋት የታየው በፖለቲካ ታማኝነት ብቻ ሥልጣንን ማግኘት አብቅቶ፣ በብቃት ይተካል ያሉት ቋሚ የአሠራር ሥርዓት እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡

ከጎንደር ጀምሮ እስከ የክልሉ ዋና ከተማ ባህር ዳር ከፍተኛ ሁከት ያስተናገደው ክልልን የሚመራው ብአዴን ባወጣቸው ሁለት ተከታታይ መግለጫዎች፣ ከዞን አመራሮች ጀምሮ እስከ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባደረጋቸው ግምገማዎች ለተፈጠረው ሁከት በሙሉ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር ኃላፊነት እንደሚወስድ አምኗል፡፡ በርካታ አመራሮች ማሰናበቱንና ለቁንጮ የፓርቲ አመራሮችም ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ቢያስታውቅም፣ በግልጽ የተወሰደው ዕርምጃም ሆነ ዕርምጃ የተወሰደባቸውን ተጠያቂ አካላት አልገለጸም፡፡ ሽፍንፍን ያለ መግለጫ ሰጥቷል ተብሎ ይተቻል፡፡ ‹‹ያላንዳች መወላወል የተቀበለውን ተጠያቂነት መሠረት በማድረግ የድርጅትና የመንግሥት አመራሩን መልሶ ያደራጃል፤›› በማለት የገባውን ቃልም ገና አልታየም ወይም አልተገለጸም፡፡ በተመሳሳይ የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትም በተደጋጋሚ ስብሰባ ላይ መሆናቸው ቢነገርም፣ በተግባር ምን እየተሠራ እንደሆነ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ በእርግጥ ከሳምንታት በፊት ሕወሓት ባወጣው መግለጫ የከፍተኛ አመራር ሽግሽግ እንደሚያካሂድ አስታውቆ ነበር፡፡ በተግባር እነማንን ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂ አድርጎ፣ እነማንን አውርዶ፣ እነማንን እንደሚተካ በዚህ ጊዜ የታወቀ ነገር የለም፡፡  

ቀደም ሲል በጥልቀት ለመታደስ ቃል የገባው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ደኢሕዴንም በግንባሩ ውስጥ ሰፍኗል ያለውን ‹‹የትምክህተኝነትን አስተሳሰብ እታገላለሁ ውስጤንም እፈትሻለሁ፤›› ከማለት ውጪ የተገለጸ ነገር የለም፡፡

ከፕሬዚዳንቱ ንግግር 20 ቀናት ቀደም ብሎ መስከረም 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ኦሕዴድ የወሰደው ዕርምጃ ይልቅ ተጠቃሽ ነበር፡፡ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለስድስት ቀናት ባካሄደው ግምገማ ሊቀመንበሩን አቶ ሙክታር ከድርና ምክትላቸውን ወ/ሮ አስቴር ማሞ ከኃላፊነታቸው ማሰናበቱ ይታወሳል፡፡ እሱን ተከትሎ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ የነበሩት አቶ ለማ መገርሳን ሊቀመንበር፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሩን ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁን ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መሰየሙ ጎልቶ የሚታይ ለውጥ አድርጎታል፡፡ የጨፌ ኦሮሚያ በዚህ አልበቃም፡፡

ጨፌው ጥቅምት 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሄደው አምስተኛ የሥራ ዘመን ሁለተኛ ዓመት ሁለተኛ አስቸኳይ ጉባዔ በብዙዎች አብዮታዊ የሚባል ለውጥ አድርጓል፡፡ የቀድሞውን አፈ ጉባዔና የኦሕዴድ አዲሱን ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳን ፕሬዚዳንት አድርጎ መርጧል፡፡ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩትን አቶ እሸቱ ደሴ ደግሞ የጨፌው አፈ ጉባዔ አድርጎ መርጧል፡፡

በአቶ ለማ መገርሳ ቀርበው ሹመታቸው በጨፌው ፀድቆ ቃለ መሃላ የፈጸሙት 21 የክልሉ መንግሥት ካቢኔ ተሿሚዎች ምሁራንና ሙያተኞቹ ሲሆኑ፣ አራቱ የዶክትሬት ዲግሪ አላቸው፡፡ አንድ ኢንጂነርና ሌሎችም ሁለተኛ ዲግሪና ከዚያ በላይ ያላቸው የባለሙያዎች ስብስብ ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ ብዙዎች በተለያዩ የፌዴራልና የክልል የመንግሥት ኃላፊነት፣ እንዲሁም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና በግል ተቋማት ያገለገሉ ሲሆን፣ ከመካከላቸው 16ቱ ከዚህ ቀደም በካቢኔ ውስጥ ያልነበሩ አዳዲስ ተሿሚዎች ናቸው፡፡

በብዙዎች የተዋጣለት ሹም ሽር ተደርጎ እየታየ ያለው የጨፌው ኦሮሚያ ዕርምጃ ሲሆን፣ ስምንቱ የአዲሱ የካቢኔ አባላት የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት አለመሆናቸው እያነጋገረ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ሦስቱ ከዚህ በፊት በጥናትና ምርምር ላይ ተሰማርተው የነበሩና ከነጭራሽኑ የድርጅቱ አባል አይደሉም፡፡ ከተሿሚዎች መካከል ሁለቱ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የተሾሙ ናቸው፡፡ እነሱም አቶ ዓብይ አህመድ ዓሊ የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ኃላፊ፣ እንዲሁም ደግሞ አቶ ስለሺ ጌታሁን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ናቸው፡፡ ሁለቱ ተሿሚዎች በፌዴራል መንግሥት ሚኒስትሮች ሆነው እያገለገሉ ነበር፡፡  

ይህንን ሹም ሽር በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፐብሊክ ፖሊሲ የዶክትሬት ዕጫ አቶ ሔኖክ ሥዩም፣ በክልሉ ምክር ቤት በተወሰደው ዕርምጃ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ብዙዎችን ገልጸዋል፡፡ የራሳቸውን የግል ጥቅማ ጥቅም ትተው ሕዝብን ለማገልገል መወሰናቸውን ያደነቁ ሲሆን፣ አቶ ወንድምአገኝ ነገራ (የንግድና የገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ) የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው በማገልገል ላይ እንደነበሩ ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ እንዲሁም ደግሞ ብዙዎች ፕሮፌሽናሎች ልምድ ያካበቱ መሆናቸውን ለምሳሌ የክልሉ የፕላን ኮሚሽን እንዲመሩ የተመረጡትን ዶ/ር ተሾመ አዱኛን ይጠቅሳሉ፡፡

ብዙዎቹ የክልሉን ሕዝብ በልማት የማሳደግ እልህ ያላቸውና በርካታ ተቋማትን በመለወጥ የሚታወቁ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ሔኖክ፣ በምሳሌነት አቶ ዓቢይ አህመድ ዓሊን (የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ) ይጠቀሳሉ፡፡

አቶ ሔኖክ በአሁኑ ወቅት በመንግሥት የፖሊሲ የጥናትና ምርምር ተቋም በመልካም አስተዳደርና በአቅም ግንባታ ተመሪማሪ ሲሆኑ፣ በተለይ በአሁኑ ወቅት የካቢኔ አባል የሆኑት ብዙዎቹ በወጣቶቹና በተማረው ክፍል ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ በዞን አካባቢም ተመሳሳይ ለውጥ እንደሚደረግ ይጠብቃሉ፡፡

ከሌሎች አባል ድርጅቶች ተመሳሳይ ለውጥ የማይጠብቁት አቶ ሔኖክ በሕወሓት ውስጥ ከፍተኛ የአስተዳደርና የፍትሕ ችግር ቢኖርም፣ ድርጅቱ ውስጥ ይህንን ያህል የፖለቲካ ቀውስ አለመፈጠሩን በምክንያትነት ያስቀምጣሉ፡፡ ተመሳሳይ ለውጥ መደረግ ካለበት በብአዴን እንደሆነ የሚናገሩት ተመራማሪው፣ የ1993 ዓ.ም. ጨምሮ በተለያዩ ወቅቶች በድርጅቱ ህዳሴ ሲደረግ በብአዴን ተደርጎ እንደማይታወቅ ያመለክታሉ፡፡ ‹‹በውስጣችን እንገማገም እንጂ እርስ በርስ ብንናቆር ለውጥ አያመጣም›› የሚል የቆየ እምነት በፓርቲው አመራር ውስጥ እንዳለ አቶ ሔኖክ ያምናሉ፡፡     

በጨፌ ኦሮሚያ የተሾሙት የክልሉ የካቢኔ አባላት

1 አቶ ኡመር ሁሴን፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር

2 አቶ ዓብይ አህመድ ዓሊ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ኃላፊ

3 አቶ ስለሺ ጌታሁን፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ

4 አቶ ቶሎሳ ገደፋ፣ የክልሉ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ኃላፊ

5 አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ፣ የክልሉ የፍትሕ ቢሮ ኃላፊ

6 ዶ/ር ደረጀ ዱግማ፣ የክልሉ የጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ

7 ዶ/ር ሐሰን የሱፍ፣ የክልሉ የደንና አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ቢሮ ኃላፊ

8 አቶ ሀብታሙ ኃይለ ሚካኤል፣ የክልሉ የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ

9 አቶ ደመላሽ ገብረ ሚካኤል፣ የክልሉ የአስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ

10 ወይዘሮ ሎሚ በዶ፣ የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ

11 አቶ አሰፋ ኩምሳ፣ የክልሉ የውኃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ

12 ወይዘሮ አዚዛ አህመድ፣ የክልሉ የሴቶችና የሕፃናት ቢሮ ኃላፊ

13 አቶ ወንድማገኝ ነገራ፣ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ

14 አቶ ካሳዬ አብዲሳ፣ የክልሉ የቴክኒክና ሙያ ቢሮ ኃላፊ

15 አቶ ብርሃኑ ፈይሳ፣ የርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ቢሮ ኃላፊ

16 ዶክተር ተሾመ አዱኛ፣  የክልሉ የዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ኮሚሽን ቢሮ ኃላፊ

17 ኢንጂነር ብርሃኑ በቀለ፦ የክልሉ የኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ  

18 አቶ ኤልማ ቃምጴ፣ የክልሉ ዋና ኦዲተር

18 ወይዘሮ ሒሩት ቢራሳ፣ የክልሉ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር

20 አቶ ጌቱ ወዬሳ፣ የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ዳይሬክተር

 

 

Standard (Image)

ግብፅና ሶማሊያ - የማያባሩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሥጋቶች

$
0
0

በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ከሁለት ዓመት በፊት የተቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ጎንደርና ጎጃም የዛሬ ዓመት አካባቢ የተቀጣጠሉት ተቃውሞዎች በኢሕአዴግ ለሚመራው መንግሥት የራስ ምታት ሆነው እስከ 2009 ዓ.ም. የመጀመሪያ ወር ድረስ ዘልቀዋል፡፡

የበርካታ መቶዎችን ሕይወት የቀጠፈውና የመንግሥት፣ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ንብረቶችን ያወደመው የአገር ውስጡ ግጭት አዘል ተቃውሞ ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ተጀምሮ ተግባራዊ በተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንፃራዊ መረጋጋትን አሳይቷል፡፡

ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢያንስ ባለፉት 25 ዓመታት የኢሕአዴግ መንግሥት ቆይታ ጊዜ ውስጥ በይፋዊ መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጣለ ነው፡፡ ከሕገ መንግሥቱ አራት አንቀጾች ውጪ ሌሎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን የሚገድብ ነው፡፡

አዋጁ መተግበር ከጀመረበት ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. አንስቶ እስካሁን ባለው ጊዜ ቢያንስ በአገሪቱ ውስጥ ሰፍኖ የነበረውን አስፈሪ የፖለቲካ ቀውስና የመበታተን ሥጋት ማስተንፈስ የቻለ ስለመሆኑ የብዙዎች እምነት ነው፡፡

በመንግሥት የተደረገው ግምገማም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ይመስላል፡፡ ‹‹በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሲከሰቱ የነበሩትን ሁከትና የአደባባይ ተቃውሞዎች መቆጣጠር ተችሏል፡፡ በመሆኑም የአገሪቱ ሕዝቦች ከአደጋና ጥቃት ሥጋቶች ተላቀው ወደ ቀድሞ የተረጋጋ ሕይወት እንዲመለሱ የሚያስችል መረጋጋትን መፍጠር ችለናል፤›› ሲሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ ረቡዕ ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መጣል ስላስገኘው ፋይዳ ለአገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

በመንግሥት የደኅንነት መረጃዎችና ግምገማ መሠረት በአገር ውስጥ ከተከሰተው ግጭት አዘል ተቃውሞ ጀርባ የግብፅ መንግሥት ተቋማት ድጋፍ እንዳለ በይፋ ተገልጿል፡፡

የግብፅ መንግሥት በኢትዮጵያ የተከሰተውን ተቃውሞ በማቀጣጠል ኢትዮጵያን የመበታተን አጀንዳ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ኢትዮጵያ ባትወነጅልም፣ በግብፅ የሚገኙ አንዳንድ ተቋማት ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገኙ ተቃዋሚ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎችን በገንዘብ በመደገፍና ሥልጠና በመስጠት ተሳትፎ እያደረጉ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ቀደም ብለው በሰጡት መግለጫ ይፋ አድርገዋል፡፡ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትንና የፌዴሬሽን ምክር ቤትን የጋራ ጉባዔ በንግግር የከፈቱት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ የግብፅ ተቋማት በኢትዮጵያ በተከሰተው ሁከትና ተቃውሞ ውስጥ እጃቸው እንዳለ በድጋሚ በይፋ ተናግረዋል፡፡

የግብፅ እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ውጪ

የዓባይ ወንዝ ኢትዮጵያን ከግብፅ ጋር ያስተሳሰረ እምብርት እንደሆነ ቢነገርለትም፣ ከትብብር ይልቅ ጥርጣሬና አለመተማመን የሁለቱ አገሮች ታሪካዊ ግንኙነት መግለጫ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ግብፅ የዓባይን ውኃ በብቸኝነትና በበላይነት ለዘመናት ስትጠቀም ብትቆይም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ከአምስት ዓመታት በፊት በዓባይ ወንዝ ላይ የጀመሩት የኃይል ማመንጫ ግድብ ለዘመናት የኖረውን ኢፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀምና የግብፅ የበላይነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያስቀር እንደሆነ ይታመናል፡፡

የግብፅ መንግሥት ከኢትዮጵያና ከሱዳን መንግሥታት ጋር በሚያደርገው ይፋዊ ግንኙነት ኢትዮጵያ በጀመረችው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ተቃውሞ እንደሌለው ከመግለጽ በተጨማሪ፣ ከግድቡ ውኃ አያያዝና አለቃቅ ጋር ተያይዞ በትብብር ጥናት ለማካሄድና ተፅዕኖዎችን ለመቀነስ ከኢትዮጵያና ከሱዳን ጋር ስምምነት አድርጓል፡፡

ይህ ቢሆንም ግብፅ የተረጋጋችና በኢኮኖሚያዊ አቅሟ እየጠነከረች በፖለቲካዊ ተፅዕኖዋ እየጐላች ወደፊት የምትጓዝ ኢትዮጵያን እንደማትፈልግ የሁለቱ አገሮችን ፖለቲካዊ ግንኙነት የሚከታተሉ የኃይድሮ ፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅሟ መፈርጠም፣ ኢኮኖሚያዊ አቅም ማጠናከርና በዓባይ ወንዝ ላይ በራሷ አቅም ብቻ የውኃውን ፍሰት ለመቆጣጠር መቃረቧ በግብፅ በኩል እንደ ህልውና ሥጋት የሚቆጠር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ግብፅ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ማስቆም በማትችልበት ደረጃ ላይ የደረሰች ብትሆንም፣ ሁሉንም አማራጮች ከመጠቀም ወደኋላ እንደማትልም ያስረዳሉ፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት ጋባዥነት ግድቡ በግብፅ ላይ የሚፈጥረው ጉልህ ተፅዕኖ እንደማይኖር ለማረጋገጥ በተጀመረው የቴክኒክ ጥናት ላይ በኦፊሴላዊ መንገድ እየተሳተፈች፣ በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ እንደ አማራጭ በሌላ እጇ እንደምትጠቀምበት የኢንተለጀንስ ማስረጃዎች ባይኖሩም፣ ከታሪካዊ ግንኙነታቸው መገመት የሚቻል እንደሆነ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ሁነቶች ላይ ያለውን የአድራጊና ፈጣሪነት ሚና የማኮላሸት እንቅስቃሴ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግብፅ በኩል የተያዘ ሥልት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም እንደ ማስረጃ ከሚጠቀሱት እንቅስቃሴዎች መካከል በአዲስ አበባ የግብፅ አምባሳደር በነበሩት አምባሳደር ሞሐመድ እድሪስ የሚመራ የግብፅ መንግሥት የዲፕሎማቶች ቡድን በሶማሊያ ሞቃዲሾ፣ በሶማሌላንድ (ሐርጌሳ)፣ እንዲሁም ከደቡብ ሱዳን መንግሥታት ጋር በቀጣናው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዙሪያ ግብፅ ሚና እንዲኖራት ያደረጉትን ውይይት ይጠቅሳሉ፡፡

የግብፅ ልዑክ በሞቃዲሾና በሐርጌሳ በነበረው ቆይታ የሁለቱ አገሮች መንግሥታት ወታደራዊ ቤዝ እንዲሰጡት የጠየቀ ቢሆንም ሁለቱም መንግሥታት የግብፅን ፍላጎት በይፋ እንደነፈጉ ያስረዳሉ፡፡ ይህ ማለት ግን ምንም የተስማሙበት ነገር የለም ለማለት እንደማያስደፍር ይጠቅሳሉ፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት በአገር ውስጥ ከገጠመው አስፈሪ የፖለቲካ ቀውስ ባላነሰ ትኩረት ሊከታተለው እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

የተለያዩ የውጭ ዘገባዎች የግብፅ መንግሥት ወደ ሶማሊያ የሚያሰርጋቸው ቡድኖች በሶማሊያ የኢትዮጵያን፣ እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ተልዕኮን የማጨናገፍ ሙከራ ላይ ስለመሆናቸው ከሰሞኑ እየጠቆሙ ናቸው፡፡ ባለፈው ረቡዕ ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ መግለጫ የሰጡት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ከቱርክ የዜና ተቋም ግብፅ በሶማሊያ እያሰረገች ስላለው ቡድንና በአካባቢው እያሳየች ስላለው የፖለቲካ ፍላጎት የተመለከተ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡

አቶ ጌታቸው በሰጡት ምላሽም፣ ‹‹የግብፅ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመበጥበጥ በሶማሊያ በኩል እጁን እያሰረገ ስለመሆኑ ኦፊሴላዊ መረጃ የኢትዮጵያ መንግሥት የለውም፡፡ ነገር ግን በትኩረት የምንከታተለው ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

በማከልም በሌላኛው የዓባይ ጫፍ ያለው መንግሥት ኢትዮጵያን ለማተራመስ ፀረ ሰላም ኃይሎችን መደገፍና ማሰማራት ዘመናትን ያስቆጠረ ልማዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ በሥልጣን ላይ ያሉት የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ከኢትዮጵያ እንዲሁም ከአፍሪካ መንግሥታት ጋር አዎንታዊ ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት እያደረጉ በመሆኑ፣ ዘመናትን ያስቆጠረው የግብፅ መጥፎ ልማድ ይቀየራል የሚል ተስፋ በኢትዮጵያ መንግሥት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

በማከልም፣ ‹‹በፕሬዚዳንት አልሲሲ ላይ ተስፋ እናደርጋለን እንጂ በተስፋ ብቻ እጃችንን አጣጥፈን አንቀመጠም፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ‹‹የግብፅ አተራማሽ እጅ በሶማሊያ ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን ከቻልን አስፈላጊውን ዕርምጃ እንወስዳለን፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና መረጋጋትን በተመለከተ አዎንታዊ የፖለቲካ ተሰሚነትን እንዲያገኝ ካስቻሉ ዓብይ ጉዳዮች መካከል፣ ደም ሲያፋስስ ለቆየው የማዕከላዊ ሱዳን መንግሥትና የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ተቀናቃኞች የፖለቲካ ተቃርኖ አስከትሎት ለነበረው ቀውስ መርገብ የተጫወተው ቁልፍ ሚና ተጠቃሽ ነው፡፡

በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አደራዳሪነት ለዓመታት ሲንከባለል የነበረው የፖለቲካ ቀውስ ደቡብ ሱዳንን አዋልዶ ራሷን የቻለች ሉዓላዊ አገር እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ሪፐብሊክ ራሷን የመገንጠል ጥያቄ ጋር የተያያዘው ግጭትና የፖለቲካ ቀውስ በሰላም እንዲፈታ ሁለቱም ወገኖች በአደራዳሪነት በመረጧት ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ኅብረትና በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ ጥረት ውጤት እንዳገኘ ይታወቃል፡፡

‹‹ዕጣ ፈንታችሁ አብሮ መዋኘት አልያም ተያይዞ መስጠም ነው፤›› በሚለው መርህ አዘል ንግግራቸው የሚታወሱት አቶ መለስ ዜናዊ፣ በሁለቱም የሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች በኩል ተሰሚነትን እንዳገኙና በዚሁ መርህም መለያየትን መርጠው በሰላማዊ መንገድ መተግበራቸው ገሃድ ነው፡፡

ደቡብ ሱዳን ተገንጥላ እንደ አገር ከቆመች በኋላም ከሱዳን ሪፐብሊክ በምትዋሰንበት ያልተካለለ ድንበር ዙሪያ ያልተመለሱ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ እስኪያገኙ ድረስ፣ በሁለቱም መንግሥታት ጥያቄ በድንበሩ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላም አስከባሪ ጦር እስከ ዛሬ ድረስ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ደቡብ ሱዳን ከተገነጠለችና እንደ አገር ከቆመች በኋላ ተረጋግታ መቀጠል የቻለችው ለሁለት ዓመታት ብቻ ነው፡፡ ከሁለት ዓመታት ጉዞ በኋላ በሥልጣን ላይ ባሉት የደቡብ ሱዳን መንግሥት ኃላፊዎች መካከል የተፈጠረው ፖለቲካዊ ተቃርኖ ላለፉት አራት ዓመታት አገሪቷ በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች ትገኛለች፡፡ ይህንን ቀውስ ለመፍታት የአቶ መለስ ዜናዊን ሕልፈት ተከትሎ ሥልጣን የተረከቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና መንግሥታቸው ከፍተኛ ጥረት ውስጥ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) የቀጣናውን ፖለቲካዊ ቀውስ በራሱ ለመፍታት ባቀረበው ሐሳብ መሠረት፣ የአፍሪካ ኅብረት ለደቡብ ሱዳን ቀውስ እልባት ለመስጠት እየጣረ የሚገኘው ቡድን በኢትዮጵያ ሊቀ መንበርነት እየተመራ ሲሆን፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት፣ እንዲሁም በአውሮፓ ኅብረትና በአሜሪካ ዕውቅና እንዳገኘ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ይሁን እንጂ የምሥራቅ አፍሪካ መንግሥታት በኢጋድ ውስጥ ሆነው እያደረጉት የሚገኘው ጥረት እስካሁን ለደቡብ ሱዳን ቀውስ መፍትሔ አላመጣም፡፡ ከእነዚሁ አገሮች የተውጣጣ ሰላም አስከባሪ ኃይል በደቡብ ሱዳን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን መከራና ስደት መታደግ አለመቻሉ ገሀድ የወጣ እውነት ሆኗል፡፡ ለዚህ ስኬት አልባ ጉዞ የኢጋድ አባል አገሮች በተለይም ኡጋንዳ በደቡብ ሱዳን ላይ ያላት የግል ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የችግሩ ምንጭ እንደሆነ፣ ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ የተባለው ዓለም አቀፍ የሰላምና የደኅንነት ተቋም ትንተና ይጠቁማል፡፡

በደቡብ ሱዳን የንፁኃንን መከራና ስደት ቢያንስ መግታት እንዲቻል በኢጋድ አባል አገሮች የተሰማራው ሰላም አስከባሪ ኃይል ውጤታማ እንዲሆን ተዋጊ ኃይል ሊኖረው እንደሚገባ በኢትዮጵያ በኩል የቀረበው ሐሳብ፣ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ኅብረት እንዲሁም በጉዳዩ ተባባሪ በሆኑት የተመድ የፀጥታ ምክር ቤት፣ በአውሮፓ ኅብረትና በአሜሪካ ተቀባይነት እንዳገኘ ተዘግቧል፡፡

በዚህ ውሳኔ መሠረትም ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያና ከሩዋንዳ ብቻ የተውጣጣ ተዋጊ ኃይል በደቡብ ሱዳን እንዲሠማራ ውሳኔ ተላልፏል፡፡ ኡጋንዳን ያገለለው ይህ ውሳኔ ከተወሰነ ወራት ቢያልፉም እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም፡፡

ለዚህ ምክንያቱ በኡጋንዳ በኩል የቀረበው ጠንካራ ተቃውሞ እንደሆነ የሚያሳዩ ዘገባዎች እየወጡ ይገኛሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የግብፅ መንግሥት ፍላጎት ባልተለመደ ሁኔታ እየተንፀባረቀ ይገኛል፡፡

የግብፅ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ደቡብ ሱዳን በመገኘት ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋር መነጋገራቸውንና የውይይቱ አጀንዳም የግብፅ ጦር በሰላም አስከባሪነት በደቡብ ሱዳን እንዲሠማራ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም የግብፅ መንግሥት ከሰሞኑ የደቡብ ሱዳንን ግጭት ለመቆጣጠር የሰላም አስከባሪ ጦር የመላክ ፍላጎት እንዳለው የሚገልጽ ይፋዊ ጥያቄ ለአፍሪካ ኅብረት ማቅረቡ ተገልጿል፡፡

ይህ የግብፅ ፍላጎት ለኢትዮጵያ ሥጋትን የሚጭር እንደሆነ ባለሙያዎች ይገምታሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ከምትገነባበት ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተሻለ አካባቢያዊ ቅርበት ያላት ደቡብ ሱዳን መሆኗን ይጠቅሳሉ፡፡ በመሆኑም የግብፅ መንግሥት በግድቡ ላይ ወታደራዊ ጥቃት ለማድረስ ቀደም ሲል የተገለጸ ፍላጎቱን እውን ማድረግ የሚያስችለው በመሆኑ ነው፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ የተጠየቁት አቶ ጌታቸው፣ ግብፅ እንደ ማንኛውም አገር መንግሥት ለደቡብ ሱዳን ቀውስ የመፍትሔ አካል ለመሆን ያላትን ፍላጎት ኢትዮጵያ በሥጋት ላይ ተመሥርታ የማደናቀፍ ጥረት ውስጥ እንደማትገባ ተናግረዋል፡፡

‹‹የግብፅ መንግሥት በማንኛውም ሁኔታና በማንኛውም ቦታ ኃላፊነት የተሞላበት ተግባር በትክክለኛው አግባብ ይፈጽማል ብለን እናምናለን፡፡ ይህ እምነታችን ግን በተስፋ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው፡፡ ተስፋ ይዘን የሚሆነውን ብቻ አንጠብቅም፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ‹‹ግብፅም ሆነች ሌላ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ አሻጥር ለመፈጸም መስመር የሚያልፍ ከሆነ የምናደርገውን በጊዜው እንወስናለን፤›› ብለዋል፡፡

ያልተጠናቀቀው የቤት ሥራ በሶማሊያ

ለ16 ዓመታት መንግሥት አልባ ሆና የአፍሪካ ቀንድ ሥጋት ከዚህ አልፎም የዓለም የሽብር ተግባር መጠንሰሻ የሆነችው የኢትዮጵያ ጎረቤትና ከባህላዊ መስተጋብር የዘለለ የደም ቁርኝት ያላት ሶማሊያን ከፖለቲካዊ ቀውስ በማውጣት የኢትዮጵያን ሥጋት ለማስወገድ፣ እ.ኤ.አ. በ2006 ኢትዮጵያ ጦሯን ወደ ሶማሊያ ማስገባቷ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያን ሥጋት ውስጥ የከተተው የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት ተደራጅቶ ሶማሊያን በእስላማዊ የመንግሥት ሥርዓት ለማስተዳደር ተጠናክሮ መስፋፋቱ አይዘነጋም፡፡ በዚህ የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት ውስጥ በመሪነት የተሰበሰቡት የአገሪቱ ዜጎች የተደበቀ ማንነት ዓለም አቀፍ አሸባሪ ከሆነው አልቃይዳ ጋር ጥብቅ ትስስር እንዳለው መታወቁ፣ ለኢትዮጵያ መንግሥት ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት መነሻ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ይህንን የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት ስብስብ በወታደራዊ ጥቃት የበታተነው የኢትዮጵያ ጦር ተልዕኮውን ካጠናቀቀ በኋላ እ.ኤ.አ. በ2009 ሶማሊያን ለቆ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ የተበታተነው የእስላማዊ ኅብረት ስብስብ ዋነኛ አመራሮች በኤርትራና በሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች መደበቂያቸውን ማድረጋቸውም አይዘነጋም፡፡

ይህንን ተከትሎ በሌላ አደረጃጀት ተመሳሳይ ዓላማና ቁርኝት ከአልቃይዳ ጋር የፈጠረው የሶማሊያ ወጣቶች ፖለቲካዊ ድርጅት አልሸባብ በአገሪቱ መስፋፋት መጀመሩን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ ከአራት ወራት በኋላ ዳግም ወደ ሶማሊያ እ.ኤ.አ. በ2009 ጦሯን ለማስገባት ተገዳለች፡፡

ለኢትዮጵያ መንግሥት የአልሸባብን ስብስብ ከማዳከም ዋና ተልዕኮው ጐን ለጐን በአገሪቱ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ሌላው ዓላማ ነበር፡፡ ሁለቱም ተልዕኮዎች በተወሰነ ደረጃ በወቅቱ የተሳኩ ቢሆንም፣ አልሸባብ ሥልቱን ቀይሶ በሽምቅ ጥቃቶች የሽግግር መንግሥቱን ማዳከሙን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡

የሶማሊያ ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነትን የሚጠይቅ ቢሆንም ኢትዮጵያ አልፎ አልፎ ከአሜሪካና ከአውሮፓውያን ኃያላን ከምታገኘው ድጋፍ ውጪ ሙሉ ኃላፊነቱን እንድትሸከም መገደዷ፣ ስትራቴጂያዊ የፖለቲካ ውሳኔ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል፡፡ ይኸውም በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ላይ የተጋረጡ ሥጋቶችን ብቻ ማስወገድ የትኩረት አቅጣጫዋ በማድረግ እ.ኤ.አ. በ2010 ጦሯን ከሶማሊያ በማስወጣት ወደ ድንበሯና በድንበሯ አቅራቢያ በሚገኙ የሶማሊያ ከተሞች አስፍራለች፡፡ ስትራቴጂያዊ ትኩረቱም ኢትዮጵያን ሊፈታተኑ የሚችሉ ሥጋቶችን የኢትዮጵያ ጦር ከሠፈረበት በመወርወር መቀልበስ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

አልሸባብ ቀድሞ በደረሰበት የኢትዮጵያ ጥቃት በመዳከሙ ጥንካሬውን ለመመለስ የቀየሰው ሥልት ኢኮኖሚያዊ አቅሙን መመለስ ሲሆን፣ በዚህም በአካባቢው የንግድ መርከቦችን በመጥለፍና በማገት የንግድ መርከቦቹ አገሮችንና ባለሀብቶችን የመደራደር ግዴታ ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ እያንዳንዱን የተጠለፈ የንግድ መርከብ ለማስለቀቅ በሚደረግ ድርድር በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን በመሰብሰብ ኢኮኖሚያዊ አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ አጐልብቷል፡፡ የአልሸባብ ተዋጊዎች በንግድ መርከብ ጠለፋ ሚሊዮን ረብጣ ዶላሮችን በገሃድ ሲያካብቱ ሊገዳደራቸው የሞከረ አለመኖሩ ይታወቃል፡፡ ይህ የአልሸባብ ሥልት ኢኮኖሚያዊ ጉልበቱን ካፈረጠመ በኋላ የአሜሪካ መንግሥት የተጠለፉ የንግድ መርከቦችን ለማስለቀቅ የገንዘብ ድርድር አገሮችም ሆኑ ድርጅቶች እንዳያደርጉ ተፅዕኖ በማሳደር፣ በሰው አልባ አውሮፕላኖች የአልሸባብ ታጣቂዎችና አመራሮቻቸውን የሥለላ መረጃ በመታገዝ መደብደብ መጀመሩ አልሸባብ ከባህር ውንብድናው እንዲወጣ እንዳደረገው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ይህንን ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት ከአሜሪካና ከአውሮፓውያን ኃያላን ጋር በመሆን በሶማሊያ መረጋጋትን ለመፍጠር ከአካባቢው አገሮች የተውጣጣ ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲላክ ወስነዋል፡፡ በዚህ መሠረት በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የሚደገፍ ከአካባቢው አገሮች የተውጣጣ ሰላም አስከባሪ ኃይል በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ተልኳል፡፡ ከኬንያ፣ ከብሩንዲ፣ ከሩዋንዳና ከጂቡቲ የተውጣጣው በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ጦር በሞቃዲሾና በተለያዩ የሶማሊያ ግዛቶች ቢሰማራም፣ ውጤታማ እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻሉ ይጠቀሳል፡፡

የእነዚህ አገሮች ወታደሮች ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ የአልሸባብ ኃይሎች አገሮቹ ላይ ያነጣጠረ የሽብር ጥቃትን ማካሄድ መጀመራቸው ይታወሳል፡፡

በቅርብ ጊዜ ከፈጸሙት ውስጥም በኬንያ የውጭ ዜጎች በሚያዘወትሩበት ዌስት ጌት የገበያ ማዕከል ላይ ያደረሱት ጥቃትና ዕገታ የሚታወስ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ የኬንያ ብሔራዊ መከላከያ ኃይል ወደ ሶማሊያ በሙሉ ኃይሉ መግባቱ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ የማይወጣው አጣብቂኝ ውስጥ በመግባቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ጦር ወደ ሶማሊያ እንዲገባ በይፋ የአፍሪካ ኅብረትን መጠየቁ ይታወሳል፡፡

ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት 2,000 ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን በአፍሪካ ኅብረት ሥር ወደተደራጀው ሰላም አስከባሪ ኃይል መላኩ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን ቁጥሩ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠር ጦር ከአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ውጪ አልሸባብን በንቃት እንዲዋጋ መላኩ አይዘነጋም፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት ሥር ከተሰማራው ሰላም አስከባሪ ኃይል ውጪ ያስገባችው ጦር በሶማሊያ አልሸባብን በማጥቃትና ሰላም አስከባሪ ኃይሉን በመደገፍ የተጫወተውን ግዙፍ ሚና በርካቶች አድንቀውታል፡፡

በሶማሊያ የተፈጠረውን አንፃራዊ ሰላም በመጠቀም በሶማሊያ አገር አቀፍ ሕዝባዊ ምርጫ ዝግጅት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የሶማሊያ መንግሥትን በተናጠል የመደገፍ እንቅስቃሴ ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በሶማሊያ ሊያገኙ የሚችሉትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማጠናከር ላይ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህ ውስጥ ተጠቃሾቹ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኳታርና ቱርክ ይገኙበታል፡፡ የቱርክ መንግሥት የሶማሊያ አውሮፕላን ማረፊያን ማስተዳደር ጀምሯል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የቱርክ አየር  መንገድ የቀጥታ በረራ ወደ ሞቃዲሾ ጀምሯል፡፡ በሌላ በኩል የሶማሊያ የባህር ወደቦችን ለማስተዳደር ድርድር እያደረጉ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በሌላ በኩል የቱርክ መንግሥት ታላቋን ሶማሊያ መልሶ ለመፍጠር በሞቃዲሾ የሚገኘውን የሶማሊያ ጊዜያዊ መንግሥትና የሶማሌላንድ መንግሥትን የማደራደር ሥራ ውስጥ መግባቱን መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ የሚናገሩ አሉ፡፡

ያለማንም ድጋፍ በሶማሊያ ወታደሮቿን ያሰማራችው ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ የፖለቲካ ቀውስ መግባቷም አይዘነጋም፡፡ በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰላም አስከባሪ ጦሩ ውጪ ያሉ ወታደሮችን ከሶማሊያ ማስወጣት ጀምሯል፡፡ ይህንን ተከትሎም ከአልሸባብ ነፃ የነበሩ አካባቢዎች ዳግም በአልሸባብ ቁጥጥር ውስጥ እየወደቁ ይገኛሉ፡፡ በጉዳዩ ላይ የተጠየቁት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ‹‹ሶማሊያ የገባነው እስከ መጨረሻው እዚያ ልንቆይ አይደለም፡፡ ስለዚህ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ላለፉት ዓመታት ሁሉንም ዓይነት መስዋዕትነቶችን የኢትዮጵያ ወታደሮች መክፈላቸውንና የኢትዮጵያ መንግሥትም ላለፉት ዓመታት ከፍተኛ ወጪ ሲያወጣ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በአፍሪካ ኅብረት ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ጦር ለሰላም አስከባሪ ኃይሉ የተሰጠው የኃላፊነት ጊዜ እስኪያበቃ ድረስ እንደሚቆይ አስታውቀዋል፡፡               

   

 

Standard (Image)

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ከተዳቀለ የምርጫ ሥርዓት እስከ ግብፅ ጣልቃ ገብነት ዲፕሎማሲ

$
0
0

ቀደም ብሎ በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ተቃውሞና አመፅ ምክንያት መንግሥት በተደጋጋሚ የሕዝብ ቅሬታ በዋናነት ከመልካም አስተዳደር መጓደሎችና ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የመነጩ ችግሮች ስለመሆናቸው ሲናገር ተደምጧል፡፡ ይህንኑ ችግር ለመቅረፍና የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ መንግሥት ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ››ን ተግባራዊ ለማድረግ ስለመነሳቱ፣ እንዲሁም በመንግሥት የአስፈጻሚው አካል ላይ ለመልካም አስተዳደር ብሶቶች ምንጮች የተባሉና ደካማ አፈጻጸም ያሳዩ አካላት ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ፣ የካቢኔ ሹም ሽርና ሽግሽግ እንደሚደረግ ሲገለጽም መሰንበቱ ይታወሳል፡፡

ይህም በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም ሆነ በፓርቲያቸው ተደጋግሞ ቢገለጽም፣ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. የፓርላማው ሁለተኛ የሥራ ዘመን ሲጀመር በፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የመክፈቻ ንግግርም ዓብይ ትኩረት ተሰጥቶት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በዚህም መነሻ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው፣ በምክር ቤቱ የአሠራርና የሥነ ምግባር ደንብ መሠረት በፕሬዚዳንቱ የቀረበውን የመክፈቻ ንግግር አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያና በዚያ ላይ በመመሥረት ከአባላቱ ለሚነሱ ጥያቄዎች የሚሰጡት መልስ የበለጠ ተጠባቂ አድርጎት ሰንብቷል፡፡

የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ከተከፈተ ሦስት ሳምንታት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማክሰኞ ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በምክር ቤቱ ተገኝተው ነበር፡፡ ሙሉ ቀን ተሰይሞ በዋለው የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም 30 ከሚሆኑት የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸው ውስጥ ዘጠኙን ነባር ሚኒስትሮች በኃላፊነታቸው እንዲቀጥሉ፣ ሃያ አንዱን ደግሞ በአዳዲስና በተወሰኑት በነባር ሚኒስትሮች በማሸጋሸግ አዲሱን የመንግሥታቸውን ካቢኔ አስተዋውቀዋል፡፡

የካቢኔ አወቃቀርና ለሹመቱ የተመረጡ ግለሰቦችን በዕለቱ የጠዋቱ ፕሮግራም ካስተዋወቁ በኋላ ከቀትር በኋላ በነበረው ፕሮግራም አቶ ኃይለ ማርያም በበርካታ ጉዳዮች ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ትኩረት ሳቢ ሆነው የታዩት ፖለቲካዊና የፀጥታ ጉዳዮች ናቸው፡፡

የተዳቀለ ምርጫ ከ25 ዓመታት በኋላ

የኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ላለፉት 25 ዓመታት ሁለት ዓይነት ገጽታዎችን አስተናግዷል፡፡ በተለይ ከፌዴራላዊ ሥርዓቱ መዋቀር ጋር በተያያዘ በመጀመሪያዎቹ አሥር ዓመታት ተስፋ የሰነቀና በማበብ ላይ ያለ ይመስል ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ግን ከምርጫ 97 በኋላ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እየሞተ መምጣቱን የሚገልጹ አሉ፡፡

ለዚህ ክርክርም እንደማሳያ ከሚጠቀሱ ዓብይ ጉዳዮች ውስጥ ባለፉት ሁለት አገራዊና ክልላዊ ምርጫዎች የምክር ቤቶች ውክልና ሙሉ ለሙሉ በገዢው ፓርቲና በአጋሮቹ መያዙን፣ የተቃዋሚ ጎራውንና የግል ተወዳዳሪዎችን ሙሉ በሙሉ ማግለሉን ነው፡፡

በዚህም ምክንያት ገዢው ፓርቲ የዴሞክራሲ ግንባታውንም ሆነ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ እያጠበበው ነው ተብሎ ሲወቀስ ቆይቷል፡፡ ገዢው ፓርቲም በበኩሉ ትችቶችን ከመቀበል ይልቅ ዴሞክራሲያዊነቱንና በሕዝብ ተመራጭ በመሆን ወደ አውራ ፓርቲ እያደገ ስለመምጣቱ ይከራከር ነበር፡፡

ዘግይቶም ቢሆን ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ገዥው ፓርቲ የአውራ ፓርቲነት አካሄድ መለወጥ እንዳለበት የተቀበለ ይመስላል፡፡

በምክር ቤት ውሏቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንኑ ነበር ያረጋገጡት፡፡ ‹‹የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት የሚባለው ሥርዓት በዓለም ላይ ካሉት ሦስት የዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሥርዓቶች አንዱ ነው፡፡ አገራችን በመረጠችው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ይህን የምርጫ ሥርዓት ላለፉት አምስት ምርጫዎች ስንጠነቀቅም ቆይተናል፡፡ በዚህ ሥርዓት የአብዛኛው መራጭ ሕዝብ ውክልና ሲኖረው አነስተኛ ድርሻ ያለው ሕዝብ በምክር ቤት ውክልና የለውም ማለት ነው፤›› በማለት ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥት ይህንን ሥርዓት ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በጥናት ሲመረምረው መቆየቱን ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡

‹‹ይህንን ከግምት በማስገባት የአገራችንን ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ውክልና በማረጋገጥ፣ እንዲሁም የመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ እንቅስቃሴን በተሻለ ለማሳደግ የተዳቀለ የምርጫ ሥርዓትን በመተግበር የምክር ቤት ውክልናን ማሳደግ አለብን፤›› ብለዋል፡፡

ሌሎች ሥርዓቶች በማለት ከጠቀሷቸው የተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓትና የአብላጫ ድምፅ ውክልናን ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም የተዳቀለ የምርጫ ሥርዓትን ዕውን ማድረግ መጪው ሥራ እንደሚሆን፣ ይህንንም ገዢው ፓርቲ ብቻውን የሚተገብረው ስላልሆነ ከተቃዋሚዎችና ከሌሎች ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር እንደሚነጋገሩ ገልጸዋል፡፡ ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን በይፋ ለሕዝብ ቢገልጹም፣ ሌሎች በተለይ በተቃውሞው ጎራ ያሉ ቡድኖችም ይህንን ሥርዓት በተደጋጋሚ ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡

በተለይ ከሳምንታት በፊት ከቀረበው የፕሬዚዳንቱ የመክፈቻ ንግግር ጋር ተያይዞ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢዴፓና የመድረክ አመራሮችን ይህንኑ አረጋግጠው ነበር፡፡ የኤዴፓ የጥናትና ምርምር ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ ለሪፖርተር ሲገልጹ፣ ‹‹ኢዴፓ የዚህን የምርጫ ሥርዓት በተመለከተ ከአሥር ዓመታት በላይ ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡ ፓርቲያችንም ከዓመታት በፊት የራሱን ጥናት አቅርቦ እንዴት መተግበር እንዳለበት ሲሟገት ኖሯል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር መረራ ጉዲናም በበኩላቸው የተዳቀለ የምርጫ ሥርዓት በፕሬዚዳንቱ መጠቀሱን እንደሚቀበሉት ገልጸው፣ ሥርዓቱ ቀደም ብሎ መተግበር ይገባው እንደነበረ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን የአሁኑ የሕዝብ ጥያቄ መሠረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ያለመ በመሆኑ፣ ከዚህ በኋላ የተለየ ውጤት ያመጣል ብለው እንደማያምኑ ገልጸው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን በአገሪቱ ማጎልበት የመንግሥት አቅጣጫ መሆኑን፣ በተጨማሪም በሕጋዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመደራደር ሕጎችን የማሻሻልና ካስፈለገም የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎችን በመቀበል የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡

የግብፅና የዳያስፖራው ጣልቃ ገብነትን በተመለከተ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ የግብፅ ጣልቃ ገብነትን አስመልክተው እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለግብፅ መንግሥት ግልጽ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ በጣልቃ ገብነት የተጠቀሱት ተቋማት ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ዲፕሎማሲያዊ ምላሽ እንደተሰጠው አስረድተዋል፡፡ የግብፅ መንግሥት በአገሩ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቋማትን እንዲቆጣጠር የሚረገው ጥረት እንደሚቀጥልና ኢትዮጵያም የሰከነ ኃላፊነት የተሞላበት ዲፕሎማሲያዊ ተግባራትን በማከናወን፣ ተገቢውን ሥራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

በውጭ የሚኖሩ ጽንፈኛ የዳያስፖራ አካላትም ኢትዮጵያን ለመበታተን ያላቸውን ሴራ በግልጽ ሳያፍሩ በማንፀባረቅ ላይ መሆናቸውንና በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት መጋለጣቸውን  አስረድተው፣ የጽንፈኛ ኃይሎች መጥፊያ ቅርብ ነው ብለዋል፡፡

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌላው ከተነሱ ጉዳዮች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሚመለከተው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ነበር፡፡ አዋጁ ከታወጀ 22 ቀናት እንዳለፈው አስታውሰው፣ የአገሪቱን ሰላም ማረጋገጥ መቻሉንና በሰብዓዊ ሕይወት ላይ የሚያደርሰውን አደጋ ሙሉ በሙሉ መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በአዋጁ ምክንያት ተሽሽለዋል ያሏቸውን የፀጥታ ጉዳዮች ከጠቀሱ በኋላም፣ የአዋጁ አንዳንድ ድንጋጌዎችም ማላላት ከተቻለም የበለጠ መቀነስ እንደሚቻልም ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

በተለይም የውጭ ዲፕሎማቶች ሳይፈቀድላቸው ከ40 ኪሎ ሜትር ራድየስ ውጪ እንዳይጓዙ ገደብ የተጣለው ድንጋጌ በቅርቡ ሊነሳ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

የአገሪቱን ኤምባሲዎች ስለመጠበቅ

በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ዓብይ ክስተት ከነበረውና በምክር ቤት አባላት ከተነሱት ጉዳዮች ውስጥ፣ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ የኢትዮጵያ ማሲዮንና ቆንጽላ ጽሕፈት ቤቶች ላይ የተቃጣው ጥቃትም ይገኝበታል፡፡

በተለይም በዋሽንግተን ያለውን የኢትዮጵያ ኤምባሲን ጨምሮ በአውሮፓና በአውስትራሊያ የሚገኙ ሚሲዮን ጽሕፈት ቤቶች በትውልደ ኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች ስለመወረራቸውና ጥቃት ስለማስተናገዳቸው፣ በመንግሥት በኩል እየተወሰደ ስላለው ዕርምጃ አቶ ኃይለ ማርያም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ሚሲዮኖች ከሚገኙባቸው አገሮች መንግሥታትና በአዲስ አበባ መቀመጫቸው ከሆኑ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ጋር መንግሥት መወያየቱንና ግልጽ አቋሙን ማሳወቁን ለአብነት አንስተዋል፡፡

በተለይም በሚሲዮኖችና በቆንስላዎች ላይ ጥቃት ያደረሱ ግለሰቦችን ባሉባቸው አገሮች ሕጎች መሠረት በመክሰስ ተጠያቂ ለማድረግ መንግሥት ጠበቃ መቅጠሩንም አቶ ኃይለ ማርያም አመልክተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የውጭ መንግሥታት ለኤምባሲዎች ጥበቃ እንዲያደርጉ ማስጠንቀቃቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከሁሉም አገሮች ጋር ከመነጋገራችንም በላይ ሊያደርጉ የሚገባቸውን ጥበቃ እንዲያጠናክሩ በግልጽ አሳስበናቸዋል፡፡ እኛ የእነሱን ኤምባሲዎች ለራሳችን ተቋማት ከምናደርገው በላይ ጥበቃ እያደረግንላቸው ነው፡፡ ከዚህ በኋላ እነሱ የእኛን ተቋማት በአግባቡ የማይጠብቁ ከሆነ እኛም የእነሱን እንደማንጠብቅላቸው ጨምረን ገልጸንላቸዋል፤›› በማለት ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር

የአገሪቱን ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማረጋገጥ ግብርናውን ማዘመን ዋናው ጉዳይ መሆኑ ሌላው የተጠቀሰው ጉዳይ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የመስኖ ግብርናን ማስፋፋትና ግብርናን መሠረት ያደረጉ የግብርና ግብዓት የሚጠቀሙ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት ትኩረት ይሰጠዋልም ነው ያሉት፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ልማት ማፋጠን፣ የአልባሳትና የጨርቃ ጨርቅ፣ የምግብና የመጠጥ፣ እንዲሁም የቆዳ ኢንዱስትሪውን ማስፋፋትና ማዘመንም የሁለተኛ ዕቅድ ዘመን ልዩ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሆኑም አውስተዋል፡፡

ክልሎች አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን የማስፋፋት ድርሻ ይዘው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡

ለዚህ እንዲረዳ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተዘረጋው የማሽነሪ ሊዝ ፋይናንሲንግ ሥርዓትን አጠናክሮ ማስቀጠልም የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

የማንነት ጥያቄዎች

ከማንነት ጋር ተያይዞ ሕጋዊና አግባብነት ያላቸው ጥያቄዎች መነሳታቸውን ጠቅሰው፣ በሕዝቡ የተነሱ ጥያቄዎች ተገቢና አፋጣኝ ምላሽ ባለማግኘታቸው ግጭቶች መፈጠራቸውን በማውሳት ለዚህም አንዳንድ አመራሮችም የተጣመመ አስተሳሰብ በማራመድ የችግሩ አካል እንደነበሩም ገልጸዋል፡፡ ለተነሱ ግጭቶች ጥያቄ የሚቀርብባቸው ሥርዓቶች ለችግሩ መንስዔ መሆናቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ሥርዓቱን ባለመረዳትና ሥርዓቱን እያወቁ በሕዝብ ስም ለመጠቀም በሚደራጁ አካላት ምክንያት ግጭቶች ተከስተው፣ በሕዝብ መካከል መቃቃር መፈጠሩንም ጠቁመዋል፡፡ 

Standard (Image)

ምሁራኑ ካቢኔውን ይታደጉት ይሆን?

$
0
0

‹‹በአንድ ትውልድ የተጣመመ የፖለቲካ ግንኙነት ነው እዚህ አገር ውስጥ ያለው፡፡ ይህ የተጣመመ የፖለቲካ ግንኙነት እየቀጠለ ነው ያለው፡፡ ሁላችሁም እንደምታውቁት በአገራችን የፖለቲካ ፓርቲ መሥርተው የሚታገሉት አብዛኞቹ የግራ ፖለቲካ አራማጅ የነበሩ ናቸው፡፡ የዚያን ጊዜ የነበረ ቁርሾ መቀጠል አለበት? እንዴት ነው አዲሱ ትውልድ የዚህ ቁርሾ ተሸካሚ እንዳይሆን ማድረግ የምንችለው? በራሱ የሚያስብና ራሱ ባመነጨው አዲስ አስተሳሰብ ውስጥ የሚኖር ትውልድ እንዴት ነው መፍጠር የምንችለው?››

ከላይ የተጠቀሰው ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በመጋቢት ወር 2008 ዓ.ም. ከዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ከሌሎች ተመራማሪዎች ጋር አገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ በተወያዩበት ወቅት ለውይይቱ መጀመሪያ ያደረጉት ጥያቄ አዘል ዲስኩር ነው፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድንገተኛ ሕልፈትን ተከትሎ የተፈጠረውን የሥልጣን ክፍተት እንዲሞሉ አቶ ኃይለ ማርያም መመረጣቸው ይታወሳል፡፡

በ2007 ዓ.ም. ግንቦት ወር የተካሄደውን ምርጫ መቶ በመቶ ያሸነፈው ኢሕአዴግ ለሙሉ የአምስት ዓመታት የሥልጣን ዘመን አገሪቱን እንዲመሩ አቶ ኃይለ ማርያምን መርጧቸዋል፡፡

በመስከረም 2008 ዓ.ም. ካቢኔያቸውን መሥርተው የሥልጣን ዘመናቸውን የጀመሩት አቶ ኃይለ ማርያም ከጥቂት ወራት በኋላ ከመሬት አስተዳደርና ከማንነት ጉዳዮች ጋር የተያያዙ መሰናክሎች ገጥመዋቸዋል፡፡

የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞችና ዩኒቨርሲቲዎች ግጭት ያዘለ ተቃውሞ ሲቀሰቀስ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደግሞ፣ ከቅማንት የማንነት ጥያቄ አለመመለስ ጋር ተያይዞ ደም ያፈሰሰና የበርካታ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ግጭት ተቀስቅሶ ነበር፡፡

ለሁለቱም ፖለቲካዊ ቀውሶች መፍትሔ ከተበጀ በኋላ ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በመጋቢት ወር ከአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራንን ሰብስበው በአገራዊ የህዳሴ ጉዳይ ውይይት ያደረጉት፡፡

‹‹ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብና ዴሞክራሲያዊ ባህል መገንባት ለዚህች አገር የዕጣ ፈንታ ጉዳይ ነው፡፡ እውነት ለመናገር በዚህ ረገድ እኛ ብዙ ጉድለቶች አሉብን፡፡ ብዙ ጊዜ መንግሥት ላይ ስለሚነጣጠር ነው እንጂ የኅብረተሰቡ ጉድለቶችም ናቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ መንግሥት ጉድለቶቹን የማረም የመሪነት ሚና እንዳለው ሳልክድ ማለት ነው፡፡ በአገራችን ሥር የሰደደ አገራዊ መግባባት የለም፡፡ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ እንዴት መግባባት አይኖረንም? ምሁራን በዚህ ረገድ የሚጫወቱት ሚና ምን መሆን አለበት? ምሁራን መሸሻቸውን አቁመው የራሳቸውን ፓርቲ አቋቁመው እንዴት ነው አስተዋጽኦ የሚያደርጉት የሚል ጥያቄ ይመላለስብኛል፡፡ የዳር ተመልካች መሆን ለዚህች አገር አይበጅም የሚል እምነት ስለያዝኩ ነው በድፍረት የምጠይቃችሁ፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መድረኩን ለውይይት ክፍት አድርገው ነበር፡፡

ምሁራኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍላጎት ዕውን እንዲሆን የእነርሱም መሻት መሆኑን ቢያምኑም፣ ነባራዊው የፖለቲካ ከባቢ በታፈነበት ሁኔታ እንዴት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችሉ ጠይቀዋቸው ነበር፡፡

ከዚህ ለየት ያለ ጥያቄ ያቀረቡት ዶ/ር መሐሪ ረዳኢ በበኩላቸው፣ ትኩረታቸውን በገዢው ፓርቲ በራሱ የተገለጹ ችግሮች ላይ አነጣጥረው ጥያቄዎችን አቅርበው ነበር፡፡

የ2007 ዓ.ም. ምርጫን ተከትሎ የገዢው ፓርቲ ድርጅቶች በተናጠል ባካሄዱት ስብሰባ፣ እንዲሁም በመቐለ ከተማ ኢሕአዴግ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ከፍተኛ ችግር እንዳለበት በይፋ አምኖ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ችግሩ በታችኛው አመራር ላይ ሳይሆን በከፍተኛ አመራሩ ላይ መሆኑ በይፋ ለሕዝብ ተነግሮ እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር መሐሪ፣ ‹‹መስከረም ወር 2008 ዓ.ም. ላይ እርስዎ ካቢኔዎትን ሲያዋቅሩ ያው የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮችን ነው ያየነው፡፡ በሚኒስትርነት ያላካተቷቸውንም አማካሪ ብለው ወደ እርስዎ ነው የወሰዷቸው፡፡ ስለዚህ ለውጥ አልታየም፡፡ አሁን በመጋቢት ወርም ለውጥ አልታየም፤›› ሲሉ ጠይቀዋቸው ነበር፡፡

በማከልም ታሟል የተባለው የላይኛው አመራር እንደሆነ ተገልጾ ለውጥ እየተካሄደ ያለው ግን ታች ባለው አመራር ላይ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ጠይቀዋል፡፡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ መስጠት የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በወቅቱ ተካሂዶ በነበረው ግምገማ የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩን፣ እያቆጠቆጠ ያለ ሙስና ስለመኖሩና ሊወገዱ እንደሚገባ ተገምግሞ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ለካቢኔ ሹመኞችን ያቀረቡት ለማወቅ በሚችሉት ደረጃ ገምግመው ያመኑባቸውን መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ ልጠየቅ የምገባው እገሌ የሚባል የሚታወቅ ሌባ ነው የሾምከው ተብሎ ነው፡፡ ይኼ ባልሆነበት ሁኔታ እኔ ምን ላድርግ?›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ በጥቅሉ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ ስለተባለ ነባር አመራሮች መሾም የለባቸውም ማለት እንዳልሆነ አስረግጠው ተናግረው ነበር፡፡

በ2008 ዓ.ም. ያቀረቡት ካቢኔ ውስጥ 30 በመቶ የሚሆኑት አዳዲስ መሆናቸውን ጠቁመው ነበር፡፡ ኢሕአዴግ በተተኪነት ለሌሎች ፓርቲዎች ሥልጣን እስከሚያስረክብ ድረስ የራሱን ውስጣዊ አሠራር ተከትሎ በመረጃዎች እንደሚመለምል ጠቁመዋል፡፡

‹‹ከጥያቄው ይዘት ትንሽ የገባኝ የፓርቲ አባል ብቻ ለምንድነው የምትሾሙት? ለምንድነው ከሌሎች አካባቢዎች የማትሾሙት? የሚል በግልጽ ያልወጣ ጥያቄ ያዘለ ይመስለኛል፤›› በማለት ለዚሁ ምላሽ የሰጡት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ይህ ከሆነ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ግንኙነት የለንም፡፡ በሒደት ግንኙነት እየመሠረትን ከምሁራንም ከሌሎችም አካባቢዎች ለመሾም እንሞክራለን፡፡ አሁን ግን ጊዜው አይደለም፤›› ብለው ነበር፡፡

ከዚህ የምሁራንና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውይይት ጥቂት ወራት በኋላ በተመሳሳይ ሁለት አካባቢዎች ግጭትና ተቃውሞ ከቀድሞው የበለጠ አይሎ ተቀስቅሷል፡፡

በአማራ ክልል በተመሳሳይ ሰሜን ጎንደር ዞን ከወልቃይት የማንነትና የወሰን ለውጥ ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተቀሰቀሰው የፖለቲካ ተቃውሞ መልኩን ቀይሮ አገራዊ የፖለቲካ ሥርዓቱን በመቃወም ቀጠለ፡፡ በኦሮሚያም ረገብ ብሎ የነበረውን ተቃውሞ ዳግም እንዲቀሰቀስ ምክንያት መሆኑ ይታወሳል፡፡ የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላኑን ምክንያት ያደረገው ተቃውሞ መልኩን ቀይሮ በኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት ላይ ያነጣጠረ ፖለቲካዊ ተቃውሞ ወደ ግጭትና ደም መፋሰስ ተሸጋግሯል፡፡

የበርካታ መቶዎች ሕይወት ሲያልፍ እንደዚሁም ከፍተኛ ውድመት በውጭና በአገር ውስጥ ባለሀብቶች ኢንቨስትመንቶችና ንብረቶቹ ላይ ደርሷል፡፡ ሁኔታው ያሳሰበው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊቀመንበርነት የሚመራው ኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴውን ሰብስቦ ባካሄደው ውይይት፣ የወቅታዊው ችግር መንስዔ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግር መሆኑን ጠንከር በማለት አስቀምጦታል፡፡

የመንግሥት ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል፣ በሥልጣን መባለግና የሕዝብ ጥያቄዎችን በአግባቡና በፍጥነት ያለመመለስ ችግር መኖሩን፣ የወጣቶች ሥራ አጥነት መስፋፋቱን የችግር መንስዔ አድርጓል፡፡

በመፍትሔነት በጥልቀት የመታደስ ፕሮግራም ማስቀመጡን የጠቀሰው ፓርቲው፣ በዚህ ፕሮግራም ውስጥ ከተካተቱት መካከል የመንግሥት ካቢኔ ሹም ሽር አንዱ መሆኑን መጠቆሙ ይታወሳል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባለፈው ጥቅምት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ካቢኔያቸውን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መልሰው አዋቅረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2008 ዓ.ም. ካቋቋሙት 30 አባላትን የያዘ ካቢኔ ውስጥ ዘጠኝ የሚሆኑትን በነበሩበት ቦታ እንዲቆዩ በማድረግ፣ ሌሎች አምስት የቀድሞ ካቢኔ አባላትን እንዲሸጋሸጉ ወይም በሌላ ኃላፊነት እንዲሾሙ አድርገዋል፡፡

ሌሎች 13 አዳዲስ የካቢኔ አባላትንም በካቢኔያቸው አካተው በፓርላማው አፀድቀዋል፡፡ ከእነዚህ አዳዲስ 13 አባላት ውስጥ አሥር የሚሆኑት ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ እንዲሁም ከፖለቲካ ውጪ በሆኑ የመንግሥት ድርጅቶች ውስጥ ሲያገለግሉ የነበሩ ከፍተኛ ምሁራንን በካቢኔ አባልነት ሹመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርየም አዲስ ስለተቀላቀሉት የካቢኔ አባላት በተለይም ምሁራንን ለማካተት ስላስፈለገበት ጉዳይ ሲያብራሩ፣ የአገሪቱ የዕድገት ደረጃ የሚጠይቀው ዝንባሌ፣ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸውን መሾም ማስፈለጉን ጠቁመዋል፡፡

አዲሶቹ የካቢኔ አባላት እነማን ናቸው?

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲሱ ካቢኔያቸው እንዲካተቱ ካደረጓቸው 13 አዳዲስ ሚኒስትሮች ውስጥ አሥሩ በከፍተኛው የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተካተው የማያውቁ፣ ይልቁንም በርካታ ጊዜያቸውን በምርምርና በማስተማር ላይ ያሳለፉ ናቸው፡፡

የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ሲሆኑ በብሔራቸው ኦሮሞ ናቸው፡፡ እንዲሁም በኃይድሮሊክስና በውኃ ሀብት ምህንድስና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እንዳገኙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በሹመቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡ በቀድሞው የአርባ ምንጭ ውኃ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከጀማሪ መምህርነት እስከ ዲን የሠሩ ናቸው፡፡ በኋላም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እስኪመሠረት ድረስ ምሥረታውን በኃላፊነት የመሩ ናቸው፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሥረታ በሚካሄድበት ወቅት ጥብቅ ወዳጅነት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር እንደነበራቸው ይነገራል፡፡ ዶ/ር ስለሺ ለዶክትሬት ዲግሪያቸው ወደ ውጭ አገር በሄዱበት ጊዜ አቶ ኃይለ ማርያም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው መሾማቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ስለሺ ከዚህ በኋላ በዩኒቨርሲቲ መምህርነት አልቀጠሉም፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ከውኃ ጋር የተያያዙ ሙያዊ አገልግሎቶችን ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የውኃና የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ባለሙያ፣ እንዲሁም በኒውዮርክ የተመድ የዘላቂ ልማት ግቦች የአቅም ግንባታና የውኃና ኢነርጂ አማካሪ በመሆን እስከ አሁኑ ሹመታቸው ድረስ ቆይተዋል፡፡

ከዶ/ር ስለሺ ጋር በህዳሴ ግድብ አማካይነት እንደሚተዋወቁ፣ የህዳሴው ግድብ ተደራዳሪ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንጂነር ጌድዮን አስፋው ይገልጻሉ፡፡ የህዳሴው ግድብን በተመለከተ የኢትዮጵያ የባለሙያዎች ቡድንን በማደራጀት በሊቀመንበርነት የመሩ ከፍተኛ የማስተባበር ችሎታ ያላቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ከውኃ ጋር የተያያዙ በርካታ ጠቃሚ ጥናቶችን ያቀረቡና ብቃት ያላቸው ባለሙያ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

በንግድ ሚኒስትርነት የተሾሙት ደግሞ ዶ/ር በቀለ ቡላዶ ናቸው፡፡ ዶ/ር በቀለ በቢዝነስ ሳይንስ የማስትሬት ዲግሪያቸውን ከአየርላንድ ዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም በስትራቴጂክ ማኔጅመንትና ቢዝነስ ፖሊሲ ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

ከሥራ ልምዶቻቸው መካከል የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ደኢሕዴን) ኢንዶውመንት ድርጅት የሆነው የወንዶ ንግድ ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚ ነበሩ፡፡ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከመጋቢት 2008 ዓ.ም. በኋላ የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ሲያገለግሉ ነበር፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ተደርገው የተሾሙት ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነ ናቸው፡፡ በብሔራቸው አማራ ናቸው፡፡ በሕክምና የዶክትሬት ዲግሪ ያገኙ ሲሆን፣ በአካዳሚ ማዕረጋቸው የማሕፀንና ፅንስ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሴኔት አባልና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ሆነው የመሩ፣ እንዲሁም ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የአዲስ አበባ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡

የፕሮፌሰር ይፍሩን የአመራርነት ብቃት በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕፃናት ሕክምና ትምህርት ክፍል በማገልገል ላይ የሚገኙት ፕሮፌሰር አምሓ መካሻ፣ ‹‹ጠንካራ ሠራተኛ›› ሲሉ ይገልጿቸዋል፡፡

በማኔጅመንት ደረጃ ከፕሮፌሰር ይፍሩ ጋር የሠሩበት ጊዜ አጭር ቢሆንም፣ በጥቁር አንበሳ በነበሩበት ጊዜ እንደ አመራር ግልጽ፣ ቀናና ከሰዎች ጋር ተግባብተው መሥራት የሚችሉ ታታሪ ሠራተኛ መሆናቸውን እንደተገነዘቡ ገልጸዋል፡፡

‹‹ከጎናቸው ቀናና ጠንካራ ለለውጥ የሚተጋ ሰው ካገኙ በጤናው ዘርፍ ትልቅ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ፤›› ብለዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ደግሞ ዶ/ር ሒሩት ወልደ ማርያም ናቸው፡፡ በሥነ ልሳንና የቋንቋ ጥናት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በማግኘት በዘርፉ ያስተማሩና የተመራመሩ፣ እንዲሁም እስከ ሹመታቸው ጊዜ ድረስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ሲያገለግሉ ነበር፡፡

የሥነ ልሳንና ቋንቋ ጥናት መምህርና ተመራማሪ በመሆን ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉት ፕሮፌሰር ባዬ ይማም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሆነው ስለተሾሙት ዶ/ር ሒሩት ለሪፖርተር ሲናገሩ፣ ‹‹ላመነችበት ወደኋላ እንደማትል አውቃለሁ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ዶ/ር ሒሩትን ተማሪዬ ሆና አውቃታለሁ፡፡ ባልደረባዬም ሆና፣ እንዲሁም አለቃዬም ሆና አውቃታለሁ፤›› የሚሉት ፕሮፌሰር ባዬ፣ ዶ/ር ሒሩት በተመደቡበት ቦታ ለውጥ ያመጣሉ የሚል እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡

የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ደግሞ ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ ናቸው፡፡ በእንስሳት ዕርባታ የማስትሬት ዲግሪያቸውን፣ እንዲሁም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በወተት ልማት ቴክኖሎጂ ከኖርዌይ አግኝተዋል፡፡

በምግብ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ምርምርና ማስተማር የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ በቀድሞው የደቡብ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአካዴሚ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩ፡፡ ላለፉት አሥር ዓመታት የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ላለፉት ጥቂት ወራት ደግሞ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው እያገለገሉ ነበር፡፡

የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር እያሱ አብረሃ የማስትሬት ዲግሪያቸውን በአግሮ ኢኮኖሚ በማዕረግ ያገኙ ሲሆን፣ በዕፅዋት ሳይንስ ደግሞ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከቼክ ሪፐብሊክ አግኝተዋል፡፡

በትግራይ ክልል ከግብርና ጋር በተገናኙ የተለያዩ ቢሮዎችና የምርምር ተቋማት ያገለገሉ ሲሆኑ፣ ላለፉት አምስት ዓመታትም የትግራይ የእርሻ ምርምር ዋና ዳይሬክተር ነበሩ፡፡

የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ደግሞ ዶ/ር ገመዶ ዳሌ ናቸው፡፡ በባዮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በዕፅዋት ሳይንስ የማስተርስ ዲግሪና በግብርና ሳይንስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙ ናቸው፡፡

ለረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ኢንስቲትዩት ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች የሠሩና የተመራመሩ፣ ላለፉት አምስት ዓመታትም የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡

ስለ ዶ/ር ገመዶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዕፅዋት ሳይንስ ፕሮፌሰርና የዕፅዋት ቤተመዘክር ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው፣ ‹‹የሰው ሐሳብ የሚቀበል፣ በመወያየትና ችግሮችን በመፍታት የሚያምን ብሩህ አመለካከት ያለው ነው፤›› በማለት ይገልጿቸዋል፡፡

‹‹ካለፈው ልምድ ተነስቼ አንድ ሊያዳምጥ የሚችል ሰው መገኘቱን በበጎ አየዋለው፤›› የሚሉት ፕሮፌሰር ሰብስቤ፣ ‹‹እኔ በዶ/ር ገመዶ ላይ እምነት አለኝ፡፡ አንዳንዴ የምታናግረው መሪ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ አሁን የሚያዳምጥ፣ ለመነጋገር የማይከብድ ሰው በመመደቡ ሐሳቤን በግልጽ ለመስጠት ያስችለኛል፤›› ብለዋል፡፡

የመንግሥት ልማት ድርጅት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ግርማ አመንቴ ትምህርታቸውን ከደን ሀብት ልማት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ የሥራ ልምዳቸውም ከዚሁ ጋር የተገናኘ ነበር፡፡ የኦሮሚያ ክልል የደን ልማት ኃላፊ ነበሩ፡፡ የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነውም ያገለገሉ ናቸው፡፡

ከ2007 ዓ.ም. ሹመታቸውን እስካገኙበት ድረስ የምሥራቅ አፍሪካ ዩኒክ የደንና የመሬት አጠቃቀም ዳይሬክተር ነበሩ፡፡ የመንግሥትን የልማት ድርጅት በመምራት ቀጥተኛ ልምድ እንዳላቸው ይነገራል፡፡

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ሲሆኑ፣ እስከ ሦስተኛ ዲግሪያቸው ድረስ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ የተማሩ እንዲሁም የተመራመሩ ናቸው፡፡ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው አገልግለዋል፡፡

ለመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ዲን፣ እንዲሁም መምህር ሆነው ያገለገሉና በጋዜጠኝነት የሥራ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አቶ ርስቱ ይርዳው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ያገለገሉ ናቸው፡፡

ምሁራኑ የካቢኔ አባላት ፋይዳና ተግዳሮት

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በአጭር ወራት ውስጥ ቀድሞ የነበራቸውን አቋም ቀይረው በካቢኔያቸው የፓርቲ አባል ያልሆኑ ምሁራንን አካተዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ምንጮች እንደሚገልጹት፣ ቢያንስ አምስት የሚሆኑት የፓርቲ አባል እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡

አገሪቱ ያለችበት የዕድገት ደረጃና የሚያጋጥሙ ችግሮች ውስብስብነት ሙያዊ ብቃትንና ክህሎትን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የምሁራኑ መካተት አስፈላጊነትን ይገልጻሉ፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተንታኞች እንደሚሉት ደግሞ፣ ምሁራኑ በሙያቸው ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ባልተናነሰ በአሁኑ ወቅት የሚታየውን የገዥው ፓርቲና የመንግሥት መደበላለቅ ይለዩታል የሚል እምነት አላቸው፡፡

እስካሁን በነበረው ሥርዓት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከሞላ ጎደል በሙሉ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ እንደነበሩ፣ ይኸውም በፓርቲውና በመንግሥት መካከል መደበላለቅን ሲፈጥር እንደቆየ ገልጸዋል፡፡ ይህም የፖለቲከኞች ጉልበት ቴክኖክራት (ባለሙያ) የሆኑ የካቢኔ አባላትን ሲያደበዝዝ ቆይቷል የሚል እምነት አላቸው፡፡

በአዲሱ ካቢኔ ከተካተቱት አሥር ከሚሆኑት ምሁራን መካከል የፓርቲ አባል ያልሆኑ መኖራቸው፣ እንዲሁም የፓርቲ አባል የሆኑትም የታችኛው እርከን ላይ የሚገኙ በመሆናቸው በፓርቲ ፖለቲካና በመንግሥት ሥራ አፈጻጸም መካከል የተደበላለቀውን ድንበር ሊለዩ ይችላሉ ብለዋል፡፡

ፕ/ር ባዬ በበኩላቸው ሥጋት ቢኖራቸውም፣ ከፖለቲከኞች የሚገጥማቸውን ተግዳሮት እየተቋቋሙ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ የሚል እምነት አላቸው፡፡

በትምህርት ተቋም ውስጥ አንፃራዊ ነፃነት መኖሩን የሚናገሩት ፕ/ር ባዬ፣ ምሁራኑ ይህንን ነፃነት እንደለመዱ ይናገራሉ፡፡ አሁን የገቡበት ቦታ ይህ ነፃነት ይኖራል ወይ የሚል ጥያቄ ትልቁ ሥጋታቸው ነው፡፡

መንግሥት ምሁራንን የፈለገበትን ምክንያት ስረዳ ‹‹ሙያና ቅን ልቡና የተፈለገ ይመስለኛል፤›› የሚሉት ፕ/ር ባዬ፣ የሚገጥማቸውን ፖለቲካዊ ተግዳሮት አስፈላጊ እስከሆነው ድረስ መጋፈጥ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

መንግሥት ፖሊሲዎቹ እንዲፈጸሙ እንደሚፈልግ ሁሉ ባለሙያዎቹም ይህንን ለመወጣት ፍላጐት ያላቸው በመሆኑ፣ መሰል ችግር የሚፈጥረውን ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ታግለው ውጤታማ እንደሚሆኑ ገምተዋል፡፡   

 

Standard (Image)
Viewing all 475 articles
Browse latest View live