ዶ/ር ዓለም መብራህቱ፣ የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት
አዲሱን የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከአራት ዓመት በፊት ጀምሮ በምክትል ፕሬዚዳንትነት በማገልገል ላይ የሚገኙት ዶ/ር ዓለም መብራህቱ፣ አንደኛና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በፊዚክስ ዲፓርትመንት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ ለአጭር ጊዜ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ካገለገሉ በኋላ በጀርመን የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አጠናቀዋል፡፡ ከዚያም ተመልሰው በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ፋካልቲ ዲን ሆነው ሠርተዋል፡፡ ቀደም ሲል በአንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ ከነበረው ሁከት ጋር ተያይዞ ገዢው ፓርቲና መንግሥት እየወሰዱዋቸው ባሉ ዕርምጃዎች፣ በዩኒቨርሲቲው ስላለው ወቅታዊ የመማር ማስተማር ሁኔታን በተመለከተ የማነ ናግሽ ዶ/ር ዓለም መብራህቱን አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው ሁከት በአሁኑ ጊዜ እየተረጋጋ ነው፡፡ ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው የመንገሥት ተቋማት መካከል ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸውና ከዩኒቨርሲቲዎች ማኅበረሰቦች ጋር የተካሄዱ ውይይቶች ምን ያህል ውጤታማ ናቸው ይላሉ?
ዶ/ር ዓለም፡- የተካሄደው ሥልጠና በእርግጥ ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር እንዲዛመድ ተደርጓል እንጂ ሦስተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ በአምስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት የነበረው ጉዞ ምን እንደሚመስል በአጭር ተጨምቆ የቀረበበት ሁኔታ ነበር፡፡ በትክክል የተፈጸሙና ያልተፈጸሙ፣ እንዲሁም የተገኘውን ድልና ድክመት የዳሰሰ ነበር፡፡ በሁለኛ ደረጃ የጋራ መግባባት መፍጠር የሚደረስበት ነበር፡፡ እንዲሁም ደግሞ በትምህርት ጥራት ላይ የተገኘውን ውጤትና የነበረውን ድክመት የሚያሳይ ነበር፡፡ የተቀሩት ደግሞ እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት የትምህርት ዘመን ምን እንደሚመስልና ለሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ምን ዕቅድ እንደተያዘ የሚመለከቱ ነበሩ፡፡ እናም ሥልጠናው ብዙ ሰው እንደሚለው በወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተቃኘ አይደለም፡፡ በእርግጥ በመሀል በመሀል መነሳቱ አልቀረም፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ ሁከቶች ምክንያታቸው ምንድን እንደሆነ፣ ከኋላ የሚገፉት እነማን እንደሆኑ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በተለይ ደግሞ ዜጎችን የሚቀርፀው መምህር ለይቶ ማወቅ ስላለበት ጉዳዮቹ ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ አንድ ተማሪ ወላጆቹ በሚከፍሉት ግብር የተሠራን ሕንፃ የሚያፈርስበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ጥያቄዎች አሉ፣ ከዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ጀምሮ እስከ መንግሥት አስተዳደር ብልሹ አሠራሮችና የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉ፡፡ ጥያቄ መነሳት አለበት፡፡ እንደ አቅጣጫ የተያዘውም የሚጠይቅ ማኅበረሰብ መፍጠር አለብን የሚል ነው፡፡ የራስን ንብረትና በመከራ የተሠራች ነገርን ግን ቀና ብሎ ማየት የለበትም፡፡ ራሱን በራስ እንደ ማጥፋት ነው፡፡ ጥያቄው እስካልተመለሰለት ድረስ በአግባቡ መጠየቅና መሞገት ግን አለበት፡፡ ይህንን ነው የተነጋገርነው፡፡
በዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የመነጋገር ችግር የለብንም፡፡ ሁሌም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት እናደርጋለን፡፡ እንደ ባህል ይዘነዋል፡፡ በአጠቃላይ ግን ዘንድሮ የተደረጉ ውይይቶች በእርግጥ ትንሽ ለየት ያሉ ናቸው፡፡ የተለያዩ ስትራቴጂካዊ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ እኛም ለሚመለከታቸው አካላት አስተላልፈናል፡፡ ምላሽ እያገኙ ናቸው፡፡ መንግሥትም ውይይቶች እንዲካሄዱ ያደረገው እሳት ለማጥፋት ወይም ተራ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት አልነበረም፡፡ ከተማረው ኃይል ግብዓት ስለሚፈልግ ነው፡፡ በተለይ መምህር ተማሪውን መምራት ካለበት ጠንቅቆ ማወቅ ይኖርበታል፡፡ ተማሪዎች ገና ልጆች ናቸው፡፡ በቀላሉ ሊሳሳቱ ይችላሉ፡፡ ዋናው መምህር ነው ትልቅ ሚና የሚጫወተው፡፡ የሥልጠናዎቹ ዋና ስበትም ይኼ ነበር ለማለት ነው፡፡ በውጤቱም በአገሪቱ የተፈጠረው ሰላም እንዳለ ሆኖ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሁከት ሳይሆን የሰላምና የዕውቀት ማዕከሎች ሆነዋል፡፡ ያልተለመዱ ጥያቄዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን በብዙ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር ተችሏል የሚል እምነት አለኝ፡፡
በተለይ ከውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ጋር ተያይዞ መግባባት ተፈጥሯል፡፡ ለምሳሌ ግብፅ እዚህ የምትገባበት ምን ምክያት አላት? ኢትዮጵያን ለማተራመስ ካስቀመጠቻቸው ስትራቴጂዎች ዘጠነኛውን እየተጠቀመች ነው የሚሉ አሉ፡፡ ምንም ያህል ቅሬታ ቢኖር ግብፅ የምትፈታው አይደለም፡፡ ሁኔታውን ለመጠቀም ስለፈለገች ነው፡፡ እዚህ ላይ በዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰቡ ውስጥም፣ በአገር ደረጃም፣ በዜጎች መካከልም የጋራ አመለካከት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ሰው እንደአቅሙ ነው የሚያጠፋው፣ ትንሽ ጥፋት የለም፡፡ የመጀመሪያሙ መድኃኒት ራሱን መፈተሽ አለበት፡፡ ለምሳሌ ሁለት ከተለያዩ ብሔረሰቦች የመጡ ተማሪዎች ሲጋጩ የብሔር ጉዳይ አድርጎ ማሰብ አያስፈልግም፡፡ በሁለት ግለሰቦች መካከል ነው ግጭት የተፈጠረው፡፡ ከጀርባ በዚህ የሚጠቀሙ አይጠፉም፡፡ የራሳቸውም ሥሌት አላቸው፡፡ የእነሱ መጠቀሚያ መሆን ግን አያስፈልግም፡፡ በምንም ተዓምር አንድ ሕዝብ እንደ ሕዝብ የሌላ ሕዝብ ጠላት የሚሆንበት ምክንያት የለም፡፡ ጠላት ሆኖም አያውቅም፡፡ ሃይማኖተኛ ሕዝብ ነው፡፡ በሕዝብ ደረጃ ተደርጎ የሚያውቅ ጥፋት እስካሁን የለም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ስለትግራይ የሚስሉት ይታወቃል፡፡ ሕዝቡ በተለየ ተጠቃሚ ነው፣ በተለየ ለምቷል ይባላል፡፡ እያንዳንዱ ተማሪ ኮምፒዩተር እንዳለው ጭምር ይወራል፡፡ ተማሪዎች እዚህ መጥተው ሕዝቡን ሲመለከቱ ሲያዝኑና ሲፀፀቱ ብዙ ጊዜ የምናስተውለው ነው፡፡ ስለዚህ እኛ የምንፈልገው ተማሪው መሬት ላይ ያለን እውነት እንዲያውቅ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ገዢው ፓርቲ በጥልቀት ለመታደስ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ለጊዜው መረጋጋት ተፈጥሯል፡፡ በዚህ አካሄድ የተከሰተውን ችግር በዘላቂነት መፍታት ይቻላል ብለው ያስባሉ?
ዶ/ር ዓለም፡- እንግዲህ ትልቅ ኃላፊነት ላይ ያለ አካል የተለያዩ ፈተናዎች ሊገጥሙት የግድ ነው፡፡ ለምን ገጠመው አይባልም፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግም ዕድሜው ረዘም ያለ ነው፡፡ በዚህ ጉዞ ብዙ ችግር ገጥሞት ማለፍ ችሏል፡፡ በቃ ዛሬ አበቃለት ሲባል ብዙ ጊዜ ወድቆ ይነሳል፡፡ ሰው በተፈጥሮው ስህተት ላይሠራ አይችልም፡፡ ደረጃው ነው የሚወሰነው፡፡ መድኃኒቱም ግምገማ ማድረግ ነው፡፡ ድርጅቱ ብዙ ድሎችን አስመዝግቧል፡፡ ነገር ግን በተገኘው የልማት ዕድገት ላይ ብቻ ተዘናግቶ መቀመጥ አያስፈልግም፡፡ ምናልባትም በደንብ ቢሠራ ከተገኘው ዕድገት በላይ መሄድ ይቻል ነበር፡፡ እናም ውሱንነቶቹ አሁን የሆነ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ እሱን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- የተከሰተውን ቀውስ ለመፍታት ገዢው ፓርቲ በተለይ በመንግሥት ደረጃ አዲስ ካቢኔ አቋቁሟል፡፡ ብዙዎች የካቢኔው አባላት ከዩኒቨርሲቲ የመጡ ምሁራን ናቸው፡፡ እንዴት ያዩታል?
ዶ/ር ዓለም፡- በመጀመሪያ አካሄዱ በጣም ጥሩ ነው፡፡ በተደረገው ግምገማ መሠረት ለውጥ ለማምጣት መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን አሳይቷል፡፡ በውጤት ደረጃ ግን እንግዳ ሰዎች በካቢኔው እንዲካተቱ ተደርገዋልና ትክክለኛነቱ መመዘን የሚቻለው ሰዎቹ የሚያመጡት ለውጥ ታይቶ ይሆናል፡፡ የእኔ እምነት አዲሱ የምሁራን ኃይል የሕዝብና የመንግሥትን ፍላጎት ተገንዝቦ ሥራውን ያከናውናል የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹ በሚኒስትር ደረጃ የተመደቡ ምሁራን ከዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ ከ40 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች ነው ያሉት፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ የተማረ ኃይል የያዙ ናቸው፡፡ ሰዎቹ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ቅርበት ስለነበራቸው በሰፊው ማንቀሳቀስ ይችላሉ፡፡ እስካሁን ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያለው ማኅበረሰብ ተቺ ብቻ ነበር፡፡ ከአሁን በኋላ እሱን የሚመስል ሰው ከፍተኛ ቦታዎች ላይ ስለተቀመጠ፣ ተቺ ብቻ ሳይሆን በየዘርፉ ተናቦ መሥራት ይችላል፡፡ ምክንያቱም የነበረው ቅሬታ ሥልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች አቅም የላቸውም የሚል ነው፡፡ አሁን አቅም አላቸው የሚባሉ ሰዎች ቦታው ላይ እንዲቀመጡ ተደርገዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች እዚህ ላይ በትብብር ለመሥራት ይችላሉ፡፡ የምሁሩ የመምራት አቅም በውጤቱ ይመዘናል፡፡
ሪፖርተር፡- ሕወሓትን ጨምሮ አንዳንድ አባል ድርጅቶች የተጠበቀውን ያህል የአመራር ለውጥ አላደረጉም ተብለው እየተተቹ ነው፡፡
ዶ/ር ዓለም፡- የአመራር ለውጥ ማድረግ አንድ መፍትሔ ነው፡፡ ግን የችግሩን ጥልቀት አምኖ መቀበል ነው፡፡ ግምገማ እየተካሄደ ነው ገና አልተጠናቀቀም፡፡ በግምገማዎቹ መጀመሪያ የምንጠብቀው ችግሩ ላይ መተማመን መቻል ነው፡፡ እሱ ሆኗል፡፡ ቀጥሎ የሚሆነው ዕርምጃ መወሰድ ነው፡፡ እሱ ገና አልተገባም፡፡ ምን እንደሚሆን በቅርቡ የምናየው ይሆናል፡፡ በእርግጥ አንድን ሰው በሌላ መተካት ብቻውን ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በአጠቃላይ የኅብረተሰቡን ፍላጎትና ችግር የሚረዳ አመራር መፍጠር ትልቁ ነገር ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገር ኅብረተሰባዊ ለውጥ ማምጣት ነው፡፡ እስካሁን ብቁ ወጣቶችና ምሁራን ወደ አመራር ለመምጣት የተደረገው ጥረት እምብዛም የሚደነቅ አልነበረም፡፡ ወጣቱ ራሱ ግን ተቀምጦ መጠበቅ የለበትም፡፡ የሚገባውን ለማግኘት መንቀሳቀስ አለበት፡፡ መጠየቅ አለበት፡፡ በእርግጥ ነባሩ አመራርም ዕድሉን መንፈግ የለበትም፡፡ ለማንኛውም ግምገማዎቹ ሲጠናቀቁ የምናየው ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- በትግራይ እንደ ክልል ከድርጅቱ (ሕወሓት) ውጪ የተለየ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ወጣቶችን መፈረጅና እንደ ጠላት የማየት አዝማሚያ ይታያል፡፡ ድርጅቱ በዚሁ የመታደስ እንቅስቃሴው የአቋም ለውጥ ያደርጋል ብለው ያምናሉ?
ዶ/ር ዓለም፡- ልዩነቱ እዚህ ላይ ነው፡፡ ደርግን እንኳን ማሸነፍ የሚቻል ከሆነ አሁን ምን ያቅታል? ዛሬ የተለየ አስተሳሰብ በመያዙ የሚታሰር ሰው የለም፡፡ አንድ ባለሥልጣን ላይጥመው ይችላል፡፡ ሊጥመው የግድ አይደለም፡፡ መጀመሪያ አንድ ሰው በትክክኛ መንገድ መሆን አለበት፡፡ በነገርህ ላይ ከኢሳት ጋር ሆነው የትግራይ ሕዝብ ከጎንደር ይውጣ የሚሉ ትግርኛ ተናጋሪዎች ነበሩ፡፡ የተለየ ሐሳብ የያዘ ሰው ግን በሐሳብ ነው የሚመታው፡፡ በንፅፅር ያየን እንደሆነ የፈለግነውን ተናግረን ተኝተን ነው የምናድረው፡፡ ለመቃወም አስበሃል፣ ሬዲዮ አዳምጠሃል ተብሎ ሰው የሚገደልበት አገር ነበር፡፡ እና አሁን ያለው ወጣት አጉርሱኝ ባይ ነው፡፡ መጎራረስ ቢኖር ጥሩ ነው፡፡ ሕወሓት በጣም የዋህ ድርጅት ሆኖ ወጣቶቹን አይዞህ ና እዚህ ሁን እንዲሁ ሁን ቢላቸው ጥሩ ነበር፡፡ ግን የወጣቱ ድርሻ ምንድነው? ለምንድነው በር እስኪከፈትልህ የምትጠብቀው? ራስህ ከፍተህ ለምን አትገባም? በሩ ጠባብ ከሆነም ትተህ መሸሽ የለብህም፣ እስከ መጨረሻ መታገል ነው፡፡ በእኔ እምነት ችግሮች አሉ፡፡ ወጣቱ ግን እየሸሸ ነው፡፡ ከታንክ ጋር የሚጋፈጥ ሰው የነበረበት አገር፣ አሁን በተለያዩ አቅጣጫዎች እየጠፋ ነው፡፡ አንዳንዱ በሱዳን አንዳንዱ በሶማሊያ እየሸሸ ነው ያለው፡፡ ይህ መሠረታዊ ለውጥ አያመጣም፡፡ ለውጥ የሚመጣው ችግሩን በመጋፈጥ ነው፡፡ ሰው እየተሰደደ፣ ፍትሕ እያጣ ዙረህ የምትሄድ ከሆነ ነገሩ እኔ ላይ እስካልደረሰ ነው፡፡ ስለዚህ መፍትሔው ያለው በራሳችን ውስጥ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በመማር ማስተማር ዙሪያ የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ ምን እየሠራችሁ ነው?
ዶ/ር ዓለም፡- የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በአገር ደረጃ የተዘጋጁ ፓኬጆች አሉ፡፡ እነሱን በመከተል የተሻለ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ እንሞክራለን፡፡ ሆኖም በዚሁ ፓኬጅ ብቻ የትምህርት ጥራትን ማሻሻል አይቻልም፡፡ ጥራት በባህሪው ብዙ ጊዜ የሚወስድ ነው፡፡ በአንድ ጊዜና በአንድ ቦታ የሚረጋገጥ አይደለም፡፡ ስለሆነም ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይ በክልል ደረጃ፣ የትምህርት ቢሮ ዋና አገናኝ ሆኖ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲና ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ በጋራ የምንሠራው ሥራ አለ፡፡ በውጤቱም ተማሪዎቻችን የተሻለ አካዴሚያዊ አቅም ይዘው እንዲወጡ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በብዙ የትምህርት ማዕከላት እየተሠራበት ያለው የትምህርት ሠራዊት በመባል የሚታወቀው ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጠንክሮ የገባበት ነው፡፡ በዚህም በ2007 ዓ.ም. በነበረው የዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ እኛ ጋር ከጀመሩ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በአንደኛ ደረጃ የተቀመጥንበት ሁኔታ አለ፡፡ የተማሪዎች ቁጥር ብዛት አለው፡፡ ጥራቱንም የጠበቀ እንዲሆን ነው የተደረገው፡፡ እንደ አገር የሚጎድሉን ነገሮች እንዳለ ግልጽ ሆኖ በትምህርት ጥራት ላይ አንደራደርም፡፡ ተማሪዎችና መምህራን ተደጋግፈው የሚሄዱበትን ሥርዓት ነው የዘረጋነው፡፡ ችግሮች ሲታዩም አፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ሌላው የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ አስፈላጊ የሚባሉ ግብዓቶች እንዲሟሉ አድርገናል፡፡ ለምሳሌ ተማሪዎቻችን በሙሉ በአንድ ጊዜ ቤተ መጻሕፍት መጠቀም ቢፈልጉ፣ ይህንን ፍላጎት ግምት ውስጥ ያስገቡ አራት ትልልቅ ቤተ መጻሕፍት ሠርተናል፡፡ ሁለቱ እያንዳንዳቸው 2,500 ተማሪዎች በአንድ ጊዜ የመያዝ አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ ሁለቱ ደግሞ በአንድ ጊዜ ከ3,500 በላይ ተማሪዎች ማስተናገድ የሚችሉ ናቸው፡፡ ዲጂታል ላይብረሪ ደግሞ ከ500 በላይ ኮምፒዩተሮች ያሉትና በአገር ደረጃ በግንባር ቀደምነት የሚያስቀምጠንና ዘመናዊ የሆነ የቪዲዮ ፋሲሊቲ ያለው አለን፡፡ አንድ የታወቀ ፕሮፌሰር ጀርመን፣ አሜሪካ ወይም ደግሞ እንግሊዝ አገር ውስጥ ሆኖ እዚህ ትምህርት መስጠት ይችላል ማለት ነው፡፡ ይኼንን ቴክኖሎጂ አስገብተናል፡፡ በእርግጥ የእኛ መምህራን ብዙዎቹ ወጣቶች ናቸው፡፡ ጥልቅ ተሞክሮ ላይኖራቸው ይችላል፡፡ በእርግጥ በአካዴሚያዊ ብቃታቸው ከፍ ያሉትን ነው የምንመርጠው፡፡ ተሞክሮ የሌላቸው ግን በራሳቸውና በዩኒቨርሲቲው ጥረት እንዲለምዱ እየተደረገ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የአካባቢውን ማኅበረሰብ በመደገፍና ምርምር በማካሄድ ላይስ ምን ያህል ተሳክቶላችኋል?
ዶ/ር ዓለም፡- ከ2004 ዓ.ም. ጀምረን ምርምሮች እያካሄድን ቆይተናል፡፡ በ2004 ዓ.ም. ዘጠኝ፣ በ2005 ደግሞ 23 እያልን መጥተን በ2008 ዓ.ም. 60 ምርምሮች አድርገናል፡፡ በእርግጥ በምርምሮች የጥልቀትና የስፋት ውሱንነት እንደሚኖረን እናምናለን፡፡ ምርምሮቹ በሁሉም ጉዳይ ላይ የሚካሄዱ ናቸው፡፡ ከተፈጥሮ ሳይንስ እስከ ማኅበረሰባዊ ሳይንስ በተለይም ደግሞ ከንብ አርቢነትና ከበለስ ጋር በተያያዘ ብዙ ጥናቶች አድርገናል፡፡ በርካታ የምርምር ርዕሶች ቀርበው በውድድር ያሸነፉት ላይ ነው ምርምር እንዲካሄድ የምናደርገው፡፡ እስካሁን ያልነካነው ዘርፍ የለም ማለት ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ምርምር ያካሂዳሉ፡፡ ሆኖም የምርምሮቹ ውጤቶች ተግባራዊ የሚደረጉበት ሁኔታና ችግር ፈቺ የሚሆኑበት ዕድል የለም ተብሎ ይተቻል፡፡
ዶ/ር ዓለም፡- ከአቅምና ከተቀባይ ወገን በኩል ደግሞ ከአመለካከት ችግር ጋር ተያይዞ ነው፡፡ በኅብረተሰባችን ውስጥ ችግሮች በጥናትና በምርምር ይፈታሉ የሚል ብዙም የተለመደ አመለካከት የለም፡፡ ለምሳሌ የምርምር ግምገማ ቀን አካሂደን ነበር፡፡ የምርምሮቹ ግኝቶች ለተጠቃሚው አካል እንዲደርሱ የሚደረግበት አሠራር ነው፡፡ ሆኖም የምርምሮቹ ተጠቃሚዎች እንኳን ሊጠቀሙባቸውም ብቻ ሳይሆን ተጠርተው የማይገኙበት ሁኔታም አለ፡፡ አንዱ ችግር ይኼ ነው፡፡ በአጥኚዎቹ በኩል ደግሞ የቀረበውን ሐሳብ ወደ መሬት እንዲወርድ የማድረግ ውሱንነት አለ፡፡ እሱም ሆኖ በርከት ካሉ አርሶ አደሮች ጋር በመሆን ከአርቢነትና ከአምራችነት፣ እንዲሁም ከጤና አጠባበቅ ጋር በተያያዘ ተግባራዊ የሆኑ ምርምሮች አሉን፡፡ የሚፈለገውን ያህል አልሄድንም እንጂ ምርምሮቹ ለሚመለከታቸው አካላት ደርሰው ተፈጻሚ የሚሆኑባቸው ጥሩ ጅምሮች አሉ፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ ለምሳሌ ከቱሪዝም መስህብነት ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ ጉባዔ አካሂዳችሁ ነበር፡፡ አንዳንድ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም በመድረኩ ላይ ተገኝተው የቀረቡ የምርምር ሐሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ቃል ገብተው ነበር፡፡ በተለይ በትግራይ ክልል ሰፊ የእርሻ መሬት በሌለበት ግብርናን እንደ መር ፖሊሲ ከመጠቀም ይልቅ ቱሪዝምና ሌሎች ዘርፎች ላይ እንዲያተኩር ታስባላችሁ ወይ?
ዶ/ር ዓለም፡- ትክክል ነው፡፡ ዓላማው እሱ ነው፡፡ በእርግጥ በአገር ደረጃም ሆነ በክልል ደረጃ እርሻ ሳያድግ ለውጥ ይመጣል የሚል እምነት የለንም፡፡ መሠረተ ልማቱ የለንም፡፡ እያንዳንዱ ገበሬ መጀመሪያ በልቶ ማደር አለበት፡፡ ይኼ ሲባል ግን ግብርና ላይ ብቻ ተተክሎ፣ ሌሎች አማራጮች መታየት የለባቸውም ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ በትግራይ ክልል ውስጥ ምሥራቅ ትግራይን ይዘህ እስከ መሀል ትግራይ፣ ገርዓልታ፣ ጉንዳጉንዶ፣ ደብረዳሞ ብዙ ቅርሶችና ፀጋዎች ነው ያሉት፡፡ የአክሱምን ትተን፡፡ አብዛኛው ሕዝባችን የሚተዳደረው በእርሻ በመሆኑ ባለበት እንዲለወጥና እንዲዘምን ማድረግ ያለብንም ቢሆን፣ ቱሪዝምና ሌሎች አማራጮች በዘላቂነት መዘንጋት የለባቸውም፡፡ አቅም ካልወሰነን በስተቀር በደንብ ከተሠራበት አውሮፓውያን ወደ ሌላ አገር አይሄዱም ነበር፡፡ ምክንያቱም ብዙ አስደናቂ ቅርሶች ነው ያሉን፡፡ አየራችን ምቹ ነው፡፡ ኅብረተሰባችን እንግዳ ተቀባይ ነው፡፡ ለአውሮፓውያን ደግሞ በጣም ቅርብ ነን፡፡ ሆኖም ፀጋዎቻችንን አሟጠን አልተጠቀምንበትም፡፡ ግብርና ራሱ እንኳን በበሬ ከማረስ አላወጣነውም፡፡ በብዙ መልኩ እስራኤልን ብትወስድ እንዴት በግብርና ልቀው እንደሄዱ ተመልከት፡፡ እዚህ እኛ ጋ ያለው መሬት በእጅጉ የተሻለ ነው፡፡ ነገር ግን አላዘመነውም፡፡ እሱንም ቢሆን አሟጠን እየተጠቀምንበት አይደለም፡፡
ሌሎች አማራጮች ግን ዞሮ ዞሮ የተማረ የሰው ኃይል ሲፈጠር ነው ወደ ኢንዱስትራላይዜሽን መሸጋገር የሚቻለው፡፡ ቱሪዝምም እንዳለ ነው፡፡ ቋንቋ የሚያውቅ፣ የሚመራ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው የትምህርት ጥራት ላይ ማተኮር አለብን የምንለው፡፡ ለሁሉም አማራጮች ማጠንጠኛው እሱ ስለሆነ፡፡ ለምሳሌ በዩኒቨርሲቲያችን ለዚህም ነው የአርኪዮሎጂ ዲፓርትመንት እንዲከፈት ያደረግነው፡፡ በእጃችን ውስጥ ያለውን ሀብት ገና አልተጠቀምንበትም፡፡ ከሌሎች ጋር አብረን መሥራት አለብን፡፡ ቅድም ያነሳኸው ዓለም አቀፍ የቅርስ ጉባዔ ለሦስተኛ ጊዜ አዘጋጅተናል፡፡ ብዙ ባለሥልጣናትና የሚዲያ አካላት ተገኝተዋል፡፡ የመጀመሪያው ደረጃ ምርምር ማድረግና ማስተዋወቅ ነው ብለን ስለምናምን ነው፡፡ በጣም የሚገርመው እስከ ዛሬ ኢትዮጵያ የሦስት ሺሕ ዓመት ሥልጣኔ እንዳላት ነበር የሚነገረው፡፡ አሁን እዚሁ አካባቢ በተገኘው ቅርስ ደግሞ ከአራት ሺሕ ዓመታት በፊት እርሻ እንደነበር የሚያመላክቱ ግኝቶች ተገኝተዋል፡፡ አፈ ታሪክ አይደለም፡፡ በፕሮፌሰሮች በካርበን ዴት ተረጋግጠው የተገኙ ናቸው፡፡ ፀሐይ የሞቀ ታሪክ አለን፡፡ ግን በቂ አይደለም፡፡ በሳይንሳዊ ጥናቶች መረጋገጥ አለባቸው፡፡ እስከ ዛሬ ስለአክሱምና የየሓ ሥልጣኔዎች ነበር የምናወራው፡፡ አሁን በጉለመኸዳ አካባቢ የተገኙ ከንግሥት ማክዳ ጋር የሚያያዙ ቤተ መንግሥቶችና ቅርሶች አሉ፡፡ እናም የቱሪዝም አቅማችንን ከፍ ለማድረግ በተለይ ሦስቱ ዩኒቨርሲቲዎች (አክሱም፣ መቐለና ዓዲግራት) በጋራ እየሠሩ ነው፡፡ ትግራይ እንደ ክልል ‹ኦፕን ኤር ሙዚየም› በመባል ነው የሚታወቀው፡፡ ዓለም እንዲያውቀው ግን ማድረግ ይገባል፡፡ ይህ አንድ ምሳሌ ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃም፣ በክልል ደረጃም የምንሠራቸው በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡
