የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር፣ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)
ለማኅበራዊ መስተጋብር ዋነኛ መሣሪያ ትምህርት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ አሪስ ጣጣሊስ የተባለው ታዋቂ ፈላስፋ ትምህርት የሁሉም ነገር መሠረት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዕድገት ትልቁ መሰላል ትምህርት እንደሆነ ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ከተጀመረ ብዙ ዓመታት ቢያስቆጥርም፣ የዘመናዊነት መልክ የያዘው ግን በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው የትምህርት ሥርዓት ዋነኛ ዓላማ ሃይማኖትን ለማስፋፋት የሚሰጥ እንደነበረም ይነገራል፡፡ ዜጎች ሃይማኖታቸውን ጠንቀቀው እንዲያውቁ፣ ካወቁ በኋላም ሃይማኖቱ በሚያዘው አስተምህሮ መሠረት እንዲያልፉና ለሌሎች እንዲያስተምሩ በማሰብ የትምህርት ሥርዓት ይቀረፅና ይሰጥ እንደነበር ይነገራል፡፡
የተለያዩ አገሮችን ተሞክሮ በመቀመር የአገሪቱን የትምህርት ሥርዓት ከመንፈሳዊ ወደ ዓለማዊ በመቀየር፣ ዘመናዊ ትምህርት በኢትዮጵያ መሰጠት ከተጀመረ ከመቶ ዓመታት በላይ ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡
ከንጉሠ ነገሥቱ እስከ ደርግ ሥርዓት የነበረው የትምህርት ፖሊሲ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ምሁራንን እንዳፈራ ቢነገርም፣ የኢሕአዴግ መንግሥት አገሪቱን ከተቆጣጠረበት 1983 ዓ.ም. ወዲህ ግን ‹‹ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም›› በሚለው መፈክር በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊንን በማስተባበር የአገሪቱን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች የሚፈታ ዜጋ በመፍጠርና በመቅረፅ ረገድ የተጓዘው መንገድ አበረታች እንደነበረ ምሁራን ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ‹‹ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም›› የትምህርት ፖሊሲ በአገሪቱ ከተቀረፀ ወዲህ በአገሪቱ በአራቱም አቅጣጫ ክልሎች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ዜጎች የመማር ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ የተካሄደው መንገድ አበረታች እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡
ለትምህርት ጥራቱ አጋዥ የሆኑ የላብራቶሪ፣ የቤተ ሙከራ፣ የአይሲቲና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን አሟልቶ ትምህርቱን ከመስጠት አንፃር ያሉ ክፍተቶች ወይም ጉድለቶች እንዳሉ ግን አይካድም፡፡ ለትምህርት ጥራት ወሳኝ ናቸው ተብለው የሚጠቀሱ እነዚህ ግብዓቶች ተሟልተው በአገሪቱ ውስጥ ባሉ የመጀመርያም ሆነ ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች አለመገኘት፣ በትምህርት ጥራቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማዕከሎች በተገቢው ሁኔታ የተደራጁ አለመሆን ትልቁ ፈተና መሆኑም ተጠቃሽ ነው፡፡
‹‹ጥራት ያለው የትምህርት ለሁሉም›› በሚለው የአገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ የተነሳ በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች አሥረኛና አሥራ ሁለተኛ ክፍል በመድረስ ለብሔራዊ ፈተና እንደሚቀርቡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ካለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ በብሔራዊ ደረጃ ለፈተና የሚቀርቡትና ወደ መሰናዶና ዩኒቨርሲቲ የሚገቡት ተማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መጥቷል፡፡ በአንድ ዓመት ብቻ ወደ መሰናዶ ትምህርት ለመግባት ፈተና የሚወስዱ የተማሪዎች ቁጥር በሚሊዮን የሚቆጠር ሆኗል፡፡
ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የአሥራ ሁለተኛ ክፍልን ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ቁጥርም በመቶ ሺሕዎች ደርሷል፡፡ ባለፈው ዓመት የአሥራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ለፈተና ሲቀርቡ ያጋጠመው ችግር ግን በአገሪቱ የትምህርት ሥርዓትና ፖሊሲ ላይ ትልቁ ፈተና ሆኖ እንዳለፈ ይታወቃል፡፡ ተማሪዎቹ በተፈጠረላቸው አጋጣሚም ሆነ ግሎባላይዜሽን ባመጣው ጫና ማኅበራዊ ሚድያዎችን የመጠቀም ዕድል አግኝተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የዓለምን ሕዝብ በፍጥነት እያግባባና መረጃ እያለዋወጠ የሚገኘው ማኅበራዊ ሚድያ በተለይም ፌስቡክ፣ ዓለም ወደ ሥልጣኔ እየገሰገሰች መሆኗን ማሳያ እንደሆነ የፌስቡክ መሥራቹ ማርክ ዙከርበርግ ከዓመት በፊት ተናግሯል፡፡ እነዚህ ማኅበራዊ ሚድያዎች ለአንድ አገር የትምህርት ሥርዓት መሻሻል የራሳቸው አዎንታዊ ጎን እንዳላቸው ምሁራን ሲናገሩ ይደመጣል፡፡
የአንድ አገር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ በፍጥነት ከማሳወቅ ባሻገር የፖለቲካ ሥርዓቱና ተሞክሮው ምን እንዳሚመስል በመጠቆም ማኅበራዊ ሚድያ እየተጫወተ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በዓለም ላይ ታዋቂ የሆኑ የፖለቲካ መሪዎች፣ የአሠራርና የአመራር ጥበባቸውን እንዲሁም በምን ሁኔታ አገራቸውን ወደ ዕድገት ደረጃ ማሸጋገር እንደቻሉ፣ መረጃዎችን ተደራሽ በሆነ ዘዴ በፍጥነት በማስተላለፍ ማኅበራዊ ሚድያ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
በሌላ በኩል እነዚህ ማኅበራዊ ሚድያዎች ለሁሉም ተደራሽ ከመሆናቸው አንፃር አገርን በማፍረስና የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሥርዓቱን በመናድ በኩል ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳላቸው የሚከራከሩ አሉ፡፡ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንገላ መርከል ባለፈው ዓመት ለሕዝብ እንደራሴዎች የተናገሩትም ይኼንኑ ነው፡፡
ከዓመታት በፊት የግብፅ መሪዎች ከሥልጣናቸው መነሳት ማኅበራዊ ሚድያዎች ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደነበራቸው ‹‹አህራም ኦንላይን›› የተሰኘው የሚድያ አውታር ከወራት በፊት ዘግቧል፡፡ የግብፅ መሪ የነበሩትን ሆስኒ ሙባረክ ከሥልጣናቸው እንዲነሱ ከማቀጣጠል ጀምሮ፣ በሙስሊም ወንድማማቾች የፖለቲካ ፓርቲ ላይ ሕዝቡ እንዲያምፅና መሐመድ ሙርሲ ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ ማኅበራዊ ሚድያ ዋነኛውን ድርሻ እንደተወጣ፣ በተለያዩ ጊዜያት የወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡
በአገራችን ኢትዮጵያም ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ተቀስቅሶ በነበረው አገራዊ አመፅ፣ ተቃውሞና ሁከት ማኅበራዊ ሚድያዎች ዋነኛ መሣሪያ ሆነው ያገለግሉ እንደነበር መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ ሲናገር ተደምጧል፡፡ ከጎንደር እስከ ባህር ዳር፣ ከወለጋ እስከ ሱሉልታ፣ ከጌዴኦ እስከ አርሲ በነበረው አለመረጋጋት ማኅበራዊ ሚድያ በተለይም ፌስቡክ የራሱን ሚና እንደተጫወተ ተነግሯል፡፡ በዚህ የተነሳ መንግሥት ማኅበራዊ ሚድያውን በተለይም ፌስቡክን በተለያዩ ጊዜያት ሲዘጋና ሲከፍት ተስተውሏል፡፡
ባለፈው ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ ማኅበራዊ ሚድያው ለአንድ አገር ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዕድገት የራሱን አስተዋፅኦ እየተጫወተ ቢሆንም፣ አገርን በማፍረስ በኩልም ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በዚህ ረገድ ሊታሰብበት እንደሚገባ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ማኅበራዊ ሚድያው በተለይም ፌስቡክ ለታዳጊ አገሮች የራሱን አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ቢሆንም፣ በዚያው ልክ ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸው ይታወቃል፡፡ በዚህም ረገድ በተመድ በኩል የተለያዩ ዕርምጃዎች መወሰድ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለብዙ ወራት ለነበረው አለመረጋጋት እንደ ዋነኛ የመግባቢያ መሣሪያ ሆኖ ሲያገለግል እንደቆየ የሚገለጸው ማኅበራዊ ሚድያ፣ ከዚያ ወዲህም በአገሪቱ የትምህርት ሒደትና ሥርዓት ላይ እንቅፋት ፈጥሮ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
ባለፈው ዓመት ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ሲዘጋጁ በነበሩ ተማሪዎች፣ ወላጆችና የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አስከትሎ ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት ፈተናው ተሰርቆ በፌስቡክ በመውጣቱ ዓመቱን ሙሉ አንገታቸውን ደፍተው ሲማሩና ሲያጠኑ በቆዩ ተማሪዎች ላይ አድርሶት ያለፈው የሞራል ኪሳራ ከባድ እንደነበር፣ ተማሪዎች ዛሬም ድረስ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ተበጅቶለት የሚሰጠው ይኼ ፈተና በአገሪቱ ላይ አስከትሎት ያለፈው ኪሳራ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ለአንድ ተማሪ የሚሆን የፈተና ወረቀት ከማዘጋጀት አንስቶ እስከ መልስ መስጫው፣ እንዲሁም የፈተና ወረቀቱን ከማጓጓዝ እስከ ፈታኝ መምህራን የቀን አበል መክፈል ድረስ ያለው ወጪ ከባድ ነው፡፡ የወረቀት ዋጋ ሰማይ በደረሰበት፣ የማተሚያ ቀለም በተወደደበት በዚህ ጊዜ ፈተናውን እንደገና አዘጋጅቶ፣ እንደገና አባዝቶ፣ እንዲሁም እንደገና ወደየትምህርት ቤቶች አሠራጭቶ ሒደቱን በማከናወን ወቅት የጠየቀው ጊዜና ገንዘብ አገሪቱን በከፍተኛ ሁኔታ ጉድቷት እንዳለፈ ማሳያ ነው፡፡ ጉዳዩ በጊዜና በገንዘብ ላይ ጭምርም ጉዳት እንዳደረሰ ባለሙያዎች ሲናገሩ ተደምጧል፡፡
የአሥራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተሰርቆ በማኅበራዊ ሚድያዎች በመውጣቱ በአገሪቱ ኢኮኖሚም ብቻ ሳይሆን በፖለቲካዊ ሒደቱም ላይ ተፅዕኖ አሳርፎ እንዳለፈ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የአገሪቱን መረጃ በጥብቅና በሚስጥር በመያዝና በማስተዳደር ረገድ ጉድለት እንዳለ ማሳያ ሆኖ እንዳለፈ ተነግሯል፡፡ አገር አቀፍ ፈተናን ለዘራፊዎች አጋልጦ መስጠት በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ያለውን ክፍተት እንደሚያሳይ ባለሙያዎች ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ ለዚህ ሁሉ የጊዜና የገንዘብ መባከን፣ እንዲሁም የተማሪዎችና የወላጆች ሞራል ውድቀት መነሻ ምክንያት የሆነው ፈተናው ተሰርቆ በማኅበራዊ ሚድያ በተለይም በፌስቡክ መውጣቱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
በዚህ ዓመት ባለፈው ተከስቶ የነበረውን ችግር መልሶ ላለማስተናግድ ሲባል ማኅበራዊ ሚድያው በተለይም ፌስቡክ ተዘግቶ የሰነበተ ቢሆንም፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ግን፣ ጉዳዩ ከፈተናው መሰረቅ ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ሚኒስትሩ በጽሕፈት ቤታቸው ተገኝተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ2 ‹‹የኢንተርኔት መዘጋት ኢትዮጵያን የሚገልጽ ጉዳይ ባይሆንም ለደኅንነት ሲባል ከዚህም የባሰ ውሳኔ ሊወሰን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ ኢንተርኔት በአጠቃላይ እንዳልተቋረጠ የሚገልጹት ሚኒስትሩ፣ ትኩረት የተደረገበት በተለይም ሶሻል ሚድያው እንዲዘጋ የተወሰነበት ዋነኛው ምክንያት፣ አገር ተረካቢ የሆነው አዲሱ ትውልድ ለብዙ ዓመታት ሲለፋበት የነበረውንና አሁን ፈተና በመፈተን ውጤቱን ለማግኘት በሚጥርበትና በጉጉት በሚጠብቅበት ጊዜ በመሆኑ፣ የተፈታኙን ሞራል ለመጠበቅ ሲባል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በማኅበራዊ ሚድያዎች የሚለቀቁት አሉባልታዎችና የሐሰት ወሬዎች በሥነ ልቦናቸው ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳርፍ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
ይኼ ዘመን አመጣሽ ማኅበራዊ ሚድያ ለአዎንታዊም ሆነ ለአሉታዊ ጉዳዮች ክፍት እንደሆነ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ የሐሰት አሉባልታዎችን በመንዛት ሕዝብን የማደናገር አቅም እንዳለው አስታውቀዋል፡፡ አሁን ጥያቄው ኢንተርኔት መዘጋቱና አለመዘጋቱ ሳይሆን፣ ተማሪዎች ተረጋግተውና ምንም ዓይነት ሥነ ልቦናዊ ጫና ሳይደርስባቸው ትኩረታቸውን በጥናታቸው ላይ ብቻ አድርገው ፈተናቸውን እንዲወስዱ የማድረግ ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
‹‹የኢንተርኔት መቋረጥ ምንም መጉላላት አያደርስም ብለን አናስብም፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ጉዳቱ ታይቶና ተመዝኖ ትውልድ መጎዳት ስለሌለበት መወሰኑን አስረድተዋል፡፡ በአገር ውስጥ ያሉ የውጭ ተቋማትና ድርጅቶች የመንግሥት ተቋማትን ጨምሮ በዚህ ችግር መጉላላትና ኪሳራ እንደሚደረስባቸው ጠቁመዋል፡፡
በየጊዜው ለሚፈጠረው የኢንተርኔት መቆራረጥና መዘጋት ኃላፊነቱን ማን እንደሚወስድ ለተጠየቁት ጥያቄ ሚኒስትሩ ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡ ከኢንተርኔት መቆራረጥና መዘጋት ጋር ተያይዞ አገሪቱ ምን ያህል ገንዘብ በዓመት እንዳጣች ከጋዜጠኞች የተጠየቁት ሚኒስትሩ በተመሳሳይ መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለፈው ዓመት ለፈተናው መሰረቅ ዋነኛ ተዋናይ በሆኑ ግለሰቦችና ባለሙያዎች ላይ የተወሰደ ዕርምጃ ካለ እንዲገልጹ ሲጠየቁ፣ ወደፊት በሚመለከተው አካል ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ዘንድሮ ኢንተርኔት የተቋረጠው እንደ ባለፈው ዓመት ፈተናው ይሰረቃል ተብሎ እንዳልሆነም አክለው አብራርተዋል፡፡ ‹‹የተለያዩ ሰዎች ፈተናው እንዳይሰረቅ በማሰብ ነው መንግሥት ኢንተርኔት የዘጋው የሚሉት ውሸት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ምንም ሳይፈጠር ሆን ብለው ሥነ ልቦናዊ ጫና ለማሳደር የሚፈልጉ አካላት ያንን ዕድል እንዳያገኙ በማሰብ እንደሆነ ሞግተዋል፡፡
በፈተና ወቅት ኢንተርኔት መዝጋት ዘንድሮም የተከሰተ ሲሆን፣ ይኼንን ችግር በዘላቂነት በመፍታት ረገድ መንግሥት ምን እየሠራ እንደሆነ ሚኒስትሩ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዊያንን የመመለሱ ሥራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ዶ/ር ነገሪ ተናግረዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየዕለቱ ከአንድ ሺሕ በላይ ዜጎች የጉዞ ሰነድ በመውሰድ ላይ እንደሆኑና እስካሁን ባለው ሒደትም ከ50 ሺሕ በላይ ዜጎች የጉዞ ሰነድ መውሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡ የጉዞ ሰነዱን ከወሰዱ መካከልም 74.4 በመቶ ያህሉ ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ እስከ ዓርብ ግንቦት 25 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ 20 ሺሕ የሚጠጉ ዜጎች ወደ አገራቸው እንደተመለሱና ይኼም በራሳቸው ጊዜ የሚመለሱትን እንደማያካትት አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ብሔራዊ የዜጎች አስመላሽ ግብረ ኃይልና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቀናጅተው በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆኑ፣ በቀን ውስጥ የሚደረገውን የበረራ ቁጥርም ለማሳደግ ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ጋር በመነጋገር ተጨማሪ የበረራ ፈቃድ ተጠይቆ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን ሪፖርተር መዘገቡ ይታወቃል፡፡
ከሳዑዲ ለሚመለሱ ሰነድ አልባ ዜጎች አገር ውስጥ ሲመጡ ምን ድጋፍ ለማድረግ ታቅዷል? ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ፣ መንግሥት በሦስቱ ክልሎች በአማራ፣ በደቡብና በኢትዮጵያ ሶማሌ እንዲሁም አዲስ አበባን ጨምሮ ተመላሾች ሲመጡ በሚቋቋሙበትና በሚደራጁበት ሁኔታ ላይ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩ ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ዜጎችን በተመለከተ እንደነ ፊሊፒንስና ፓኪስታን ያሉ አገሮች ዜጎቻቸውን የአየር ትራንስፖርት እያቀረቡ እየወሰዷቸው እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሳምንታዊ በረራውን ከሃያ አንድ ወደ አርባ ሁለት ከማድረሱ ባሻገር የዋጋ ቅናሽ ስለማድረጉ አልተነገረም፡፡ ለአንድ በረራ ከሚያስከፍለው ከ800 እስከ 1,000 ሪያድ ከፍለው ከሳዑዲ መምጣት ያልቻሉ ሰነድ አልባ ዜጎች በተመለከተ እየተሠራ ያለውን ሥራ እንዲያብራሩ የተጠየቁት ሚኒስትሩ፣ በገንዘብ እጥረት ሳዑዲ የሚቀሩ ሰነድ አልባ ኢትዮጵያዊያን እንደማይኖሩ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት እንደተናገሩት፣ በአገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ድርቅ የመከላከሉ ሥራም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ካለፈው ዓመት ወዲህ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በኦሮሚያ ክልል ቦረና፣ በባሌ፣ በጉጂ፣ በምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ፣ በደቡብ ክልል፣ ደቡብ ኦሞ፣ ሰገን ሕዝቦችና ጋሞጎፋ በዝናብ እጥረት ወገኖችን ለመታደግ የምግብና የውኃ አቅርቦት፣ እንዲሁም የጤናና የትምህርት አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡
ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው 7.8 ሚሊዮን ወገኖች በዋናነት በኢትዮጵያ መንግሥት፣ እንዲሁም ቀሪው በዓለም ምግብ ፕሮግራምና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ጥምረት 98,587 ሜትሪክ ቶን እህል መሠራጨቱን አስረድተዋል፡፡ በ173 ወረዳዎች በሚገኙ 3,012 ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ምገባ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ከፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ጋር በተያያዘ አሜሪካ ከአባልነቷ መውጣቷ ይታወቃል፡፡ የተለያዩ የዓለም አገሮችም የአሜሪካን ድርጊት እየኮነኑና እየተቃወሙ እንደሚገኙ ሰሞኑን የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ የተነሳም በአሁኑ ወቅት ፈጣን የኢኮኖሚው ዕድገት እያስመዘገበች ያለችው ቻይና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር አዲስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት አድርጋለች፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለውን አቋም እንዲገልጹ የተጠየቁት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ይኼ የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ ስለሆነ ውሳኔውን እናከብራለን፡፡ የተለያዩ አገሮች ይኼንን እያወገዙ እንደሆነም እንሰማለን፡፡ በእኛ በኩል ማውገዙ ተገቢ ሆኖ አይታየንም፡፡ ድርሻችንን መወጣቱ ላይ ነው ትኩረት የምናደርገው፤›› ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በየዓመቱ ሪፖርት በሚያቀርብበት ወቅት የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሚሊዮን የሚቆጠር የጥሬ ገንዘብ ጉድለት እንደሚገኝባቸው፣ በዘንድሮው ሪፖርቱ ላይም ይኼ ጉዳይ እንዳልተሻሻለ ሪፖርተርን ጨምሮ በተለያዩ የሚድያ ውጤቶች መገለጹ ይታወሳል፡፡ መንግሥት ደግሞ ለእስካሁን ድረስ ዕርምጃ ሲወስድ አይታይምና ይኼ ጉዳይ እስከ መቼ ነው በዚህ ሁኔታ የሚዘልቀው ተብለው ለተጠየቁት፣ ‹‹እነዚህ የበጀት ጉድለት ያሳዩ መሥሪያ ቤቶች ተመርምረው በዚህ ችግር እጃቸው ያለበት የመንግሥት የአመራር አካላት ዕርምጃ እንዲወስድባቸው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከአሥር ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በፌዴራል ፖሊስና በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመንግሥትና የሕዝብን ገንዘብ ባጎደሉ አካላት ላይ ምርመራ ይጀመራል፤›› ብለዋል፡፡ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ኦዲት በተደረጉ 113 መሥሪያ ቤቶች 5.2 ቢሊዮን ብር ያልተወራረደ መሆኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከወራት በፊት በአገሪቱ ተከስቶ ስለነበረው አለመረጋጋት ባቀረበው ሪፖርት ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባቸዋል የተባሉ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች እስከ ዛሬ ምን ዕርምጃ ተወስዷል ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ፣ ክልሎች የወሰዱትን ዕርምጃ በተመለከተ ኮሚሽኑ በሚቀጥለው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል፡፡
