ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው አመፅና ተቋውሞ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሎ አልፏል፡፡ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ንብረት ወድሟል፡፡ ከጎንደር እስከ ባህር ዳር፣ ከአሞቦ እስከ ወለጋ እንዲሁም ከኮንሶ እስከ ጉጂ ዞን ድረስ የተለያዩ ግጭቶችም ተፈጥረው ነበር፡፡
ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ በእንደዚህ ዓይነት ችግር ሲፈተን ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወዲህ ይኼ ሁለተኛውና ትልቁ እንደሆነ ተንታኞች ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ወጣቶች ስለቅማንትና ወልቃይት የማንነት ጥያቄ፣ ስለጠገዴና ፀገዴ፣ ኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ልታገኘው ስለሚገባት ጥቅም፣ በአገሪቱ ስለተንሰራፋው ሙስናና ብልሹ አሠራር፣ በዳኝነት ስላለው የፍትሕ መጓደል፣ ስለወጣቱ የሥራ ዕድል ፈጠራና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ጥያቄና ተቃውሞ ሲያነሱ ነበር፡፡
በእነዚህና ሌሎች ጥያቄዎች የተነሳ ተከስቶ በነበረው ተቃውሞ የበርካታ የሰው ሕይወት ከመጥፋቱ ባሻገር፣ የመሠረተ ልማቶችና የኢንቨስትመንት ተቋማት ወድመዋል፡፡ በርካታ ዜጎችም ለአስከፊ ችግር ተዳርገዋል፣ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትርና ከሳምንት በፊት የፈረሰው ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት ኃላፊ የነበሩት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ብጥብጥ ዜጎች በሰላም ወጥተው መግባትና መደበኛ ሥራቸውን ማከናወን የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ በወቅቱ ተፈጠሮ በነበረው አመፅና ተቃውሞ ወጥቶ መግባት አዳጋች የሆነበት ደረጃ ላይ ተደርሶ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ይኼንን ጉዳይ መንግሥት በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት መቆጣጠር እንደማይችል በመገምገም፣ በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጎ ቆይቷል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 መሠረት ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ አገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቆይታለች፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ ኮማንድ ፖስቱ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የፀጥታ ኃይሎችን በአንድ ሥር በማድረግና በተለያዩ ቀጣናዎች ከፋፍሎ በማደራጀት ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ሦስት መመርያዎችንም አውጥቶ ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባቀረቡት ሪፖርት፣ በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው አመፅና ተቃውሞ ወቅት በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 28,846 ዜጎች ሠልጥነው መለቀቃቸውንና የተወሰኑትም በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው እስካሁን ድረስ በፍርድ ቤት እየታየ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
‹‹በዚህም የተነሳ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ መነሻ የነበሩ ሁኔታዎች በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንሱ ተደርገዋል፡፡ በአንዳንድ በውል የሚታወቁ አካባቢዎች የቀሩ አነሰተኛ ሥራዎች ቢኖሩም፣ በመደበኛው የሕግ አግባብ መቆጣጠር ይቻላል፤›› ብለው ነበር፡፡ እነዚህ በውል የሚታወቁ አካባቢዎች እነማን እንደሆኑ እንዲጠቅሱ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄ የቀረበላቸው ቢሆንም ከመግለጽ ተቆጥበው ነበር፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ለአሥር ወራት ያክል ተጥሎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዓርብ ሐምሌ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. አንስቷል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲታወጅ ተደንግገው የነበሩ ዕግዶች ማለትም ሁከትና ጥብብጥ የሚያነሳሳ ቅስቀሳና ማድረግ፣ ከሽብርተኛ ጋር ግንኙነት ማድረግ፣ ያለፈቃድ ሠልፍና የአደባባይ ስብሰባ ማድረግ፣ በትምህርት ተቋማት አድማ ማድረግ፣ የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ማወክ፣ በመሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረስ፣ ለሕዝብ አገልግሎት አለመስጠት፣ ወዘተ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ገደቦች ተጥለው እንደነበር ይታወሳል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመነሳቱ በፊት በኮማንድ ፖስቱ ተደንግገው የነበሩ አንዳንድ ድንጋጌዎች ሲጣሱም ተስተውሏል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ከቀን ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ በአዋጁ የተደነገገውን ለሕዝብ አገልግሎት አለመስጠት የሚለውን ድንጋጌ በመሻር፣ በክልሉ ውስጥ ያሉ ነጋዴዎች ለተወሰኑ ቀናት የንግድ ተቋማቸውን ዘግተው መዋላቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በመሰል ልማቶችና ንብረቶች ላይ ጉዳት አለማድረስ የሚለውን ድንጋጌ በመሻር በክልሉ ከቀን ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ በአምቦ ከተማ ተቀስቅሶ በነበረው ተቃውሞ በተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡
በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ የጦር መሣሪያ ይዞ መገኘት የሚለውን ድንጋጌ በመተላለፍ ሐምሌ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በከተማዋ ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች፣ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር እንደዋሉም ተገልጾ ነበር፡፡
አቶ ሲራጅ በውል ያልታወቁ አንዳንድ አካባቢዎች የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ጠቅሰው እነዚህ አካባቢዎች እነማን እንደሆኑ ባይገልጹም፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመነሳቱ በሁለት ቀናት ልዩነት በባህር ዳር ከተማ የቦምብ ፍንዳታ ተከስቷል፡፡ በሳምንቱ ደግሞ በከተማዋ ለሁለተኛ ጊዜ የቦምብ ፍንዳታ ተከስቷል፡፡ በዚህም የተነሳ ዜጎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲነሳ በአገሪቱ የተሻለ መረጋጋት እንደሚታይ ቢገመትም፣ ይኼ ሲሆን ግን እምብዛም አልታየም፡፡
አዋጁ ከተነሳ በኋላም በክልሎች በተለይም በአማራ ክልል የንግድ ተቋማትን የመዝጋት ተቃውሞ ታይቷል፡፡ በተለይም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ውስጥ የሚገኙ ወረዳዎች ለምሳሌ በቢቡኝ፣ ስናን፣እንዲሁም ደቡብ ጎንደር ደብረ ታቦርና ደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ ባሉ ወረዳዎች ተቃውሞ ተስተውሏል፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ማክሰኞ ነሐሴ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በኦሮሚያ ክልል ፀረ ሰላም የሆኑ ኃይሎች በአገሪቱ እየተፈጠረ ያለውን ሰላምና መረጋጋት ለማደፍረስና ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ ጥረዋል፡፡ ‹‹ቢሆንም ግን ሕዝቡ ሰላም ወዳድ በመሆኑ ዓላማቸውን ማሳካት አልቻሉም፤›› ብለዋል፡፡
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላም በአገሪቱ የተለየ ነገር ተደርጎ እንዳልታየም ገልጸዋል፡፡ አሁን ለተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት ዋነኛው ምክንያት በአገሪቱ ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደነበር ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የመድረክ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ግን አስቸኳይ ጊዜያዊ አዋጁ ተነሳም አልተነሳም፣ በአገሪቱ ያሉ ችግሮችን መቅረፍ እንዳልተቻለ ይሞግታሉ፡፡ የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ችግር ከአስቸኳይ ጊዜያዊ አዋጁ መነሳትና አለመነሳት ጋር እንደማይያያዝ ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያን ለዚህ ችግር የዳረጓት ዋነኛ ምክንያቶች የፖለቲካ ምኅዳሩ መጥበብ እንደሆነ አቶ ይልቃል ጠቁመዋል፡፡
ሚኒስትሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ በአገሪቱ የፖለቲካ ይዞታ ላይ የተረጋጋ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡ አቶ ይልቃል ግን በመሠረታዊነት በፖለቲካ ይዞታው ላይ ከአዋጁ መነሳት በኋላ የታየ ለውጥ የለም ብለው፣ በአዋጁ መነሳት የሕዝቡም ሆነ የመንግሥት ባህሪ እንዳልተቀየረ አመልክተዋል፡፡ ዜጎች አሁንም ተቃውሟቸውን በተለያዩ ዘዴዎች እየገለጹና መንግሥትም ዕርምጃ እየወሰደ መሆኑን ያብራራሉ፡፡
ፕሮፌሰር በየነ በበኩላቸው፣ ‹‹አዋጁ በነበረበት ጊዜም ሕዝቦች ሲጋጩ ነበር፡፡ አማሮና ጉጂ በሚባል አካባቢ ተነስቶ የነበረው ግጭት አዋጁ ከመነሳቱ በፊት ነው የነበረው፡፡ በዚህ ግጭት የብዙ ሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፡፡ ይኼንን መሰል ተቃውሞና ግጭት በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም አለ፤›› ብለዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ ገና ትንሽ ጊዜ በመሆኑና በእነዚህ ቀናት ውስጥ ልዩነቶች ይመዘገባሉ ተብሎ እንደማይጠበቅ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ከአዋጁ በኋላም በአገሪቱ ተዓምር ተፈጥሯል ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡ ምክንያታቸውን ሲያብራሩም በተለይ የሁለተኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ ወዲህ በአገሪቱ የነበሩ ነገሮች ወደ ቀድሞ ሁኔታዎች ተቀይረው እንደነበርም አብራርተዋል፡፡ ሕዝቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስለመኖሩ ይጠራጠር እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ይኼ ደግሞ ሆነ ተብሎ የተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
‹‹በውጭው ዓለም በአንድ ዜና ብቻ ገበያው ከፍና ዝቅ የሚልበት ሁኔታ ቢኖርም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ግን አስቸኳይ ጊዜያዊ አዋጁ በነበረ ጊዜም ሆነ ከተነሳ በኋላ ተፅዕኖ አላመጣም፤›› ብለዋል፡፡
ነገር ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ መረጋጋት መታየቱን ገልጸዋል፡፡ ከአዋጁ መነሳት በኋላ በኢትዮጵያ የሚገኘው የእንግሊዙ ከፊ ሚነራልስ የስቶክ ኤክጄንጅ ዋጋ ከፍ ማለቱን እንዳስታወቀ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
‹‹በአገር ውስጥ ያሉ ውስን ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይም በድርድሩ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ባይሆኑም፣ ከቀን ገቢ ግምቱ ጋር በተያያዘ የተነሳውን ተቃውሞ እንደ ዕድል በመቁጠር ኅብረተሰቡ በመንግሥት ላይ ጥርጣሬ እንዲኖረው ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ይኼ ድርጊታቸው ከአዋጁ መነሳት በኋላም የቀጠለ ቢሆንም፣ በሚገርም ሁኔታ ለእነሱ ምላሽ አልሰጠንም፤›› ብለዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ዋነኛው በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት የተሻለ ሰላምና መረጋጋት መፈጠሩ ነው፡፡ ይኼም ሆኖ ግን በባህር ዳርና ውስን ሌሎች አካባቢዎች ተቃውሞ እየተነሳ ነው፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ምንድነው? የሚል ጥያቄ ለሚኒስትሩ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በሰላማዊ መንገድ ሳይሆን የፖለቲካ ሥልጣን መያዝ የሚቻለው በአመፅ ነው ብለው የሚያስቡ የፖለቲካ ተዋንያን፣ በተለይም ደግሞ ከውጭ ሆነው በተለያዩ የመረጃ መረቦች ማኅበራዊ ሚዲያን ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም የለም፣ አመፁ ቀጥሏል በማለት ለማደናገር በመሞከራቸው ነው፤‹› ብለዋል፡፡
አዋጁ መውጣት እንደሌለበትና ተፈጥሮ የነበረውን አመፅና ተቃውሞ በሃይማኖትም ሆነ በባህላዊ ዘዴ መፍታት ይቻል እንደነበር የገለጹት ፕሮፌሰር በየነ፣ ከወጣ በኋላም መንግሥት ዜጎችን ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለማሰር የተጠቀመት ዘዴ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ለተፈጠሩት ቀውሶች እንደ ምክንያት ከተወሰዱ ጉዳዮች መካከል አንዱ ከወጣቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር የተያያዘ እንደሆነ መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ ሲናገር ተደምጧል፡፡ ይኼንን ችግር ለመፍታትም አሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ በመበጀት ወጣቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ መለማድረግ እየጣረ መሆኑን ገልጿል፡፡ ይኼ ተዘዋዋሪ ፈንድ ሙሉ በሙሉ በአገሪቱ ያሉ ወጣቶችን ችግር ይፈታል ተብሎ ባይታሰብም፣ ጥሩ ጅምር መሆንን የተለያዩ ባለሙያዎች በተለያየ ጊዜ ሲገልጹ ተደምጧል፡፡ ዶ/ር ነገሪም በአገሪቱ ተከስቶ የነበረውን የወጣቶች ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ይኼን ተዘዋዋሪ ፈንድ መበጀቱ፣ ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡ ይኼን ተዘዋዋሪ ፈንድ በመጠቀም በአሁኑ ወቅት በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ወጣቶች ተጠቃሚ መሆናቸውንም አክለው ገልጸዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ መንግሥት ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች መካከል ሌላው ጉዳይ ከሙስና ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎችን ተጠያቂ ማድረግ መጀመሩን ነው፡፡ ከመልካም አስተዳደር ዕጦትና ከብልሹ አሠራር ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲነሳ ቆይቷል፡፡ በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት በሙስና ከ50 በላይ ዜጎች በሕግ እንዲጠየቁ ለማድረግ ሒደቱ ተጀምሯል፡፡ ዶ/ር ነገሪ ይኼንን ጉዳይ በተመለከተ፣ ‹‹በመልካም አስተዳደር ችግር የተነሳ ዜጎች መብቶቻቸውን በአግባቡ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ በእነዚህ ኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ እየተወሰደ ያለው ዕርምጃም ሕዝቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ታልሞ ነው፤›› ብለዋል፡፡
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ ማግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጭ ዲፕሎማቶችን ሰብስቦ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመነሳቱ ምክንያት በቱሪዝም ዘርፍ ተከስቶ የነበረው ክፍተት ሊሞላ እንደሚችል የብዙዎች ተስፋ መሆኑ ተገልጿል፡፡
አቶ ይልቃል በቱሪዝም ዘርፍም ሆነ በኢኮኖሚው ለውጥ እንዳልታየ ይናገራሉ፡፡ ሚኒስትሩ ግን በቱሪዝምና በኢንቨስትመንት ዘርፎች አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ ወዲህ መሻሻሎች መታየቸውን ጠቁመዋል፡፡
ለአሥር ወራት በአገሪቱ ተጥሎ የነበረው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተነሳ ከአንድ ሳምንት በላይ ቢሆንም፣ ብዙ ነገሮች እየተሻሻሉና ለውጥ ያሳያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ምንም እንኳ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በነበረበት ጊዜም ቢሆን ከዚያ በፊት በነበሩት ጊዜያት የተለየ ብዙም ሁኔታ እንዳልነበረ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገልጽ ቢሰማም፣ ዜጎች በተቀመጡ ገደቦች ላይ ከፍተኛ ፍርኃት አድሮባቸው እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ አንዳንዶች አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኖረም አልኖረ ፍርኃት እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ መንግሥት ደግሞ በአስቸኳይ አዋጁ ተደንግገው የነበሩ ገደቦች በመነሳታቸው ሕጋዊና ሰላማዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ይቻላል ይላል፡፡
